የ2018 የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪሚየር ሊግ ነሐሴ 25 ቀን 2017 ዓ.ም ጀምሯል። በመድረኩ 14 ክለቦች የሚሳተፉ ይሆናል። በአዲሱ የውድድር ዓመት በሊጉ ከሚካፈሉ ክለቦች መካከል የባሕር ዳር ከተማ ሴቶች ክለብ ይገኝበታል።
ባሕር ዳር ከተማ የሴቶች ክለብ በ2013 ዓ.ም መጨረሻ ነበር ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ፕሪሚየር ሊጉ ያደገው። ነገር ግን የግዮን ንግሥቶች ሊጉን መላመድ ባለመቻላቸው በመጡበት ዓመት ተመልሰው ወደ ታችኛው የሊግ እርከን መውረዳቸው አይዘነጋም። ከሁለት ዓመታት በኋላ ደግሞ ድጋሚ ወደ ፕሪሚየር ሊጉ በመመለስ እየተፎካከሩ ይገኛሉ።
የግዮን ንግሥቶች በ2017 የውድድር ዓመት ሊጉ ከብዷቸው ተስተውለዋል፡፡ ከመውረድ ለጥቂት መትረፋቸውም አይዘነጋም። ከ14 ክለቦች በደረጃ ሰንጠረዡ 12ኛ ሆነው መጨረሳቸውም የሚታወስ ሲሆን የወረደውን ቂርቆስ ክፍለ ከተማን በሁለት ግቦች በመብለጥ ነበር ከመውረድ የተረፉት። በአዲሱ የውድድር ዓመት ግን ጠንካራ ፉክክር ለማድረግ ቀደም ብለው ተጫዋቾችን በማስፈረም ጭምር የቅድመ ዝግጅት ሥራዎችን ሠርተዋል።
የክለቡ ዋና አሰልጣኝ ሰርካዲስ ሰውነት ከአሚኮ ስፖርት ጋር በነበራት ቆይታ ከዚህ በፊት የነበሩባቸውን ችግሮች ለመቅረፍ ሜዳ ውስጥም ከሜዳ ውጪም ጥሩ ዝግጅት እያደረጉ መሆናቸውን ተናግራለች። በ2017 የውድድር ዓመት በተጫዋች ዝውውር በንቃታ ባለመሳተፋቸው ምክንያት ደካማ የውድድር ጊዜ ማሳለፋቸውን ያስታወሰችው አሰልጣኟ ዘንድሮ ግን በርከት ያሉ ተጫዋቾችን አስፈርመናል ብላለች።
የግዮን ንግሥቶች በሁሉም የሜዳ ክፍል የሚፈልጓቸውን ተጫዋቾች ወደ ቡድናቸው አምጥተዋል። በዚህ ክረምት ባጠቃላይ 12 አዳዲስ ተጫዋቾችን አስፈርመዋል፤ የሰባት ነባር ተጫዋቾችንም ውል ያደሱ ሲሆን ታዳጊዎችንም ከታች አሳድገዋል። ለቡድኑ አዲስ የፈረሙት ተጫዋቾች በተጠናቀቀው የውድድር ዓመት በቀድሞ ክለባቸው ምርጥ ብቃታቸውን ያሳዩ ናቸው። እናም እነዚህ ተጫዋቾች የክለቡን ዕቅድ ለማሳካት እና ተፎካካሪ ለመሆን ይጠቅሙናልም ብላለች።
በሊጉ ተፎካካሪ እንዲሆኑ የስፖርት ክለቡ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ መሆኑንም ዋና አሰልጣኟ ተናግራለች። የክለቡ ኃላፊዎች እና የቦርድ አመራሮች የክለቡን ችግር በጥልቀት በመረዳት መፍትሔ መስጠታቸውንም አሰልጣኝ ሰርካዲስ አስታውሳለች። “የክለቡ አመራሮች እና የቦርድ ኃላፊዎች ለሴቶች የሚያደርገው ድጋፍ ጥሩ ነው፤ በሚገባ እያበረታቱን ይገኛሉ”። ብላለች አስልጣኟ።
ዘንድሮ ከተጫዋቾች ምልመላ ጀመሮ የተሻለ ሥራ ተሠርቷል ያለችው አሰልጣኝ ሰርዲስ ባሳለፍነው ዓመት የነበሩባቸውን ድክመቶች በማረም እና ጠንካራ ጎናቸውን በማስቀጠል አዲሱን የውድድር ዓመት ለመጀመር ቡድኑ ውስጥ ከፍተኛ ተነሳሽነት አለ ተብሏል። አዲስ ፈራሚዎችን ከነባሮች ጋር በማዋሀድ እና ቅንጅት በመፍጠር በውድድር ዓመቱ መጨረሻ ጥሩ ውጤት ለማስመዝገብ ዕቅድ ይዘዋል።
በ2018 የውድድር ዓመት ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ለዋንጫ ትልቅ ግምት የተሰጠው ሲሆን ሀዋሳ ከተማ፣ ሲዳማ ቡና፣ ኢትዮ ኤሌክትሪክ እና መቻልን የመሳሰሉትም ልክ እንደ ወትሮው ጠንካራ ተፎካካሪ ይሆናሉ ተብሎ ይጠበቃል። በወረዱት ቂርቆስ ክፍለ ከተማ እና ሀምበሪቾ ዱራሚ ምትክ ሸገር ከተማ እና ይርጋጨፌ ቡና በሊጉ የሚሳተፉ ይሆናል።
የመጀመሪያው ዙር ውድድር አዲስ አበባ ላይ የተጀመረ ሲሆን በመክፈቻው መርሀ ግብር ልደታ ክፍለ ከተማ ከአዲስ አበባ ከተማ፣ አርባምንጭ ከተማ ከይርጋ ጨፌ ቡና እና ሲዳማ ቡና ከቦሌ ክፍለ ከተማየመጀመሪያ ሳምንት ጨዋታቸውን አድርገዋል፡፡ መቻል ከኢትዮ ኤሌክትሪክ፣ ሸገር ከተማ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ፣ ባሕር ዳር የሴቶች ክለብ ከድሬዳዋ ከተማ እና አዳማ ከተማ ከሀዋሳ ከተማ የሚጫወቱ ይሆናል፡፡
የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪሚየር ሊግ የቅርብ ጊዜ ውድድር ነው። ገና 13 ዓመታት ዕድሜን ብቻ ነው ያስቆጠረው። በዚህ አጭር ጊዜ ውስጥ ማራኪ እና ጥሩ ፉክክር የሚታይበት ሊግ ሆኗል። ምንም እንኳ ክለቦች የንግድ ባንክን ኃያልነት መግታት ቢሳናቸውም እስከ መጨረሻው ሳምንት መርሀግብር ድረስ የሚያደርጉት ተጋድሎ ግን ሊጉ እንዲወደድ እና ድባቡ እንዲደምቅ አስችሎታል። የሴቶች ፕሪሚየር ሊግ ታዳጊዎች ዕድል የሚያገኙበት እና የብሄራዊ ቡድን ተጫዋቾችም የሚወጡበት ቢሆንም አሁንም ድረስ ግን ሊጉ በብዙ ችግሮች የተተበተበ ነው።
(ስለሺ ተሾመ)
በኲር የነሐሴ 26 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም