“ችግርን ችግር ሁኑበት”
ተማሪ መልካሙ ውድነህ “ችግርን ችግር ሁኑበት” የሚለው የመምህሩ ንግግር በሕይወቱ ላይ አወንታዊ ተጽእኖ ፈጥሮለታል:: መልካሙ ተወልዶ ያደገው፣ እስከ 11ኛ ክፍል ትምህርቱንም የተከታተለው በምዕራብ ጎጃም ዞን ደምበጫ ወረዳ ነው:: ከ2015 ዓ.ም መጨረሻ ጀምሮ በአማራ ክልል ያጋጠመው የሰላም መደፍረስ ግን የ11 ዓመታት የትምህርት ጉዞውን ገታው፤ የሰላም እጦቱ በ2016 ዓ.ም ቀጥሎ ከትምህርት ውጪ ሆኖ እንዲከርም አደረገው::
በ2017 የትምህርት ዘመን ዳግም ለሁለተኛ ዓመት ከትምህርት ውጪ ሆኖ መክረምን አልፈቀደም:: የ11 ዓመታት የትምህርት ጉዞው መቋጫም 2017 ዓ.ም መሆን እንዳለበት ራሱን አሳመነ:: በተጠናቀቀው የትምህርት ዘመን “ትምህርት ዛሬ፣ ነገ፣ ወይስ ከወራት በኋላ ይጀመራል?” በሚል ሐሳብ መንታ መንገድ ላይ መቆየት አልፈለገም:: አንጻራዊ ሰላም ያለባቸውን አካባቢዎች የ11 ዓመታት የትምህርት ጉዞ መቋጫው ቀዳሚ መዳረሻው አደረገ:: መሸኛ ይዞ ወደ ባሕር ዳር ከተማ አመራ::
ባሕር ዳር ከተማ እንደገባም የክልሉ ትምህርት ቢሮ ከባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር ባመቻቸው ዕድል ተጠቃሚ ሆኖ ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ትምህርቱን ሲከታተል እንደከረመ ተማሪ መልካሙ ያስታውሳል:: የ12ኛ ክፍል ትምህርቱንም በውጤታማነት ቋጨ፤ ያስመዘገበው ውጤትም 540 ሆነ:: ይህ ውጤቱም በክልሉ ትምህርት ቢሮ ዕውቅና እና ሽልማት እንዲቸረው አድርጎታል::
እንደ ተማሪ መልካሙ ገለጻ ውጤቱ በቀላሉ ሳይሆን በብዙ ውጣ ውረድ እና ፈተና የተገኘ ነው:: ከትምህርት ውጪ ሆኖ የቆየበት የአንድ ዓመት ቁጭት እና የክልሉ ትምህርት ቢሮ የጣለበት ኃላፊነት ትምህርቱን ማጠናቀቅ ብቻ ሳይሆን ከፍተኛ ውጤት እንዲያስመዘግብም አቅም ሆነው:: ከዚህ በተጨማሪ የዓመታት የቤተሰብ ውለታ በጊዜ አጠቃቀሙ ላይ ተጽእኖ መፍጠራቸውን ተናግሯል::
“ችግርን ችግር ሁኑበት” የሚለው የመምህሩ ንግግርም ትልቅ ስንቅ እንደሆነው ነው የገለጸው:: ይህ ንግግር ክልሉ የገጠመው የሰላም እጦት በተማሪዎች ስነ ልቦና ላይ ተጽእኖ እንዳይፈጥር፤ ችግሮችን እንደ መስፈንጠሪያ መውሰድ እንደሚገባ የሚያትት ይዘት ያለው ነው:: እነዚህ ሁሉ ጥረቶች ከ500 በላይ ውጤት አስመዘግባለሁ ብዬ እንድነሳ አደረገኝ፤ ዕቅዴም ተሳክቶ 540 ውጤት አስመዘገብሁ” ሲል ጥረቱን ተናግሯል::
የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ተማሪ መልካሙ ውድነህን ጨምሮ በ12ኛ ክፍል ብሄራዊ መልቀቂያ ፈተና ከፍተኛ ውጤት ላስመዘገቡ ተማሪዎች ዕውቅና እና ሽልማት ሰጥቷል::
የተጠቃለሉ አኃዞች ምን ይነግሩናል?
በምክትል ርእሰ መስተዳደር ማዕረግ የማኅበራዊ ዘርፍ አስተባባሪ እና የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ሙሉነሽ ደሴ (ዶ/ር) እንዳስታወቁት ባለፉት ሦስት ዓመታት የ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተናዎችን የሚወስዱ ተፈታኞች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየቀነሰ መጥቷል:: በአንጻሩ በማለፊያ ነጥብ እና በከፍተኛ ውጤት ማስመዝገብ ከፍተኛ መሻሻል እየታዬ ነው ብለዋል::
እንደ ቢሮ ኃላፊዋ ገለጻ በ2014 ዓ.ም 246 ሺህ 946 ተማሪዎች የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና ወሰዱ:: ከእነዚህም ሦስት ነጥብ ስድስት በመቶ ተፈታኞች የማለፊያ ነጥብ አምጥተዋል:: ከእነዚህም ውስጥ ከፍተኛ ውጤት ያስመዘገቡት ተማሪዎች ቁጥር 70 ነበር::
በ2015 ዓ.ም የ12ኛ ክፍል የተፈታኞች ቁጥር ካለፈው ዓመት በ36 ሺህ 623 ዝቅ ሲል የማለፍ ምጣኔው አራት ነጥብ አንድ ሆኖ ተመዘገበ:: በትምህርት ዘመኑም 60 ተማሪዎች ከፍተኛ ውጤት አስመዘገቡ:: ይህም ከ2014 የትምህርት ዘመን ጋር ሲነጻጸር በአሥር ተማሪዎች ያነሰ ነበር::
በ2016 ዓ.ም የ12ኛ ክፍል ብሄራዊ መልቀቂያ ፈተና የወሰዱ ተማሪዎች ቁጥር 95 ሺህ 879 እንደነበር ዶ/ር ሙሉነሽ አስታውሰዋል:: ይህም ከ2015 ዓ.ም ጋር ሲነጻጸር በ114 ሺህ 444 ያነሰ ነው:: ለዚህም ዋናው ምክንያት አሁንም ድረስ የትምህርት ዘርፉ ዋነኛ ፈተና ሆኖ የዘለቀው የጸጥታ ችግር ነው::
በየዓመቱ የሚመዘገበው የማለፍ ምጣኔ ከተፈታኝ ተማሪዎች ቁጥር አንጻር ሲቃኝ እጅግ የወረደ ቢሆንም ከባለፉት ሁለት ዓመታት አኳያ ሲታይ ግን የተሻለ ነበር:: የስድስት ነጥብ ስድስት በመቶ አፈጻጸሙ የሚያሳየውም ይህንኑ ነው:: በዚህ ወቅት 219 ተማሪዎች ከፍተኛ ውጤት አስመዝግበው ዕውቅና እና ሽልማት እንደተሰጣቸውም ይታወሳል::
በ2017 የትምህርት ዘመንም 94 ሺህ 668 ተማሪዎች የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና ወስደዋል:: የማለፊያ ነጥብ ያስመዘገቡት ተማሪዎች የመቶኛ ስሌትም 12 ነጥብ አምስት በመቶ እንደሆነ ዶ/ር ሙሉነሽ አስታውቀዋል::
በዚህም አገላለጽ መሠረት በአጠቃላይ ከተፈተኑት ውስጥ የዩኒቨርሲቲ መግቢያ የመጣላቸው ተማሪዎች ቁጥር 11 ሺህ 833 ናቸው ማለት ነው::
ከፍተኛ ውጤት አስመዝግበው በክልሉ ትምህርት ቢሮ ዕቅና እና ሽልማት የተሰጣቸው ተማሪዎች ቁጥርም ባለፉት ሦስት ዓመታት ከተመዘገበው በ103 ተማሪዎች ብልጫ አለው:: 452 ተማሪዎች ከፍተኛ ውጤት አስመዝግበው ዕውቅና እና ሽልማት በተበረከተላቸው ወቅት ዶ/ር ሙሉነሽ ባደረጉት ንግግር፤ “ዘንድሮ የተመዘገበው ውጤት ባለፈው ዓመት ከተመዘገበው በእጅጉ መሻሻል ታይቶበታል” ብለዋል::
ተሸላሚዎች በቀጣይ ሕይወታቸው ውስጥ ይበልጥ አሸንፎ ለመውጣት፣ በተለያዩ ነባራዊ ሁኔታዎችም ውስጥ ራስን ለማላመድ በሥነ ልቦና ዝግጁ እንዲሆኑ መልዕክት አስተላልፈዋል:: “የዛሬው አርአያነታችሁ ለተተኪ እህት እና ወንድሞቻችሁም ትልቅ ኅይል እንዲሆን የዛሬውን ስኬታችሁን በቀጣይ የትምህርት ዘመንም ይበልጥ እንድታጠናክሩት” በማለትም ቢሮ ኃላፊዋ ከአደራ ጋር አሳስበዋል::
በክልሉ በከፍተኛ ውጤት የተመዘገበው ለውጥ እና ያስፈተኗቸውን ተማሪዎች ሙሉ ለሙሉ ያሳለፉ ሰባት ትምህርት ቤቶች ለነገው የትምህርት ሥራ አነሳሽ መሆናቸውን ቢሮ ኃላፊዋ ጠቁመዋል:: በአንጻሩ ያስፈተኗቸውን ሙሉ ለሙሉ ማሳለፍ ያልቻሉ 61 ትምህርት ቤቶች ደግሞ ትልቅ የቤት ሥራ እንዳለ ያሳዩ መሆናቸውን ተናግረዋል::
ለተሻለው ነገ ምን ተባለ?
የክልሉ የትምህርት ሥራ ከባለፉት ሦስት ዓመታት ወዲህ በሰው ሠራሽ እና ተፈጥሯዊ ችግሮች ክፉኛ እየተፈተነ መሆኑን ዶ/ር ሙሉነሽ ጠቁመዋል:: ያጋጠመው ፈተና በትምህርት ተሳትፎ፣ ጥራት እና ተደራሽነት ላይ ተጽእኖ መፍጠሩንም ገልጸዋል:: የክልሉ ሕዝብ ለትምህርት የሚሰጠው ከፍ ያለ ዋጋ ግን አሁንም ውጤታማ ልጆችን ከማውጣት እና ከማፍራት እንዳላገደ ነው የጠቆሙት:: ሆኖም ግን የገጠመውን ችግር ፈጥኖ ማስተካከል ካልተቻለ በቀጣይ ብቁ እና ተወዳዳሪ ልጆችን ለማፍራት ለሚደረገው ጥረት እንቅፋት መሆኑ አይቀሬ ነው ብለዋል::
እንደ ዶ/ር ሙሉነሽ ገለጻ “የልጆቻችን የወደፊት የትምህርት ጉዞ የሰመረ የሚሆነው ዛሬ ላይ ዕድሜያቸው ለትምህርት የደረሱ ሕጻናትን ስናስመዘግብ ነው:: በሥነ ምግባር የተካኑ፣ በአመለካከት እና በዕውቀት የዳበሩ፣ ቴክኖሎጂን የሚጠቀሙ እና የሚያላምዱ፣ ሥራ ፈጣሪ እና ሀገር ተረካቢ ዜጎችን ለማፍራት የዛሬው ትውልድ ትልቅ ኃላፊነት አለበት:: በመሆኑም በየቤቱ ዕድሜያቸው ለትምህርት የደረሱ ሕጻናት ወደ ትምህርት ቤት እንዲሄዱ ሁሉም ኃላፊነት ስላለበት መረባረብ ይኖርበታል” በማለት ጥሪ አስተላልፈዋል::
የፈተና ሂደት ለውጡ፣ ተስፋ እና ስጋቱ
የ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተና ውጤት መለቀቅን አስመልክቶ የትምህርት ሚኒሥትሩ ፕሮፌሰር ብርሐኑ ነጋ መግለጫ በሰጡበት ወቅት እንዳስታወቁት ከ2014 ዓ.ም ጀምሮ በፈተና አሰጣጥ ሂደቱ ላይ የተወሰደው እርምጃ ኢትዮጵያ በኢኮኖሚ፣ በማኅበራዊ እና በቴክኖሎጂ መድረስ ከምትፈልግበት ደረጃ የሚያደርሳት ነው:: የፈተና ስርቆት፣ ኩረጃ እና ሌሎች አግባብ ያልሆኑ መንገዶች ማን በትክክል ተምሮ ምዘናውን አለፈ? የሚለውን ለመለየት እንቅፋቶች ሆነው ለዓመታት መስተዋላቸውን አስታውሰዋል:: “እነዚህ ችግሮች የሞራል ክስረታችን ማሳያዎች ናቸው” ሲሉም አጽንኦት ሰጥተዋል::
