“የጋዜጠኝነት ፍቅር ያሳደረብኝ መገናኛ ብዙኃንን የመከታተል ልምዴ ነው”

0
154

የተወለደው ከፍኖተ ሰላም ከተማ አሥር ኪሎ ሜትር ያህል ርቃ በምትገኝ ጠበታ ማርያም በተባለች የገጠር ቀበሌ ነው:: የአንደኛ ደረጃ ትምህርቱን ማንኩሳ ተከታትሏል:: ከዚያም ከሰባተኛ እስከ 12ኛ ክፍል ፍኖተ ሰላም መለስተኛ እና ሁለተኛ ደረጃ እንዲሁም ዳሞት አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተምሮ በ1977 ዓ.ም አጠናቋል::

የዩኒቨርስቲ ትምህርቱን ደግሞ ከ1978 እስከ 1981 ዓ.ም በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተከታትሎ በ1981 ዓ.ም የአርት ባችለር ዲግሪ በኢትዮጵያ ቋንቋዎች እና ሥነ ጽሑፍ (አማርኛ) ይዟል:: ከዚያም በ2001 ዓ.ም በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ በቢዝነስ ማኔጅመንት  የመጀመሪያ ዲግሪ እንዲሁም በ2004 ዓ.ም የማስተርስ ዲግሪ በቢዝነስ አስተዳደር ተቀብሏል::

ጥቅምት 5 ቀን 1982 ዓ.ም በሰሜን ሸዋ አስተዳደር አካባቢ ባህል እና ስፖርት መምሪያ በሥነ ጽሑፍ አጥኚነት የሥራውን ዓለም የተቀላቀለው እንግዳችን ለ35 ዓመታት  ከሥነ ጽሑፍ አጥኝነት በተጨማሪ በሕዝብ ግንኙነት ባለሙያነት እንዲሁም በጋዜጠኝነት አገልግሏል፤ እያገለገለም ይገኛል:: የሙያ አጋሮቹ ፊደላት በትክክለኛ ቦታቸው ጥቅም ላይ መዋል አለባቸው፤ በንግግርም ሆነ በጽሑፍ  ወቅት ባዕድ ቃላትን አላስፈላጊ መጠቀም የለብንም የሚል ጠንካራ ሀሳብ እንዳለው ሲገልጹ ይደመጣሉ::

ከ34 ዓመታት አገልግሎት በኋላ ባለፈው ዓመት ሁለት መጻሕፍትን ለሕትመት አብቅቷል፡- የዚህ እትም እንግዳችን ጋዜጠኛ እና ደራሲ አባትሁን ዘገየ:: ከጋዜጠኝነት እንዲሁም ቋንቋ እና ሥነ ጽሑፍ ጋር በተያያዘ የተለያዩ ጥያቄዎችን አቅርበንለት ሀሳቡን እንደሚከተለው አካፍሎናል::

መልካም ንባብ!

የጋዜጠኝነት ፍቅር እንዴት አደረብህ?

ልጅ ሆኜ እንደማስታውሰው ማንኩሳ ከተማ አባ ረዳቴ የሚባሉ ትልቅ ሰው ነበሩ:: አባ ረዳቴ ብርቄ የምትባል ትንሽ ሬድዮ ነበረቻቸው:: ያቺን ሬድዮ አንግተው እያዳመጡ ከተማ ውስጥ ሲዘዋወሩ ይውላሉ:: እኛም በወቅቱ ልጆች ስለነበርን ሲሄዱ እየተከተልን፣ ሲቀመጡ በዙሪያቸው እየተቀመጥን ያችን ሬድዮ እናዳምጥ ነበር::

በዚህ ሁኔታ ላይ እያለሁ የአንደኛ እና መለስተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቴን ጨርሼ ወደ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተሸጋገርሁ:: የሁለተኛ ደረጃ ተማሪ እያለሁ በአብዛኛው ከገጠር ፍኖተ ሰላም እየተመላለስሁ ነበር የምማረው:: በዚያን ወቅት በማገኛት ሳንቲም አዲስ ዘመን  እንዲሁም የዛሬዪቱ ኢትዮጵያ ጋዜጣ እየገዛሁ ከፍኖተ ሰላም  ወደ ገጠር  ስሄድ መንገድ ለመንገድ ከመጀመሪያው  እስከ መጨረሻው ገጽ  ጮክ እያልሁ አነብ ነበር:: መንገድ ለመንገድ ያነበብሁትን ጋዜጣ ቤት ስደርስ ግድግዳው ላይ በእሾክ እለጥፍና ድምጼን ከፍ አድርጌ አነበዋለሁ:: የጋዜጠኝነት ፍቅር ያሳደረብኝ እንግዲህ  ይህ መገናኛ ብዙኃንን የመከታተል ልምዴ ነው ብየ አስባለሁ::

ወደ ጋዜጠኝነት መቼና እንዴት ገባህ?

ወደ ጋዜጠኝነት የገባሁት በ1983 ዓ.ም  ጽሑፎችን በማዘጋጀት ለአዲስ ዘመን እና ለየዛሬዪቱ ኢትዮጵያ ጋዜጣ ባህል አምድ  እንዲሁም   ለኢትዮጵያ ሬድዮ የኪነ ጥበባት ምሽት፣ በተጨማሪም ለለገዳዴ ሬድዮ የእሁድን ለአንዳፍታ የመዝናኛ ዝግጅት በመላክ ነው:: ለእነዚህ የብዙኃን መገናኛ አውታሮች ጽሑፎችን የምልከው በእጄ እየጻፍሁ ሲሆን የምልከውን ጽሑፍ የካርቦን ቅጅ አስቀር ነበር:: በማስቀረው ቅጂ ላይም ጽሑፉን ለየትኛው የብዙኃን መገናኛ አውታር፣ ለየትኛው አምድ ወይም ፕሮግራም እንደላክሁት ማስታወሻ እይዝ ነበር:: የላክሁት ጽሑፍ ሲታተምም ሆነ ሲነበብ ከቀሪው ጽሑፍ ጋር አገናዝበዋለሁ:: ይህን የማደርገው በአርትኦት የተስተካከለ ነገር ካለ ለመማር እና ተመሳሳይ ስህተት ላለመድገም ከመፈለግ የተነሳ ነው:: ሆኖም ጽሑፎችን የምልከው ደጋግሜ ካረምሁ በኋላ በመሆኑ የሚታተሙት እንዲሁም ለአድማጮች የሚቀርቡት እርማት ሳይደረግባቸው ነው::

ጽሑፎቼ በጋዜጣ ታትመው ወጥተው ሳይም ሆነ በሬድዮ ሲቀርቡ ስሰማ ከፍተኛ ደስታ ይሰማኛል:: በተለይም “የአጭር ልቦለድ ድርሰት አጻጻፍ” በሚል ርዕስ ለየዛሬዪቱ ኢትዮጵያ ጋዜጣ የላክሁት  ጽሑፍ ኅዳር 27 ቀን 1984 ዓ.ም በባህል አምድ ታትሞ ሳየው የተሰማኝ ደስታ ወሰን አልነበረውም:: “የቆሎ ተማሪ እና ሥነ ቃሉ” በሚል ርዕስ ለኢትዮጵያ ሬድዮ የላክሁት ጽሑፍም በኪነ ጥበባት ፕሮግራም ሲቀርብ እጅግ ከፍ ያለ ደስታ ነበር የተሰማኝ::

የለገዳዴ ትምህርት ማሠራጫ ሬድዮ አዘጋጆች ግጥሞችን እንዲሁም አጫጭር አዝናኝ ጽሑፎችን ለሁለት ዓመታት ያህል በተከታታይ በመላክ ለአደረግሁት ተሳትፎ ዕውቅና በመስጠት ሬድዮ ጣቢያውን እንድጎበኝ ጥሪ አድርገውልኛል:: እኔም ጥሪያቸውን በመቀበል ተገኝቼ ጉብኝት አድርጌያለሁ፤ ግጥሞቼንም ስቱዲዮ ተገኝቼ አንብቤያለሁ::

ከአሚኮ ጋር እንዴት ተገናኛችሁ?

ከአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን (አሚኮ) ጋር እንድገናኝ ምክንያት የሆኑኝ  ለጋዜጦች እና ለሬድዮ ጣቢያዎች እልካቸው የነበሩት ጽሑፎቼ ናቸው:: ጽሑፎችን ለእነዚህ የብዙኃን መገናኛዎች እልክ የነበረበት ወቅት ክልሎች እንዲሁም የክልል ቢሮዎች በአዲስ መልክ የተደራጁበት (የተቋቋሙበት) ነበር:: እናም ቢሮዎችን በሰው ኃይል ለማጠናከር የተለያየ ሙያ ያላቸው ሰዎች ከየአካባቢው እየተዛወሩ ወደ ባሕር ዳር እንዲሄዱ ይደረግ ነበር:: በዚህ መሠረት በወቅቱ ከፍ ሲል ለጠቀስናቸው የብዙኃን መገናኛ አውታሮች እልካቸው የነበሩትን ጽሑፎች ያነቡ እንዲሁም ያዳምጡ የነበሩ የክልል ሦስት የባህል እና ስፖርት ጉዳይ ቢሮ ኃላፊዎች ጥር 1 ቀን 1986 ዓ.ም  ከሰሜን ሸዋ ባህል እና ስፖርት መምሪያ  ወደ ክልል ሦስት ባህል እና ስፖርት  ቢሮ  በፍላጎቴ አዛውረውኛል::

በወቅቱ ክልል ሦስት ባህል እና ስፖርት ቢሮ “ዜና ባህል እና ስፖርት” የሚል መጽሔት በየስድስት ወሩ እያዘጋጀ ያወጣ ነበር:: እናም በዝውውር ወደ ባሕር ዳር እንደመጣሁ የመጽሔቱ አዘጋጅ ሆኜ እስከ 1987 ዓ.ም ሠርቻለሁ:: በተጨማሪም የክልል ሦስት ማስታወቂያ ቢሮ  በ1987 ዓ.ም  ከ1984 እስከ 1986 ዓ.ም በነበረው የሽግግር ወቅት በክልሉ የተከናወኑ የልማት ሥራዎችን የሚዘግብ “ሽግግር” የተሰኜ መጽሔት ለማዘጋጀት አቅዶ ነበር:: ሆኖም ቢሮው መጽሔቱን የሚያዘጋጅ በቂ የሰው  ኃይል አልነበረውም:: እናም ከተለያዩ ቢሮዎች የሥነ ጽሑፍ እና ጋዜጠኝነት ዝንባሌ ያላቸው ሰዎች ተመርጠው እንዲያዘጋጁ ተወሰነ:: ወደ ሰው ምርጫ ሲገባም ከአዘጋጆች አንዱ ሆኜ ተመደብሁ:: ለሁለት ወራት ያህል በክልሉ ሁሉም አካባቢዎች ተዘዋውረን መረጃዎችን አሰባስበን መጽሔቱን አዘጋጅተን ለቢሮው አስረከብን::

ከአንድ ዓመት በኋላ በ1988 ዓ.ም ባህል እና ስፖርት ቢሮ እንዲሁም ማስታወቂያ ቢሮ  ይባሉ የነበሩ ተቋማት በአዲስ መልክ እንዲደራጁ  ሲወሰን ባህል፣ ቱሪዝም እና  ማስታወቂያ ቢሮ (ባቱማ) ተቋቋመ:: ከአንድ ዓመት በፊት ማለትም ከመጋቢት 1987 ዓ.ም ጀምሮ በኲር የሚባል  ወርሃዊ መጽሔት ሲዘጋጅ ነበር:: እኔም ከግንቦት 9 ቀን 1988 ዓ.ም እስከ ሚያዝያ 9 ቀን 1992 ዓ.ም የበኲር መጽሔት እንዲሁም የበኲር ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ ሆኜ ሠርቻለሁ::

በኲር ጋዜጣ እንዴት ተመሠረተች?

ሐምሌ 15 ቀን 1986 ዓ.ም የክልል ሦስት አራተኛ መደበኛ ጉባኤ የተከፈተባት ዕለት ናት:: በወቅቱ ክልል ሦስት የእኔ የሚለው የብዙኃን መገናኛ አውታር አልነበረውም:: በዚህ የተነሳ ጉባኤው የተወያየባቸውን እንዲሁም የሚያሳልፋቸውን ውሳኔዎች  የሚዘግብ ልሣን በማስፈለጉ ሐምሌ 19 ቀን 1986 ዓ.ም በኲር ጋዜጣ በልዩ እትምነት ለመጀመሪያ ጊዜ ለንባብ በቅታለች:: ጋዜጣዋ ልዩ እትም እየተባለች ስትወጣ ቆይታ ታህሣሥ 7 ቀን 1987 ዓ.ም ሳምንታዊ መደበኛ ጋዜጣ ሆና ተመሥርታለች:: በወቅቱ ዜና ገጽን ጨምሮ አምስት አምዶች እና ስምንት ገጾች ይዛ ነበር ለንባብ የበቃችው::

በወቅቱ እንዴት ነበር የምትሠሩት?

በወቅቱ የምንከተለው አሠራር እጅግ ኋላ ቀር እና አድካሚ ነበር:: በእጅ ተጽፈው የሚመጡ የዘገባ ሥራዎች በነበረችን አንዲት ኮምፒዩተር ከተጻፉ በኋላ “ከተር” በሚባል ምላጭ መሰል ነገር እየተቆራረጡ “ዳሚ” ወይም የጋዜጣዋ ገጽ መሥሪያ ወረቀት ላይ ይለጠፋሉ:: በ“ከተር” ስንቆርጥ እጃችንን እየተቆረጥን እንደማ፣ ያዘጋጀነው ጋዜጣም በደም እየተጨማለቀ እንደገና ሌላ “ዳሚ” እናዘጋጅ ነበር:: አደጋው በዚህ የተወሰነ አልነበረም፤ ምላጩን ስንሰብር እየበረረ ዓይናችንን ሊወጋ የሚችልበት መጥፎ አጋጣሚም ላለመከሰቱ ምንም ዋስትና አልነበረንም:: ስለሆነም ከእንዲህ ዓይነቱ አደጋ ለማምለጥ ምላጩን ስንሰብር ዓይናችንን እየጨፈንን ፊታችንን እናዞር ነበር::

በማጣበቂያነት የምንጠቀምበት ሙጫም ልብሳችንን ከነካ ስለማይለቅ አውልቀን ለመጣል እንገደድ ነበር:: እኔ ለምሳሌ አንድ ኮቴ እጅጌው በሙጫ በመጨማለቁ አውልቄ መጣሌን አስታውሳለሁ::

ይህን በመሰለ ውጣ ውረድ የምናዘጋጀው ጋዜጣ ይታተም የነበረው አዲስ አበባ በአውሮፕላን እየተላከ ነበር:: ይህ ሂደት በራሱ ችግሮች ነበሩበት:: ምክንያቱም እንዲያደርስ የተሰጠው ሰው ረስቶ ቤቱ ይዞት የሚሄድበት እና የሚጠፋበት ጊዜ አልፎ አልፎም ቢሆን ያጋጥም የነበረ መሆኑ ነው::

አብሮ የመሥራት ባህላችሁ ምን ይመስል ነበር?

በኲር ስትመሠረት አጫጭር የጋዜጠኝነት ሥልጠናዎችን ከመውሰድ በዘለለ በሙያው የተመረቀ በቂ ባለሙያ አልነበረም:: ሆኖም የነበሩት አሥር የማይሞሉ ጋዜጠኞች ለሙያው በጣም ከፍተኛ ፍቅር ያላቸው ከመሆናቸውም በላይ ሥራን ተሻምተው ነበር የሚሠሩት::  በተጨማሪም በኲር በተመሠረተችበት ወቅት አማተር የሥነ ጽሑፍ እንዲሁም የጋዜጠኞች ክበባት በየቦታው እየተደራጁ ስለነበር አባሎቻቸው ጽሑፎችን በመላክ በንቃት ይሳተፉ ነበር::

በኲር መጽሔት  ይታተም እንደነበርና አንተም በዋና አዘጋጅነት ስለመሥራትህ ነግረኸኛል:: አሁን ላይ መጽሔቱ የለም፤ ለምን ተቋረጠ?

ግንቦት 1995 የአማራ ክልል ማስታወቂያ ቢሮ ልሣን የሚል መጽሔት ማሳተም ጀምሯል:: ልሣን መጽሔት ዝግጅት የተለያዩ አካላትን ባሳተፈ መልኩ ይፈጸም ዘንድ የመጽሔቱ ዝግጅት ይመራ የነበረው በቦርድ ሲሆን እኔ  በአማራ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድርና የማስታወቂያ ቢሮ ኃላፊ የቦርዱ ሰብሳቢ ሆኜ  ተመድቤ ሠርቻለሁ:: ልሣን መጽሔት መታተም ሲጀምር ታዲያ ድግግሞሽን ለማስቀረት በሚል የበኲር መጽሔት ሕትመት እንዲቋረጥ ተደርጓል::

በኲር ከተመሠረተችበት ጊዜ ጀምሮ ያበረከተችውን አስተዋጽኦ እንዴት ትገልጸዋለህ?

በኲር ጋዜጣ ለመልካም አስተዳደር መስፈን፣ ለልማት መፋጠን ጉልህ ሚና ተጫውታለች:: በኲር እንደተመሠረተች ይስተዋሉ የነበሩ የመልካም አስተዳደር ጉድለቶች እንዲስተካከሉ በመረጃ ላይ ተመስርታ ስለምትጠቁም የመንግሥት ባለሥልጣናት ጋዜጣችን በዚህ እትሟ ምን ዘገበች በማለት ጉዳዩን አጣርተው የማስተካከያ ርምጃ ይወስዱ እንደነበር አስታውሳለሁ::

የልማት እንቅስቃሴዎችን ተከታትላ በመዘገብ አንዱ አካባቢ ከሌላው ተሞክሮ እንዲቀስም ከፍተኛ ጥረት አድርጋለች:: ማኅበራዊ ችግሮች እንዲወገዱ፣  ቋንቋ እንዲሁም የፈጠራ ባህል እንዲያድግ  ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበርክታለች::

ይቀጥላል

(ቢኒያም መስፍ)

በኲር የታኅሳስ 7  ቀን 2017 ዓ.ም  ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here