የጠፉት አዛውንት መጨረሻ

0
27

በፈረንሳይ ምዕራባዊ ቀጣና ቻቲሎን – ሱር – ቱዊት የተሰኘች ከተማ ኗሪው የ85 ዓመት የዕድሜ ባለፀጋ አስራ ዘጠኝ ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ወደ ነበራቸው የሀኪም ቀጠሮ ለመድረስ በተሳሳተ አቅጣጫ አሽከርክረው ከሀገራቸው ውጪ መገኘታቸውን  ኦዲቲ ሴንትራል ድረ ገጽ ሰሞኑን አስነብቧል::

አዛውንቱ በሚከታተላቸው ሀኪም ቀጠሮ የተሰጣቸው  “ኤርቫውልት” በተባለ ከመኖሪያ ቤታቸው አጐራባች 19 ኪሎ ሜትር በሚርቅ ቀጣና ነበር:: መኪናቸውን ይዘው ወደ ቀጠሯቸው ያመሩት አዛውንቱ ግን በቀጠሯቸው ቦታ አልደረሱም::

የ85 ዓመቱ የእድሜ ባለፀጋ በዚያው እለት ሌላ በአባልነት የሚሳተፉበት ስብሰባም ነበራቸው፤ በስብሰባው ላይ አለመገኘታቸውን የተገነዘቡ የቤተሰብ አባላትም “የት ቀሩ? ለምን ቀሩ?” ሀሳብ ይገባቸዋል::

ቤተሰቦቻቸው በየጐረቤቱም ይጠይቃሉ:: “የሉም” የሚል መልስ ይሰጣቸዋል:: ይሄኔ ጉዳዩን በአቅራቢያቸው ለሚገኝ የፓሊስ ጽ/ቤት ያስታውቃሉ:: መላ ቤተሰቡ መጥፎ ሁኔታ አጋጥሟቸው ይሆናል በሚልም ጭንቀት ውስጥም ይገባል::

የቀጣናው ፖሊስ ጽ/ቤት በአቅራቢያው ከሚገኝ ወታደራዊ ተቋም ጋር በመገናኘት የአዛውንቱ ቤተሰብ ከፖሊስ አንዳች መለስ ይገኛል ብሎ ባልጠበቀበት፣ በእጃቸው በያዙት ሞባይል የአቅጣጫ መጠቆሚያ (ጂፒኤስ)አማካይነት ከቤታቸው 1500 ኪሎ ሜትር ርቀት ክሮሺያ ውስጥ የሚገኝ ሆቴል መድረሳቸው ይረጋገጣል:: ቤተሰባቸውም አዛውንቱን ለማምጣት ወደ ተገኙበት ማምራታቸው በማደማደሚያነት ተገልጿል::

 

(ታምራት ሲሳይ)

በኲር የሕዳር 22 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here