ሁሉን ነገር በስርቆት፣ በማጭበርበር… ማግኘት ይቻላል ተብሎ የሚታመንበት የሞራል መሠረት ላይ የቆመ ሀገር በምንም አይነት መመዘኛ ዕድገቱን ሊያረጋግጥ እንደማይችል አስገንዝበዋል:: ፈተናዎች አስተዳደር ላይ የተወሰደው ማስተካከያ ከጊዜ ወደ ጊዜ ለውጥ እየታየበት መምጣቱን ያስታወቁት ፕሮፌሰሩ፣ በዚህ ዓመት ከስርቆት እና ከማጭበርበር ጋር የተያያዙ ችግሮች በእጅጉ መቀነሳቸውን በማንሳት ነው:: በ2014 ዓ.ም 20 ሺህ 400 ማጭበርበሮች መከሰታቸውን ያስታወሱት ፕሮፌሰር ብርሐኑ፤ በዚህ ዓመት ወደ 120 ዝቅ ማለቱን ለተወሰደው እርምጃ ውጤት አድርገው አንስተዋል::
በተጠናቀቀው የትምህርት ዘመን 585 ሺህ 882 ተማሪዎች የ12ኛ ክፍል ብሄራዊ መልቀቂያ ፈተና መውሰዳቸውን ሚኒሥትሩ አስታውቀዋል:: የማለፊያ ነጥብ ያስመዘገቡት ግን 48 ሺህ 929 እንደሆኑ ተናግረዋል:: ይህም ባለፈው ዓመት የማለፊያ ውጤት ካስመዘገቡት አንጻር ሲታይ የሦስት በመቶ ብልጫ እንዳለው አሳውቀዋል:: ይህ አኃዝ ትምህርት ሚኒሥቴር የማለፊያ ነጥብ ማሻሻያ ያደረገበትን ያካተተ አይደለም::
በፈተናው ከ500 በላይ ውጤት በማስመዝገብ የተገኘውን እመርታም ሚኒሥትሩ በዝርዝር አስረድተዋል:: አዲሱ የፈተና ሂደት ሙሉ ለሙሉ ተግባራዊ መሆን በጀመረበት 2014 ዓ.ም ከ500 በላይ ውጤት ያስመዘገቡት 173 ተማሪዎች ብቻ ነበሩ:: ይህ ቁጥር በ2016 ዓ.ም ወደ አንድ ሺህ 221 አድጓል:: በ2017 የትምህርት ዘመን ደግሞ ወደ ሁለት ሺህ 384 ከፍ እንዳለ ሚኒሥትሩ አስታውቀዋል::
አዳሪ ትምህርት ቤቶች ከፍተኛ ቁጥር ያላቸውን ተማሪዎች በማሳለፍ ቀዳሚውን ስፍራ ይዘዋል:: የዓለም ዓቀፍ ማኅበረሰብ ትምህርት ቤቶች፣ የግል እና የመንግሥት መደበኛ ትምህርት ቤቶች ቀጣዩን ደረጃ ይዘው ያጠናቀቁ መሆናቸውን ፕሮፌሰር ብርሐኑ አረጋግጠዋል::
አንድ ሺህ 249 ትምህርት ቤቶች ደግሞ ያስፈተኗቸውን ሁሉንም ተማሪዎች ያላሳለፉ ናቸው:: አሁንም በመንግሥት ትምህርት ቤት ተማሪዎች ላይ ሰፊ ሥራ መሠራት እንደሚገባ ውጤቱ ማሳያ እንደሆነ አረጋግጠዋል::
በቀጣይ ለትምህርት ዘርፉ ውድቀት ምክንያት የሆኑትን ችግሮች ለይቶ በማውጣት መንግሥት፣ ወላጆች፣ ተማሪዎች… ከፍተኛ ሥራ እንዳለባቸው አስገንዝበዋል::
(ስማቸው አጥናፍ)
በኲር የመስከረም 26 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም