የጥቁር ፈርጦች

0
35

በዘመናት ታሪክ አያሌ ጀግኖች ለሰብዓዊ መብት እኩልነት ሲሉ ዋጋ ከፍለዋል:: ሕይወታቸውንም እስከማጣት ደርሰዋል:: ከእነዚህ ጀግኖች መካከል ሦስት ታሪክ የማይረሳው ተግባር የፈጸሙ ሰዎችን እናስተዋውቃችሁ::

ፓርክስ

የጥቁር አሜሪካዊቷ እድሜ 43 ዓመታትን አስቆጥሯል። ዕለተ ሐሙስ እ.አ.አ ታህሳስ አንድ ቀን 1955 ነበር የተወለደችው። ሮዛ ረዳት ልብስ ሰፊ ሆና ትሠራበት ከነበረው ሱቅ ውላ ስትመለስ በጣም ድክም ብሏታል:: የሞንትጎመሪ አለባማ የከተማ ሕዝብ ማመላለሻ አውቶብስ ሲመጣ እንደማንኛውም መንገደኛ ተሳፈረች:: የተቀመጠችው ግን ለነጮች ብቻ በተፈቀደ የፊት ለፊት መቀመጫ ወንበር ላይ ነበር:: የፊት መቀመጫዎቹ ወዲያውኑ ሞሉ:: አንድ ነጭ ቆሞ ይታያል:: ሾፌሩ ሲመለከት አራት ጥቁር ተሳፋሪዎች “ለነጮች ብቻ” ተብሎ በተከለለው መቀመጫ ወንበር ላይ ተቀምጠዋል:: “ለራሳችሁ ደህነት ስትሉ መቀመጫዎችን ልቀቁልኝ” አለ አሽከርካሪው:: አንድ ወንድ እና ሁለት ሴቶች ሲነሱ የ43 ዓመቷ ልባም ሴት ግን አልተነሳችም፤ ወንበሯን አለቀቀችም፤ ይች ሴት ሮዛ ፓርክስ ትባባላለች::

ተሳፋሪዎች ፀጥ ብለው ትዕይንቱን በአንክሮ ይመለከታሉ:: ሁሉም የከተማውን የአውቶቡስ ጉዞ  ደንብ እና ሥርዓት ያውቃሉ:: ጥቁሮች ከኋላ መቀመጥ አለባቸው:: “ለነጮች ብቻ” የሚፈቀዱት መቀመጫዎች ሁሉም ከተያዙ “ልዮ ዞን “ተብሎ በተከለለው የጥቁሮች መቀመጫ የተቀመጡ ጥቁር ተሳፋሪዎች እንዲቆሙ ይደረጋል። ይህም ማለት ጥቁሮች የራሳቸውን መቀመጫ ለነጮች እንዲለቁ ይደረጋል:: በወቅቱ ሁሉም የአውቶቡስ ሾፌሮች ነጮች ነበሩ:: እነዚህ ሾፌሮች “የጉዞ ደንብ” ያላከበሩ ጥቁሮችን የማሳሰር ስልጣን ነበራቸው:: በመሆኑም ሾፌሩ ጄምስ ብሌክ አውቶቡሱን አቁሞ “ስሚ ሴትዮ መቀመጫው ስለሚፈለግ ልቀቂ እያልኩሽ ነው! አትነሽም?” አለ መናደዱ ፊቱ ላይ እየተነበበ:: “አልነሳም!” አለች ፓርክስ ካደረገችው መነጽር ሥር ያሉትን ዓይኖቿን ፍጥጥ አድርጋ::

“እሺ ካልተነሳሽ የማሳስርሽ መሆኔን እወቂው”

“ቀጥል ማሳሳር ትችላለህ” አለች ሮዛ ፓርክስ:: ብሌክ ለፓሊስ ሲደውል ፓሊሶቹ ወዲያውኑ ከተፍ አሉ::

“ለምንድነው የማትነሽው” ሲል የፓሊስ መኮንኑ ሮዛን ጠየቃት።

“አስፈላጊውን ክፍያ ፈጽሜያለሁ:: መቀመጫየን ለመልቀቅ የሚያስችል  አሳማኝ ሁኔታ ያለ አይመስለኝም” አለች::

ሮዛ ፖርክስ በፓሊስ መኪና ተወሰደች:: ጥቁር ተሳፋሪዎች   ርስ በርስ እየተያዩ ራሳቸውን ነቀነቁ:: አድሎአዊ የሆኑ ሕጎችን መቃወም ለእስር፣ ለግርፋት አለፍ ሲልም ለሞት ያበቃ ነበር:: ይህ የሮዛ ፓርክስ የዘረኝነት ተቃውሞ እና የተወሰደባት እስራት ማርቲን ሉተር ኪንግ ትንሹና እርሱ ያለበት የዴክስተር ቤተክርስቲያን ከአከባቢው የጥቁር ማህበረሰብ አባላት ጋር የሚከተለውን ውሳኔ አስተላለፉ።

“ሰኞ ታህሳስ አምስት ወደ ከተማ ትምህርት ቤት ወይም ወደማንኛውም ቦታ ስትሄዱ በአውቶቡስ እንዳትሳፈሩ!” ሰኞ ቀንም ደረሰ በጠዋት በጃክሰን ጎዳና የሚያልፈው የመጀመሪያውን የህዝብ ማመላለሻ አውቶቢስ ተመለከቱ:: የዚህ መስመር ተሳፋሪዎች በብዛት ጥቁሮች ነበሩ:: አንድም ጥቁር ግን በአውቶቡሱ አልተሳፈረም ነበርና አውቶቢሱ ባዶ ነበር:: ሁለተኛው አውቶቡስ መጣ:: አሽከርካሪው ብቻ ነው የሚታየው:: ከኋላ ያሉት መቀመጫ ወንበሮች የሰው ያለህ የሚሉ ይመስላሉ:: ያን ዕለት ጥቁሮች ሁሉ በእግራቸው ነበር የሚጓዙት:: እጃቸውን የሚያውለበልቡ በበቅሎ የሚጓዙ አንዳንዶች ደግሞ ቀድሞ የረሱትን የፈረስ ጋሪ ገጣጥመውና ጠጋግነው በጋሪ የሚንቀሳቀሱ ነበሩ:: መኪና ወይም ታክሲ የያዙ ሰዎችም መንገድ ላይ እየቆሙ ለሌሎች ተሳፋሪዎች አገልግሎት ይሰጡ ነበር:: በሮዛ ፓርክስ የተጀመረው ተቃውሞ ያስከተለው የአንድ ቀን አመጽ በሞንቶጎመሪ ታሪክ ታይቶ የማይታወቅ የመሰረት ድንጋይ ጥሎ አልፏል::

 

ኪንግ

“ሕልም አለኝ” የሚለው የማርቲን ሉተር ኪንግ ንግግር አሜሪካ ውስጥ ያለውን የዘር ጭቆና እና የእኩልነት መብት አለመከበር የሚቃወም ነበር። በርካቶችን ለተሻለ አስተሳሰብ አነሳስቷል፤ ታዋቂና ቀንደኛ ሰዎችን አከራክሯል፤ ዛሬም ድረስ የሚነገርለት ሐሳብ ሆኗል። ነገር ግን ዛሬም ላይ እነዚህ ጉዳዮች እልባት አላገኙም። ጥቁር እና ድሀ ማኅበረሰቦችን ለማግለል ተብለው የሚወጡ የምርጫ እገዳዎችና ሌሎችም ተግባራት ማርቲን ሉተር ኪንግ ሲታገልለት የነበረው ጭቆና አሁንም ድረስ ስለመኖሩ ማሳያ ነው ሲል ብላክ ሂስትሪ መንዝ ድረገጽ በ2025 መረጃው አስፍሯል።

ነሐሴ ወር 1963 ዓ.ም ላይ እስከ 250 ሺህ የሚደርሱ ሰዎች ዋሽንግተን ዲሲ ወደሚገኘው ታዋቂው ሊንከን ሜሞሪያል (የሊከን ማስታወሻ)  ተምመው ነበር። ይሄ ሁሉ ሰው ታዲያ አንድ ሰው ንግግር ሲያደርግ ለማዳመጥ ነበር። ስሙም ዶክተር ማርቲን ሉተር ኪንግ ጁኒየር ይባላል። ንግግሮቹ ዛሬም ድረስ በመላው ዓለም እንደ ነጻነት ማብሰሪያ ይታያሉ።

እ.በአ. በ1998 ‘The Autobiography of Martin Luther King, Jr.’ በሚል ርዕስ በደራሲ ክሌይቦርን ካርሰን ለንባብ የበቃው መጽሐፍ ላይ እንደሰፈረው፣ ማርቲን ሉተር የተወለደው እ.አ.አ  ጥር 15 ቀን 1929 በደቡባዊ አሜሪካ ጆርጂያ ግዛት ውስጥ ነበር:: አባቱ እሳቸው ካለፉበት የሕይወት ዓይነት በተለየ መልኩ ልጆቻቸው እንዲሄዱ ከፍተኛ ፍላጎት ነበራቸው። ዘርና ቀለምን መሠረት ያደረገ መድልዎ በመላው ደቡባዊ አሜሪካ ተንሰራፍቶ ነበር። በርካታ ይህንን የሚደግፉ ሕጎችም ተግባራዊ ይደረጉ ነበር። ጥቁር ሰዎች እና ነጭ ሰዎች በተለያየ አካባቢ ነበር የሚኖሩት። እንዲገናኙ አይፈለግም። ጥቁሮች ለጥቁሮች ብቻ ተብለው በተሰሩ ምግብ ቤቶች እና መጠጥ ቤቶች ብቻ ነበር የሚዝናኑት። ሌላው ቀርቶ ከቦታ ቦታ ለመንቀሳቀስ እንኳን ጥቁሮች  እጅግ ባረጁ መኪናዎች እንዲጓዙ ተደርጓል። በአጠቃላይ ጥቁሮች ምንም ያህል ጥሩ ሥራ ቢሠሩም ከነጮች ያነሰ ክፍያ እንዲሰጣቸው የሚፈቅዱ ሕጎች ነበሩ።

የጥቁሮች ትምህርት ቤት፣ የጥቁሮች የጤና ተቋማት እና የጥቁሮች መንደር እየተባለ መከፋፈል በጊዜው የተለመደና ተቀባይነት ያለው ተግባር ነበር። በፖለቲካው ዘርፍ ደግሞ ጥቁሮች እነሱ የፈለጓቸውን መሪዎች እንዳይመርጡ በተጠና እንዲሁም በተዘዋዋሪ መልኩ ሲሠራ ነበር። ነገር ግን አሁን ላይ የማርቲን ሉተር ኪንግ ሕልሞች በሙሉ ተሳክተዋል ብላችሁ ካሰባችሁ ተሳስታችኋል።

የእርሱ ቤተሰቦች እንደሚሉት በተለይ በቅርብ ወራት እየተስተዋሉ ያሉ ነገሮች ከማርቲን ሕልም በእጅጉ የራቁና የተቃረኑ ናቸው። በእነማርቲን ሉተር ኪንግ ዘመን ጥቁሮችን በግልጽ ያገልሉ የነበሩ ሕጎች አሁንም መልካቸውን ቀይረው እንዳሉ ናቸው ሲሉ  አያሌ የጥቁሮች መብት ተሟጋቾች ይገልጻሉ።

 

ማልኮም

“በሰላምም ይሁን በአመፅ – ነፃነት በአስፈላጊው መንገድ ሁሉ!” ይል ነበር ማልኮም ኤክስ በየንግግሩ አዝማች፤ እንደልማድም ሆኖበት፤ ደግሞም የነፃነትን አስፈላጊነት ለማፅናት:: ጥቁሩ የመብቶች ተሟጋችና ታጋይ ማልኮም ኤክስ  የካቲት 14 ቀን 1957 ዓ.ም ኒው ዮርክ ከተማ ላይ ንግግር እያደረገ ሳለ በተተኮሰበት ጥይት በ39 ዓመት ዕድሜው መገባደጃ አካባቢ ተገደለ::

ማልኮም በ21 ዓመት ዕድሜው በዘረፋ ወንጀል ተከስ ወኅኒ በገባ ጊዜ ወጣቱ ማልኮም ኤክስ “ኔሽን ኦፍ ኢስላም” ወይም “እሥላማዊ መንግሥት” ይባል የነበረው ንቅናቄ መሪ የኤላይጃ ሙሐማድ ተከታይ እንደሆነ በሕይወት ታሪኩ ላይ የሚያጠነጥነው “the Authobiography of malcom x 1965” መጽሐፍ ላይ ተጽፏል:: በኋላም የተዋጣለት የንቅናቄው መሪና ሰባኪ፣ ስሜት አቀጣጣይ ተናጋሪነትም ወጣው::

የማልኮም ኤክስ የትግል ሥልት በዘመኑ በአሜሪካ ጥቁሮች ንቅናቄ ውስጥ እጅግ ተናኝቶ ከነበረውና ከሕንዳዊው ማኅትመ  ጋንዲ ከተቀዳው የማርቲን ሉተር ኪንግ ሰላማዊ መሥመር በፍፁም የተለየ ነበር:: ማልኮም ኤክስ ራስን መከላከልንና ከነጮች ራስን ማራቅን አበርትቶ ይመክር ነበር:: ፕሬዚዳንት ጆን ኤፍ ኬኔዲ በኅዳር ወር  1956 ዓ.ም በነፍስ ገዳይ ጥይት የወደቁ ጊዜ ማልኮም ኤክስ ሁኔታውን ጣል ጣል አድርጎ ሲናገር የ“ኔሽን ኦቭ ኢስላም” መሪው ኤላይጃ ሙሐማድ ማልኮም “እጅግ ኃይለኛ ሆነ” በሚል ከንቅናቄው እንዲወገድ ወሰነ::

ማልኮም ኤክስ ከሜካ “ሃጂ ማሊክ ኤል-ሻባዝ” ተብሎ ወደ ሃገሩ ተመለሰና በሰኔ 1966 ዓ.ም “የአፍሮ-አሜሪካ አንድነት ድርጅት”ን መሠረተ:: ይህ ድርጅት የጥቁርን ማንነት ማስተማር፣ የአሜሪካ ጥቁሮች ጠላት የነጭ ዘር ሳይሆን ዘረኝነት መሆኑን አበርትቶ መስበክ ያዘ:: ይህ የተለሳለሰ የማልኮም ፍልስፍና በሲቪል መብቶች ንቅናቄ፣ በተለይ ደግሞ በተማሪዎች ሁከት-አልባነት አስተባባሪ ኮሚቴ ዘንድ እጅግ የተወደደ እየሆነ መጣ::

ማልኮም ኤክስ በኔሽን ኦፍ ኢስላም አባላት በተተኮሰ ጥይት ከመገደሉ ከአንድ ሳምንት በፊት መኖሪያ ቤቱ በቦምብ ተደብድቦ ተቃጥሏል:: በማልኮም ኤክስ ግድያ ላይ መሣተፉን ያመነው ብቸኛ ሰው ታመስ ሄጋን በ1958 ዓ.ም የዕድሜ ልክ እሥራት ተፈርዶበት 44 ዓመቱን በወኅኒ ከፈፀመ በኋላ ምኅረት ተሰጥቶት ወጥቷል::

ማልኮም ኤክስ በአሜሪካ ጥቁሮች የሲቪል መብቶች ትግል ታሪክ ውስጥ ሲታወስ ይኖራል::

 

ሳምንቱ በታሪክ     

የአልጋወራሹ ሞት

 

ልዑል ራስ ስዩም መንገሻ ታህሳስ 7 ቀን 1953 ዓ.ም ሞቱ፡፡ ራስ ስዩም በጎጃም ጠቅላይ ግዛት ዝምብሪ በምትባል የአገው ምድር ከተማ ውስጥ ሰኔ 17 ቀን 1878 ዓ.ም ነው የተወለዱት፡፡ አባታቸው፣ የዐፄ ዮሐንስ 4ኛ ልጅና አልጋ ወራሻቸው የሆኑት ራስ መንገሻ ዮሐንስ ሲሆኑ፣  እናታቸው የአገው ምድር ባላባት የሆኑት ወይዘሮ ተዋበች ወልደገብርኤል ይባላሉ፡፡

ልዑል ራስ ስዩም  ሕዝባቸውን በቀናነት እና በታማኝነት ያገለግሉ ነበር:: የቤታቸውን በር ለሕዝብ ክፍት በማድረግ ግብሩ ዓመት እስከ ዓመት ሳያቋርጥ ይወጣ ነበር:: ለታረዘው፣ ልብስ ለሌለው፣ ገንዘብ ለቸገረው እንደየፍላጎቱ ይረዱ እንደነበር ደጃዝማች ከበደ ተሰማ “የታሪክ ማስታወሻ’’ በሚል በ1962 ዓ.ም በአወጡት መጽሐፍ አትተዋል::

በ1953 ዓ.ም በተደረገው የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ ወቅት የመፈንቅለ መንግሥት ጠንሳሾቹ የመንግሥት ልዑላንን፣ መሳፍንትን፣ መኳንንትን እና ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናትን ጠርተው አሁን የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በሆነው በገነተ ልዑል ቤተ መንግሥት ውስጥ አስረዋቸው ነበር:: ከታሰሩትም ውስጥ ልዑል ራስ ስዩም መንገሻ አንደኛው ስለነበሩ የታሰሩት በሙሉ ያለምንም ምህረት በጥይት ሲረሸኑ እርሳቸውም አብረው ተረሽነዋል።

 

የሰብአዊ መብቶች ዓለም አቀፍ መግለጫ

እ.ኤ.አ ታህሳስ 10 1948 የሰብአዊ መብቶች ዓለም አቀፍ መግለጫ በተባበሩት መንግሥታት ጠቅላላ ጉባኤ ተቀባይነት አግኝቶ ጸድቋል፤ ይህም በዓለም አቀፍ ደረጃ ለሰብአዊ መብቶች እውቅና ትልቅ ምዕራፍ ነበር ሲል የዩኤን ፋዉንዴሽን መረጃ ያመላክታል።

 

(ቢኒያም መስፍን)

በኲር የህዳር  29 ቀን 2018 ዓ.ም  ዕትም

 

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here