የጎርፍ አደጋን ለመከላከል ዝግጅት መደረጉ ተገለጸ

0
136

የአማራ ክልል አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ኮሚሽን በክረምቱ ወቅት በክልሉ የጎርፍ እና የመሬት መንሸራተት አደጋ ሊከሰትባቸው የሚችሉ ቦታዎችን በመለየት የቅድመ መከላከል ሥራ መሠራቱን  አስታውቋል፡፡

የክልሉ አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ኮሚሽን የቅድመ ማስጠንቀቂያ እና የአስቸኳይ ጊዜ ምላሽ ዳይሬክተር ብርሐኑ ዘውዱ በክረምት ወቅት በዝናብ መብዛት ምክንያት በክልሉ በአንዳንድ አካባቢዎች ቅጽበታዊ ጎርፍ እና የመሬት መንሸራተት አደጋዎች ሊከሰቱ እንደሚችሉ ገልፀዋል። ክረምቱን ተከትለው ሊከሰቱ የሚችሉትን አደጋዎች ለመከላከልም  የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች መሠራታቸውን ተናግረዋል፡፡

እንደ ዳይሬክተሩ ማብራሪያ በክልሉ ከክረምት ወቅት ጋር በተያያዘ የሚከሰቱ የጎርፍ አደጋዎችን ለመከላከል ቀድሞ የማጥናት እና መረጃ የማሰባሰብ ተግባራት ተከናውነዋል። በቀጣይም ችግሮችን ቀድሞ በመከላከል፣ አደጋዎች ከመከሰታቸው በፊት እና ሲከሰቱ ፈጥኖ ምላሽ በመስጠት ደረጃ በደረጃ የሚከናወኑ ናቸው ብለዋል።

በክልሉ በጎርፍ አደጋ እና በመሬት መንሸራተት አደጋዎች ተጋላጭ የሆኑ 35 አካባቢዎች ተለይተዋል። በእነዚህ አካባቢዎች የጎርፍ እና የመሬት መንሸራተት አደጋ ቢከሰት ሊያደርስ የሚችለውን የጉዳት መጠን በመለየት ፈጣን ምላሽ ለመስጠት የሚያስችል የቅድመ መከላከል ሥራ መከናወኑን ዳይሬክተሩ አስገንዝበዋል። ምን ያህል ሰዎች፣ ቤቶች፣ የሰብል ማሳ፣ ተቋማት፣ እንስሳት እና መሰል ንብረቶች ለአደጋ ሊጋለጡ ይችላሉ የሚለው በጥናት መለየቱንም ተናግረዋል፡፡ ይህንን መሠረት በማድረግ በመንግሥት እና በአጋር ድርጅቶች በኩል መሸፈን የሚገባውን ሀብት በመለየት ዞኖች እና ወረዳዎችም እንደየአካባቢያቸው አቅደው እንዲሠሩ እየተደረገ መሆኑን አመላክተዋል።

በቅድመ ዝግጅት ሥራው መሰረት ተጋላጭ የሆኑ ግለሰቦች ለችግሩ ሰለባ እንዳይሆኑ ቀድሞ ከቦታው የማውጣት ሥራም ይከናወናል። የመረጃ ልውውጡን የሚያሳልጡ ተግባራትም ይከናወናሉ ብለዋል።

የመሬት መንሸራተት እና ቅጽበታዊ ጎርፍ ሊከሰትባቸው  በሚችሉ አካባቢዎች ለመጠለያነት ሊያገለግሉ የሚችሉ ቤት እና ድንኳን መዘጋጀታቸውን የተናገሩት አቶ ብርሐኑ፤ ከእነዚህ በተጨማሪም በየአካባቢው ባሉ ትምህርት ቤቶችም በጊዚያዊነት  እንዲያርፉ ይደረጋል ብለዋል፡፡

በቀጣይ በክልሉ የሚከሰቱ አደጋዎችን ለመከላከል ከክልሉ መንግሥት እና መንግሥታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች 145 ሚሊዮን ብር በጀት መመደቡን ገልፀዋል። የሚከሰቱ ችግሮችን ለመከላከል ከሌሎች ተቋማት ጋር በቅንጅት ለመሥራት ስምምነት ላይ ተደርሷል። በጤና፣ በምግብ፣ በውኃ፣ በአልባሳት፣ በመጠለያ እና መሰል ግብዓቶች እንዲሟሉ ሀብት የማሰባሰብ ሥራ እየተከናወነ ነው።

በዚህ ዓመት ከፍተኛ መጠን ያለው ዝናብ ሊኖር እንደሚችል የሜቲዎሮሎጂ መረጃ እንደሚያሳይ የተናገሩት አቶ ብርሐኑ፤ ድንገተኛ ጎርፍ እና የመሬት መንሸራተት አደጋ ሲከሰት አደጋው በተከሰተበት አካባቢ ያሉ የኅብረተሰብ ክፍሎች እና በየደረጃው የሚገኙ የመንግሥት ተቋማት ጉዳቱ የከፋ እንዳይሆን የሚጠበቅባቸውን ሁሉ ተግባር ማከናወን እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡

በክረምት ወቅት የሚከሰቱ ቅፅበታዊ አደጋዎችን ለመከላከል በጎ አድራጊ ግለሰቦችን በማቋቋም የግንዛቤ ፈጠራ እየተሠራ መሆኑንም አስረድተዋል። ማኅበረሰቡ የሚወጡ የቅድመ ጥንቃቄ መረጃዎችን መከታተል እንዳለበት አሳስበዋል። የክረምት ወቅት አደጋዎች ቅጽበታዊ በመሆናቸው ኅብረተሰቡ ሁሌም አደጋው ሊከሰት እንደሚችል አስቦ ጥንቃቄ እንዲያደርግም ጥሪ አቅርበዋል።

(መልካሙ ከፋለ)

በኲር የሰኔ 30 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here