የጥቅምት ወር ዓለም አቀፍ የጡት ካንሠር ግንዛቤ መፍጠሪያ ወር ነው:: ዘንድሮም “እያንዳንዱ ታሪክ ልዩ ነው፣ እያንዳንዱ ጉዞ አስፈላጊ ነው”። በሚል መሪ ሀሳብ ከጥቅምት 1 እስከ ጥቅምት 30/2025 ስለጡት ካንሠር ግንዛቤ በመፍጠር ይከበራል:: የዓለም ጤና ድርጅት ላይ ያገኘኘው መረጃ እንደሚያስረዳው የጡት ካንሠር የሚከሰተው በአንዱ ወይም በሁለቱም ጡቶች የሚገኙ ሕዋሳት (Cells) ከተፈጥሮ ውጭ ሆነው በፍጥነት ሲራቡ እና ሲበዙ ነው።
ሕመሙ ብዙውን ጊዜ የሚጀምረው ወተት በሚፈጥሩት እጢዎች ውስጥ (Lobular Carcinoma) ወይም ወደ ጡት ጫፍ በሚወስዱት ቱቦዎች (Ductal Carcinoma) ነው። ካንሠሩም በጡት ውስጥ ይጀምርና በአቅራቢያ ወዳሉ ንፍፊት (Lymph Nodes) ወይም በደም በኩል ወደ ሌሎች የአካል ክፍሎች ሊሰራጭ ይችላል::
ከዚያም ካንሠሩ በመስፋፋት በጡት አካባቢ ያሉትን እንደ ቆዳ ወይም የደረት ግድግዳ የመሳሰሉ ሕብረ ሕዋሳትን (Tissues) ሊያጠቃ ይችላል። የጡት ካንሠር ቁጥሩ አነስተኛ ቢሆንም ወንዶችንም ሊያጠቃ የሚችል በሽታ ነው::
የጡት ካንሠር ምልክቶች
ሕመም አልባ ወይም ሕመም ሊኖረው የሚችል ከጡት ሥር ያለ አዲስ ዕባጭ ይከሰታል፣ ይህም የጡት ካንሠር የመጀመሪያው ምልክት ተደርጎ ይወሰዳል።
የጡት ጫፍ ስርጉድ ማለት፣ የጡት ቀለም መቀየር (የብርቱካን ልጣጭ አይነት ቀለም መኖር)፣ የጡት ጫፍ ሕመም፣ የጡት ቆዳ መሸብሸብ (ቁስለት)፣ ክብደት መቀነስ፣ ከጡት ጫፍ ውኃማ ፈሳሽ ወይም ደም መውጣት፣ የሁለቱ ጡት መጠን መለያየት እና ከብብት ሥር እብጠት መኖር፣ ለመተንፈስ መቸገር ዋናዎቹ የጡት ካንሠር ምልክቶች መሆናቸውን የዓለም ጤና ድርጅት መረጃ ያመላክታል::
ሁሉም እብጠቶች ካንሠር አለመሆናቸውን ልብ ይሏል፤ ነገር ግን ማንኛቸውንም ለውጦችን በጤና ባለሙያ መመርመሩ አስፈላጊ ነው ሲል ድርጅቱ ያስገነዝባል::
ለጡት ካንሠር አጋላጭ ምክንያቶች
የጡት ካንሠር አጋላጭ ምክንያቶች መካከል አልኮል አዘውትሮ መጠጣት፣ ሲጋራ ማጨስ፣ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ አለማድረግ፣ ከመጠን ያለፈ ውፍረት፣ ከ30 ዓመት እድሜ በኋላ ልጅ መውለድ፣ ጡት አለማጥባት፣ አንዳንድ የእርግዝና መከላከያዎች፣ የወር አበባን ከ12 ዓመት ዕድሜ በፊት ቀድሞ ማየት እና ከ55 ዓመት ዕድሜ በኋላ ማረጥ እንዲሁም ዕድሜ እየገፋ ሲሄድ በጡት ካንሠር የመያዝ አጋጣሚን ይጨምራል። አብዛኛዎቹ የጡት ካንሠር ታማሚ ሴቶች ዕድሜያቸው ከ50 ዓመት በላይ ነው። ብዙዎች የጡት ካንሠር እንዳለባቸው በፍጥነት ካወቁ የመትረፍ እድላቸው ሰፊ ነው::
የጡት ካንሠር ምርመራ እና ሕክምና
ጡት ላይ ከበፊቱ የተለየ ነገር ወይም ለውጥ በሚታይበት ጊዜ ወደ ሕክምና ተቋማት ማምራት ግድ ነው::
የጡት ካንሠር ምርመራ በዋናነት የሚከናወነው በማሞግራም ነው:: ማሞግራም አነስተኛ መጠን ያለውን ራጅ (X-Ray) በመጠቀም የጡት ውስጣዊ ክፍልን ይመረምራል:: የጡትን ያልተለመዱ ለውጦችን እና ዕጢዎችን ለመለየት የሚያስችል ነው:: መሣሪያው ካንሠርን በጊዜ በመለየት የመዳን ዕድልን ይጨምራል:: በጡት ካንሠር የሚከሰትን ሞት ከ30 እስከ 40 በመቶ ይቀንሳል::
የጡት ካንሠር የሚጀምረው በጡት ውስጥ ከሚነሳ ዕባጭ ስለሆነ ምርመራ በሚያደርጉበት ጊዜ ማንኛውም መጓጎል እና ዕብጠት ካስተዋሉ ወደ ጤና ተቋማት ሄዶ ምርመራ ማድረግ አስፈላጊ ነው::
በየወሩ ከወር አበባ በኋላ በራስ ዕባጭ መኖሩን መፈተሽ ተገቢ ነው:: በእጅ ጡትን በመዳበስም ጠጣር ነገር መኖር እና አለመኖሩን መለየት ይቻላል:: የጡት ምርመራ አድርገው ምንም የካንሠር ምልክት ያልታየባቸው ሰዎች ለተጨማሪ ሦስት ዓመታት ምርመራ አያስፈልጋቸውም።
ማዮ ክሊኒክ ድረ ገጽ ላይ ያገኘነው መረጃ እንደሚያመላክተው የጡት ካንሠር ሕክምና በሦስት ክፍሎች ይከናወናል፤ የመጀመሪያው ሕክምና ከደረጃ አንድ እስከ ደረጃ ሦስት ላሉ የጡት ካንሠሮች ቀዶ ጥገና ማድረግ ነው:: አልፎ አልፎም ደረጃ አራት ላይ ለደረሱም ቀዶ ጥገናው ሊሰጥ ይችላል::
በቀዶ ጥገናው ካንሠር ያለበትን ቦታ ብቻ ለይቶ በማስወገድ (Breast Conservation Surgery) እና በካንሠር የተጠቃውን ጡት ሙሉ በሙሉ በቀዶ ጥገና (Mastectomy) በማስወገድ ይሠራል።
ሁለተኛው የጡት ካንሠር ሕክምና ደግሞ ሲስተሚክ ትሪትመንት (Systemic Treatment) ይባላል:: ሕክምናው በካንሠር የተጠቁ ሕዋሳትን ለማከም ኬሞቴራፒ፣ ሆርሞናል ቴራፒ እና የበሽታ የመከላከልን የሚጨመሩ መድሃኒቶችን ይጠቀማል:: መድኃኒቶቹ በአፍ የሚወሰዱ ወይም በደም ሥር የሚሰጡ መርፌዎች ናቸው። ግቡ የካንሠሩን ዕድገት መግታት ወይም በካንሠር የተጠቁ ሕዋሳትን ማጥፋት ነው:: አንድ ታካሚ እንደ ካንሠሩ አይነት እና ደረጃ ከእነዚህ ሕክምናዎች አንድ ወይም ጥምር ሕክምና ሊወስድ ይችላል።
ኬሞቴራፒ ከአንደኛ እስከ ሦስተኛ ደረጃ ላይ ያለ የጡት ካንሠርን ለማከምና ካንሠሩ ተመልሶ እንዳይመጣ ለመከላከል ያገለግላል::
እንዲሁም ደረጃ አራት ላይ ለደረሰ ካንሠር ኬሞቴራፒ የሕመሙን ስቃይ ለመቆጣጠርና የበሽተኛውን ዕድሜ ለማራዘምም ያገለግላል። የሆርሞናል ቴራፒ በዋነኝነት በአፍ የሚወሰድ (የሚዋጥ) መድኃኒት ነው::
ሌላው የሕክምና አይነት ደግሞ የጨረር ሕክምና (Radiotherapy)ነው፤ ሕክምናው በካንሠር የተጠቁ ሕዋሳትን ለማጥፋት ከፍተኛ ኃይል ያላቸው ጨረሮችን ይጠቀማል:: በተለይም ከቀዶ ጥገና በኋላ የበሽታውን ድጋሚ የመከሰት ስጋትን ለመቀነስ ይሰጣል።
የጡት ጤናን ለመጠበቅ፡-
የጡትን ጤንነት ለመጠበቅ የሚከተሉትን ምክረ ሐሳቦች መተግበር ከጡት ካንሠር እንደሚጠብቅ የሕክምና ባለሙያዎች ይመክራሉ፤ የቤተሰብዎን ታሪክ ይወቁ እና ለሐኪምዎ ያካፍሉ።
ከቤተሰብ ውስጥ የጡት ወይም በሌላ ካንሠር ተይዞ የነበረ ሰው ካለ ለበሽታው የመጋለጥ አጋጣሚው ከፍተኛ ነው፤ በመሆኑም ከ40 ዓመት በፊት ምርመራ መጀመር ተገቢ ነው:: ምርመራዎቹ በየዓመቱ ማሞግራም (ማሞግራፊ) እና ኤም አር አይ (MRI) ምርመራዎችን እና የዘረመል ምርመራ ማድረግን ሊያካትቱ ይችላሉ።
በአማካይ ለጡት ካንሠር የተጋለጡ ሴቶች ምን ዓይነት የምርመራ ማካሄድ እንዳለባቸው ሐኪሞቻቸውን መጠየቅ አለባቸው:: ጡትን በየጊዜው መፈተሽም ይገባል::
ጤናማ አመጋገብን ማዳበር ተገቢ ነው። በንጥረ -ምግብ የበለጸጉ ምግቦችን (ፍራፍሬ፣ አትክልት፣ ዓሳ፣ ባቄላ፣ ያልተፈተጉ እህሎችን እና ለውዝን) መመገብ የጡት ካንሠር ተጋላጭነትን ይቀንሳል። በተጨማሪም ክብደትን ለመቀነስም ይረዳሉ:: ከመጠን በላይ መወፈር ለጡት ካንሠር ማጋለጡንም አይዘንጉ::
አዘውትረው የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ያድርጉ። በሳምንት ለአምስት ቀናት ቢያንስ ለ30 ደቂቃ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ የሚያደርጉ ሴቶች በጡት ካንሠር የመጠቃት አጋጣሚያቸው አነስተኛ ነው። የሰውነት ክብደትን ለመቆጣጠር ከመርዳቱ በተጨማሪ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማድረግ በሽታን የመቋቋም አቅምን ይጨምራል። አልኮል መጠጣትን መገደብ ወይም ማቆም ይመከራል።
በተጨማሪም ሲጋራ የሚያጨሱ ከሆነም አሁኑኑ ያቁሙ። ማጨስ በጡት ካንሠር የመጋለጥ ዕድልን ይጨምራል። የመጀመሪያ ልጅዎን ከ30 ዓመት ዕድሜዎ በፊት ለመውለድ ይሞክሩ። ጡት ማጥባት የጡት ካንሠርን ለመከላከል ከሚረዱ ነገሮች አንዱ ነው፤ ተግባራዊ ያድርጉት።
ጤና አዳም
* እንደ የዓለም ጤና ድርጅት የቅርብ ጊዜ መረጃ ሁለት ነጥብ ሦስት ሚሊዮን ሴቶች በጡት ካንሠር የተያዙ ሲሆን 670 ሺህ ሞተዋል።
* እ.አ.አ. በ2050 የሟቾች ቁጥር 40 በመቶ ሊጨምር ይችላል፡፡
* 99 በመቶ የጡት ካንሠር በሴቶች ላይ የሚከሰት ሲሆን ከዜሮ ነጥብ አምስት እሰከ አንድ በመቶ ደግሞ በወንዶች ላይ የመከሰት አጋጣሚ አለው።
* የጡት ካንሠር በሁሉም የዓለም ሀገራት በሚገኙ ሴቶች ላይ ለአቅመ ሔዋን ከደረሱ በኋላ ይከሰታል፤ ነገር ግን ዕድሜ እየገፋ ሲሄድ እየጨመረ ይሄዳል።
(ሳባ ሙሉጌታ)
በኲር የጥቅምት 17 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም


