የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪሚየር ሊግ የመጀመሪያው ዙር ውድድር በአዲስ አበባ አበበ ቢቂላ ስቴዲየም ተደርጎ ተጠናቋል። በዚህ መድረክ 14 ክለቦች እየተሳተፉ ሲሆን የአምናው ሻምፒዮና ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የመጀመሪያውን ዙር ውድድር በበላይነት ጨርሷል። ንግድ ባንክ የሴቶች ቡድን ከተከታዩ ሀዋሳ ከተማ በስምንት ነጥብ ቢርቅም ሌሎች ክለቦች ግን ተቀራራቢ ውጤት ይዘው ነው በደረጃ ሰንጠረዡ የሚገኙት።
በዚህ መድረክ ሻምፒዮን የሚሆነው ክለብ በካፍ ሻምፒዮንስ ሊግ የሴካፋ ዞን ማጣሪያ ኢትዮጵያን የሚወክል ይሆናል። ሊጉን መቋቋም ያልቻሉ ሁለት ክለቦች ደግሞ ወደ ታችኛው የሊግ እርከን ይወርዳሉ። የባሕር ዳር ከተማ ሴቶች ክለብ አሰልጣኝ ሰርክዓዲስ እውነቱ ከአሚኮ በኩር ስፖርት ዝግጅት ክፍል ጋር በነበራት ቆይታ የመጀመሪያው ዙር ውድድር ጠንካራ ፉክክር የታየበት እንደነበር ነግራናለች።
“ከባለፉት ዓመታት በላይ ሁሉም ቡድን የተሻለ ስብስብ ይዞ የጀመረ በመሆኑ ፉክክሩ ጠንካራ ነው። እንደ በፊቱ ውጤቱን ቀድሞ መገመት የማይቻልበት እና አንዱ ክለብ ሌላኛውን በቀላሉ የማያሸንፍበት ሆኖ ነው የመጀመሪያው ዙር የተጠናቀቀው” ስትል ተደምጣለች፤ አሰልጣኟ።
በሴቶች ፕሪሚየር ሊግ ብቸኛው የአማራ ክልል ተወካይ ባሕር ዳር ከተማ የሴቶች ቡድን ነው። የግዮን ንግሥቶች የመጀመሪያውን ዙር ውድድር 15 ነጥብ በመሰብሰብ ዘጠነኛ ደረጃን ይዘው ጨርሰዋል፤ ካደረጓቸው 13 ጨዋታዎችም በአራቱ ብቻ ነው ያሸነፉት። ሦስቱን ሲሸነፉ በስድስቱ ደግሞ ነጥብ ተጋርተዋል። አዲስ አዳጊው ክለብ በዚህ ዓመት ደካማ የኋላ ክፍል ካላቸው ቀዳሚ ክለቦች መካከልም ሦስተኛ ደረጃ ላይ ይቀመጣል። በእርግጥ የፊት መስመራቸውም ቢሆን መሻሻል እንዳለበት ቁጥሮች ይመሰክራሉ።
የግዮን ንግሥቶች በ2013 ዓ.ም መጨረሻ ነበር ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ፕሪሚየር ሊጉ ያደጉት። ነገር ግን ሊጉን መልመድ ተስኗቸው በመጡበት ዓመት ተመልሰው ወደ ታችኛው የሊግ እርከን ወርደዋል። በ2015 እና 2016 ዓ.ም በከፍተኛ ሊጉ በመቆየት ዘንድሮ ድጋሚ በፕሪሚየር ሊጉ እየተሳተፉ ነው። በአሰልጣኝ ሰርክዓዲስ እውነቱ የሚመሩት የግዮን ንግሥቶች ከመጀመሪያው የፕሪሚየር ሊግ ቆይታቸው አንጻር ዘንድሮ የተሻሉ ቢሆኑም ከወራጅ ቀጣናው ግን በአራት ነጥብ ብቻ ነው የሚርቁት።
አጀማመራቸው ጥሩ የነበረ ቢሆንም በተለይ በመጨረሻዎቹ አራት መርሀግብሮች ደካማ አቋም አሳይተዋል፤በእነዚህ ጨዋታዎች ሁለት ነጥብ ብቻ መሰብሰባቸውም አይዘነጋም። የመጀመሪያው ዙር ውድድር ፈታኝ እንደነበር የተናገረችው አሰልጣኟ ቡድናቸው የኋላ ክፍሉ የመከላከል ድክመት እንደነበረበት አልሸሸገችም፡፡
እነዚህን ችግሮች ላለመድገምም የተሻለ ዝግጅት በማድረግ በሁለተኛው ዙር እንደሚመለሱ ነው የተናገረችው። ምንም እንኳ በጥር የተጫዋቾች የዝውውር ወቅት ተጫዋች ማግኘት ከባድ ቢሆንም ያሉባቸውን ክፍተቶች ለመሙላት ወደ ገበያ እንደሚውጡም ፍንጭ ሰጥታለች ። ግብ ጠባቂ፣ የመሀል ተከላካይ እና የአማካይ ሥፍራ ተጫዋች ቡድኑ ማስፈረም እንደሚፈልግም ጠቁማለች።
የግዮን ንግሥቶች በውድድር ዓመቱ መጨረሻ በደረጃ ሰንጠረዡ ወገብ ላይ ሆነው ለማጠናቀቅ እቅድ አላቸው። ታዲያ በመጀመሪያው ዙር ውድድር ስቴዲየም በመግባት ሲያበረታቷቸው እና ሲደግፏቸው የነበሩትን ደጋፊዎች አስተዋጽኦቸው የላቀ መሆኑን በማስታወስ በቀጣይም ድጋፋቸው እንዳይለያቸው አሰልጣኝ ሰርክዓዲስ ተናግራለች።
በአሰልጣኝ ብርሃኑ ግዛው የሚመራው ቡድን ቀሪ አንድ ጨዋታ እያለው ነው በ34 ነጥብ የደረጃ ሰንጠረዡን እየመራ የጨረሰው። ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የሴቶች ቡድን የፕሪሚየር ሊግ ዋንጫውን ለማሳካት ዘንድሮም በትክክለኛው መንገድ እየተጓዘ ነው። ንግድ ባንክ የሴቶች ቡድን በሁሉም የሜዳ ክፍል ጠንካራ የተጫዋቾች ስብስብን ይዟል። ክለቡ በፕሪሚየር ሊጉ አስፈሪ የፊት መስመር እና በቀላሉ የማይረበሽ ጠንካራ የኋላ ክፍል የያዘ ቀዳሚ ክለብ ነው።
በአጠቃላይ 31 ግቦችን በተጋጣሚዎቹ ላይ አዝንቧል። ይህም በአማካይ ከሁለት ግብ በላይ በየጨዋታው የተጋጣሚን መረብ እንደሚጎበኝ ቁጥሮች ይመሰክራሉ። ከየትኛውም ክለብ ያነሰ ሰባት ግቦች ብቻ ተቆጥሮበታል። እስካሁንም አንድም ጨዋታ ያልተሸነፈ ብቸኛው የፕሪሚየር ሊግ ክለብ ነው። ካደረጋቸው 12 ጨዋታዎች በዘጠንኛ ሳምንት ብቻ ነው ከልደታ ክፍለ ከተማ ጋር ነጥብ ተጋርቶ ከሜዳ የወጣው።
ቀሪውን 11 መርሀ ግብር ግን በድል ተወጥቷል። ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የሴቶች ቡድን ልክ እንደ ባለፉት ዓመታት ዘንድሮም አስደናቂ አቋም በማሳየት ነው የመጀመሪያውን ዙር የጨረሰው። ለተከታታይ ስድስተኛ ጊዜ የፕሪሚየር ሊጉን ዋንጫ ለማንሳት በሁለተኛው ዙር የበለጠ ተጠናክሮ ይመጣል ተብሎ ይጠበቃል።
ከመሪው ንግድ ባንክ በስምንት ነጥብ ርቆ በ26 ነጥብ ሁለተኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ሀዋሳ ከተማ ነው። ክለቡ እንደ ወትሮው ዘንድሮም ጠንካራ ተፎካካሪ መሆን ችሏል። ከንግድ ባንክ ቀጥሎ ጠንካራ የፊት መስመር ያለው ክለብም ነው። ካከናወናቸው 13 ጨዋታዎች ስምንቱን አሸንፏል፤ በሦስቱ ሲሸነፍ፤ ሁለት ጨዋታዎችን ደግሞ ነጥብ ተጋርቶ ከሜዳ ወጥቷል።
የውድድር ዓመቱ ከመጀመሩ ቀደም ብሎ የዘንድሮውን የፕሪሚየር ሊግ ዋንጫ ያሳካሉ የሚል ተስፋ ተጥሎባቸው እንደነበር አይዘነጋም። ቡድኑ በመክፈቻው መርሀ ግብር በሲዳማ ሦስት ለባዶ ተሸንፎ መጥፎ አጀማመር ቢያደርግም ቀስ በቀስ ወደ ቀድሞ አቋማቸው በመመለስ ተፎካካሪ ሆነዋል። በአሰልጣኝ መሰረት ማኔ የሚመሩት ሀዋሳ ከተማዎች በሁለተኛው ዙር የተሻለ የውድድር ጊዜ እንደሚያሳልፉ በብዙዎች እምነት ተጥሎባቸዋል።
የመጀመሪያውን ዙር 24 ነጥብ በመያዝ ሦስተኛ ደረጃን ይዞ ያጠናቀቀው መቻል የሴቶች ክለብ ነው። ቡድኑ ከባለፈው ዓመት አንጻር ሲታይ ዘንድሮ ሜዳ ላይ ብዙ መሻሻል ታይቶበታል። የፊት መስመሩ ግን አሁንም አልፎ አልፎ ግብ የማስቆጠር ችግር ይስተዋልበታል። የኋላ ክፍሉ በቀላሉ የማይረበሽ ሲሆን ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ቀጥሎ በፕሪሚየር ሊጉ ጠንካራ የተከላካይ ክፍል የያዘ ቡድንም ነው። ስምንት ግቦች ብቻ እንደተቆጠሩበት መረጃዎች ያመለክታሉ።
መቻል የሴቶች ቡድን ካደረጓቸው 13 ጨዋታዎች በሰባቱ ሲያሸንፉ፤ በሦስት ጨዋታዎች ተሸንፈዋል። በተመሳሳይ በሦስት መርሀ ግብሮች ነጥብ ተጋርተዋል። ምንም እንኳ ከመሪው ንግድ ባንክ ጋር ያለው የነጥብ ልዩነት 10 ቢሆንም በሁለተኛው ዙር ያሉባቸውን ክፍተቶች መድፈን ከቻሉ ጥሩ የሊጉ ተፎካካሪ ይሆናሉ ተብሎ ይጠበቃል።
ሲዳማ ቡና በ23 ነጥብ አራተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። ለወትሮው ጠንካራ የነበረው ኢትዮ ኤሌክትሪክ የሴቶች ቡድን ግን በዚህ ዓመት ትንሽ ተዳክሞ ታይቷል። የፊት መስመሩ ደካማ ሲሆን የኋላ ክፍሉ ግን ልክ እንደ አምናው አስደናቂ አቋም እያሳየ ይገኛል። ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እኩል ሰባት ግቦች ብቻ እንደተቆጠሩበትም መረጃዎች ያሳያሉ። ኢትዮ ኤሌክትሪክ የሚያገኙትን የግብ ዕድሎች መጠቀም ከቻሉ ወደ መሪው የሚያስጠጋቸውን ውጤት ማስመዝገብ ይችላሉ።
ቂርቆስ ክፍለ ከተማ እና ሀምበሪቾ ዱራሜ ከታች ግርጌ ላይ የሚገኙ ክለቦች ናቸው። አዲስ አዳጊው ቂርቆስ ክፍለ ከተማ በዘጠኝ ነጥብ 13ኛ ደረጃ ላይ ነው የተቀመጠው። ክለቡ እስካሁን በሁለት ጨዋታዎች ብቻ ነው ያሸነፈው። ቂርቆስ ክፍለ ከተማ ከፕሪሚየር ሊጉ ደካማ የተባለውን የፊት መስመር የያዘ ክለብ ጭምር ነው። ቡድኑ በመጀመሪያው ዙር የነበሩበትን ክፍተቶች በሁለተኛው ዙር አስተካክሎ ካልተመለሰ በቀጣይ ዓመት በፕሪሚየር ሊጉ ከማናያቸው ክለቦች አንዱ የመሆን እድሉ ሰፊ ነው።
እስካሁን በአንድም ጨዋታ ማሸነፍ ያልቻለው ሀምበሪቾ ዱራሜ በውድድር ዓመቱ መጨረሻ ወደ ከፍተኛ ሊጉ የመውረዱ ጉዳይ እርግጥ የሚሆን ይመስላል። ሀምበሪቾ አንድ ነጥብ ብቻ ይዞ ነው በደረጃ ሰንጠረዡ መጨረሻ የተቀመጠው። የኢትዮጵያ ንግድ ባንኳ ሴናፍ ዋቁማ 14 ግቦችን በማስቆጠር የመጀመሪያውን ዙር አጠናቃለች። ሴናፍ በስድስት ግብ ልዩነት ነው ተፎካካሪዎቿን እየመራች የምትገኝው። የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪሚየር ሊግ ሁለተኛው ዙር ውድድር በሀዋሳ ከተማ ከየካቲት 29 ቀን 2017 ዓ.ም ጀምሮ እንደሚደረግ አወዳዳሪው አካል አሳውቋል።
(ስለሺ ተሾመ)
በኲር የጥር 19 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም