ያደጉ ሄገራት የዜጎቻቸዉን መለያ አንድ ብቻ እና ወጥ እንዲሆን ስራወችን ሰርተዋል፤ ሥርዓት ዘርግተዋል። ለምሳሌ በአሜሪካ የአንድ ግዛት ነዋሪ የነዋሪነት መታወቂያ ወይም የመንጃ ፈቃድ አለው። ከዚህ በተጨማሪ የማህበራዊ ደኅንነት ቁጥር ይኖረዋል። የማህበራዊ ደኅንነት ቁጥሩ በፌደራል ደረጃ የሚያገለግል ሲሆን፣ በየግዛቱ ደግሞ የመኖሪያ መታወቂያ ይኖረዋል።ኢትዮጵያም በቅርቡ ከተበታተነው የመታወቂያ ሥርዓት አልፋ ዲጂታል የፋይዳ መታወቂያ በመተግበር ላይ ትገኛለች።
የፋይዳ መታወቂያ አንድ ሰዉ አንድ መሆኑ የሚረጋገጥበት ስርኣት ሲሆን ሰዎችን ከአገልግሎት ጋር በተያያዘ ተጠቃሚ ለማድረግ እና ከሚደርስባቸዉ እንግልት ለመታደግም ሁነኛ መፍትሄ እንደሆነ ከሌሎች ሃገራት ተሞክሮ መረዳት ያቻላል። የፋይዳ መታወቂያ በብሄራዊ ደረጃ የሚዘጋጅ ብቻ በመሆኑ ለግለሰቦችም ሆነ ለአገር በርካታ ጠቀሜታወችን ያስገኛል።
ከጠቀሜታወች መካከል ዋና ዋናወቹን ለመጥቀስ ያህል የፋይዳ መታወቂያ ተጠያቂነትን ያሰፋል፤ህገ ወጥ አሰራር እና ስራወችን ያስቀራል፤ ስለግለሰቡ ሙሉ መረጃን ይሰጣል፤ግለሰቡ የተለያዩ ወንጀሎችን በመስራት ከቦታ ቦታ በመቀየር ከተጠያቂነት እንዳያመልጥ ያግዛል።
በሃገራችን ከዚህ በፊት በነበረዉ የመታወቂያ ስርአት ግለሰቦች በየአካባቢዉ የተለያዩ መታወቂያወችን በማዉጣት እና አገልግሎት ሰጭ ተቋማት እና ሃላፊወችን በማደናገር አላግባብ ለመበልጸግ ሲጠቀሙበት ተስተዉሏል። የህዝብ እና የመንግስት ቦታን በተደጋጋሚ ለመዉሰድ፣ መክፈል የነበረባቸዉን ትክክለኛ ግብር ላለመክፈል መታወቂያወችን በመቀየር እንዲሁም የግብር ከፋይ ቁጥር እና ንግድ ፈቃድን በመቀየር በርካታ ህገ ወጥ ተግባራትን ሲተገብሩበት ተስተዉሏል። በዚህም ኢትዮጵያ ልታገኘነዉ የሚገባዉን ገቢ እንድታጣ በማድረግ በኢኮኖሚዉ እና በልማቱ ላይ ብዙ ክፍተቶች እንዲፈጠሩ ጫና ፈጥሯል።
የፋይዳ መታወቂያ በርካታ አገልግሎቶችን ለማሳለጥ ይረዳል፡፡ በተለይ ከገቢዎች ፣ ከመሬት እና ከገንዘብ ነክ ጉዳዮች ጋር ተያያዞ የሚፈጠሩ ማጭበርበሮችን ለመከላከል እንደሚያግዝ በብሄራዊ መታወቂያ ከፍተኛ አማካሪ አቶ ኦላና አበበ ጠቁመዋል።
የፋይዳ መታወቂያ እነዚህንና መሰል ህገ ወጥ ተግባራትን ለመስራት ስለማያስችል እና ይልቁንም ተጠ ያቂነትን እና ህጋዊነትን እንዲሁም መተማመንን የሚፈጥር በመሆኑ ጠቀሜታዉ ከፍተኛ ነዉ።
በተጨማሪም ብሔራዊ መታወቂያ በልዩ የፋይዳ ቁጥሩ ሰዎችን ከተለያዩ መሥሪያ ቤቶች ጋር ለማስተዋወቅ፣ ከክልል ክልል ለማስተሳሰር ይረዳል፡፡ ለአብነት ባሕር ዳር ላይ ያለውን ሥርዓት አዳማ፣ አዋሳ፣ መቀሌ… ካለው ሥርዓት የሚያስተሳስር ወጥ የሆነ የግንኙነት መረብ የሚፈጥር ሥርዓት መሆኑን አማካሪዉ አስታዉሰዋል ፡፡
የፋይዳ መታወቂያ ማለት የዲጂታል መታወቂያ ሲሆን፣ ቴክኖሎጂን በመጠቀም የሰዎችን የተመጠነ ግላዊ መረጃዎችን (የባዮሜትሪክ እና ዲሞግራፊክ) መረጃዎችን በመሰብሰብ “አንድ ሰው አንድ ነው” በሚል መርኅ እያንዳንዱን ዜጋ በልዩ ሁኔታ መለየት የሚያስችል ሥርዓት መሆኑን የብሔራዊ መታወቂያ ፕሮግራም ያስረዳል።
በውስጡም መሠረታዊ የግል መረጃ የሚባሉትን ስም፣ ፆታ፣ የትውልድ ቀን እና የመኖሪያ አድራሻን ይይዛል። በተጨማሪም ለተግባቦት እና ለማረጋገጫ የሚያገለግሉ ኢሜይል እና ስልክ ቁጥርን አካቷል። ዋናው መረጃ ደግሞ ባዮሜትሪክ ነው፤ ይህም የሁለት የዓይን፣ የአስሩም የእጅ ጣቶች እና የፊት አሻራን ይይዛል።
የፋይዳ መታወቂያ ከሌሎች መታወቂያዎች የተለየ ሲሆን በዋናነት የሚለየዉ በብሔራዊ ደረጃ ወጥነት ያለው መሆኑ እና የምዝገባው እና የቁጥር አሰጣጡ ወጥ በሆነ መልኩ በአገር አቀፍ ደረጃ የሚሰጥ መሆኑ፣ ግላዊ መረጃን ሚስጥራዊ አድርጐ በመጠበቅ በኩል አስተማማኝ መሆኑ፣ ከሌሎች መታወቂያዎች ልዩ እንደሚያደርገው በአዋጁ ላይ ተቀምጣል።
በመሆኑም ይህንን አገልግሎት በማሳለጥ ህብረተሰቡን ተጠቃሚ ለማድረግ፣ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመፍታት፣ በየተቋማቱ አገልግሎት ለማግኘት የሚገጥመውን እንግልትና ምልልስ ለማስቀረት የዲጅታል ሥርዓቱ መሠረት ስለሆነ ለግለሰቦችም ሆነ ለሃገር የሚሰጣቸዉን ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታወች በመረዳት መታወቂያዉን በአፋጣኝ በማዉጣት ራሳችን እና ሃገራችንን ተጠቃሚ ልናደርግ ይገባል።
በኲር የግንቦት 25 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም