የጡት ማጥባት በረከቶች

0
140

“ልጄን ከወለድኩ በኋላ ጡቴ ወተት ስለሌለው አራስ ሊጠይቁኝ የመጡ ሰዎች ሁሉ የተለያዬ ምክር ይሰጡኝ ነበር። እኔም ከጭንቀቴ ብዛት የነገሩኝን  ሁሉ ስሞክር ነበር። ጠላ፣ ቡና እንዲሁም አመድ ሁሉ በጥብጬ ጠጥቻለሁ። ግን ውጤት አልነበረውም።” ይህን ሐሳብ ያካፈለችን የባሕርዳር ከተማ ነዋሪዋ እናት ወ/ሮ እንጉዳይ ውብየ ነች። የጀበና ቡና በመሸጥ የምትተዳደረው ወ/ሮ እንጉዳይ ይህን ሁሉ ሙከራ ያደረገችው ባለባት የኢኮኖሚ ችግር የጣሳ ወተት መግዛት ባለመቻሏ እንደሆነ ነግራናለች።

 

ከሙከራዋ አንድ ሳምንት በኋላ ግን መልካም ነገር ተከሰተ። ጡቷ በቂ ወተት ማምረት ጀመረ። እሷም ከጭንቀቷ ተገላገለች። ወ/ሮ እንጉዳይ “ልጄ ጤነኛ ነች። የከፋ ሕመም አጋጥሟት አያውቅም። ቢያማትም ቶሎ ቶሎ ጡት ስለማጠባት በፍጥነት ትድናለች” ነው ያለችን።

 

በዛሬው የጤና አምዳችን ስለ ጡት ማጥባት በረከቶች ልናስነብባችሁ ወደናል። በጉዳዩ ላይ በባሕር ዳር ዩኒቨርስቲ የስነ ምግብ እና አመጋገብ ትምህርት ክፍል መምህርት ከሆኑት ከወ/ሮ ገነት እንዳልክ ጋርም ቆይታ አድርገናል። መምህሯ እንዳሉት ጡት ማጥባት ልዩ እና ድንቅ የሆነ ተፈጥሯዊ ስጦታ ነው። ምክንያቱም እናት ለልጇ እስከ ስድስት ወራት ድረስ የሚያስፈልገውን የተመጣጠነ ምግብ እና የውኃ መጠን የምታቀርብበት ነው። ሌላ ተጨማሪ ሰው ሠራሽ ምግብ ሳያስፈልገው ለአዕምሮም ለአካልም የሚያስፈልገውን ምግብ አግኝቶ የሚያድግበት ነው – ጡት ማጥባት።

 

የስነ ምገብ መምህሯ ወ/ሮ ገነት እንዳስገነዘቡት አንድ ጨቅላ ሕጻን በተወለደ በአንድ ሰዓት ውስጥ የእናት ጡት ወተት ማግኘት አለበት። ከዚያም እስከ ስድስት ወር በቀን ከስምንት እስከ 12 ጊዜ መጥባት ይኖርበታል። አንዱን ጡት ሲጠባም ከ20 እስከ  30 ደቂቃ መቆየት አለበት። በመቀጠልም ወደ ሁለተኛው ጡት መሸጋገር ይኖርበታል።

 

ስድስት ወር ካለፈው ግን በየመሃሉ ተጨማሪ ምግብ ስለሚጀምር ጡት የሚጠባበት መጠን ሊቀንስ ይችላል። ጡት ማጥባትም ልጁ ሁለት ዓመት እስኪሞላው የሚቀጥል ይሆናል።

ጡት ማጥባት ሕጻኑን ከብዙ በሽታዎች ይከላከላል። በተለይም ከመተንፈሻ አካላት ኢንፌክሽን፣ ከጉንፋን እና ከአለረጂ ይጠብቃል። ከዚህ በተጨማሪም ጡት ጠብቶ ያደገ ሕጻን  ብሩህ አዕምሮ  አለው። ለዚህም ነው በማሕበረሰቡ ዘንድ  በአስተሳሰብ ከታናሾቻቸው ያነሱ ሰዎች ሲኖሩ ጡት አልጠባም የሚባለው።

የሕጻናት ከመጠን በላይ ውፍረትን በመከላከል አስተማማኝ ዕድገት እንዲኖራቸው ማድረግ ሌላው ጡት የማጥባት በረከት መሆኑን መምህርት ገነት ያነሳሉ።  በሕፃናት ላይ የሚከሰትን የካንሠር መጠንን እና ድንገተኛ የሆነ የጨቅላ ሕጻናትን ሞትም ይቀንሳል።

 

ባለሙያዋ እንደሚሉት የመጀመሪያው እንገር  የሚባለው የእናት ወተት እንደ ክትባት ይቆጠራል። ምክንያቱ ደግሞ በውስጡ በርካታ በሽታ ተከላካይ “አንቲ ኦክሲደንት” አሉትና ነው። ስለዚህ እናቶች ዋናው ወተት አልወጣም በሚል ማፍሰስ ሳይሆን ሕጻኑ እንዲጠባው ማድረግ አለባቸው።

ዘርፈ ብዙ ጥቅም የሚያስገኘው ጡት ማጥባት ለሕጻኑ ከሚያስገኘው ጥቅም በተጨማሪ የእናትንና የልጅን ትስስር (ፍቅርን) እንደሚያጠነክር መምህርት ገነት ይገልጻሉ። ሕጻናት ከተወለዱ ጀምሮ ለነሱ ቅርብ ለሆነ እና ፊት ለፊት ለሚያዩት ሰው ነው ፍቅር የሚኖራቸው እናም ፍቅራቸው ይጨምራል።

 

ሕጻናት ቢያንስ በቀን ውስጥ ለስምንት ጊዜ በእናታቸው እቅፍ ውስጥ (ቢያንስ ስምንት ጊዜ ጡት ማጥባት ስላለባቸው) ናቸው። ይህ የእናት እና የልጅ ንኪኪ ፍቅር እንዲጨምር ያደርጋል። ስለዚህ ለእናታቸው ያላቸው ፍቅር የተለዬ ይሆናል።  ሲርባቸው ምግብ የሚያገኙት እሷ ጋር እንደሆነም ያውቃሉ።   እናትም ልጇን ዓይን ዓይኑን እያየች ነው የምታጠባው። ይህም  በመሀላቸው ያለውን ፍቅር የጠበቀ ያደርገዋል።

የእናት ጡት የማይጠባ ልጅ ጡጦ  እየጠባ ነው የሚያድገው። ይህን ደግሞ ማንኛውም የቤተሰብ አካል ሊያደርገው ስለሚችል የእናት እና የልጅ ፍቅር ጡት ጠብቶ  ካደገው ልጅ ጋር ሲነጻጸር የላላ (ደካማ) ነው። ለእናቱም የተለዬ ፍቅር አይኖረውም።

 

ሌላው ጡት ማጥባት ከሚያስገኘው ጠቀሜታ መካከል ወሊድን ማዘግየቱን ነው መምህርት ገነት የነገሩን። የስነ ምግብ መምህሯ እንዳሉት ጡት የሚያጠቡ እናቶች ጡት ከማያጠቡ እናቶች ያነሰ የወሊድ ዕድል አላቸው። ይሁንና ሙሉ በሙሉ እርግዝናን እንደማይከላከልም አስረድተዋል። እንዲሁም ጡት ማጥባት እናትዬውን ለጡት ካንሠር እና ለማሕጸን በር ካንሠር እንዳትዳረግ ይከላከላል። የምታጠባ እናት ከማታጠባ እናት በጡት እና በማህጸን በር ካንሠር የመያዝ ዕድሏ ይቀንሳል። ከወሊድ በኃላ ቶሎ ክብደት ለመቀነስም ይረዳል።

ጡት ማጥባት ከተዘረዘሩት በረከቶች ባሻገር ምንም አይነት ክፍያ ስለማይፈፀምበት ወጪ ቆጣቢ ነው። በአሁኑ ጊዜ የቆርቆሮ የዱቄት ወተት ዋጋው የማይቀመስ ከመሆኑ ባሻገር ሕጻናትን ለድርቀት፣ ለተቅማጥ እና ለሆድ ሐመም ሲያጋልጥ ይስተዋላል።

 

ለመምህርት ወ/ሮ ገነት እናቶች ጡት የማያጠቡበት ሁኔታ ሲያጋጥም ይስተዋላል። ይህ ነገር ከምን የመጣ ነው? ብለን ላነሳንላቸው ጥያቄም  የጡት አለማጥባትን ካለመቻል ወይስ ካለመፈለግ ነው በሚል ማየት እንደሚገባ ጠቁመዋል። ጡት ማጥባት አለመቻል የጡት በበቂ ሁኔታ አለመመረት ወይም  የወተት አለመኖር ጋር ይያያዛል። ይህ ደግሞ በብዙ አይነት መንገዶች ሊከሰት ይችላል። በተለያዩ የጤና ችግሮች ምክንያት እናትዬዋ መድኃኒት የምትወስድ ከሆነ ወተት እንዳይመረት ሊያደርግ ይችላል። አንዳንድ መድኋኒቶች ይህንን ሊያስከትሉ እንደሚችሉ ልብ ይሏል።

 

ሌላው የሆርሞን መለዋወጥ ነው። በወሊድ ጊዜ የሚፈጠሩ አንዳንድ ሆርሞኖች የጡት ወተት ሙሉ በሙሉ እንዳይመረት ሊያደርጉ ይችላሉ። እንዲሁም እናትዬው የሚያጋጥማት ጭንቀት በቂ ወተት እንዳይኖር ያደርጋል። ቶሎ ቶሎ እና በተደጋጋሚ ጡት የማይጠባ ከሆነም በራሱ ሊደርቅ ይችላል። የእናትዬው አመጋገቧ ደካማ ከሆነ እና ቶሎ ቶሎ ፈሳሽ የማትወስድ ከሆነም የጡት ምርት ሊቀንስ ይችላል።

 

ሁለተኛው በኛ ሀገር ጎልቶ ባይታይም በአደጉ ሀገሮች ጡት ማጥባት ‘የጡቴን ቅርፅ’ ያበላሻል በሚል የማያጠቡበት ሁኔታ እንዳለ ያነሱት መምህርት ገነት ይህም ፈጽሞ መሆን የሌለበት  እንደሆነ ነው ያሳሰቡት። አንዳንድ እናቶች ቅርፃቸው እንዳይበላሽ ወይም ከልጃቸው ጋር ብዙ ጊዜ ላለማሳለፍ ‘ጡት አላጠባም ‘ ይላሉ። በዚህም ሰው ሠራሽ ወተትን ለልጆቻቸው ይመግባሉ። ይህንንም ራስ ወዳድነት ልንለው እንችላለን ነው ያሉት። ታዲያ ይህን የማይገባ ድርጊት የሚፈፅሙ የሀገራችን እናቶች ካሉ ቆም ብለው በማሰብ ከስህተታቸው ሊታረሙ ይገባልም ሲሉም መክረዋል።

 

የጡት ወተትን ሊጨምሩ የሚችሉ ነገሮች በሚል በሀገራችን የሚተገበሩ ልማዶች አሉ። ለአብነትም የአልኮል መጠጦችን እና ቡና አልፎ አልፎም እንደ ወለዱ ወተት  አልወጣ ላላቸው እናቶች አመድ በጥብጠው እንዲጠጡ ይደረጋል። እነዚህን ድርጊቶች በተመለከተ ለጠየቅናቸውም መምህርት ገነት ሲያብራሩ ልማዳዊው ድርጊት ፈጽሞ የተሳሳተ በመሆኑ መወገድ አለበት። አልኮሉ እና ቡናው ፈሳሽ ስለሆኑ ወተት እንዲመረት ያደርጋሉ።  ነገር ግን ቡናውም ይሁን አልኮሉ ጤነኛ ምግብ ስላልሆኑ ልጆቹን ሊጎዱ ስለሚችሉ ባይጠቀሙ ሲሉ ነው ሙያዊ ምክራቸውን ያካፈሉን።

 

አልኮሉም የሕጻኑን የአዕምሮ ዕድገት እንዲቀነጭር ያደርጋል። የእንቅልፍ መዛባት እና መነጫነጭም ያስከትልበታል። ቡናም ሆነ ሶዳ ያላቸው የለስላሳ ምርቶችን በተደጋጋሚ መጠጣት በውስጣቸው ካፌይን የተባለ አነቃቂ ነገር ስለሚኖር እናትዬው  ውስጥ ያለውን ብረት (አይረን) ሙሉ በሙሉ እንዲወገድ ያደርጋል። ይህ ደግሞ እናትዬው የተመጣጠነ ምግብ ብትመገብም አይረኑ በካፌይኑ ይጠፋል። የቡና ሱስ ካለባት ግን መጠኑን መቀነስ እንደሚኖርባት እና  ምግብ ከተመገበች ከሳላሳ ደቂቃ በኋላ ብትጠጣ የተሻለ እንደሚሆን ጠቁመዋል።

 

መምህርት ገነት እንዳሉት አንዲት የምታጠባ እናት የጡት ወተት እንዲመረት የሚያስችሉ ምግቦችን ማለትም  ካሎሪ ወይም ኃይል ሰጪ  ምግቦችን መመገብ ይኖርባታል። በቂ ፕሮቲን፣ ካርቦሃይድሬት እና ካሎሪ  ያላቸውን ምግቦች በብዛት መመገብ በቂ ወተት እንዲመረት ያስችላል። ይሁንና ከዚህ በተቃራኒው በቂ እና የተመጣጠነ ምግብ የማትመገብ ከሆነ ጡቷ የሚያስፈልገውን ምግብ ለልጇ ማድረስ አይችልም። ፈሳሽ ነገሮችን አጥሚትም ይሁን ጭማቂ መውሰድ አለባት። “ለምታጠባ እናት ምግቦችን መርጦ ይህን ተመገቢ ብለን አንለይም። ነገር ግን የተመጣጠነ ምግብ በብዛት የምትመገብ ከሆነ በቂ የጡት ምርት እንደሚኖራት ልትገነዘብ ይገባል” ነው ያሉት።

 

የስነ ምግብ መምህሯ በሰጡን የማጠቃለያ ሐሳብም የጡት መመረትን የሚጎዱ ምግቦች አልኮልንና ቡናን ባታዘዎትር ይመከራል። መድኃኒቶችን በጤና ባለሙያ አማክሮ መውሰድ ይገባል ብለዋል። የእናት ጡት በቂ በማይሆንበት ጊዜ  ግዴታ የሚሆነው ለሕጻናቱ በዕድሜያቸው ልክ የተዘጋጀውን የቆርቆሮ ዱቄት ወተት የአገልግሎት የማብቂያ ጊዜውን በማየት በአግባቡ መስጠት ይገባል። ነገር ግን የላም ወተት ከአንድ ዓመት በታች ላሉ ልጆች መሰጠት እንደሌለበት በአጽንኦት ተናግረዋል። በተጨማሪም  ስድስት ወር ላልሞላው ሕጻን የመግብ መፈጨት ስርዓቱ በደንብ ስላልዳበረ አጥሚት መስጠት እንደማይገባም ነው የመከሩት።

ጤና አዳም

የጡት ማጥባት በረከቶች

*  የሕፃኑን ትክክለኛ እድገት ያስቀጥላል ።

* እንዲሁም   በበሽታ የመሞት እድልን ይቀንሳል።

* ጡት ማጥባት ሊፈጠሩ የሚችሉ የተዛባ የአካል ክፍሎችን ችግርን ይቀንሳል።

* በቅርቡ የተደረጉ ጥናቶች እንደሚያሳዩት ጡት ማጥባት በልጆችና በጉርምስና ዕድሜ ላይ የሚገኙ ወጣቶችን ከመጠን ያለፈ ውፍረት እና በዓይነት 2 የስኳር በሽታ የመያዝ እድልን ይቀንሳል።

* የአዕምሮ እድገትን (IQ) ይጨምራል።

* የሕጻናት በባክቴሪያ  የመያዝ እድልን ይቀንሳል ።

* በመካከለኛው ጆሮ ውስጥ የሚከሰት እብጠትን ለመከላከል ይረዳል።

*ጡት ማጥባት እናትን የጡት እና የማህፀን ካንሠር ተጋላጭነት ይቀንሳል።

* ጡት ማጥባት በእናት እና በጨቅላ ሕጻኑ መካከል ጠቃሚ የባክቴሪያ እና የሆርሞን ግንኙነቶችን ያመቻቻል።

 

ምንጭ:-የዓለም ጤና ድርጅት

(ሳባ ሙሉጌታ)

በኲር የነሐሴ 5  ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here