የግንባታ ቦታ ብክለትን ማገጃ

0
59

በቻይና ጂናን ከተማ በመካሄድ ላይ ባለ ግንባታ የድምፅ እና የብናኝ ብክለት በዙሪያው ወደ ሚገኝ አካባቢ እንዳይዛመት በዓየር በተወጠረ ግዙፍ የኘላስቲክ ፊኛ  በማልበስ ማገድ መቻሉን ኦዲቲ ሴንትራል ድረገጽ  አስነብቧል፡፡

 

ግዙፉ በዓየር ተሞልቶ የግንባታ ቦታውን ያለበሰው የኘላስቲክ ድንኳን 20 ሺህ ስኩዌር ሜትር ስፋት እና 50 ሜትር ቁመት  ተለክቷል፡፡

የግንባታ ቦታውን ባለበሰው  ኘላስቲክ ውስጥ ለሚገኙ ባለሙያዎች የሚተነፍሱትን ዓየር የሚያጣራ መሳሪያም ተገጥሞለታል፡፡ በመሆኑም ብክለቱ በዙሪያው ወደ ሚገኝ አካባቢ እንዳይዛመት ብቻ ሳይሆን በግንባታ ክልሉ ውስጥም ዓየሩ ንጹህ፣ የተጣራ እንዲሆን ያስቻለ መሆኑን ነው ድረ ገጹ ያስነበበው፡፡

 

ግዙፍ የኘላስቲክ ልባስ በግንባታ ላይ ለሚገኙ ባለሙያዎች በቂ ብርሃን እንዲያገኙም ብርሃን አስተላላፊ  እንዲሆን ተደርጓል፡፡ ይህ በራሱ  በሰው ሰራሽ መብራት  ሌላ ተጨማሪ ኃይል  እና ወጪ እንዳያስከትል ታስቦበት መከወኑም ነው የተብራራው፡፡ ሰው ሰራሽ ብርሃን ለለሊት ተግባራት ብቻ የሚያገለግል መሆኑን ልብ ይሏል፡፡

 

የኘላስቲክ ድንኳኑ ያለምንም ቋሚ እና ማገር ነው ተወጥሮ የግንባታ ቦታውን ያለበሰው፡፡ ይህን ለማድረግ በኘላስቲኩ ውስጥ በቋሚነት ዓየር በመግፋት የሚሞሉ (የሚወጥሩ) ሞተሮች መኖራቸው ነው በድረ ገጹ የተብራራው፡፡ የግንባታ ስራው ሲጠናቀቅ ዓየር መሙያዎቹን በማቆም እና የተወጠረው ኘላስቲክ እንዲተነፍስ ማድረግ ይቻላል፡፡ ከዚያም በቀላሉ አጣጥፎ በማጓጓዝ ለሌላ ግንባታ ማዋል እንደሚቻል ነው ድረገጹ ያስነበበው፡፡

 

(ታምራት ሲሳይ)

በኲር የሐምሌ 21 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here