የጢያ ትክል ድንጋዮች

0
604

 

በሽዎች የሚቆጠር እድሜ ያስቆጠሩ የጥንት ኢትዮጵያውያን የጥበብ እና የታሪክ አሻራዎች የታተመባቸው፣ ዘመን ተሻጋሪ እፁብ ድንቅ  ቅርሶች ባለቤት የሆነችው ኢትዮጵያ ብዙዎችን በዓለም ቅርስነት አስመዝግባለች። ሰሜን ብንሄድ አክሱም፣ ላሊበላ እና የፋሲል ግንብየመሰሉትን፤ ምስራቅ  ብንሄድ ጀጎልን…አይነት አያሌ ድንቅ የኩራት ምንጭ የሆኑ ቅርሶችን እናገኛለን።  የደቡብ ኢትዮጵያ አሻራ ያረፈበት የጢያ ትክል ድንጋዮች ውበት አለማድነቅ አይቻልም። ጉራጌ ዞን ገብቶ ወደ ሶዶ በመውረድ፤ ጢያ ደርሶ እነዚህን ድንቅ የታሪክ አሻራዎች ሳይጎበኝ መመለስ ኪሳራ ነው። ታዲያ ለዚህ ሳምንት የሽርሽር አምዳችን የጢያ ትክል ድንጋዮችን ለመቃኘት መርጠናል።

ከአዲስ አበባ 86 ኪሎሜትር ርቀት  ደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች ክልል፤  ጉራጌ ሶዶ ወረዳ ውሰጥ የጢያ ትክል ድንጋዮች መካነ ቅርስን እናገኛለን። በአግባቡ በተከለለው የመካነ ቅርሱ ግቢ በር በኩል ሲገባ ወደ ቅርሶቹ ስፍራ የሚወስድ የኮብል ንጣፍ የእግር መንገድ አለ። ብቻችሁን አይደላችሁም፣ ከእርስዎ ጋር እየተዘዋወረ ቅርሶቹን የሚያሳይ እና መረጃ የሚሰጥ አስጎብኚ አለልዎት። በለመለመው ጫካ ዙሪያውን በተከለለው ሰፊ ቅጥር ግቢ ውስጥ ስላሉት የጥያ ትክል ድንጋዮች አንድ በአንድ እያብራሩ ታሪካዊ እና ባህላዊ እንድምታዎቻቸውን እየገለፁ በማስረዳት ቅርሶችን በሚደንቅ ብቃት እና ትህትና ያስጎበኟችኋል። እርሱማ  የደጋጎች ምድር ደቡብ አይደል..!

ብርሊያንት ኢትዮጵያ በተሰኘ ድረገፅ ላይ እንደተፃፈው አዳዲስ የቁፋሮ ምርምር በስፍራው የተካሄደ ሲሆን አሁን 40 ያህል ቅርሶች ከምድር ተቆፍረው ወጥተዋል። ነገር ግን እስካሁን ከእይታ የጠፉ ብዙ የተቀበሩ ቅርሶች እንደሚኖሩ ይገመታል። በአፍሪካ ውስጥ እንደዚህ ያሉ ትልቅ እና ገላጭ የሆኑ የድንጋይ ላይ ጥርቦች ስብስብ መኖር የሚገርም   ነው።

ከስር ሰፋ ወደ ጫፍ ሾጠጥ ያለ ቅርፅ በያዙት ትክል ድንጋዮች ላይ የቀረፁት  አነስተኛ የድንጋይ ምስሎች ከስር የተቀበሩትን ሰዎች ፈተናዎችን  እና መከራዎችን ይዘረዝራሉ። ቅርሶች የመካከለኛው ዘመን የኢትዮጵያ ባህል ቅሪቶች  ሲሆኑ እድሜያቸው በቀጥታ ከ12ኛው እስከ 14ኛው ክፍለ ዘመን እንደሆነ ይገመታል።

