የውጭ ሀገራት ዩኒቨርሲቲዎች ይበልጥ ትኩረት የሰጡት የግእዝ ቋንቋ ኢትዮጵያዊነቱን እንዳይረሳ መሥራት እንደሚገባ ተጠቆመ፡፡
ለግእዝ ትምህርት ትኩረት መስጠት እንደሚገባ የተገለጸው የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ “የአብነት ትምህርት ለዘመናዊ የኢትዮጵያ ሥነ-ትምህርት” በሚል መሪ ሐሳብ ዐውደ ጥናት ባካሄደበት ወቅት ነው፡፡ በዐውደ ጥናቱ ላይ የግእዝ ቋንቋ ጥናት ለኢትዮጵያ የዕውቀት እና የምርምር ዘርፍ ያበረከተው አስተዋጽኦ እና ቀጣይ ቢሆኖች ተመላክተውበታል፡፡
በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የሂውማኒቲ ፋኩልቲ ዲን ዋልተንጉሥ መኮንን (ዶ/ር) የመክፈቻ ንግግር አድርገዋል፡፡ የኢትዮጵያ የትምህርት ሥርዓት ከ19ኛው ክፍለ ዘመን ጀምሮ ከውጪ በመጣው የትምህርት ሥርዓት ተጽዕኖ እንዳረፈበት ተናግረዋል፡፡ ይህም የኢትዮጵያ ትምህርት ከውጪ የመጣ እንደሆነ ተደርጎ እንዲታይ አድርጓል ብለዋል፡፡
ዶክተር ዋልተንጉሥ አክለውም የኢትዮጵያውያንን አዕምሮ ያበሩ፣ ምድራዊ ዕውቀትን ያካበቱ፣ የሥነ ምግባር መሠረት የሆኑ እና በሀገር ግንባታ ላይ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ያበረከቱት የአብነት ትምህርት ቤቶች መሆናቸውን ሁሉም ሊገነዘብ ይገባል ብለዋል፡፡
ግእዝ የሁሉም ኢትዮጵያዊ ቋንቋ ነው ያሉት ደግሞ በባሕርዳር ዩኒቨርሲቲ መምህር እና ተመራማሪ ሙሉቀን አንዱዓለም (ዶ/ር) ናቸው፡፡ በመሆኑም ወጣቱ ትውልድ የሀገሩን ታሪክ፣ ወግና እና ባሕል በቅጡ ለመረዳት የግዕዝ ቋንቋን ሊማር ይገባል ብለዋል፡፡
በዓለም ላይ 31 ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ግእዝን እያስተማሩ እንደሚገኙ ዶክተር ሙሉቀን ገልጸዋል፡፡ ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲም በመጀመሪያ እና ሁለተኛ ዲግሪ የግእዝ ቋንቋን እያስተማረ እንደሚገኝ አስታውቀዋል፡፡ የሦስተኛ ዲግሪ ለመጀመርም ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
ጥንታዊውን የግእዝ ቋንቋ ከታችኛው የትምህርት ደረጃ ጀምሮ በመስጠት ወደ ቀድሞ ክብሩ መመለስ እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡
(ስማቸው አጥናፍ)
በኲር የጥቅምት 24 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም


