የጠፋዉ አትራፊ መንገድ

0
152
Anti war posters, two tanks grow peace trees

የህዳር 2 ቀን 2017 ዓ.ም

በኢትዮጵያ ባለፉት ዘመናት የተመዘገቡ አኩሪ ድሎች እንደ መመንጠቂያ እንዲሆኑ፤ ድክመቶች ደግሞ እንደ ትምህርት እንዲወሰዱ ሆኗል:: ለዚህም ነው “የኋላው ከሌለ የለም የፊቱ” የሚባለው:: ኢትዮጵያውያን የሚታወቁበት ይህ ወርቃማ አባባል በተለይ ሩዋንዳውያን በአግባቡ ተጠቅመውበታል::
ሩዋንዳ እ.አ.አ በ1994 ዓ.ም ባጋጠማት ጎሳን መሠረት ባደረገ ፍረጃ በ100 ሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎቿን አጥታለች፤ ሚሊዮኖች ዛሬን ለማየት በወቅቱ ረሀብ እና የውኃ ጥሙን ተቋቁመው ተሰደዋል:: የወቅቱ ክስተት ሩዋንዳ ዛሬ ላይ እንደ ሀገር ትቀጥላለች ብሎ ያሰበ አልነበረም:: ሩዋንዳ ትናንት ላይ የተፈጸመውን ዘግናኝ ክስተት ዛሬ ላይ አልረሳችም፤ የሞቱትን በየዓመቱ ታስባለች:: ያለፈው ልጆቿን የበላው ታሪኳ ግን ዳግም እንዲደገም አትፈልግም፣ ጦርነት ለኪሳራ እንጂ ለትርፍ አልዳረጋትም:: ሩዋንዳ እንደ ሀገር እንድትቀጥል እውነተኛ ይቅርታን አስቀድመዋል። ይህም ይቅርታ አሻግሯታል፤ በዕድገት ጎዳና ላይም እንድትጓዝ አድርጓታል፤ ያለፈው ላይደገም ዘላቂ ሰላምን ገንብታለች፤ በአሁኑ ወቅት በግጭት ውስጥ ለሚገኙ ሀገራትም የሰላም ተምሳሌት ሆና የምትነሳ ሀገር ሆናለች:: በዚህ ምክንያት ነው እንግዲህ ሩዋንዳ ኢትዮጵያውያን የሚታወቁበትን ወርቃማ አባባል ወርሰዋል የሚባለው::
እንደ ደቡብ አፍሪካ፣ ጋና እና መሰል ሌሎች ሀገራትም ለሰላም በሰጡት ትልቅ ዋጋ ትርፋማ ሆነዋል:: ዜጎቻቸው የማይሳቀቁበትን ሀገር ገንብተዋል፤ በነጻነት የመንቀሳቀስ ሕገ መንግሥታዊ መብቶቻቸውን አረጋግጠዋል::
በአንጻሩ የሕዝብ ጥያቄ ማስመለሻው ዋናው መሳሪያ ኅይል ብቻ ነው ብለው ወደ ነውጥ የገቡ ሀገራት ዛሬ ላይ ሀገርነታቸውን አጥተዋል፤ ሕዝቦቻቸው ለስደት ተዳርገውባቸዋል:: ለአብነት ሶሪያን እንመልከት፡- ሶሪያውያን ለስደት የተዳረጉት እና እጃቸው ለልመና የተዘረጋው የሰላምን ዋጋ ጠንቅቀው ባለመረዳታቸው፤ ይልቁንም የሁሉም ነገር መፍቻ ቁልፉ የኀይል የበላይነት ነው ብለው በማመናቸው ነበር:: ከፍተኛ የሥራ አጥነት ችግር፣ ሙስና እና የፖለቲካ ነፃነት እጦት የሶሪያውያን ያላባራ ጩኸት ሆኖ ዓመታትን ተሻግሯል:: ይህ የሆነው ግን በሽር አል አሳድ አባታቸውን ሃፌዝ አል አሳድን ተክተው ወደ ሥልጣን ከመምጣታቸው በፊት ነው:: በሽር አል አሳድ በአውሮፓውያኑ 2000 መንበረ ሥልጣኑን ቢይዙም ለሶሪያውያን ጩኸት ምላሽ ከመስጠት ይልቅ በኀይል ድምጽን ለማፈን መሞከራቸው ሀገሪቱን ወደ እርስ በእርስ ግጭት አስገባት:: እዚም እዚያም የአማጺ ቡድኖች መፈጠር፣ የውጭ ኃይሎች ጦርነቱን በበላይነት ያሸንፋል ለሚሉት ኀይል ይፋዊ ድጋፍ ማድረጋቸው በሀገሪቱ የዛሬ እጣ ፋንታ ላይ ጥላሸት ፈጥሯል::
አትራፊው መንገድ የጠፋባቸው ሶሪያውያን እና የሶሪያ መንግሥት በመጨረሻም ሀገራቸውን በዓለም ለጦርነት ምቹ ተብላ የተሰየመች እስክትመስል ለፍልሚያ ጥለዋት ሸሽተዋል:: ሶሪያውያንም ዛሬ ላይ በኢትዮጵያ እና በሌሎች ሀገራት ተሰደው ሥራ ፈላጊ ሆነዋል፤ ሕይወታቸውን ለማቆየትም ልመናን መውጫ መንገዳቸው አድርገዋል::
ለኢትዮጵያ እንደ ሀገር መቀጠል እና ለሕዝቧም እፎይታ የሚበጀው ሩዋንዳን መሆን ወይስ እንደ ሶሪያ ዛሬም የኀይል አማራጭን እስከ መጨረሻው ማስቀደም? የሚለው ጥያቄ ነው:: ኢትዮጵያ በተለይም ከ2013 ዓ.ም ወዲህ በሉዓላዊ ግዛቴ ላይ ተደቅኖብኛል ያለችውን ስጋት እና ተጨባጭ ሁኔታዎች ከግምት ውስጥ በማስገባት ሀገራዊ አንድነትን ለማስቀጠል በጦርነት እና በሕግ ማስከበር እርምጃ ውስጥ ትገኛለች:: የሰሜኑ ጦርነት ያደረሰው ሰብዓዊ ጠባሳ ሳይሽር፣ ምጣኔ ሐብታዊ ጉዳቱ ሳያገግም፣ ማኅበራዊ ምስቅልቅሎሹ ሳይረጋጋ፣ ስነ ልቦናዊ ስብራቱ ሳይጠገን ዛሬም በአማራ ክልል እና በሌሎችም የሀገራችን አካባቢዎች ግጭቶች እልባት አጥተው እንደቀጠሉ ናቸው:: የሰሜኑ ጦርነት በሰላም ስምምነት መቋጨት በሕዝቡ ዘንድ አሳድሮት የነበረው የሰላም ተስፋ እንደ ጉም በኖ በተለይ ጦርነቱ መልኩን ቀይሮ በአማራ ክልል ከ2015 ዓ.ም መጨረሻ ጀምሮ ተቀስቅሷል:: ይህም ሕዝቡን ለዳግም ሰብዓዊ ኪሳራ፣ ሰቆቃ እና ማኅበራዊ ምስቅልቅል እንዲሁም በምጣኔ ሐብትም ወደ ኋላ እንዲቀር እያደረገው መሆኑን የሰላም ችግሩን በሰላም ስምምነት ለመፍታት በመንግሥት በኩል እየተመቻቹ ባሉ ሕዝባዊ ውይይቶች ሕዝቡ እያረጋገጠ ነው:: በተጨማሪም በክልሉ ያጋጠመው የሰላም መደፍረስ እገታ እንዲስፋፋ፣ የዝርፊያ እና የውንብድና ወንጀሎች እንዲጨምር ማድረጉን የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን መረጃ ያመላክታል:: እነዚህ ሕገ ወጥ እንቅስቃሴዎች ሕዝቡ ተረጋግቶ መደበኛ ሥራውን እንዳይሠራ በማድረጋቸው ብዙዎች መኖሪያ ቀያቸውን ለቀው አንጻራዊ ሰላም ወዳለባቸው አካባቢዎች ተሰደዋል:: ሕገ ወጥ እንቅስቃሴዎችን እንደ ስጋት ከማየት በተጨማሪ የክልሉ የሰላም ሁኔታ በዘላቂነት ባለመረጋገጡ በ2016 ዓ.ም ብቻ ከ2 ነጥብ 4 ሚሊዮን በላይ ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ ውጪ ሆነው ከርመዋል:: በ2017 ዓ.ም 7 ሚሊዮን ተማሪዎችን መዝግቦ የተሟላ መማር ማስተማር ለማከናወን ዕቅድ የያዘው የክልሉ ትምህርት ቢሮ እስካሁን ግማሽ ያህሉን እንኳ ማሳካት አለመቻሉ የክልሉ የሰላም ሁኔታ አሁንም ልዩ ትኩረት እንደሚሻ ማሳያ ነው::
ሁለተኛ ዓመቱን ይዞ የሚገኘውን የክልሉን የሰላም ሁኔታ በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ያሳየሁት ጥረት መፍትሄ ባለመማምጣቱ፤ በአሁኑ ወቅት ወደ ሕግ ማስከበር እርምጃ ተሸጋግሬያለሁ ሲል መንግሥት አስታውቋል:: የአማራ ክልል መንግሥት እና የሀገር መከላከያ ሠራዊት መስከረም 21 ቀን 2017 ዓ.ም መግለጫ በሰጡበት ወቅት የክልሉ ኮሙኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ መንገሻ ፈንታው (ዶ/ር) እንዳስታወቁት መንግሥት ወደ ሕግ ማስከበር እርምጃ የገባዉ እስካሁን የተደረጉ የሰላም ጥረቶች ለውጥ ባለማምጣታቸው ነው::
የአማራ ክልል የሰላም ካውንስል በበኩሉ ችግሩን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ከታጣቂ ኅይሉ አባላት ጋር ንግግር መጀመሩን፣ ከምስራቅ አፍሪካ በይነ መንግሥታት (ኢጋድ)፣ ከአሜሪካ ኤምባሲ ጋር ሁሉ መነጋገሩን እና ከአፍሪካ ሕብረት ጋር ለመነጋገር ቀጠሮ መያዙን ማስታወቁ አይዘነጋም::
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 4ተኛ ዓመት የሥራ ዘመን 4ተኛ መደበኛ ስብሰባውን ባካሄደበት ወቅት የሰላም ችግሮች እንደ ክልልም ሆነ እንደ ሀገር እያደረሱት ያለው ምስቅልቅል እና የመውጫ መንገዱ ቀዳሚ አጀንዳ ሆኖ በአባላቱ ተነስቷል:: ሕዝቡ ያለ ስጋት በመንቀሳቀስ የነገ መዳረሻ ኢኮኖሚያዊ አቅሙን እንዲያጎለብት፣ የልማት ሥራዎች ሳይደናቀፉ እንዲቀጥሉ፣ እንደ ትምህርት እና ጤና ያሉ ማኅበራዊ አገልግሎቶች ሳይቋረጡ እንዲቀጥሉ፣ የትምህርት ተቋማት በሮቻቸውን ከፍተው ተማሪ እና አስተማሪዎቻቸውን ተቀብለው ሀገርን በተማረ ዜጋ ለማሳደግ፤ መሠረት ለሆነው ሰላም ቅድሚያ ሊሰጥ እንደሚገባ አባላቱ ጠቁመዋል::
በትጥቅ የታገዙ ግጭቶች እልባት አለማግኘት፣ የጅምላ እስር፣ ዜጎች በነፃነት እና በሰላም ተንቀሳቅሰው መሥራት አለመቻላቸው፣ የሰዎች እገታ፣ ፆታዊ ጥቃት፣ መፈናቀል… ንፁኃንን ከፍተኛ ዋጋ እያስከፈለ እንደሚገኝ የምክር ቤት አባላት አንስተዋል:: በመሆኑም ያጋጠመው የሰላም መደፍረስ አክትሞ ሕዝቡ በነጻነት እንዲንቀሳቀስ ችግሮች በእውነተኛ ውይይት እና ድርድር ሊፈቱ ይገባል ሲሉ አጽንኦት ሰጥተው ጠይቀዋል::
ከምክር ቤት አባላት ለተነሱ ጥያቄ እና አስተያየቶች ምላሽ እና ማብራሪያ የሰጡት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ (ዶ/ር) ሰላም መንግሥትም ሆነ ማንኛውም ሰው መሆን ለሚፈልገው ዋና መዳረሻ መሆኑን አንስተዋል:: በመሆኑም ለዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ከመሞት እና ከመግደል ይልቅ የፈጀውን ጊዜም ቢወስድ በሰላማዊ መንገድ መታገል ውጤቱ የተሻለ እና ሀገርን ወደ ፊት የሚያሻግር እንደሆነ አጽንኦት ሰጥተው ሲናገሩ፤ ይህ የመንግሥት አቋም መሆኑን ጭምር ጠቁመዋል::
መንግሥት ከማንም በላይ ሰላም ይፈልጋል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ባለፉት ዓመታት የተደረጉ ጦርነቶች ብዙዎችን መቅጠፉን እና እንደ መንግሥትም የቀጣይ መዳረሻው ሩቅ በመሆኑ ከጦርነት ይልቅ ሰላም እጅጉን እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል:: መንግሥት እንደ ሀገር ያጋጠመውን የሰላም እጦት በዘላቂነት ለመፍታት ተደጋጋሚ የሰላም ጥሪ ማድረጉን ጠቅላይ ሚኒስትሩ አስታውቀዋል:: አሁንም መንግሥት ከታጣቂ ኅይሎች ጋር ለመነጋገር በሩ ክፍት መሆኑን አረጋግጠዋል::
በአማራ እና በኦሮሚያ ክልሎች ከሚንቀሳቀሱ ኀይሎች ጋር ንግግር መኖሩንም ገልጸዋል:: ነገር ግን በታጣቂ ኀሎችም በኩል ሆነ በመንግሥት በኩል የቆሙ ሰላም የማይፈልጉ አካላት ደግሞ ሰላም ፈልገው ከመንግሥት ጋር በንግግር ላይ ያሉትን እንዴት ከዚህ መንግሥት ጋር ትነጋገራላችሁ በሚል ለማደናቀፍ ጥረት ሲያደርጉ መስተዋላቸውን አስታውሰዋል:: በዚህ ምክንያት ችግሩን በሰላም ለመቋጨት የሚደረገው ጥረት ረጅም መንገድ እንዲወስድ አድርጎታል ብለዋል:: ያም ሆኖ መንግሥት አሁንም ልዩነቶችን በድርድር ለመቋጨት ዝግጁ መሆኑን አረጋግጠዋል። የምክር ቤት አባላትም የማቀራረብ ሥራ እንዲሠሩ ጠይቀዋል::

(ስማቸው አጥናፍ)

በኲር የህዳር 2 ቀን 2017 ዓ.ም ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here