የጢያ ትክል ድንጋዮች በሶዶ አካባቢ ካሉ 160 የድንጋይ ሀውልት የቅርስ ስፍራዎች አንዱ ነው። በጢያ ከ45 በላይ የተተከሉ ድንጋዮች አሉ። ጥቂቶቹም ለተጨማሪ ጥናት እና ምርምር ወደ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ እንደተወሰዱ መረጃዎች ያመለክታሉ። አብዛኛዎቹ የጢያ ትክል ድንጋዮች ቁመት ከአንድ ሜትር እስከ 3 ሜትር ሲሆን ትልቁ ደግሞ 5 ሜትር ይደርሳል። ትክል ድንጋዮቹ ጠፍጣፋ እና ሞለል ያለ ቅርፅ አላቸው። ድንጋዮቹ  የተለያዩ ነገሮችን በሚወክሉ  ምስሎች አጊጠዋል። አብዛኞቹ የተቀረፁት ምስሎች ጎራዴዎች ናቸው። ከዚያ በተጨማሪ ጥንድ የበሬ ቀንድ፣ የተጋደመ መስቀል፣ የተክሎች ወይም የቅጠሎች ምስል፣ ጋሻ እንዲሁም ከበሮ ይታያሉ።

በጢያ ትክል ድንጋዮች መካነ ቅርስ ከ45 እስከ 48 የሚደርሱ ታሪካዊ ትክል ድንጋዮች እንደተተከሉ ይገመታል። ትክል ድንጋዮቹ ተበታትነው  ሦስት ቦታዎች ላይ ይገኛሉ፤ አንደኛው በዋናው የጢያ  ትክል ድንጋዮች መካነ ቅርስ ውስጥ ያሉት 41 ትክል ድንጋዮች ናቸው። ወደ 25 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ  ደግሞ አራት ትክል ድንጋዮችን የያዘ ሌላ ምድብ እናገኛለን። በሦስተኛነት ከዋናው መካነ ቅርስ ስፍራ 25 ኪሎሜትር ርቀት ላይ ደግሞ ሦስት የትክል ድንጋዮች ያሉበት ስፍራ አለ።

በዋናው መካነ ቅርስ ውስጥ 41 ትክል ድንጋዮች ያሉ ሲሆን በርካታ ምስሎች ተቀርፀውባቸው ይታያል። የጢያ ትክል ድንጋዮች አስጎብኝዎች ማህበር ባለሙያዎች በሚሰጡት ማብራሪያ ቅርሶቹ በ1972 ዓ.ም  በዩኖስኮ የዓለም ቅርስነት ተመዝግበዋል። በ1974 ዓ.ም ላይ ደግሞ በኢትዮጵያ እና በፈረንሳይ ተመራማሪዎች በአካባቢው የቁፋሮ ምርምር የተካሄደ ሲሆን በውጤቱም ከ700 እስከ 900 ዓመታት የቆየ የነገሥታት ፣ የታዋቂ ሰዎች እና የተዋጊዎች መቃብር ተገኝቷል። በቁፋሮውም 52 የሰው አጥንቶች ተገኝተዋል። ከአጥንቶቹም ጋር የሸክላ ስብርባሪዎች፣ ባልጩት፣ ጨሌ፣ ዶቃ እና ሰዎቹ ይጠቀሙባቸው የነበሩ ሌሎች መገልገያዎች አብረው ተገኝተዋል።

በትክል ድንጋዮቹ ላይ ካሉት ምስሎች ባህሪ አኳያ ቅርሶቹ በአምስት ምድብ ይከፈላሉ። የጎራዴ ምድብ፣ የጋሻ ምድብ፣ የሴት ምስል ምድብ፣ የከበሮ እና የወንድ ብልት ምስል ተብለው ይከፈላሉ። አንደኛው አስራ ዘጠኝ የተቀረፁ ጎራዴዎች ያሉበት ምድብ ነው። ይህም የተቀበረውን ሰው ተዋጊነት እና የገደለውን መጠን የሚገልፅ ነው። ሁለተኛው ያጋሻ ምድብ ሲሆን የተዋጊዎቹን ለጦርነት የሚከላከሉበት መሳሪያ እንደሚጠቁሙ ያመለክታል። ሦስተኛው ምድብ የሴት ምስል ያለበት ነው። ይህም ሴት በስፍራው መቀበሩን ለማሳየት ነው። አራተኛው የከበሮ ምድብ የተቀበረውን ግለሰብ እምነት ያመለክታል። አምስተኛው የወንድ ብልትን ምስል የሚያሳየው ምድብ በስፍራው የተቀበረው ግለሰብ ወንድ መሆኑን እንደሚገልፅ የአስጎብኝዎች ማብራሪያ ያስረዳል።

የጢያ ትክል ድንጋይ የአውሮፓውያንን ዓይን መሳብ ከጀመረ ብዙ ዓመትን ያስቆጠረ ሲሆን የዛሬ 84 ዓመት ወደ ኢትዮጵያ መጥቶ የነበረው ጀርመናዊ አጥኚ በዚህ ሥፍራ በኩል አልፎ እንደነበረ እና የጎራዴ ምስል ያላቸው የድንጋይ ትክሎች እንዳየ በጥናቱ አመልክቷል፡፡ ከዚህ አጥኚ ቀደም ሲልም ኑቪለ እና ፔር ዛይስ (Neuville and Pere Azais.) የተባሉ አውሮፓውያን ጥያን መጎብኘታቸውን የዩኔስኮ ጥናቶች ያመለክታሉ፡፡

ትራቭል አፍሪካ በተሰኘው የጎብኝዎች ድረ ገፅም ጢያ የሚገኙት ትክል ድንጋዮች የሚገኙት አዳዲ ማርያም ከተባለው ከድንጋይ ፍልፍል የተሠራው ቤተ ክርስቲያን፣ ሀረ ሸይጣን ከተባለው ክሬተር ሐይቅ፣ ከመልካ አዋሽ መስመር ጋር ስለሚገኙ ለጎብኝዎች በአንድ ጉዞ ብዙ ታሪካዊ ቦታዎችን ለመጎብኘት ያስችለዋል በማለት አስፍሯል፡፡ ፊሊፕ በሪግ የተሰኙት አጥኚም የጥያ ትክል ድንጋይ ጥንታዊነትን ለዓለም በማስተዋወቅ አዎንታዊ አስተዋጽኦ ማበርከታቸው ይታወቃል፡፡ የፈረንሳይ አርኪዮሎጂ ባለሙያዎች መረጃ እንደሚያመለክተው የጢያ ትክል ድንጋይ ባለበት ቦታ ዕድሜያቸው ከ18-30 የሚገመቱ ብዙ ወጣቶች በአንድ ላይ የተቀበሩበት ሥፍራ ነው፡፡

የጥያ ትክል ድንጋይዬችን ስፍራ በዓለም ቅርስነት እንዲመዘገቡ ያደረጉ ምክንያቶችን በተመለከተ አንደኛው እድሜያቸው ነው፤ የአርኪዮሎጂ አጥኚዎች እንደሚሉት የጢያ ትክል ድንጋዮች ከሰሐራ በታች ካሉ ትክል ድንጋዮች ከአክሱም በስተቀር በዕድሜ የሚበልጣቸው የለም፡፡ በሌላ በኩል 52 የሰው አፅሞች እስከመገልገያ ቁሳቁሳቸው መገኘታቸው፣ በድንጋዮቹ ላይ የተቀረፁት ምስሎች እና ለትውልድ መተላለፍ የቻለ ትውፊት ያላቸው መሆኑን ከግምት ውስጥ ባስገቡት ምክንያቶች የተነሳ ከ1972 ዓ.ም ጀምሮ በዓለም የቅርስ መዝገብ ላይ ሰፍሮ እንዲገኝ አድርጎታል፡፡

 

(መሰረት ቸኮል)

በኲር ጥቅምት 4  ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here