በአማራ ክልል በርካታ ትምህርት ቤቶች ወደ መማር ማስተማር ሥራ እንዳልገቡ የዞን ትምህርት መምሪያዎች አስታውቀዋል። በሌላ በኩል ትምህርትን ማቋረጥ የትውልድን የዕድገት ሂደት ማቋረጥ በመሆኑ ሁሉም አካል ተማሪዎች ወደ ትምህርት ቤት እንዲመጡ መተባበር እና ተማሪዎችም በአግባቡ እየተማሩ ስለመሆኑ መከታተል እንዳለበት የክልሉ ትምህርት ቢሮ አሳስቧል።
በጸጥታ ችግር አብዛኛዎቹ ትምህርት ቤቶች ካልተከፈተባቸው መካከል የምዕራብ ጎንደር ዞን አንዱ ነው። የዞኑ ትምህርት መምሪያ ኃላፊ ደሳለኝ አያና እንደተናገሩት በዞኑ የሚገኙ አብዛኛዎቹ ትምህርት ቤቶች በጸጥታ ምክንያት ባለመከፈታቸው ተማሪዎች እየተጎዱ ነው። ችግሮችን ተቋቁመው እየሠሩ ያሉት ከ238 ትምህርት ቤቶች ውስጥ 101 ትምህርት ቤቶች ናቸው።
ትምህርት ቤቶችን በመዝጋት እና የመማር ማስተማር ሥራቸውን እንዳያከናውኑ እንቅፋት በመፍጠር ለመደራደሪያነት የሚጠቀመው ኀይልም ራሱን ቆም ብሎ ማየት እንደሚገባው ነው ኃላፊው የተናገሩት። ከማኅበረሰቡ ጋር ተከታታይ ውይይት መደረጉን በማንሳት ተማሪዎች የነገ ሀገር ተረካቢ በመሆናቸው ትምህርታቸውን ያለ እንከን መከታተል እንዲችሉ ሁሉም መሥራት እንደሚገባው ነው የተናገሩት።
በተመሳሳይ በዞኑ ከሚገኙት 996 ትምህርት ቤቶች ውስጥ 86ቱ ብቻ እንደተከፈቱ የምሥራቅ ጎጃም ዞን ትምህርት መምሪያ አስታውቋል። የመምሪያው ኃላፊ ጌታሁን ፈንቴ እንዳሉት በትምህርት ዘመኑ በምሥራቅ ጎጃም ዞን 710 ሺህ ተማሪዎችን መዝግቦ ለማስተማር ታቅዶ ነበር። ከዚህ ውስጥ መመዝገብ የቻሉት ግን 70 ሺህ ብቻ ናቸው።
ተከፍተው ሥራ የጀመሩት ትምህርት ቤቶችም ከችግሮች የጸዱ አለመሆናቸውን ኃላፊው ተናግረዋል፤ ተማሪዎች ከትምህርት ገበታቸው ርቀው ቤት ሲውሉ በተለይ ሴት ልጆች ያለዕድሜ ጋብቻ እየተፈጸመባቸው መሆኑን እና ሌሎችም ያልተገባ ቦታ በመዋል ለወላጆቻቸው የጭንቀት ምንጭ እንደሆኑ በማንሳት የችግሩን አሳሳቢነት ገልጸውታል።
“ትምህርት ኋላቀርነትን የመዋጋት፣ ሀገርን እና ትውልድንም የማስቀጠል ተልዕኮ ነው፤ ማንም ይሁን ማን የልጆችን የትምህርት መንገድ ሊጠርግ እንጂ ሊዘጋ አይገባም” ብለዋል። በመሆኑም ችግሮችን በሰላም በመፍታት የለውጥ መሠረት የሆነውን ትምህርት እና ሌሎች ማኅበራዊ መስተጋብሮቻችንን ማስቀጠል የሁሉም ኃላፊነት ሊሆን እንደሚገባ አሳስበዋል።
ሰላም ተረጋግጦ ልጆች ወደ ትምህርት ቤት መመለስ በቻሉበት ጊዜ ሁሉ እየተቀበሉ ሁሉንም የትምህርት ይዘቶች በመሸፈን ለፈተና እንደሚያዘጋጁም አቶ ጌታሁን አስታውቀዋል።
በሌላ በኩል የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ እንዳስታወቀው በትምህርት ዘመኑ ሰባት ሚሊዮን ያህል ተማሪዎችን መዝግቦ ለማስተማር በዕቅድ ተይዞ ወደ ሥራ ተገብቷል፤ ቢሮው አክሎም “ትምህርትን ማቋረጥ የትውልድን የዕድገት ሂደት ማቋረጥ በመሆኑ ሁሉም አካል ተማሪዎች ወደ ትምህርት ቤት እንዲመጡ መተባበር እና የተመዘገቡ ተማሪዎችም በአግባቡ እየተማሩ ስለመሆኑ መከታተል ይኖርበታል” ብሏል።
በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የማኅበራዊ ዘርፍ አስተባባሪ እና የትምህርት ቢሮ ኃላፊ ሙሉነሽ ደሴ (ዶ/ር) “ረጅሙን የሕይወት መንገድ አንዳንዶቹ በጨለማ፣ ብልሆቹ ደግሞ በብርሃን ይጓዙታል፤ የሰው ልጅ ራሱን የሚቀይርበት እና የሕይዎት ጉዞውን ተስፋ የሚያንጸባርቅበት ትልቁ መሣሪያ ትምህርት ነው” ብለዋል።
በክልሉ በሰላም እጦት ምክንያት እየተፈተነ ያለውን ትምህርት ለመታደግ ሁሉም የድርሻውን እንዲወጣ ተጠይቋል።
(ጌትሽ ኃይሌ)
በኲር የጥቅምት 25 ቀን 2017 ዓ.ም ዓ.ም ዕትም)