የግዮን ንግሥቶች ከፍታ

0
151

የ2016 የሴቶች ከፍተኛ ሊግ ውድድር በቅርቡ መጠናቀቁ ይታወሳል። የሀገሪቱ ሁለተኛው የሊግ እርከን በሆነው ከፍተኛ ሊግ ዘንድሮ ሁለት የአማራ ክልል ክለቦች ተሳትፈዋል፣ ባሕር ዳር ከተማ የሴቶች እግር ኳስ ክለብ እና ፋሲል ከነማ።

በዘንድሮው የሴቶች ከፍተኛ ሊግ ውድድር 11 ክለቦች ናቸው የተሳተፉት። ሁሉም ክለቦች ተቀራራቢ ነጥቦችን በመያዝ ዋንጫ ለማንሳት እና ላለመውረድ ከፍተኛ ፉክክር ሲያደርጉ ተስተውሏል።

በደረጃ ሰንጠረዡ አናት ላይ ሆነው የጨረሱት ሁለቱ ክለቦች ወደ ላይኛው የሊግ እርከን ፕሪሚየር ሊጉን ተቀላቅለዋል።  ቂርቆስ ክፍለ ከተማ እና ባሕር ዳር ከተማ የሴቶች ፕሪሚየር ሊግን የተቀላቀሉ ክለቦች ናቸው።

በደረጃ ሰንጠረዡ ግርጌ ላይ ሆነው የጨረሱት ሁለት ክለቦች ደግሞ ከከፍተኛ ሊጉ ወርደዋል። ሞጆ ከተማ እና ጉለሌ ክፍለ ከተማ ከከፍተኛ ሊጉ የወረዱ ክለቦች ሆነዋል።

ቤተልሔም ሽመልስ ከፋሲል ከነማ እና ምህረት ታፈሰ ከወረደው ሞጆ ከተማ በ11 ግቦች ከፍተኛ ኮከብ ግብ አስቆጣሪዎች ሆነው ጨርሰዋል። የመድረኩ እንግዳ የነበሩት ሸገር ከተማዎች የስፖርታዊ ጨዋነት ዋንጫ ተበርክቶለታል። በሊጉ ረዥም ጊዜ የቆዩት ቂርቆሶች በመጨረሻ ተሳክቶላቸው ፕሪሚየር ሊጉን ተቀላቅለዋል። አዲስ አዳጊዎቹ 43 ነጥቦችን በመሰብሰብ ነው ዓመቱን ያጠናቀቁት። ድንቅ የውድድር ጊዜ ያሳለፉት ቂርቆስ ክፍለ ከተማዎች  ካደረጓቸው 20 መርሐ ግብሮች 12ቱን ረተዋል። በሰባቱ ነጥብ ሲጋሩ አንድ ጨዋታ ብቻ ነው የተሸነፉት። በመድረኩ አስፈሪ የፊት መስመር ካላቸው ውስጥም ከቀዳሚዎች ተርታ ይሰለፋሉ። 31 ግቦችንም ከመረብ ማገናኘት ችለዋል። በተመሳሳይ በሊጉ ጠንካራ የተከላካይ ክፍል ካላቸው ክለቦች በሦስተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል- ቂርቆሶች። በአጠቃላይ 16 ግቦች ብቻ ተቆጥሮባቸዋል።

በደረጃ ሰንጠረዡ ሁለተኛ ሆነው ያጠናቀቁት ባሕር ዳር ከተማ የሴቶች ቡድን፣ ድጋሚ ከአንድ ዓመት በኋላ ወደ ፕሪሚየር ሊጉ ተመልሰዋል። የባሕር ዳር ከተማ የሴቶች ቡድን በ2013 ዓ.ም የውድድር ዓመት መጨረሻ ፕሪሚየር ሊጉን ተቀላቅለው እንደነበር አይዘነጋም። የግዮን ንግሥቶች በ2014 ዓ.ም በሴቶች ፕሪሚየር ሊግ ቢያሳልፉም ውድድሩ ከብዷቸው ባደጉበት ዓመት ወደ መጡበት ከፍተኛ ሊግ ወርደው ነበር፡፡

ሁለተኛ ደረጃን ይዘው የጨረሱት የግዮን ንግሥቶች ካደረጓቸው 20 ጨዋታዎች ግማሹን አሸንፈዋል። በአምስቱ ነጥብ ሲጋሩ በተመሳሳይ በአምስት ጨዋታዎች ተሸንፈዋል። ባሕር ዳር ከተማ የሴቶች ቡድን በመጀመሪያው ሳምንት በአምቦ ፊፋ ጎል አንድ ለባዶ መሸነፉን ተከትሎ ጥሩ አጀማመር እንዳልነበራቸው ይታወሳል።

ይሁን እንጂ ቀስ በቀስ እየተሻሻሉ ተፎካካሪ ክለብ መሆናቸውን አስመስክረዋል። በመጀመሪያው ዙር ሦስት ጨዋታዎችን ብቻ የተሸነፉ ሲሆን በዘጠነኛ ሳምንት በአቃቂ ቃሊቲ ሁለት ለአንድ የተሸነፉበት እና በ11ኛ ሳምንት በቂርቆስ ክፍለ ከተማ የተሸነፉበት ሌላኛው መርሐ ግብር ነው። በሁለተኛው ዙር ደግሞ በ17ኛ ሳምንት በፋሲል ከነማ እና በ22ኛ ሳምንት በቂርቆስ ክፍለ  ከተማ በተመሳሳይ ተረትተዋል።

የግዮን ንግሥቶች በ2013 ዓ.ም ለመጀመሪያ ጊዜ የሴቶችን ፕሪሚየር ሊግ በተቀላቀሉበት ዓመት ጋር ካሳዩት አቋም ጋር ሲነፃፀር ዘንድሮ ትንሽ ደከም ብለው ታይተዋል። ምንም እንኳ በወቅቱ አስር ክለቦች ብቻ የተፎካከሩ ቢሆንም በአንድ መርሐ ግብር ብቻ መሸነፋቸው የሚታወስ ነው። በዚህ ዓመት በሴቶች ከፍተኛ ሊግ ውድድር ልክ እንደ ቂርቆስ ክፍለ ከተማ አስፈሪ የፊት መስመር ያላቸው እንደነበሩ ቁጥሮች ይመሰክራሉ።

31 ግቦችን በተጋጣሚያቸው መረብ ላይ አሳርፈዋል። በአንፃሩ ደግሞ ጠንካራ የኋላ ክፍል ካላቸው ክለቦች መካከል በቀዳሚነት ይቀመጣሉ። 11 ግቦች ብቻ ነው የተቆጠሩባቸው። ባሕር ዳር ከተማ የሴቶች እግር ኳስ ክለብ ባለፉት ሦስት ዓመታት በመድረኩ ከታዩ አስደናቂ የኋላ ክፍል ካላቸው ክለቦች ውስጥ ቀዳሚውን ሥፍራ ይይዛሉ።

አሚኮ በኲር ዝግጅት ክፍል ከቡድኑ ዋና አሰልጣኝ ሰርካዲስ ሠውነት ጋር ቆይታ አድርጓል። አሰልጣኝ ሰርካዲስ ሠውነት ድጋሚ ወደ ፕሪሚየር ሊጉ በመመለሳቸው ወደር አልባ ደስታ ተሰምቶናል ብላለች። በ2014 ዓ.ም ወደ ፕሪሚየር ሊጉ ባደጉበት ዓመት ወደ ከፍተኛ ሊግ መውረዳቸው ቅር አሰኝቷቸው እንደነበር አሰልጣኟ ታስታውሳለች።

እንዲሁም ባለፈው ዓመትም በመጨረሻዎቹ ጥቂት ሳምንታት ባሳዩት ደካማ አቋም ባለመሳካቱ ደስታ ርቋቸው እንደቆየ በመናገር፣ ዘንድሮ ግን ጥረታቸው ፍሬ በማፍራቱ ትልቅ ደስታ ተሰምቷቸዋል።  የአምናውን ስህተታቸውን ላለመድገም በልዩ ትኩረት መሥራታቸው ለውጤት እንደበቁ አሰልጣኝ ሰርካዲስ ተናግራለች።

እንደ አሰልጣኟ ገለጻ ጥቃቅን ስህተቶች ሳይቀሩ ዋጋ እንደሚያስከፍላቸው በመረዳት በተቻለ መጠን ስህተቶችን ቀንሰው ዓመቱን ጨርሰዋል። በየጊዜው በሚፈጠሩ ክፍተቶች  በመነጋገር ችግሮቻቸውን መቅረፋቸው ዓመቱን በደስታ እንዲጨርሱ አግዟቸዋል።

በቀጣይ በአዲሱ የ2017 ዓ.ም የውድድር ዘመን ደግሞ ተፎካካሪ ለመሆን እና በሊጉ ለመቆየት ከወዲሁ በርካታ ሥራዎችን ለመሥራት  ዝግጅት እያደረጉ ነው። የስፖርት ክለቡ የቦርድ አመራሮችም የሴቶችን ክለብ ለማጠናከር እና የማይቋረጥ ድጋፍ ለማድረግ ቃል መግባታቸውን አስልጣኝ ሰርካዲስ ነግራናለች።

የግዮን ንግሥቶች  በከፍተኛ ሊግ ቆይታቸው የነበሩባቸውን ከፍተኛ ጭንቀት፣ ግብ ለማስቆጠር እና ለማሸነፍ ያላቸውን ከልክ ያለፈ ጉጉት በውድድር ዓመቱ ሜዳ ላይ የታዩ ችግሮች ናቸው። በመጪው ክረምት ወራት በሚከፈተው የተጫዋቾች የዝውውር ወቅት አዳዲስ ተጫዋቾችን በማስፈረም እና የነባሮችን ውል በማደስ ቡድናቸውን የማጠናከር ሥራም ይሠራሉ።

ከወዲሁ በርካታ ዕቅዶችም ተዘጋጅተዋል። በመጀመሪያው የፕሪሚየር ሊግ ቆይታቸው በርካታ ነገሮችን የተማሩ ሲሆን በአዲሱ የውድድር ዓመት በሊጉ ለመፎካከር እንደሚረዳቸው አሰልጣኝ ሰርካዲስ ሠውነት ገልጻለች።

የአማራ ክልል ሌላኛው ተወካይ ፋሲል ከነማ የሴቶች እግር ኳስ ቡድን ዘንድሮ አስደናቂ የውድድር ጊዜ ነው ያሳለፈው። ቡድኑ በ31 ነጥቦች አራተኛ ደረጃን ይዞ ነው የጨረሰው። ልክ እንደ ባሕር ዳር እና ሸገር ከተማ በአጠቃላይ በውድድር ዓመቱ አምስት ጨዋታዎችን ብቻ ነው የተሸነፈው። ምንም እንኳ በርካታ ግቦችን ካስቆጠሩት ክለቦች ተርታ ቢሰለፉም ካስቆጠሯቸው ግቦች ያልተናነሰ 24 ግቦች ተቆጥሮባቸዋል።

ፋሲል ከነማ የሴቶች ቡድን ከባለፉት ዓመታት አንጻር በዚህ ዓመት የተሳካ የውድድር ጊዜ ማሳለፉ አያጠያይቅም። ነገር ግን የተከላካይ ክፍሉን ክፍተቶች  እና ሌሎችን ሜዳ ውስጥም ከሜዳ ውጪም ያሉባቸውን ችግሮች መቅረፍ ከቻሉ በአጭር ጊዜ ውስጥ በፕሪሚየር ሊጉ የምንመለከታቸው ይሆናል።

(ስለሺ ተሾመ)

በኲር ግንቦት 12 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here