“የፊደል ስህተት ካለ የተስተካከለ ፊደል ቆርጠን በማምጣት እንደገና እንለጥፋለን”

0
151

በአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን ታሪክ የመጀመሪያዎቹ ከሚባሉት ይመደባሉ:: በብዕር ስማቸውም የሰሉ ጽሑፎችን በማቅረብ፣ ችግር ፈቺ ዘገባዎችን በመሥራት የሚሞገሱ ጋዜጠኛ ነበሩ:: በበኲር ጋዜጣ፣ በአማራ ራዲዮ እና በአማራ ቴሌቪዢን ሠርተዋል:: የጋዜጠኝነት፣ የቋንቋ፣ ማኔጅመንት እና ከተማ አስተዳደር ትምህርት የተማሩ ሲሆን የሁለተኛ ዲግሪያቸውንም ይዘዋል፤ የቀድሞው ጋዜጠኛ ዘውዱ ሞኝነቴ:: በአሁኑ ወቅት በከተሞች እና መሠረተ ልማት ቢሮ በዓለም ባንክ የከተሞች ልማታዊ ሴፍትኔት ፕሮግራም የጀንደር ስፔሻሊስት ናቸው:: ከእሳቸው ጋር የነበረንን ቆይታ በክፍል አንድ እንደሚከተለው አቅርበናል፤

መልካም ንባብ!

 

የልጅነት እና የትምህርት ሁኔታዎን ያጫውቱን?

የተወለድኩት በደብረ ማርቆስ ከተማ ነው:: ከአንደኛ እስከ ሰባተኛ ክፍል በንጉሥ ተክለ ሃማኖት አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ነው የተማርኩት:: በትምህርቴ በጣም ጎበዝ ከሚባሉ ተማሪዎች ውስጥ አንዱ ነበርኩ:: እኖር የነበረውም ከእናቴ ጋር ነው:: ታላቅ ወንድሜ አዲስ አበባ ይኖር ነበር:: ሰባተኛ ክፍል ላይ “ከደረጃ አንደኛ ከወጣህ አዲስ አበባ አመጣሃለሁ” ብሎ ቃል ገባልኝ:: አዲስ አበባ መሄድ አለብኝ ብየ ጠንክሬ ተማርኩ:: አይደለም ከክፍል ከትምህርት ቤቱ አንደኛ ወጣሁ:: በዚህም አዲስ አበባ ሄድኩ፤ ከስምንተኛ እስከ 10ኛ ክፍል በዳግማዊ ምኒልክ እንዲሁም 11ኛ እና 12ኛ ክፍል ቦሌ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማርኩ:: ከዘጠነኛ እስከ 12ኛ ክፍል ከግቢው አንደኛ ነበር የምወጣው:: ከዛ ጥሩ ውጤት አምጥቼ ዩኒቨርሲቲ ገባሁ:: በእንግሊዝኛ ቋንቋ የመጀመሪያ ዲግሪየን አገኘሁ:: በመምህርነትም ተመደብኩ::

 

ለምን መምህርነትን መረጡ?

በነበረኝ ከፍተኛ ውጤት ህክምና ወይም ምህንድስና መማር እችል ነበር:: ነገር ግን ለመምህርነት ፍቅር ነበረኝ:: እዛ ደረጃ ላይ ያደረሱኝ መምህሮቼ ናቸው:: በወቅቱ አጋዥ መጽሐፍ የለም፤ በቅጡ የተሰናዳ ቤተ መጽሐፍት የለም፤ ኢንተርኔት አልነበረም:: ከመምህሮቼ ጋር ጥብቅ ቁርኝት ነበረኝ፤ እነሱም ናቸው የእውቀት ምንጮቼ፤ ስለሆነም መምህር የመሆን ከፍተኛ ፍላጎት አደረብኝ::

ሁለተኛ ደረጃ በነበርኩበት ጊዜ በተለያዩ የትምህርት ዓይነቶች ሌሎች ተማሪዎች አንብበው ለፈተና የሚዘጋጁባቸውን መርጃ ጽሑፎች እናዘጋጅ ነበር፤ መምህሮቼ በዚህ ልክ አብቅተውኛል:: በሌላ በኩል ደግሞ ታላቅ ወንድሜ ትምህርት ሚኒስቴር ይሠራ ስለነበር በሱም በኩል ዝንባሌው አድሮብኛል:: የሚያሳዝነው በመምህርነት አንድ ዓመት ከስድስት ወር ብቻ ነው የሠራሁት::

 

ምን ተፈጠረ?

በመምህርነት እየሠራሁ ደብረ ማርቆስ የአካባቢ ሬዲዮ ላይ ማሕደረ ቅዳሜ እና ዝክረ ሰንበት የተሰኙ ፕሮግራሞች ላይ በስነ ጽሑፍ እሳተፍ ነበር:: “ዘውዱ ሞኝነቴ ከሰፈረ ቅሬ” በሚል የብዕር ስም ነበር የምሳተፈው:: የፕሮግራሙ አዘጋጆች በብዕር ስም ይጽፉ ነበር፤ ከእነሱ ጋር ሁሉ እንሟገታለሁ:: በአካል አንተዋወቅም ነበር::

በኋላ የትምህርት መገናኛ ዘዴዎች “ለምን በአካባቢ ሬዲዮ ላይ የሚሳተፉ ልጆችን የጋዜጠኝነት አጭር ስልጠና አንሰጣቸውም?” በሚል በአድራሻችን ተፈልገን አዲስ አበባ ተጠራን:: የፕሮግራም አዘገጃጀት ላይ 15 ቀን ስልጠና ተሰጠን:: በወቅቱ ደግሞ የየክልሎችን መገናኛዎች ለማቋቋም ጥረት እየተደረገ ነበር:: የኮተቤ መምህራን ኮሌጅ የቋንቋ መምህር የነበሩት እና በዛን ጊዜ የክልሉ ማስታወቂያ ቢሮ ኃላፊ የነበሩት አቶ ብቃለ ስዩም በክልሉ እየተዘዋወሩ ለሚዲያው የሚያስፈልጉ ሰዎችን ይሰበስቡ ነበር:: በዚያን ጊዜ “ዘውዱ ሞኝነቴን ብታገኙት?” ተብሎ ጥቆማ ተሰጣቸው::

በአድራሻየ ተደውሎ ባሕር ዳር ትፈለጋለህ ተባልኩ:: በ1986 ዓ.ም ነበር ጊዜው፤ ባሕር ዳር መጥቼ ሪፖረት አደረኩ:: ከአዲስ ዘመን እና ከኢትዮጵያ ሄራልድ ጋዜጣ የመጡ ጋዜጠኞች መጀመሪያ ፈተና ሰጡን፤ ጠዋት ተፈትነን ከሰዓት ውጤቱ ተለጠፈ:: ፈተናውን ያለፍን 12 ሰዎች ለስልጠና ተመረጥን:: በወቅቱ “ይህ የኢትዮጵያ ሬዲዮ ነው” የሚለውን መለያ (አይዲ) ከጋዜጠኛ ደጀኔ ጥላሁን በፊት የነበረውን ያነበበው አቶ ወንድወሰን ዓለሙ እንዲሁም የሄራልዱ ኤፍሬም እንዳለ እና የአዲስ ዘመን ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ ደምሴ ጽጌ ስልጠናውን ሰጡን:: እነሱን በአካል ማየት እጅግ አስደሳች እና የማይታመንም ነበር በወቅቱ:: ጋዜጠኛ ጌታቸው ፈንቴ፣ እምርት ሕገ እግዚአብሔር፣ ጌጤነሽ ዘውዱ፣ ወንድምኩን አላዩ፣ መስፍን ዘለቀ እና ሌሎች ሰልጣኞችም  ነበሩ::

 

ለጋዜጠኝነት ያደረብዎት ፍቅር ከምን የመነጨ ነው?

ከልጅነቴ ጀምሮ የስነ ጽሑፍ ፍቅር ነበረኝ:: ፍቅር እስከ መቃብርን ያነበብኩት ገና የሰባተኛ ክፍል ተማሪ ሆኜ ነው:: ያነበብኩትን ማታ ማታ ለቤተሰቦቼ በቃሌ አነበንብ ነበር:: አሁንም ቢሆን በቃሌ መናገር እችላለሁ (በዛብህ አዲስ አበባ ሆኖ ለሰብለ የጻፈውን ደብዳቤ በቃሉ አለው):: ትምህርት ቤት ውስጥም በአማርኛ ክፍለ ጊዜ ያነበብኳቸውን ድርሰቶች በየክፍሉ እየዞርኩ እተርክ ነበር:: እኔ ዘጠነኛ ልጅ ነኝ፤ እናታችን ክረምት ክረምት ጋዜጣ ትሰጠን እና ይህን አስመስላችሁ ገልብጡ ትለናለች፤ ሁሉን ነገር አስመስየ ምንም ሳላዛንፍ እጽፍ ነበር:: “ከታይፕ የእሱ ጽሑፍ ይሻላል” ይባል ነበር::

በሌላ በኩል ደግሞ ከሰው ፊት ወጥቶ ሀሳብን መግለጽ ወይም መናገር እወዳለሁ:: ይሄ ፍላጎት ከስነ ጽሑፍ ጋር ሲዋሃድ ወደ ጋዜጠኝነቱ ለመግባት ምክንያት ሆኖኛል:: ቅድም እንዳልኩት መምህርነቱንም ሳልጠግበው በገለጽኩት ምክንያት ለቅቄያለሁ::

የደብረ ማርቆስ አካበቢ ሬዲዮ ተሳትፎየ ወደ ማስታወቂያ ቢሮ እንድመጣ እድል ከፈተልኝ:: ከዚያ ስልጠና ወሰድኩ:: በወቅቱ የማይረሳኝ ስልጠና ከሚሰጡን መካከል የአዲስ ዘመን ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ  ደምሴ ጽጌ አንዱ ነው:: ቁመቱ እጅግ ከመርዘሙ የተነሳ ወደ ታች ጎብጧል:: እናም ጽሑፍ በደንብ ያጽፉን ነበር፤ ጽሑፌን ወጥቼ ሳቀርብ የሱን ረጅም ቁመት እና የእኔን አጭር ቁመና በማነጻጸር “ብዙ ጊዜ ረዥም ሰዎች አጭር ጽሑፍ ይጽፋሉ በሚል በስነ ልቦና ተመራማሪዎች ዘንድ ይነሳል፤ ዛሬ ግን ያየሁት አጭር ሆኖ አጭር እና ግልጽ ጽሑፍ የጻፈ ዘውዱ ሞኝነቴ ነው” ያለውን አልረሳውም:: ጽሑፎቹ በሳል ናቸው እያለ ያደንቀኝም ነበር፤ እኔ ደግሞ አንዱ ጋዜጠኛ እንድሆን ካነሳሱኝ ሰዎች ዋነኛው እሱ ነው:: በእሱ ሙገሳ ማግኝት የበለጠ ወደ ሙያ እንድገባ እና ፍቅር እዲያድርብኝ አድርጎኛል::

 

በወቅቱ  የአሁኑ አሚኮ የነበረበጽን ሁኔታ ይንገሩን?

ማስታወቂያ ቢሮን እንደተቀላቀልን ምንም ሚዲያ አልነበረም፤ የእኛም ሥራችን ለኢትዮጵያ ሬዲዮ እና ለኢትዮጵያ ቴሌቪዢን ወኪል ሆነን በየአካባቢው እየተዘዋወርን በጽሑፍ መረጃ መስጠት ነበር:: ከዚያ ታህሳስ ሰባት ቀን 1987 ዓ.ም በኲር ጋዜጣ ተመሰረተች:: አምድ ይዤ መጻፍ ጀመርኩ::

በወቅቱ አንድ ኮምፒውተር ብቻ ነበረን:: ጸሐፊዋ ተፈትና ስትቀላቀለን ምን አይነት ጸሐፊ ናት በሚል አጃኢብ ተብሎ ነበር:: እንደ አሁኑ ስላልነበር ግንዛቤያችን “ምን አይነት የቴክኖሎጂ እውቀት ያላት ናት?” ብለን እንገረም ነበር:: ከዚያ በፊት ታይፕ ራይተር ነው በደንብ የሚታወቀው:: ኮምፒውተር እንደ አሁኑ እንደልብ የሚገኝ ሳይሆን ከፍተኛ እና ውድ ቴክኖሎጂ ተደርጎ ነው የሚቆጠረው:: የኮምፒተሩን ገመድ እንኳ ላለመንካት ተጠንቅቀን ነበር የምንወጣ፤ የምንገባው:: ምክንያቱም ነክተነው ከጠፋ ብዙ ነገር አብሮ የሚጠፋ ነበር የሚመስለን::

 

የወቅቱ ቴክኖሎጂ ምን ይመስል ነበር?

እንደ አሁኑ በአዶቤ ወይም በሌላ መተግበሪያ አልነበረም የሚሠራው፤ በመጀመሪያ በኮምፒውተር በወርድ መተግበሪያ ይጻፋል፤ ከዚያ ዳሚ የሚባል አለ፤ ዳሚ ማለት የጋዜጣውን ዓይነት ቅርጽ ያለው ወረቀት ነው፤ የሚለጠፍበት ደግሞ መስታዎት አለ፤ ከስሩ የሸምበቆ (ፍሎረሰንት) መብራት አለ፤ ከዚያ  የተጻፈውን እየቆረጥን በየአምዳችን እየለለጠፍን እንሠራለን:: ለምሳሌ 16 ገጽ ከሆነ 16 ዳሚ ይሠራል:: ፎቶግራፍ የሚያስፈልገውም ከሆነ በጥቁር ወይም በቀለም ፎቶግራፉ ተቆርጦ ዳሚው ላይ ይለጠፋል:: የፊደል ስህተት ካለ የተስተካከለ ፊደል ቆርጠን በማምጣት እንደገና እንለጥፋለን:: ይህንን በጥንቃቄ ሠርተን ከጨረስን በኋላ ዐርብ ለህትመት አዲስ አበባ እንልካለን:: ጋዜጣዋን ወደ አዲስ አበባ ለመላክ ጥድፊያ ስላለ ዐርብ ዐርብ በኩር ትሸበራለች ይባል ነበር፤ ዐርብ በዚህ ሁኔታ የተላከች ሰኞ ታትሞ ትመጣለች::

ይቀጥላል

(ቢኒያም መስፍን)

በኲር ነሐሴ 13 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here