የጋዜጣ አሻራ

0
46

አሜሪካዊው ደራሲ ሪቻርድ ክሉገር  “መጥፎ ጋዜጣ እንኳ ቢሆን አንድ ጋዜጣ በሞተ ቁጥር፤ ሀገር ወደ አምባገነንነት ትንሽ ትቀርባለች” በሚለው አባባሉ ይታወቃል።

የጋዜጣ መኖር  ለሀገር ዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ወሳኝ ሚና እንደሚጫዎት ማሳየቱ ነበር።

ዘመናዊው የብዙኃን መገናኛ አማራጭ ሬዲዮ፣ቴሌቪዥን እና ማህበራዊ የብዙኃን መገናኛ ከመምጣቱ በፊት ጋዜጣ የሰው ልጆችን ንቃተ ሕሊና በማሳደግ ከዓለም ጋር እንዲራመዱ አድርጓል።

የራቀውን አቅርቦ፣ ረቂቁን አጉልቶ፣ ውስብስቡን አቅልሎ፣ ረጅሙን አሳጥሮ የእውቀት ምንጭ በመስጠት ጋዜጣ የታሪክ አሻራ አለው።

ጋዜጦችን ማንበብ ለህብረተሰብ  ከሚሰጠው ጥቅም አንጻር የማይተካ ሚና አለው። የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ቶማስ ጄፈርሰን “ጋዜጣ የሌለው መንግሥት ከሚኖር እና መንግሥት የሌለው ጋዜጣ ከሚኖር ብባል ለአፍታም ሳላመነታ መንግሥት በሌለበት ጋዜጣ እንዲኖር እመርጣለሁ” ብለው ነበር።

ጋዜጣን ያነበበ ማህበረሰብ ለሁከት፣ ብጥብጥ እና ስርዓት አልበኝነት ቦታ አይሰጥም። ጋዜጦች ሀገርን በመምራት ከመንግሥት ተወዳዳሪ ስልጣን አላቸው።

አሜሪካዊ ፀሐፌ ተውኔት አርተር ሚለር  “ጥሩ ጋዜጣ ማለት አንድ ሕዝብ ከራሱ ጋር የሚነጋገርበት መድረክ ነው” ያለውም ለዚህ ነው። በዚህም መሠረት ጋዜጦች የሕዝብ መወያያ መድረክ በመሆን እና የጋራ ጉዳዮችን በማንሳት ሀገራዊ ውይይትን የማሳለጥ አቅማቸው ገዝፎ ይስተዋላል። ጋዜጣን ማንበብ ዜና ከማወቅ የዘለለ ጥቅም አለው።

“ማንበብ ሙሉ ሰው ያደርጋል” የሚለው አባባል በሀገራችን በስፋት የሚነገር ሆኗል። አባባሉ ጥልቅ ፍልስፍናን ይዟል። የእንግሊዛዊው ፈላስፋ ፍራንሲስ ቤከን (ሪዲንግ ሜክስ ኤ  ፉል ማን) ከሚለው ዝነኛ ንግግሩ የተቀዳ መሆኑን  መረጃዎች ያመለክታሉ። ይህ አባባል የንባብን አስፈላጊነት እና በአንድ ሰው ስብዕና ግንባታ ላይ ያለውን ጉልህ ሚና የሚገልጽ ነው።

ከፊደል መቁጠር ባሻገር  ዕውቀትን፣ ጥበብን፣ ልምድንና የአስተሳሰብ ብስለትን በማጎናጸፍ አንድን ሰው የተሟላ ሰብዕና እንዲኖረው እንደሚያደርግ ያመላክታል።

ንባብን ልምዳቸው ያደረጉ ሀገራት ዛሬ ምድርን ጨርሰው ሕዋን ስለመቆጣጠር ያስባሉ። ማርስን ካልኖርንባት ብለው ይሠራሉ። እጅግ የተራቁቁ የቴክኖሎጂ ፈጠራዎችን ለዓለም ያበረከቱት አንባቢ ሰዎች ናቸው። የንባብን ሁለንተናዊ ጥቅሞች እንመልከት፤

ዕውቀትን ያሳድጋል

ማንበብ ሰፋ ያለ ዕውቀት እንዲኖረን ያደርጋል። ታሪክን፣ ሳይንስን፣ ፍልስፍናን እና ሌሎች በርካታ የዕውቀት ዘርፎችን እንድንገነዘብ ያደርገናል። ይህ ዕውቀት በህይወታችን ውስጥ ለሚገጥሙን ችግሮች መፍትሄ እንድናገኝ እና የተሻለ ውሳኔ እንድንወስን ይረዳናል። ደራሲ እና ጋዜጠኛ ጳውሎስ ኞኞ “ዕውቀቴን ሁሉ ያገኘሁት በማንበብ ነው። በአጭሩ ማንበብ ዐዋቂ ብቻ ሳይሆን ሙሉ ሰው ያደርጋል” በማለት የንባብን የዕውቀት ምንጭነት መስክሯል።

የአስተሳሰብ እና የትንተና ክህሎትን ያዳብራል

በተለይም ወሳኝ አስተሳሰብን የሚጠይቁ ጽሑፎችን ማንበብ፣ የማሰብ እና የማገናዘብ ችሎታን ያሳድጋል። የተለያዩ ሀሳቦችን እንድንመረምር፣ እንድንተነትን እና የራሳችንን አመለካከት እንድንቀርጽ ያግዘናል።

ማህበራዊ ግንዛቤን ያሰፋል

ንባብ ከተለያዩ ባህሎች፣ የህይወት ልምዶች እና አመለካከቶች ጋር ያስተዋውቃል። ይህ ደግሞ ሌሎች ሰዎችን ለመረዳት እንዲሁም በህብረተሰብ ውስጥ የተሻለ ግንኙነት እንዲኖረን ያደርጋል። በማንበብ ያልኖርንበትን  ትላንት ዛሬ ላይ መኖር እንድንችል ዕድል እናገኛለን።

ውስጣዊ ጥንካሬን ይገነባል

ንባብ ከህይወት ፈተናዎች ጋር ለመታገል የሚያስችል ውስጣዊ ጥንካሬን እና ጥበብን ይሰጣል። የመጻሕፍት ዓለም ተስፋን፣ መነሳሳትን እና የህይወት መመሪያን በማቅረብ መንፈስን ያበረታል።

 

የዲሞክራሲ ምሶሶ ነው

ጋዜጦች መንግሥታትን ተጠያቂ በማድረግ፣ ሙስናን በማጋለጥ እና የዜጎችን ድምጽ በማሰማት እንደ “አራተኛው መንግሥት” ሆነው ያገለግላሉ። ይህ ለዲሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ ወሳኝ ሚና አበርክቷል።

የማህበራዊ ለውጥ አራማጅ ነው

በታሪክ ውስጥ ጋዜጦች ማህበራዊ እንቅስቃሴዎችን በማቀጣጠል እና በህብረተሰቡ ውስጥ ለውጥ እንዲመጣ በማድረግ ረገድ ትልቅ ሚና ተጫውተዋል። የሴቶች መብት፣ የሲቪል መብቶች እና የፀረ ቅኝ ግዛት ትግሎች በጋዜጦች አማካኝነት ከፍተኛ ድጋፍ አግኝተዋል።

የባህል መለዋወጫ መድረክ

ጋዜጦች የተለያዩ ባህሎችን፣ ወጎችን እና አመለካከቶችን በማስተዋወቅ በህዝቦች መካከል መግባባት እና መደማመጥ እንዲኖር አግዘዋል።

ዓለም አቀፋዊ ግንዛቤ መፍጠር

ጋዜጦች ስለሌሎች ሀገራት ዜናዎችን እና ክስተቶችን በማቅረብ የዓለም ህዝብ እርስ በእርሱ እንዲተዋወቅ እና እንዲረዳዳ ያደርጋሉ። ይህ ዓለም አቀፋዊ ግንዛቤን በመፍጠር ለሰላም እና ለትብብር አስተዋጽኦ አድርጓል።

የባህል እና የታሪክ መዝገብ

ጋዜጦች ታሪክን በወቅቱ ይመዘግባሉ። ለታሪክ አጥኚዎች እና ተመራማሪዎች እንደ ዋና ምንጭ ያገለግላሉ። የዛሬ ጋዜጣ ከዓመታት በኋላ ታሪክ ሆኖ ይቀርባል።

የጋዜጣ ንባብ ዕውቀትን ከማስጨበጥ ባለፈ፣ ጥልቅ ግንዛቤን፣ የዳበረ አስተሳሰብን እና ጠንካራ ሰብዕናን በመገንባት አንድን ሰው በህይወቱ የተሟላ እና ስኬታማ እንዲሆን ያግዘዋል።

በኩር ጋዜጣም ባለፉት ሠላሳ ዓመታት እነዚህን ሁሉ ጥቅሞች ለአንባቢዎቿ ስትሰጥ ኖራለች።

(አቢብ ዓለሜ)

በኲር የነሐሴ 19 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here