“የፊልም ዘርፉ እንዲያድግ ሃያሲዎች ያስፈልጋሉ!”

0
62

የወንዶች ጉዳይ የተሰኘውን ተወዳጅ የአማርኛ ፊልም አዘጋጅቷል:: ከአዘጋጅነቱ በፊት በአብርሃም ፀጋዬ በተዘጋጀው “ነጻ ትውልድ” የተሰኘ ፊልም ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ ተውኗል:: ከዚያ ወደ አዘጋጅነቱ በማዘንበል በድርጊት የተሞሉ፣ የፍቅር፣ አስፈሪ እና ሌሎች ዘውግ ያላቸው ከ15 በላይ ፊልሞችን አዘጋጅቷል:: በቅርቡ በአባ ጊዮርጊስ ዘ ጋስጫ ላይ ያተኮረ አዲስ ፊልም ለተመልካች ያደርሳል፡- የፊልም አዘጋጅ እና ተዋናይ ሄኖክ አየለ:: በኢትዮጵያ ሲኒማ ዙሪያ ከሄኖክ አየለ ጋር ያደረግነውን ቆይታ እነሆ!

ትያትር እና ትወና ምንድን ነው የሚለውን ያስተማረኝ ብርሃኑ በቀለ ነው:: ያኔ አዲስ ከተማ ወወክማ ውስጥ ኃላፊ ነበር:: በኋላም የሁለተኛ ደረጃ እና ኮሌጅ መምህሮቼ መሠረት ጥለውብኛል:: በስም አንዱን ጠርቼ አንዱን መተው አልችልም:: በኋላም “ነጻ ትውልድ” የተሰኘውን ፊልም ለመሥራት የመለመለኝ አብርሃም ጸጋዬ ነበር::

ኢትዮጵያ ውስጥ ሲኒማ የለም! እያሉ የሚከራከሩ ሰዎች አሉ፤ በአንተ ዘንድ ሲኒማ ኢትዮጵያ ውስጥ አለ? ወይስ የለም?

ሲኒማ አለ! ነው የምለው:: አለ! ብየ ከቆምኩ ግን ሊያደናግር ስለሚችል እንዳብራራው ይፈቀድልኝ:: ሲነማ የሚባል ነገር ኢትዮጵያ ውስጥ በመኖሩ ነው ይሄን ቃለ ምልልስ እያደረግን ያለነው:: ሲኒማ ስንል ሁልጊዜ ሆሊውድን እንዲመስል ወይም እጅግ በጣም ውስብስብ በሆነ ካሜራ መቀረጽ አይደለም ጉዳዩ:: በካሜራ ተቀርጾ፣ አርትኦት ተሠርቶ ታሪክ መውጣት ሲችል የሲኒማ ሥራ ይባላል:: ሌላ ምንም ልንለው አንችልም:: ደረጃ ልንሰጠው እና ልናወዳድረው እንችላለን:: ኢትዮጵያ ውስጥ ሲኒማ የለም! ማለት ለእኔ ይከብደኛል:: ምክንያቱም ብዙ ተመልካች ያፈሩ ሥራዎች አሉ:: ዛሬም ድረስ እየታዩ ነው:: አነሰ በዛ እዚህ ጋር ጎደለ እንላለን እንጂ ሲኒማ አለ! የለም! በሚለው መከራከር የለብንም:: ሲኒማው ምን አይነት ነው የሚለው ሌላ ርዕስ ነው::

ኢትዮጵያ ውስጥ ምን አይነት ሲኒማ ነው ያለው? ደረጃውስ ምን ይመስላል?

የእኛ ሀገር ሲኒማ የብዙ ሀገሮች ተጽዕኖ አለበት:: የመጀመሪያው የአሜሪካ ሲሆን የሆሊውድ ተጽዕኖ ከፍተኛ ነው:: ይሄን ደግሞ ከአኗናር ዘይቤያችን ጋር ስናይ ካደግንበት መንገድ የሚመጣ ነው:: የእነ ቻክ ኖሪስ እና የእነ ጆን ክላውድ ቫንዳም ተጽዕኖ ቀላል አይደለም:: ተጽዕኖውን ማምለጥ አይቻልም ወይም ማምለጥ ከባድ ነው:: ረጅም ዓመት ሲሠራብን ቆይቷል፤ አዕምሯችን ውስጥ ተቀርጿል:: ካሜራ ከጠመድክ በኋላ ይሄንን ፍሬም መተው አትችልም:: ስለዚህ በተወሰነ መልኩ ሆሊውድ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ሲኒማችን ውስጥ ይንጸባረቃል::

በሌላ በኩል ደግሞ ሕንድ አለች:: ቦሊውድ በሙዚቃዎቹ እሹሩሩ ብሎ ነው ያሳደገን:: ይሄንንም ተጽዕኖ እና ፍሬም ማምለጥ አይቻልም:: ትንሽ ደግሞ ከሄድን የቻይና በድርጊት የተሞሉ ፊልሞችን እናገኛለን:: ይህም ተጽዕኖ አለው:: ስለሆነም ኢትዮጵያ ውስጥ ፊልም እየሠሩ ያሉ ልጆች የኋላ ታሪካቸው ቢጠና ሲያዩ የመጡት ይሄንን ነው:: ስንቃቸው ይሄ ነው:: ከዚህ ውስጥ ትንሽ ሊካተት የሚችለው በሬዲዮ የምንሰማቸው ትረካዎች፣ ድራማዎች፣ አካባቢያችን የሚሰጠን እውቀት ነው፣ ዘየ እና ሌሎች ግብዓቶች ናቸው::

አንዳንድ ፊልም ሠሪዎች ተጽዕኖውን በመረዳት ከራሱ ከተጽዕኖው ለመላቀቅ እና ሀገራዊ ነገር ይዞ ለመምጣት ይጥራሉ:: ሌሎች ደግሞ ተመችቷቸው ዓለም አቀፍ ህግ አድርገው ይዘውት ቀጥለዋል:: ከላይ የጠቀስናቸው ሀገሮች ተጽዕኖ አለበት ማለት ግን እነሱን አክሏል ማለት አይደለም:: ተጽዕኖው ግን የሚታይ እና በጥናቶችም የተረጋገጠ ነው:: በአጭሩ የኢትዮጵያ ሲኒማ የሌሎች ሀገራት ባሕል፣ ቴክኒክ እና የአነጋገር ዘዬዎች ተጽዕኖ አለበት::

የአሜሪካ፣ ሆሊውድ፣ የሕንድ ቦሊዉድ፣ የናይጀሪያ ኖሊውድ የሚባሉ የፊልም ኢንደስትሪዎች አሉ፤ የኢትዮጵያን የፊልም ኢንድስትሪ በዛ ደረጃ

ማምጣት ያስፈልጋል ብለህ ታምናለህ? ይህስ አንዴት ሊሆን ይችላል?

ይህ እኔ ያስፈልጋል ብየ የምከራከርበት ጉዳይ ነው:: ለአንዳንዶች የቆየ እና ያረጀ ክርክር ይመስላቸዋል:: ለእኔ ግን እስካሁን አዲስ እና ያላለፈበት ሀሳብ ነው:: በደንብ ልናወራበት ይገባል:: ሆሊውድን የመሳሰሉ ኢንደስትሪዎች በቀጥታ የመንግሥት አይደሉም፤ ነገር ግን የየሀገራቱን ርዕዬተ ዓለም ያስፈጽማሉ:: ስለዚህ ኢትዮጵያ ውስጥ የሚሠሩ ፊልሞች እሴት እስከፈሰሰባቸው ድረስ የኢትየየጵያ ፊልሞች ሚል ስያሜ ይኖራቸዋል:: ዘለቅ ብለን ገብተን ይዘቱን ካየን ደግሞ እንዴት ራሳችንን ይገልጻል? ምን ምን የጋራ መገለጫዎች አሉት? ብለን ስናወጣ ያን ጊዜ የኢትዮጵያ ሲኒማ መለያዎች እና ቀለሞች ይወጣሉ::  ያ ደግሞ ብዙ ጥቅም አለው፤ የራስን ታሪክ በራስህ ሳይበረዝ መተረክ መቻል አንዱ ጥቅም ነው::

አንዳንዶች በነጭ ካሜራ በመጣ መሣሪያ ቀርጻችሁ “የኢትዮያ የኢትዮጵያ” አትበሉ የሚሉ አሉ:: ካሜራው ታሪክን ለመንገር የምትጠቀምበት ነው:: በዋናነት ታሪክ ነገራው ላይ ነው ትኩረት መደረግ ያለበት:: በእርግጥ ቴክኖሎጂው አንዳንድ ነገሮች ላይ አሠራሩ ተጽዕኖ ሊኖረው ይችላል:: ለምሳሌ በነጮች የተሠራ ካሜራ የብርሃን ምጣኔው፣ ጥራቱ ለነጮች ቆዳ ታስቦ ተሠርቶ ሊሆን ይችላል:: ዘመኑ እስኪፈቅድ ይሄንን ትተነው የእኛ ሀገር የሚመስል ሲኒማ እና ኢንደስትሪ እዲኖር መታገል አለብን:: እኛ ከጀመርነው የሚቀጥለው ትውልድ ደግሞ አጠናክሮ ያስኬደዋል:: የሀገር ገጽታን እንገንባ! ሕዝብ እንጥቀም! ከተባለ በዚህ መንገድ መኬድ አለበት::

የኢትዮጵያ ሲኒማ የታሪክ ችግር አለበት የሚሉ አሉ፤ ሌሎች ደግሞ ታሪክ አለ ያንን በስርዓት መተረክ ነው ያቃተን ብለው የሚከራከሩ አሉ፤ አንተ ምን ትላለህ?

እንደዚህ አይነት ነገሮች በጥናት ነው መገለጽ ያለባቸው:: ጥናቶቹም ሳይቀር ብዙ ማሟላት ያለባቸው ክፍተቶች አሉ:: ነገሮችን አጠቃሎ በመደምደም አልስማማም:: የኢትዮጵያ ፊልሞች እንደዚህ ናቸው ለሚል የጅምላ ውሳኔ ገና ነን:: በጣም ምርጥ ምርጥ ታሪኮች አሉ፤ ነገር ግን ጥሩ ባልሆነ መንገድ ስለቀረቡ ተቃባይነት አላገኙም:: በጣም ደካማ ታሪክ እያላቸው አቀራረባቸው በማማሩ ግን ትልቅ ተቀባየይነት ያገኙ ሲኒማዎች አሉ:: የኢትዮጵያ ሲኒማ በአብዛኛው እንደዚህ ነው ተብሎ ቢቀርብ ይሻላል:: ሁሉን መደምደሙ ለሲኒማ ዘርፉም ጥሩ አይደለም:: የማይካደው ነገር ተደጋጋሚ ዓይነት ታሪኮች ይቀርባሉ፣ ገበያውን ተከትሎ የሚመጡ ሥራዎችም ይኖራሉ፣ ተመሳስለው የተሠሩ ፊልሞችም አሉ:: የተሻለ ተቀባይነት አገኘ የተባለውን አይነት የፊልም ዘውግ መሥራት እየቆየ ችግሩን ነው የሚብሰው፤ ይሄም በተግባር ታይቷል:: ታሪኮች አሉን በዚያ ላይ በተቻለ መጠን የራስን እሴት እና እውቀት ጨምሮ መሥራት ውጤታማ ያደርጋል::

የኢትዮጵያ ሲኒማ መድረስ አለበት ተብሎ የሚፈለግበት ደረጃ ለመድረስ የሦስት አካላት መኖር እና መቀናጀት አስፈላጊ ነው ስትል ትደመጣለህ::

እነዚህ አካላት እነማን ናቸው? እንዴት መቀናጀት አለባቸው?

እነዚህ አካላት ፊልም ሠሪው፣ ተመልካቹ እና ሃያሲው ናቸው:: የየራሳቻው ድርሻም በሲኒማው ዘርፍ አላቸው:: ፊልም ሠሪው ከሕብረተሰቡ ያየውን ግብዓት ወስዶ በምናቡ ታሪክ አዳብሮ የሚያቀርበው ነው:: ተመልካቹ ደግሞ የፊልሙ ተደራሽ ነው:: በፊልሙ ይማራል፣ ይዝናናል አሊያም መልዕክት ያገኛል፤ በዚህ መካከል ሃያሲ የሚባል አካል ያስፈልጋል:: ይህ አካል የተሠሩ ስህተቶች ካሉ ለማረም ይጠቅማል:: ሙያዊ በሆነ መንገድ አዲስ አቅጣጫም ይጠቁማል:: ይህ አካል በጣም ጠቃሚ ነው፤ ከአሉባልታ እና ከስድብ የጸዳ ሥርዓት ያለው ሙያዊ አስተያየት ይሰጣል:: ሃያሲው አስተያየት እና ሂስ ለመስጠት በሙያው ከፊልም አዘጋጁ የተሻለ መሆን አለበት:: በኢትዮጵያ ሲኒማ የታሪክ እና ዘውግ መመሳሰል የመጣው ሃያሲ የሚባለው አካል በመጥፋቱ ነው:: አንዳድ ጊዜ እጅግ ጥሩ ሥራ ተሠርቶ በተመልካቹ ላይወደድ ይችላል፤ በዚህ ጊዜ “አይሆንም! በዚህ መንገድ እዩት! ተሳስታችኋል!” የሚል አካል ያስፈልጋል:: በዚህ መንገድ ነው ሲኒማ የሚያድገው:: ከዚህ ባሻገር ዕወቅት በጣም ያስፈልጋል:: ሌላው ደግሞ ገንዘብ ነው:: ገንዘብ እና ስነ ምግባር ለሲኒማችን እድገት ወሳኝ ነገሮች ናቸው::

ኢትዮጵያ ውስጥ ብቁ ሀያሲያን አሉ?

የሉም! ብልጭ ብልጭ ብለው ነበር! አንዳንዶቹን ተቆጥተን አስደነገጥናቸው መሰለኝ፤ የበቁ ሀያሲያን አልነበሩም! ከሊትሬቸር እና ትያትር መጥተው ሞክረው ነበር፤ ፊልሙ ላይ እኛ ማደግ እንደምንፈልገው እነሱም እደዚያ ቢሄዱ ጥሩ ነበር::

ስለነበረን ቆይታ እናመሰግናለን!

እኔም አመሰግናለሁ!፡፡

(ቢኒያም መስፍን)

በኲር የሰኔ 30 ቀን 2017 ዓ.ም  ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here