በአሜሪካ የደቡብ ካሮላይና ተመራማሪዎች አደገኛውን ሦስተኛ ደረጃ የጡት ካንሰር የእጢ እድገትና ወደ ሳንባ መሰራጨቱን ለመግታት የበሽታ ተከላካይ ህዋሳትን የሚያነቃቃ ፀረ እንግዳ አካል (አንቲቦዲ) ማዘጋጀታቸውን ሳይንስ ዴይሊ ድረ ገጽ አስነብቧል፡፡
“ትሪኘል- ኔጌቲቭ ብረስት ካንሰር” ከጡት ካንሰር የከፋው ደረጃ መሆኑን ያስነበበው ድረ ገጹ በፍጥነት አድጐ የሚሰራጭ ለመፈወስም አዳጋች የሆነ ነው፡፡ ከዚህ ባሻገርም ህሙማንን በመጀመሪያው ህክምና የዳኑ አስመስሎ ለሁለተኛ እና ሦስተኛ ጊዜ አገርሽቶ እንዲጠቁ ያደርጋል፡፡
አዲስ የተዘጋጀው ፀረ እንግዳ አካል ግን የካንሰር ህዋሳትን መድሃኒት የመላመድ ዓቅምን የሚገታ እና በሽታ የመቋቋም አቅምን የሚያሳድግ ነው፡፡ በኘሮቲን ላይ የሚያነጣጥረው መድሃኒቱ የካንሰር ህዋሳት በጨረር እንዳይጠቁ ማድረግን ወይም የመቋቋም ኃይልን ያዳክማል፡፡ በዚህም ካንሰርን የሚያሰፋፉ ህዋሳት ላይ አነጣጥሮ ማጥቃት ያስችላል ነው የተባለው፡፡
ከተመራማሪዎቹ የቡድን አባላት አንዱ ዶክተር ክላውበር ዴሞር ግኝቱ በሽታ የመከላከል አቅምን ለማሳደግ አዲስ እውቀት የሚያስጨብጥ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በምርምር የተዘጋጀው ፀረ እንግዳ አካል(አንቲ ቦዲ) የካንሰር እጢ እድገት እና የስርጭቱን መስፋፋት ገትቶ ከከፋው ደረጃ ወደ ቀዳሚው ወይም መዳን ወደ ሚችልበት ደረጃ የሚያሸጋግር መሆኑን ነው ያረጋገጡት- ተመራማሪው፡፡
በመጨረሻም ፀረ እንግዳ አካሉ የጨረር ህክምና የሚቋቋሙ የካንሰር ህዋሳትን እድገት መግታት እና በሽታ የመከላከል አቅምን ማደስ እና ማሳደግ ያስችላል ነው ያሉት- ተመራማሪዎቹ፡፡
(ታምራት ሲሳይ)
በኲር የጥር 25ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም


