የጮቄ ሰንሰለታማ ተራራ

0
17

የጮቄ  ሰንሰለታማ ተራራ መገኛው በአማራ  ብሔራዊ ክልል ምሥራቅ ጐጃም ዞን ነው፡፡ ለተራራው በሰሜን ባህር ዳር በደቡብ ደብረ ማርቆስ በቅርበት የሚገኙ ትልልቅ ከተሞችም ናቸው፡፡ በምሥራቅ በኩል የቢቸና እና ሞጣ አነስተኛ ከተሞችም ይገኛሉ፡፡ የጮቄ ሰንሰለታማ ተራራ ከአዲስ አበባ 300 ኪሎ ሜትር ይርቃል፤ ከምስራቅ ጐጃም ዞን ዋና ከተማ ደብረ ማርቆስ የሰባት ሰዓት መንገድ መጓዝንም ግድ ይላል፡፡ የጮቄ ሰንሰለታማ ተራራ ዝቅተኛው 1000 ሜትር፣ ከፈተኛው ደግሞ 4070 ሜትር ተለክቷል፡፡ ተራራው የዓባይ ወንዝ የውኃ ማማ በመባልም ይታወቃል፣ ለ59 ትልልቅ እና 273 አነስተኛ ጅረቶች መነሻ በመሆኑ ወንዞቹም ሆኑ ትንንሾቹ ጅረቶች ተደማምረው ዓባይን እንደሚያጐለብቱ ድረ ገፆች አስነብበዋል፡፡

በጮቄ ሰንሰለታማ ተራራ የበርካታ አጥቢ እንስሳት ዝርያዎች ይገኛሉ- ከነዚህ መካከል አቦ ሸማኔ፣ ቀበሮ፣ ዝንጀሮ፣ የዱር ዓሳማ እንዲሁም በአካል መጠናቸው አነስተኛ አጥቢ እንስሳትንም አካቶ ይዟል፡፡

የጮቄ ሰንሰለታማ ተራራ ቀጣና ከ85 በላይ የእፅዋት እና ዓዕዋፍ ዝርያዎች ይገኙበታል፡፡ ከነዚህ መካከል በሌሎች ቦታዎች የማይገኙ ብርቅዬዎች መኖራቸውም ተረጋግጧል፡፡ለአብነት  “አቢሲኒያን ሎንግ ክላው” ባለረዥም ጥፍሩ የወፍ ዝርያ የመጥፋት አደጋ ያንዥበበበት መገኛ መሆኑም ተመላክቷል፡፡

በቀጣናው የሚገኘው “ኢኮ ቪሌጅ”ም በተባበሩት መንግሥታት የቱሪዝም ድርጅት በምርጥነቱ እውቅና ተሰጥቶታል፡፡

የቀጣናውን ብዝሃ ህይወት፣ ስነምህዳሩን ለመጠበቅ የመሬት  መንሸራተት፣ ልቅ ግጦሽ፣ የደን መመንጠር በስጋትነት ተቀምጠዋል፡፡

ለዘገባችን በመረጃ ምንጭነት ቪዚት ኢትዮጵያ እና ወርቃምባ ቱር ድረገፆችን ተጠቅመናል፡፡

(ታምራት ሲሳይ)

በኲር የካቲት 2 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here