የግብ ጠባቂዎችን ትንሳኤ የሚያበስረዉ የጣና ዳርቻዉ ተስፋ

0
23

የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግን ስታዲየም ገብተው ጨዋታዎችን ሲመለከቱ አንድ ጎልቶ የሚታይ እውነታ አለ፤ በበርካታ ክለቦች በቋሚነት የግብ ክልሉን የሚጠብቁ የውጪ ሀገር ግብ ጠባቂዎች መሆናቸውን። ይህ ለምን ሆነ? የኢትዮጵያ እናቶች ግብ ጠባቂ መውለድ ተሳናቸው ወይስ የክለቦች የትኩረት ቅጣጫ ተዛባ? የሚለው ምላሽ የሚፈልግ ጥያቄ ነው። በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ በተለይም ባለፉት ዓመታት የውጪ ሀገር ግብ ጠባቂዎች ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ መጨመር በሀገሪቱ እግር ኳስ ላይ ግብ ጠባቂዎች ለማፍራት እና ለማብቃት የሚደረገው ጥረት መጨናገፉን ያሳያል። የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግን በቅርበት ለሚከታተል ማንኛውም ሰው የግብ ጠባቂ ቦታ በውጪ ዜጎች መወረሩ አዲስ ዜና አይሆንበትም። ከዩጋንዳ፣ ከጋና እና ከሌሎች የአፍሪካ ሀገራት የሚመጡ ግብ ጠባቂዎች የሊጉን አብዛኛውን ቦታ ተቆጣጥረውታል። ክለቦች ለአጭር ጊዜ ውጤት ሲሉ የውጪ ሀገር ተጫዋቾችን በውድ ዋጋ ሲያስፈርሙ ሀገር በቀል ግብ ጠባቂዎች የመሰለፍ እድል አጥተው ብሄራዊ ቡድኑ  አደጋ ላይ ወድቋል።

በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ከሚሳተፉት ክለቦች መካከል አብዛኛዎቹ ቁልፍ የሚባለውን የግብ ጠባቂ ቦታ ለውጪ ሀገር ተጫዋቾች ነው የሰጡት። የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የውጪ ተጫዋቾችን ቁጥር መቀነሱ ዘንድሮ ችግሩ በመጠኑም ቢሆን ቀንሶ እየተመለከትን ነው። ምንም እንኳ ቁጥሩ ቢቀንስም ችግሩ ግን ሙሉ በሙሉ አልተቀረፈም። አሁንም የሊጉ ጠንካራ ክለቦች ቁልፍ ቦታቸውን (የግብ ጠባቂ ቦታን) ለውጪ ዜጎች እየሰጡ ነው። ለምሳሌ ባሕር ዳር ከተማ ፓፔ ሰይዶን  ከሴኔጋል፣ ኢትዮጵያ ቡና ኢብራሂም ዳንላንዳ ከጋና፣ ፋሲል ከነማ ሞይስ ፓዋቲን- ከካሜሮን፣ መቻል አሊዮንዚ ናፊያናን -ከኡጋንዳ፣ ቅዱስ ጊዮርጊስ ሻኂኪሎ ፍርክን- ከኬኒያ  እና ሀዲያ ሆሳዕና አንድሪው ኦውሱ- ከጋና እንደ አንደኛ ተመራጭ እየተጠቀሙ ነው። በአጠቃላይም ዘጠኝ የውጪ ሀገር ተጫዋቾች በፕሪሚየር ሊጉ  ተመዝግበው እየተጫወቱ ይገኛሉ። በየክለቡ ያሉ የሀገር ውስጥ ግብ ጠባቂዎች የመሰለፍ እድል ሲያጡ ብቃታቸው ይወርዳል፤ በራስ መተማመናቸውም ይሸረሸራል። ይህ ደግሞ የግብ ጠባቂ ድርቅን ይፈጥራል።  ታዲያ አንድ ሀገር የራሷን ሊግ እያካሄደች ብዙ የሊጉ ግብ ጠባቂዎች ከውጪ የሚመጡ ከሆነ ለብሄራዊ ቡድን የሚሆን ግብ ጠባቂ ከየት ይገኛል?

ባለፉት ሦስት ዓመታት (2015-2017 ዓ.ም) አንድ የፕሪሚየር ሊግ ክለብ እስከ አምስት የውጪ ዜጎችን አስፈርሞ ማሰለፍ ይፈቀድለት ነበር። ይህ ሕግ ክለቦች በተለይም የገንዘብ አቅም ያላቸው ታላላቅ የሀገራችን ክለቦች የግብ ዘባቸውን ለውጪ ዜጎች አሳልፈው እንዲሰጡ በር ከፍቶ ነበር።  በወቅቱ ከ16ቱ የሊጉ ክለቦች ውስጥ ከ10 እስከ 12 የሚሆኑት ( 75 በመቶ የሚጠጉት ክለቦች) ቋሚ ግብ ጠባቂዎቻቸው የውጪ ዜጎች እንደነበሩ ቁጥራዊ መረጃዎች ያመለክታሉ። እነ ቻርለስ ሉኩዋጎ፣ ሚካኤል ሳማኪ እና ሌሎች ከምዕራብ እና ምሥራቅ አፍሪካ የመጡ ግብ ጠባቂዎች የሊጉን የግብ ክልል ተቆጣጥረውት እንደነበር አይዘነጋም። በውቀቱ ታዲያ የሀገር ውስጥ ግብ ጠባቂዎች ዕጣ ፈንታ የተጠባባቂ ወንበርን ማሞቅ ብቻ ሆኖ ነበር። ክለቦች ለውጤት ሲሉ ልምድ ያላቸውን የውጪ ተጫዋቾች መምረጣቸው- ኢትዮጵያውያን ግብ ጠባቂዎች በገዛ ሀገራቸው ሊግ የመጀመሪያ ተመራጭ እንዳይሆኑ አድርጓቸዋል። በእርግጥ በሀገር ውስጥ ለቦታው የሚመጥን ብቁ ተጫዋች የማፍራት ሥራ አለመሰራቱ ደግሞ ለችግሩ ዋነኛው መንስኤ ነው። እናም በእነዚህ ምክንያቶች የውጪ ግብ ጠባቂዎች የበላይነት ለኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን (ዋሊያዎቹ) የሚመጥን ግብ ጠባቂ ለማግኘት ትልቅ እንቅፋት ሆኖ ቆይቷል።

ዘንድሮ የእግር ኳስ ፌዴሬሽኑ የውጪ ተጫዋቾችን ቁጥር ከአምስት ወደ ሦስት ዝቅ ማድረጉ በሊጉ የኃይል ሚዛን እና የተጫዋቾች ምርጫ ላይ መሠረታዊ ለውጥ አምጥቶ ተመልክተናል። ክለቦች የግብ ዘቡን ለሚጠብቅላቸው ሳይሆን ግብ ለሚያስቆጥርላቸው (Strikers) እና ጨዋታ በሚቀይሩ አማካዮች ላይ ፊታቸውን እንዲያዞሩ አስገድዷቸዋል። በተጨማሪም ሀገሪቱ ያለችበት የውጪ ምንዛሬ እጥረት ተዳምሮ ክለቦች ፊታቸውን ወደ ሀገር ውስጥ ግብ ጠባቂዎች እንዲመልሱ አስገዳጅ ሁኔታ ፈጥሯል። እናም ዘንድሮ የውጪ  ሀገር ተወላጅ ግብ ጠባቂዎችን በቋሚነት የሚገለገሉ ክለቦች ቁጥር ከባለፉት ዓመታት ጋር ሲነፃፀር መቀነሱን የሊጉ አክሲዮን ማህበር ከሚያዘጋጀው ሳምንታዊ መጽሔጵት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል። ይህም ለሀገር ውስጥ ግብ ጠባቂዎች መልካም ዜና ነው።

በ2018 ዓ.ም የውጪ  ሀገር ተወላጅ ግብ ጠባቂዎች ቁጥር መቀነስ እና የሀገር ውስጥ ተጫዋቾች  የመሰለፍ እድል ማግኘት ግን ብቃት ያላቸው የሀገር ውስጥ ግብ ጠባቂዎች እየወጡ አለመሆኑን አንባቢያን ሊገነዘቡ ይገባል። አንድ ግብ ጠባቂ በቋሚነት ካልተሰለፈ የጨዋታ ልምድ (Match Fitness) እና በራስ መተማመን (Confidence)  እንደሚያጣ የኤስፒኤን መረጃ ያመለክታል።

የያዝነው የ2018 ዓ.ም ለኢትዮጵያ እግር ኳስ በተለይም ለግብ ጠባቂዎች አዲስ ምዕራፍ የተከፈተበት ዓመት ቢሆንም ከባለፉት ዓመታት የተሸጋገረው ጠባሳ ግን አሁንም በብሄራዊ ቡድኑ ላይ የራሱን ጥላ እንዳጠላ ይገኛል። ይህንን ሀገራዊ ክፍተት ለመድፈን ግን በባሕር ዳር ከተማ አንድ ተስፋ ሰጪ እንቅስቃሴ ተጀምሯል።

የቀድሞው የባሕር ዳር ከተማ የግብ ጠባቂ አሰልጣኝ አሻግሬ አድማሱ ይህንን ክፍተት ለመሙላት እና የነገውን ብሄራዊ ቡድን ወርቃማ ግብ ጠባቂዎች ለማፍራት እየተንቀሳቀሰ ይገኛል። አሰልጣኝ አሻገሬ አድማሱ ከአሚኮ ስፖርት ጋር በነበረው ቆይታ “የዋና አሰልጣኞች (Head Coaches) ትኩረታቸው የሜዳ ተጫዋቾች ላይ ብቻ ነው” ሲል ይናገራል። “በግብ ጠባቂዎች ላይ ትኩረት አድርጎ የሚሰራ የለም። ይህንን ክፍተት ለመሙላት የግብ ጠባቂዎች ፕሮጀክት በመንደፍ መንቀሳቀስ ጀምሬያለሁ” ብሏል። አሰልጣኝ አሻግሬ ችግሩን በሩቅ ከመተቸት ይልቅ የመፍትሄው አካል ለመሆን ከሐምሌ 25 ቀን 2016 ዓ.ም ጀምሮ ታዳጊዎችን እና ወጣቶችን በመመልመል በግብ ጣበቂዎች ላይ ትኩረት አድርጎ እየሰራ ይገኛል። በቀጣይ አራት ዓመታት ውስጥ አሁን የምናያቸውን የውጪ ሀገር ግብ ጠባቂዎች  በሚያሰለጥናቸው ታዳጊዎች  የመተካት እቅድ እንዳለው ተደምጧል።

በኢትዮጵያ እግር ኳስ ውስጥ ለግብ ጠባቂዎች የሚሰጠው ትኩረት ምን ያህል ነው? የሚለው ጥያቄ የብዙዎች መነጋገሪያ ነው። የግብ ጠባቂዎች ቦታ ከአካል ብቃት ባልተናነሰ በፍጥነት የመወሰን እና የጠቆመው የአዕምሮ ጥንካሬን የሚጠይቅ ቦታ ነው። አንድ ግብ ጠባቂ ስህተት ሲሰራ የሚደርስበት ጫና ከሌሎች ተጫዋቾች የበለጠ ከፍ ያለ ነው። ይሁን እንጂ ለቦታው ክለቦች አሰልጣኞች እና የእግር ኳስ ባለሙያዎች ብዙ ትኩረት ሲሰጡት አይስተዋልም። በፕሪሚየር ሊግ ደረጃ እንኳን የግብ ጠባቂ አሰልጣኝ መቅጠር እና ራሱን የቻለ ስልጠና የተጀመረው በቅርብ ጊዜ  መሆኑን የግብ ጠባቂዎች አሰልጣኝ አሻግሬ አድማሱ ያስረዳል። በፕሮጀክቱ ውስጥ እየሰለጠነ የሚገኘው ግብ ጠባቂ ገብረማርያም አዱኛ በሊጉ ውስጥ የውጪ ዜጎች መብዛት በሀገር ውስጥ ልጆች ላይ የስነ ልቦና ጫና ፈጥሮ እንደቆየ አልሸሸገም።

ችግሩ በፕሪሚየር ሊግ ብቻ የተወሰነ አይደለም። “በከፍተኛ ሊግ እና በአንደኛ ሊግ ውድድሮች ላይም ለግብ ጠባቂዎች የሚሰጠው ትኩረት ዝቅተኛ ነው ለማለት ያስደፍራል። ሜዳ ላይ ስንሰራ አሰልጣኞች ትኩረት የሚያደርጉት ተጫዋቾች (Outfield players) ላይ ነው። በረኞች የምንታየው መቼ እንደሆነ ታውቃላችሁ? ትንንሽ ጨዋታዎች (Minor Game) ሲኖር ነው ገብተን የምንጫወተው። ያ ለኛ ብዙ ነገር አጉድሎብናል” ሲል የችግሩን ስፋት ያስረዳል።

ሌላኛው ሰልጣኝ ሀብታሙ ደረበው ከሀገራችን ይልቅ በውጭ ሀገር ግብ ጠባቂዎች ላይ የሚደረገው ጥገኝነት መቆም እንዳአለበት ገልፆ መፍትሄው እንደዚህ አይነት ፕሮጀክቶችን ማበረታታት ነው ሲል ተደምጧል።  ሰልጣኝ ናሆም ፈለቀ በበኩሉ  ከታች ከታዳጊዎች ጀምሮ መሰራት እንዳለበት ይመክራል። “ተለዋዋጭነት (Flexibility) እና ክህሎትን በቀላሉ የመቀበል አቅም የሚኖረው ከታዳጊነት ሲጀመር ነው” ይላል። ናሆም ይህን ፕሮጀክት ከተቀላቀለ በኋላ ከፍተኛ ለውጥ እንዳመጣም ይናገራል። የፕሮጀክቱ ሰልጣኞች በሳምንት ሦስት ቀናት (ማክሰኞ፣ ሐሙስ እና ቅዳሜ) በከፍተኛ ወኔ ልምምዳቸውን እያከናወኑ ይገኛሉ። በወጣቶቹ ፊት ላይ የሚነበበው ተነሳሽነትም ነገ ሀገራቸውን ወክለው ትልቅ ደረጃ ለመድረስ ያላቸውን ጉጉት ያሳያል።

የባሕር ዳር አካባቢ ስፖርት ተቋማት የፕሮጀክቱን አስፈላጊነት ተረድተው እጃቸውን ዘርግተዋል። የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ስፖርት አካዳሚ ለስልጠናው የሚሆኑ ኳሶችን እና ቁሳቁስ አቅርቧል። የክልሉ ወጣቶች እና  ስፖርት ቢሮ ደግሞ የኳስ እና የሎጂስቲክስ ድጋፍ አድርጓል። አሁን ላይ ፕሮጀክቱ ገና የአራት ወራት እድሜ ቢኖረውም እያሳየ ያለው ለውጥ ግን ፈጣን ነው።

የፕሮጀክቱ እቅድም ለባሕር ዳር ከነማ ብቻ ሳይሆን ለሌሎችም የፕሪሚየር ሊግ ክለቦች ግብ ጠባቂዎችን ማቅረብ ነው። ኢትዮጵያ የራሷን ልጆች አምና ለትልቅ መድረክ ማብቃት ከቻለች የውጪ ምንዛሬ ማዳን ብቻ ሳይሆን በብሄራዊ ቡድን ደረጃ ያለባትን የግብ ጠባቂዎች ክፍተት በዘላቂነት መፍታት ትችላለች። የኢትዮጵያ እግር ኳስ ትንሳኤ የሚጀምረው ከግብ ክልል ነውና የበኩር ጋዜጣ የስፖርት ዝግጅት ክፍላችን ይህ ተግባር በሌሎች ከተሞችም መቀጠል የሚገባው የተቀደሰ ተግባር መሆኑን ያምናል::

(ስለሺ ተሾመ)

በኲር የታህሣስ 13  ቀን 2018 ዓ.ም  ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here