በባህርዳር ከተማ የቀድሞው ቀበሌ አምስት ከድብ አምበሳ ጀርባ በሚገኘው ሰፈር ነበር ተወልደው ያደጉት። ጠበቃና አማካሪ አደራው አዲሱ ይባላሉ። በሕግ የመጀመሪያ ዲግሪ እና በአመራርነት ሁለተኛ ዲግሪ አላቸው። በሙያቸው ስኬታማ እና በበጎ አድራጎታቸውም የተመሰከረላቸው ናቸው። የትዳር እና የሙያ ጉዟቸውን፣ ለማሳየት የበኩር ጋዜጣ እንግዳችን አድርገናቸዋል። መልካም ንባብ!!!
በቅድሚያ ጠበቃ አደራው አዲሱ የበኩር እንግዳችን ለመሆን ፈቃደኛ በመሆንዎ በአሚኮ እና በበኩር ዝግጅት ክፍል ስም እናመሰግናለን!
እኔም እንግዳ ስላደረጋችሁኝ አመሰግናለሁ!
መልካም! እንግዲህ ቃለ መጠይቃችንን የምንጀምረው በትዝታዎችዎ ነው እና ጠበቃ እና አማካሪ አደራው አዲሱ ትውልድ እና እድገታቸው በአጭሩ እንዴት ይገለፃል?
እሺ! እኔ የተወለድኩት እና ያደግሁት ባህር ዳር ከተማ ቀበሌ አምስት ወይም ከድብ አንባባ ጀርባ ባለው ሰፈር ነው። ሰፈራችን በጣም ጠንካራ ወላጆች የነበሩበት ሰፈር ነው። አንዱ ካለው ለሌላው አካፍሎ የሚበላበት፣ ተጣልቶ ወዲያው የሚታረቅበት እና የሃይማኖት ልዩነት ሳይገድባቸው እንደ አንድ ቤተሰብ የሚኖርበት የፍቅር ሰፈር ነበር። ብዙ ባለሙያዎችን እና ነጋዴዎችን አፍርቷል።
ስራ የጀመርኩት እዚሁ ሰፈር ፀጉር ቤት በመክፈት ነበር። በዛው ጎን ለጎን ትምህርቴን ቀጥዬ በባህርዳር ዩኒቨርሲቲ በመጀመሪያ ዲግሪ ሕግ፣ በሁለተኛ ዲግሪ ደግሞ በአመራር ሳይንስ ተመርቄያለሁ።
ከዚያ በኋላ ጠበቃና አማካሪ አደራው አዲሱ በጥብቅና እና በማማከር ስራ ላይ ተሰማርተዋል እና ምን ይሰማዎታል?
የሕግ ሙያ ለእኔ ከሥራ በላይ የሞራል ግዴታ ነው። ወደ እኔ የሚመጣው የተቸገረ ሰው ነው፤ የጨነቀው ሰው ነው፤ መፍትሔ ያጣ ሰው ነው። ስለዚህ በዚህ ጉዳይ ላይ አንተ ክፍተቱን ሞልተህ ስትገባለት፣ እንዲሁም ደግሞ የተቸገረ ሰው፣ መብቱ የተጣሰበት ሰው፣ በኢኮኖሚም አነስተኛ የሆነ ሰው ወደ አንተ ሲመጣና ያንን መፍትሔ ስትሰጠው ስሜቱ እጅግ በጣም ደስ ይላል። በተለይ የጠበቃ ሥራ በትክክል ከሠራህበት በእኔ በኩል የጽድቅም ሥራ ነው ብዬ ነው የምገምተው።
የህግ ሙያ ስራዎን ከበጎ ፍቃድ ጋርም ያያይዙታል የሚባል ነገር አለ። እኔም የተወሰኑ ማህበራዊ ድረ-ገጾች ላይ አይቻለሁ፤ እርስዎ ምን ይላሉ?
አዎ! አንድም መግቢያ አጥተው፣ የት ቦታ እንደሚሄዱ፣ የት እንደሚከራከሩ፣ ነገር ግን መብታቸው መጣሱን ብቻ የሚያረጋግጡ ምስኪኖች አሉ። እና እነዚያን ሰዎች ማለፍ አልችልም። አሁን አብዛኛው መዝገቦቼ፣ እንደውም ይበልጡ ማለት እችላለሁ እንዲህ አይነት ነገሮች ላይ የተመለከቱ ናቸው። እንደውም ማህበራዊ ገጼ ላይ ምናልባት በጣም የተቸገሩ ሰዎች ካሉ እባካችሁ ላኩልኝ ብዬ ሁሉ መልእክት አስቀምጣለሁ። በነጻ ነው የማማክረው። የምበላው ካላጣሁ፣ የምተኛበት ካላጣሁ፣ ከአቅም በላይ የሆነ ገንዘብ ማግበስበስ አልወድም፤ አልፈልግምም።
በተቸገሩት ሰዎች ዙሪያ በተለይ ከህክምና ጋር በተያያዘ በአካል ሩቅ ቦታም እየሄዱ፣ ቪዲዮዎችን እየቀረፁ የነብስ አድን ጥሪ ያደርጋሉ፤ በዚህ ጉዳይስ ምን ያህል ይሳተፋሉ?
የብዙ ሰዎችን ጉዳይ ለጥፌ አፍሬ አላውቅም። በህክምና ላይ ሰዎች ሲቸገሩ በመለጠፍ በሚሊዮኖች ገንዘብ እናሰባስባለን። በቅርብ እንኳን በሁለት ሳምንት ከጓደኞቼ ጋር በመሆን እስከ አምስት ሚሊዮን ብር ድረስ እንዲዋጣ አድርገናል። በማምንበት ጉዳይ ላይ ነው ምሰራው። በአሁኑ ሰዓት በእርግጥ ሶሻል ሚዲያ በጣም አስቸጋሪ ስለሆነ ሰው አምኖ ለመስጠት በጣም ስለሚቸገር ይህን ታማኝነታችንን ተጠቅመን እውነትን አረጋግጠን ስለማገለግል በጣም ደስተኛ ነኝ በዚህ በተለይ።
ችሎት ላይ ቀርበው ስያሸንፉ ምን አይነት ስሜት ነው የሚሰማዎ?
ተበድያለሁ ብሎ ወደ አንተ መጥቶ ጉዳዬን ጨርስልኝ ብሎ የመጣ ሰው ከማገኘው አንዳንድ ጥቅም በላይ እርካታው ልነግርህ አልችልም፤ እፎይታ ነው የሚሰማኝ፤ ደስ ይለኛል። እና ባለጉዳዬ ውሳኔ ሲያገኝ፣ በፍርድ ቤት ሲያምን እና መሰል ነገሮች ተፈጥረው ሳይ እጅግ በጣም እረካለሁ።
በሙያዊ ጉዞዎ በሂደት የማይረሱት ገጠመኝ ካለ ቢያካፍሉን?
ትልቅ ትምህርት ያገኘሁበት አንድ ገጠመኝ አለ። አሁን ሦስት አመቴ ነው በጥብቅናው አለም ከተሰማራሁ፤ ከዚያ በፊት ግን የክልል አቃቤ ሕግ ነበርኩ። እና እየሠራን እያለን አንዲት እናት ምስክር ሆና ቀረበች፤ የታዘለ ሕፃንም ይዛለች። ምስክርነት እየተሰማ እያለ እኔ የምጠይቀውን የመስቀለኛ ጥያቄ በትክክል ለመመለስ አልቻለችም። እኔ ዋናው ነጥብ ላይ ለመድረስ ስሞክር ከስሜት እናቲቱን እያገላመጥኳት ነበረ። ያ የታዘለው ሕፃን ደግሞ ሁሉንም ነገር ይታዘባል፤ ይመለከታል። እናቱን ስቆጣ ተሰምቶታል፤ ድንገት ልጁ ከታዘለበት ሆኖ ሲያስቸግር ዳኛው አውርጅው ስላሏት አወረደችው፤ ልክ እንደወረደም ከውጭ ጠጠር ድንጋይ ይዞ መጣና በእኔ ላይ ወረወረብኝ። ያ ሕፃን ትልቅ ነገር አስተማረኝ፤ በፍትሕ ሥርዓታችን ላይ ምስክር አይንና ጆሮ መሆኑን፣ ስናናግርም በትሕትና መሆን እንዳለበት ተረዳሁ።
ባለቤትዎትም የሙያ አጋርዎ እንደሆኑ ሰምቻለሁ፤ ከወረዳ ዓቃቤ ሕግነት ተነስታችሁ እስከ ባህር ዳር ድረስ የዘለቃችሁበት የሙያ ጉዞ እንዴት ይገለጻል?
በዚህን ቀን እንጋባለን ተባብለን አናውቅም ነበር። ነገር ግን ፀጉር ስሰራ ሳለም ጓደኞች ነበርን። ከዚያም አጋጣሚ ሆነና ትምህርታችንም አንድ አይነት ሆነ። የሕግ ትምህርት ተማርን፤ የሕግ ባለሙያ ሆንን። ሌላው የሚገርመው ወደ ስራ ከመግባታችን በፊት የቅድመ ስራ ስልጠና፣ ማለትም ዳኛና አቃቢ ህግ ከመሆን በፊት ስልጠና ይሰጠናል። በዚህም ሁለታችንም ወረታ የመጀመሪያ ዙር ፍትህ ማሰልጠኛ ውስጥ ደረሰን። ያኔ ስልጠና ስንገባ የመጀመሪያ ልጃችንን ዛብሎንን ነፍሰ ጡር ነበረች። ከዚያም ከአንድ ወር በኋላ ስልጠና እንዳለን ወለደች። ልክ ከሁለት ዓመታት በኋላ ደግሞ ወደ አፓረንት ልንወጣ ስንል ሁለተኛ ልጃችን ዲና ተወለደች። በዚህ መልኩ የአፓረንት ጊዜያችንን ጨርሰን ወጣን።
ከዚህ በኋላ እርሷ ምስራቅ ጎጃም ሰሜን አቸፈር እኔ ደግሞ አይናቡግና ሰሜን ወሎ ተመደብን። ተራርቆ መስራት በጣም ፈተና ነበር። ከዚያ በኋላ እንደምንም ብለው አንድ ቦታ እንድንሰራ አመቻቹልን እና እኔ እርሷ ወዳለችበት ሰሜን አቸፈር መጥቼ አብረን መስራት ጀመርን።
ከትዳር ባሻገር የአደራው እና የአበባ ስኬቱ እየጎመራ የመጣው ከዚያ በኋላ ነው ማለት ነው? እስኪ አቸፈር ላይ ምንድን ነው የተከናወነው? ባል እና ሚስትስ በአንድ አይነት ሙያ ከመሰማራት ባለፈ በአንድ ወረዳ በአንድ ሂደት ውስጥ አብሮ መስራትን እንዴት አስኬዳችሁት?
አዎ! ባልና ሚስት አንድ ላይ መስራት በጣም ይከብዳል ነው የሚባለው። ያውም ደግሞ እርሷ የስራ ሂደቱ አስተባባሪ ሆና እኔ ፈፃሚ ሆኜ ከእርሷ በታች ሆኜ ነበር የምንሰራው። እንደውም በመተጋገዝ ሒደቱ ውጤታማ እንዲሆን እንደፈፃሚ አያገዝኩ ጥሩ ሰርተናል። እውነት ለመናገር በስራዋ በጣም ጎበዝ ናት እና ወጣ ያሉ ስራዎችን ትሰራ ነበር። እና እኔ እንደውም አጋዢ ነው የሆንኩት።
በራሷ ተነሳሽነት ልክ እንደ ርቀት ትምህርት መሰረታዊ የሕግ ትምህርቶችን በሞጁል እያዘጋጀች ለካቢኔው ስልጠና ትሰጥ ነበር፤ ምክንያቱም ካቢኔው ስራ ሲመራ ሕግ እንዳይጥስ፣ ስህተት እንዳይሰራ፣ ከሕዝቡ ጋር ስለሚገናኝ ደግሞ ሕጎችን እግረ መንገዱን እንዲያስተምር፣ ፈፃሚም ስለሆነ ባለጉዳይን እንዳያንገላታ የሕግ የበላይነትን በትክክል ማወቅ አለበት በሚል እያሰለጠነች ሰርቲፊኬት ይሰጣቸው ነበር። በዚህ እና በሌሎች ጠንካራ እንቅስቃሴዎቻችን የእኛ ሂደት ተሸልሟል። እስከ ክልልም ድረስ እውቅና አገኝቷል።
ከዚያ በኋላ ባለቤቴም ለክልል አቃቤ ሕግነት አልፋ እኔም ለክልል የህብረት ስራ ማህበራት የህግ ባለሙያነት በማለፍ በቀናት ልዩነት ተከታትለን ባህር ዳር ገባን።
ወደ ባህር ዳር ከመጣችሁ በኋላ የክልል አቃቢያነ ሕግ ማህበር እንዲቋቋም የእርስዎ ሚና ሰፊ እንደሆነ ይነገራል፤ ይህን እና ሌሎች ውጤታማ ስራዎችዎን በተመለከተ ምን ይሉናል?
ባህር ዳር ከመጣን በኋላም በልቤ አንድ ነገር መጣብኝ፤ የአቃቤ ህግ ሙያ ማህበር አልተመሰረተም፤ በሌሎች የኢትዮጵያ ክልሎችም አልተመሰረተም። ከዚያ በኋላ የአቃቤ ህግ ሙያ ማህበር እንዲመሰረት በፌስቡክ እና በተለያዩ አማራጮች ቅስቀሳ ጀመርኩ። ከ2011 ዓ.ም መጨረሻ እስከ 2012 ዓም ድረስ ማለት ነው። ከዚያ በኋላ ቅስቀሳ ስጀምር በሁሉም ዞን ያሉት ባለሙያዎች ሁሉ የማህበሩን መቋቋም ፈለጉት። በ2012 ዓ.ም አካባቢ ስብሰባ አደረግንና ለመጀመሪያ ጊዜ በአማራ ክልል የአቃቤ ህግ ሙያ ማህበር መሰረትን። እኔንም የማህበሩ ፕሬዝዳንት አድርገው መረጡኝ። ከዚያ በኋላ በዚያ አማካይነት ከፍተኛ እንቅስቃሴ አደረግን፣ ለውጦች ታዩ።
በጋራ መሆናችን ሙያችንን ለሌሎች ለማካፈል እድል ፈጥሮልናል። ስለዚህ ባህር ዳር ላይ በአንድ አካባቢ መስራት ስለቻልንም ልጆቻችን በስርዓት እንዲያድጉ አግዞናል።
(መሰረት ቸኮል)
በኲር የካቲት 2 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም


