ግንቦት 4 1938 ዓ.ም በቀድሞው አጠራር ሰኮሮ ከተማ ጅማ አውራጃ፣ ከፋ ክፍለ ሀገር ተወለዱ:: የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸውን በዐፄ ኃይለ ሥላሤ የመጀመሪያ ደረጃ የሴቶች ትምህር ቤት፣ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በሚያዝያ 27 ሁለተኛ ደረጃ ተከታትለዋል:: ከዚያም የመምህርነት አጭር ሥልጠና ወስደዋል:: ቀጥሎም በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በጤና አጠባበቅ የባችለር ዲግሪያቸውን አግኝተዋል:: በዚሁ የትምህርት ዘርፍ ከፍተኛ ዲፕሎማቸውን እና ዶክትሬት ዲግሪያቸውን ከሎማ ሊንዳ ዩኒቨርሲቲ በአሜሪካን ሀገር ይዘዋል፡- ዶ/ር ተዋበች ቢሻው::
በህዝብ ጤና አጠባበቅ ሥራ ለ35 ዓመታት ቆይተዋል። በዩኒሴፍ ውስጥ ለ20 ዓመታት በተለያዩ ኃላፊነቶች በአፍሪካ እና እስያ ተዘዋውረው ሠርተዋል። ወደ ሀገራቸው ከተመለሱ በኋላ Alliance for Brain-Gain and Innovative Development (ABIDE) በተባለ ግብረ-ሰናይ ድርጅት በማኔጂንግ ዳይሬክተርነት ይሠራሉ። ድርጅቱ በውጭ ሀገራት ያሉ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ባለሙያዎች የዕውቀት ሽግግር እንዲያደርጉ በማድረግ በሀገር ልማት እንዲሳተፉ ይሠራል።
ዶ.ር ተዋበች በመምህርነት በተለያዩ የሀገራችን ገጠራማ አካባቢዎች አገልግለዋል:: በጤናው ዘርፍ ደግሞ እስከ ጤና መምሪያ ኃላፊነት ደርሰው ሠርተዋል:: ዩኒሴፍን ወክለው ደግሞ በተለያዩ የአፍሪካ እና ሌሎች ሀገራት አገልግለዋል:: ከዶ.ር ተዋበች ጋር የነበረን ቆይታ እነሆ!
ጂማ ውስጥ ኮሌጅ የገቡ እና የጨረሱ የመጀመሪያዎቹ ሴቶች እርስዎ እና እህትዎ ናችሁ፤ ለዚህ ምን አበቃችሁ?
አባቴ የቤተ ክህነት እና ትንሽ ዘመናዊ ትምህርት ተከታትለዋል:: ከሁለተኛው የጣሊያን ወረራ ዘመቻ በኋላ አርበኛው በምስጋና ሲሸኝ የተወሰኑ የተማሩ ሰዎች የሥራ እድል ተፈጠረላቸው:: አባቴም ቴሌ ኮምኒኬሽን ውስጥ ሥራ ያዙ:: በኋላም የቴሌ መሠረተ ልማቶችን እያስፋፉ ሲንቀሳቀሱ ወደ ጂማ መጥተው እዛው ቀሩ:: ልጆችም ተወለድን:: አባቴ ትምህርት ያመጣላቸውን ፀጋ ስላዩ ሁልጊዜ ተማሩ ይሉን ነበር::
ቤታችን የድሮ ቤት፣ በጭቃ የተሠራ ብዙ ልጆችን ያሳደገ ነው:: እኛን ብቻ ሳይሆን የዘመድ ልጆችን ሁሉ ለማስተማር አስበው ምቹ ቦታ ላይ አባቴ የሠሩት ይመስለኛል:: ከእቤት እኔ ሁለተኛ ልጅ ነኝ፤ እናቴን ትመስላለች ብለው በእናታቸው ስም ተዋበች ብለው ሰየሙኝ::
እኔ እና ታላቅ እህቴ ጂማ ዉስጥ ዩኒቨርሲቲ ገብተን ያጠናቀቅን የመጀመሪያዎቹ ሴቶች ነን:: በአካባቢያችን ሴት ልጅ ትንሽ ከጎረመሰች ወደ ትዳር ነበር ምተገባው:: አባቴ ግን ትዳር ይደርሳል፤ ኮሌጅ እስክትገቡ ተማሩ:: ይሉን ነበር:: የኮሌጅ ጽንሰ ሀሳቡ በዛን ጊዜ እንዴት እንደመጣላቸው እንኳ የሚገርም ነው:: ይህን በማየት ምን ያክል ሴቶች ላይ ጫና እንደነበረ ማየት ይቻላል:: ወደ ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ለመግባት ሳመለክት መስኩ የአመራር እና የኃላፊነት ቦታ ነው ብለው ስለሚያምኑ ሴቶችን ለማስገባት አይደፍሩም ነበር:: የእሷን ሁኔታ ሳናይ ሌላ አንቀበልም ማለት ሁሉ ጀመሩ:: እኔ ደግሞ ፈተናውን ብወድቅ ራሴን እንጂ ሴቶችን ወክየ አልወድቅም፤ የኢትዮጵያ ሴቶች ወደቁ ማለት ስላልሆነ ለሴቶች እድል መሰጠት ይገባል የሚል እምነት ነበረኝ:: ከብዙ ክርክር በኋላ ሃሳቡን ተቀበሉ፤ ለሴቶችም ሥልጠናው ክፍት ሆነ::
ወደ ሕክምናው የገቡበት አጋጣሚ አለ? ስለእሱ ይንገሩን!
የስምንተኛ ክፍል ተማሪ እያለሁ አባቴ አስም ያማቸው ነበር:: ጂማ ብዙ ሰው በአስም ይታመማል፤ አባቴም አካባቢ ቀይር ይሻልሃል ተብለው አይ እዚሁ የኖርኩበት ቦታ ነው አሁንም የምኖረው ብለው ነው እዛው ጂማ የቆዩት::
አንድ ጊዜ አሟቸው ሆስፒታል ገቡ፤ እናቴ እና እህቴ ቀን ቀን ይጠብቋቸዋል፤ እኔ ደግሞ ማታ እተካላቸዋለሁ:: አንድ ማታ አብሬያቸው ሆኜ እፍን አደረጋቸው:: የማደርገው ሳጣ ነርሷ ጋር ሮጬ ሄድኩ:: ሲስተር አባቴን በጣም አፍኖታል አልኳት፤ “እና እኔ ነብስ በመሀረብ ቋጥሬ አስቀራለሁ?” አለችኝ::
ከእሷ ጋር ከምሟገት ሄጄ እያራገብኩም ምን እያልኩም አተርፋቸዋለሁ፤ እግዚአብሄር ይረዳኛል ብዬ እያለቀስኩ ተመለስኩ:: በኋላ እግዚአብሄርም ረዳኝ፤ ያፈናቸው እየቀለላቸው መጣ:: ቆይታ እሷም መጥታ አየቺኝ፤ አበረታታቺኝ:: ሊሞቱ ነው እያልኳት ሮጣ መምጣት ነበረባት:: ከዚህ ጊዜ በኋላ የጤና ባለሙያ ሆኜ አገልግሎቱ ለሁሉም በጥራት እንዲሰጥ ወሰንኩ:: ስምንተኛ ክፍል ከደረሱ በወቅቱ ነርስ መሆን ይቻል ነበር፤ ሄጄ ስጠይቅ እድሜሽ አልደረሰም አሉኝ:: እድሜየ እስኪደርስ መጠበቅ ጀመርኩ:: በኋላ ላይ ቤተሰባችን የኢኮኖሚ ችግር ስለገጠመው አቋርጬ የመምህርነት ስልጠና ወስጄ ማስተማር ጀመርኩ:: ከዚህ በኋላ ነው እንደገና ወደ ኮሌጅ ተመልሼ በጤናው ዘርፍ የተማርኩት እና ማገልገል የጀመርኩ::
ከአረንቻታ ጋር ተያይዞ እርስዎ እና እህትዎ ገጠመኝ አለዎት! እስኪ እሱን ይንገሩን!
የሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች እያለን ፒስኮር የሚባል የአሜሪካ ግብረ ሰናይ ድርጅት ነበር:: በወቅቱ ሴት ተማሪዎች ትምህርታቸውን እንዲያቋርጡ ይገደዱ እና ወደ ሴተኛ አዳሪነት እንዲገቡ ይደረጋል:: ይህ ፒስኮር የተሰኘው ድርጅት ልጆቹ ከሴተኛ አዳሪነት እንዲወጡ የተለያዩ የሙያ ስልጠናዎችን ይሰጣል::
እኔ እና ታላቅ እህቴ (ዶ.ር ደስታ ቢሻው) ደግሞ አስተርጓሚ ሆነን ተመድበናል:: ከልጆቹ ጋር በዚህ ድርጅት አማካኝነት እንግባባለን፤ ከአንዳንዶቹ ጋርም ጓደኞች ሆነናል:: አንድ ቀን ከትምህርት ቤት ስንመለስ ቡና ቤት ውስጥ ልጆቹ ተቀምጠው አዩን፤ “ኑ አረንቻታ እንጋብዛችሁ?” አሉን:: በወቅቱ እንኳን ቡና ቤት መግባት ሴተኛ አዳሪዎቹን ማናገር እንደ ነውር ነበር የሚቆጠረው:: እኛ በቅን ልብ ቡና ቤቱ ውስጥ ገብተን አረንቻታችንን ተጋብዘን ወደ ቤታችንም ሄድን::
ሰዎች ለካ ለአባታችን “ይሄው ልጆችህን ዳር ብንልህ አይሆንም ብለህ አስተምረህ ይሄው ቡና ቤት ገብተው አረንቻታ መጠጣት ጀመሩ” ብለው ነግረውታል:: ማታ ሲመጣ እኛ በቅንነት ቡና ቤት ገብተን አረንቻታ ተጋበዝን አልነው:: አባታችንም “ሰው እንዲህ ብሎ ነግሮኛል፤ እኔ ግን ልጆቼን የማውቃቸው እኔ ነኝ ብየ መለስኩላቸው” አለን:: ይህ የአባታችን መረዳት እና የስነ ተግባቦት ክህሎት እጅግ አስተማሪ እና ለወደፊት ሕይወታችንም የጠቀመን ነው::
እናት ባንክ ማኅበረሰብ ግልጋሎት ላበረከቱት አስተዋጽኦ በአዲስ አበባ ከተማ ጎፋ ገብርኤል አካባቢ ቅርንጫፉን በስምዎት ሰይሟል፤ ስለዚህ ምን ይላሉ?
እናት ባንክ የጀመረው አዲስ ባሕል፤ የሚበረታታ ነው:: ለማኅበረሰቡ በጎ አስተዋጽኦ ያደረጉ መልካም ተግባራትን የሠሩ ሰዎችን ዋጋ መስጠቱ ጥሩ ነው:: ሰዎች የበለጠ መልካም ሥራዎችን ለማኅበረሰባቸው እንዲሠሩ የሚያደርግ፤ በተለይ ወጣቶች የሚያደርጉት አስተዋጽኦ ዋጋ እንዳለው እንዲረዱ እና በማኅበረሰብ አገልግሎት ላይ በስፋት እንዲሳተፉ ያደርጋል:: በእናት ባንክ የተጀመረው ተግባር በሌሎች ባንኮችም አርአያነቱ ተወስዶ ሊተገበር ይገባል::
የሚስተላልፉት መልዕክት ካለ?
ፈጣሪ የሰጠን እድሜ፣ ጤና፣ እውቀት እና ፀጋ ይዞ እስከመጨረሻ ኅብረተሰቡን ለማገልገል መንቀሳቀስ አስፈላጊ ነው:: በተለያዩ ምክንያቶች ባደርግ ኖሮ እየተባለ ውስን ሥራ ሲሠራ የነበረውን ሰፋ ያለ ጊዜ ወስዶ ህልምን ማሳካት ይቻላል:: ከጤና አንጻር ልረፍ በቃኝ ብሎ መወሰን ሰውነትንም አእምሮን ማድከም ስለሆነ የሚመከር አይደለም:: እድሜ የሚሰጠው ማስተዋል እና ዕውቀት አለ፤ ነገር ግን እድሜ የሚለካው በልብ እና በመንፈስ ነው:: በተለይ ጤናማ ሆኖ መንቀሳቀስ ከተቻለ ሴቶች መቀመጥ የለባቸውም፤ መሥራት አለባቸው:: የሴት ልጅ መንገድ ትግል ስለሆነ ልረፍ በቃኝ ለማለት ምቹ ነው:: በትግል ያለፈው ጊዜ በቃኝ ለማለት የሚያስገድድ መሆን የለበትም:: አቅም እስካለ ማኅበረሰብን ማገልገል የበለጠ ጉልበት ይሰጣል::
(ቢኒያም መስፍን)
በኲር የመስከረም 26 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም