ስደተኞች የስደት ታሪክ ብቻ እንደሌላቸው በርካታ ስፖርተኞች አስመስክረዋል። በትውልድ ሀገራቸው በተፈጠረው ቀውስ ምክንያት በተለያዩ የዓለም ሀገራት ቢሰደዱም በስፖርቱ ዘርፍ ትልቅ አስተዋጽኦ ማድረጋቸውን ዘ ጋርዲያን አስነብቧል። በርካቶችም በጦርነት ምክንያት ከሀገራቸው ሸሽተው በተጠጉባቸው ሀገራት እና በስደተኞች መጠለያ (Refuge camp) አድገው ታላቅ እና ታዋቂ ስፖርተኛ መሆን ችለዋል።
እነዚህ ስፖርተኞች የጥንካሬ እና የቁርጠኝነት ምሳሌ በመሆን ታሪካቸው ለትውልድ ይተላለፋል። የስደተኞች መጠለያ በርካታ ባለተሰጥኦ እና ድንቅ ስፖርተኞችን አፍርቷል። የእነዚህ ስፖርተኞች ታሪክ በጀብዱ የተሞላ ነው፤ የመጡበት መንገድ በወጣቶች ዘንድ የይቻላል ስሜት እንዲፈጠር አድርጓል ይላል የዘ ጋርዲያን ዘገባ። ሞ ፋራህ፣ ሉካ ሞድሪች፣ ቪክተር ሞሰስ እና የመሳሰሉት ከአስከፊ የጦርነት ድባብ ወጥተው ራሳቸውን ወደ ታላቅ ስፖርተኛነት አሸጋግረዋል።
የረጅም ርቀት ሯጩ ሞ ፋራህ በአትሌቲክስ ስፖርት ከታላላቅ ሯጮች መካከል አንዱ ስለመሆኑ ስሙ ይጠቀሳል። ሞ ፋራህ አራት የኦሎምፒክ እና ስድስት የዓለም ሻምፒዮና የወርቅ ሜዳሊያዎችን አሸንፏል። ስኬታማው የ42 ዓመቱ ሯጭ በምስራቅ አፍሪካዊቷ ሀገር ሶማሊ ላንድ ነው የተወለደው። ሞ ፋራህ የአራት ዓመታት ታዳጊ እያለ ነበር አባቱ ካህን በሶማሊ ላንድ የነፃነት ጦርነት ወቅት ህይወቱ ያለፈው።
ታዲያ በዚህ ወቅት ከእናቱ ጋርም ተለያይቶ ወደ ሶማሊያ ዋና ከተማ ሞቃዲሾ አቀና። በስምንት ዓመቱም በጅቡቲ አድርጎ በህገወጥ መንገድ ወደ እንግሊዝ አቅንቷል። በፈረንጆች ሚሊኒየም የእንግሊዝ ዜግነት በማግኘት በአትሌቲክስ ስፖርት መሳተፍ ጀመሯል። ሞ ፋራህ ገና በለጋ እድሜው ከቤተሰቦቹ ቢለይም በምንም ሳይበገር የእንግሊዝ የምንጊዜም ታላቅ ሯጭ ለመሆን በቅቷል።
በእግር ኳስ ታሪክ ከምርጥ የመሀል ሜዳ ሞተሮች መካከል ክሮሺያዊው ሉካ ሞድሪች አንዱ ነው። ሞድሪች በ2018 እ.አ.አ ባሎን ዶርን ማሸነፉ የሚታወስ ነው። በወቅቱ ቡድኑን በአምበልነት በመምራት ክሮሺያን በዓለም ዋንጫ ለፍጻሜ ማድረሱ አይዘነጋም። የመሀል ሜዳው ሰው እ.አ.አ 1985 በክሮሺያ እንደተወለደ ዘ ጋርዲያን ያስነብባል። ሞድሪች በአያቶች ቤት ነው ያደገው። ከ1991 እስከ 1995 እ.አ.አ ክሮሺያ ራሷን ከዩጎዝላቪያ ለመገንጠል ከዩጎዝላቪያ ሕዝብ ጦር ጋር እና ከአካባቢው የሰርብ ኃይሎች ጋር ጦርነት ማድረጓን የታሪክ ድርሳናት ይነግሩናል።
ታዲያ በዚህ ጦርነት ምክንያት ወንድ አያቱ ሞቷል። ይህንን ተከትሎም ቀሪ የቤተሰብ አባሎች በዚያ በሀገራቸው በሚገኙ የስደተኞች መጠለያ ገብተዋል። ለረጅም ዓመታት በመጠለያ ጣቢያ የቆየው ታዳጊው ሞድሪችም ከሌሎች ታዳጊዎች ጋር እግር ኳስ መጫወት እንደጀመረ የግል የታሪክ ማህደሩ ያሳያል። በሆቴል የመኪና ማቆሚያ፣ በመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤቶች እና የእግር ኳስ አካዳሚዎችም መጫወት ያዘወትር እንደነበር ታሪኩ ያስረዳል።
የተደላደለ ኑሮ የሚኖሩ እግር ኳሱን ለመቀላቀል ምቹ ሁኔታ የተፈጠረላቸውን በርካታ ወጣቶች የሉካ ሞድሪች አስደናቂው የእግር ኳስ ህይወት ብዙዎችን አንቅቷል። ለዐስር ዓመታት በክርስቲያኖ ሮናልዶ እና ሊዮኔል ሜሲ ብቻ ተይዞ የነበረውን የባሎንዶር ሽልማት የበላይነት በመግታት ያሸነፈ ምርጥ የአማካይ ስፍራ ተጫዋች ነው።
አሁን ላይ በዓለም ላይ ካሉ ምርጥ የግራ መስመር ተከላካዮች መካከል ከቀዳሚዎች ተርታ ይሰለፋል- አልፎንሶ ቦይሌ ዴቪስ። የ24 ዓመቱ ተከላካይ በቡንደስ ሊጋው ክለብ ባየርሙኒክ የሚጫወት ሲሆን በፍጥነቱ፣ ኳስ በመግፋት እና በፈጠራ ክህሎቱ የላቀ ተጫዋች ነው። አልፎንሶ ዴቪስ ከላይቤሪያ ስደተኛ ቤተሰቦቹ ነው ጋና ውስጥ የተወለደው።
ቤተሰቦቹ በሁለተኛው የላይቤሪያ የእርስ በእርስ ጦርነት ወቅት ወደ ጋና መሰደዳቸውን የዓለም አቀፉ የስደተኞች ድርጅት አመልክቷል። እ.አ.አ በ2005 የአልፎንሶ ዴቪስ ቤተሰቦች ጋና ከሚገኘው የስደተኞች መጠለያ ጣቢያ ወጥተው ወደ ካናዳ አቅንተዋል። ዴቪስ ካናዳ በሚገኙ የተለያዩ ክለቦች ጎልብቶ በጀርመኑ ኃያል ክለብ ባየርሙኒክ ቤት አስደናቂ ጊዜ አሳልፏል፤ እያሳለፈም ይገኛል። ተከላካዩ የተባበሩት መንግስታት የስደተኞች በጎ አድራጎት ድርጅት አምባሳደርም መሆን ችሏል።
በትውልድ አንጎላዊ በዜግነት ፈረንሳያዊ የሆነው ካማቪንጋ ከምርጥ ወጣት አማካዮች መካከል ይጠቀሳል። ሁለገቡ ተጫዋቹ የኋላ ተመላላሽም ሆኖ መጫዎት ይችላል። የሪያል ማድሪዱ ወጣቱ ኮከብ በ2002 እ.አ.አ በአንጎላ የስደተኞች ጣቢያ ነው የተወለደው። ቤተሰቦቹ በጦርነት ምክንያት ከዲሞክራቲክ ኮንጎ ተሰደው ነው በአንጎላ የስደተኞች መጠለያ የተጠጉት። ካማቪንጋ የሁለት ዓመት ህጻን እያለ ከቤተሰቦቹ ጋር ወደ ፈረንሳይ አቅንቷል።
የፈረንሳይ ህይወት እና ኑሮ ለካማቪንጋ ቤተሰቦች አልጋ ባልጋ አልነበረም። በ2013 እ.አ.አ የቤተሰቦቹ ቤት ሙሉ በሙሉ በመውደሙ ምክንያት ካማቪንጋ ትምህርቱን አቋርጦ ወደ እግር ኳስ ፊቱን እንዲያዞር ምክንያት ሆኖታል። አሁን ላይ ተጫዋቹ የሪያል ማድሪድ እና የፈረንሳይ ብሄራዊ ቡድን ወሳኝ ተጫዋች መሆን ችሏል።
የቀድሞው የቸልሲው አጥቂ ቪክተር ሞሰስ በኢንተር ሚላን እና ሊቨርፑልን ጨምሮ በበርካታ ክለቦች በውሰት ውል ተጫውቶ አሳልፏል። የ34 ዓመቱ ሞሰስ በናይጀሪያ ካዱና ከተማ ነው የተወለደ። የአስራ አንድ ዓመት ታዳጊ እያለ በሀገሪቱ በነበረው የእርስ በእርስ ጦርነት ቤተስቦቹን አጥቷል። በወቅቱ እርሱ ከጓደኞቹ ጋር ኳስ እየተጫወተ በመሆኑ ህይወቱ ሊተርፍ እንደቻለ ዘ ጋርዲያን አስነብቧል። በጓደኞቹ እርዳታ ከሞት የተረፈው ታዳጊው ሞሰስ ከተወሰነ ጊዜያት በኋላ ወደ እንግሊዝ ተሰዷል። በእንግሊዝ የስደተኞች መጠለያ ጣቢያም ድጋሚ ከሚወደው እግር ኳስ ጋር ተገናኝቷል። የመጀመሪያ ክለቡም ክሪስታል ፓላስ ሆኗል። ሞሰስ በፈጣን እግሮቹ ድህንነትን እስከወዲያኛው በመሸኘት ስኬታማ ለመሆን በቅቷል።
ሳራ እና ዩስራ ማርዲኒ እ.አ.አ በ2015 በጦርነት የምትታመሰውን ሶሪያን ሸሽተው ግሪክ ገብተዋል። ወደ ተርኪዬ በሚያቀኑበት ወቅትም የሚጓዙበት ጀልባ ሞተር በመበላሸቱ ከጥልቅ የሜዲትራንያን ባህር በታምር መትረፋቸውን የተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን ( UNHCR) መረጃ አመልክቷል። እህትማማቾች በሶሪያ ደማስቆ ከልጅነታቸው ጀምሮ የውኃ ዋና ስፖርትን ሲያዘወትሩ እንደነበር መረጃው ያመለክታል። ከሶሪያ ወደ ተርኪዬ ሲያቀኑ ድንገት መርከቧ መበላሽቷን ተከትሎ በሜዲትራንያን ባህር ጨለማ እና ቀዝቃዛ ውኃ ውስጥ ከሦስት ሰዓታ በላይ ዋኝተው ህይወታቸውን አትርፈው ተርኪዬ ገብተዋል። ከዚያም መቄዶኒያ፣ ሰርቢያ፣ ሀንጋሪ እና ኦስትሪያ ተጉዘዋል። በመጨረሻ ጀርመን መዳረሻቸው ሆኗል። ትንሿ ዩስራ በውኃ ዋና ስፖርት ስትገፋበት ታላቅ እህቷ ሳራ ግን ወደ ሌላ ሙያ ተሸጋግራለች።
በወቅቱ ሳራ 20 ዓመቷ ሲሆን እህቷ ደግሞ ዩስራ ገና 18 ዓመቷ ነበር። ታዲያ ዩስራ ማርዲን በ2016 እና 2020 እ.አ.አ ኦሎምፒኮች መሳተፏን የግል የታሪክ ማህደሯ ያስነብባል። አይበገሬነቷ እና ጥንካሬዋ በኔትፍሊክስ ዘጋቢ ፊልም ተዘጋጅቶላታል። “ስደተኞች ይህ የመጨረሻቸው ባለመሆኑ ተስፋ መቁረጥ የለባቸውም” ስትል መልዕክት ታስተላልፋለች።
የቀድሞው የሊቨርፑሉ ተከላካይ ዲያን ሎቨርን፣ በቦሲኒያ ሄርዞጎቪኒያ ጦርነት ከወላጆቹ ጋር ጀርመን ተሰዶ በኋላ ወደ ክሮሺያ ተመልሷል። ግራኒት ዣካ በኮሶቮ ጦርነት ወቅት ከቤተሰቦቹ ጋር ወደ አልባኒያ ከዚያም ወደ ስዊዘርላንድ በማቅናት ምርጥ የእግር ኳስ ተጫዋች መሆን ችሏል። እነዚህን ለአብነት አነሳን እንጂ በርካታ ስፖርተኞች ከአስጨናቂ እና አስከፊ የጦርነት፣ የስደት ህይወት በመውጣት ለታላቅ ስኬት የበቁ ስፖርተኞች እንዳሉ የዘ ጋርዲያን መረጃ ያስነብባል።
ጽናት፣ ተስፋ እና በችግር ወስጥ ሆኖ እንዴት እምቅ ተሰጥኦን አውጥቶ የመጠቀም ጥበብን ለሁሉም አስተምረዋል። ይህም በጦርነት ቀጣና እና በስደተኞች መጠለያ ጣቢያ ተሰጥኦ እና ክህሎት ሊገኝ እንደሚችል ዓለም ያወቀበት ነው። ስፖርት የሰው ልጆች ሁሉ እኩል የሚደሰቱበት ዓለም አቀፍ ቋንቋ መሆኑ የታየበት ጭምር ነው። ታዲያ በዚህ ምክንያት ባለፉት ሦስት ኦሎምፒኮች የዓለም ኦሎምፒክ ኮሚቴ የስደተኞች ቡድን በማቋቋም ማሳተፍ ጀምሯል።
(ስለሺ ተሾመ)
በኲር የሰኔ 30 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም