የፋይዳ መታወቂያ ሥርዓትን ቀድመው ከተገበሩ ሀገራት መካከል ኢስቶኒያ አንዷ ናት። ጂቢጂ (gbg.com) እንደዘገበው ዜጎች ዲጂታል መታወቂያቸውን በመጠቀም ከ99 በመቶ በላይ የመንግሥት አገልግሎቶችን በኦንላይን ማግኘት ችለዋል። በዚህም ኢ አይ ዲ (EID) ተብሎ በሚጠራው የኢስቶኒያ ዲጂታል መታወቂያ አማካኝነት የሀገሪቱ ዜጎች ከ600 በላይ አገልግሎቶችን እንደሚያገኙ መረጃው አክሏል።
እንደ መረጃው ከሆነ ዜጎች በኦንላይን ምርጫ መሳተፍ፣ የግብር ክፍያን መፈጸም፣ የጤና አገልግሎቶችን በቀላሉ ማግኘት እና የንግድ ፈቃድ ምዝገባ ማድረግ ዲጂታል መታወቂያ ያስገኘላቸው ዋና ዋናዎናቹ አበርክቶዎች ናቸው፤ ቢሮክራሲን በእጅጉ የሚቀንስ እና ጊዜን የሚቆጥብ ሲሆን ኢስቶኒያውያን በዓመት በአማካይ አምስት የሥራ ቀናት መቆጠብ እንዳስቻላቸውም መረጃው ያመላክታል።
ከዚህ ጋር በተያያዘ ታዲያ ኢትዮጵያም ፋይዳ ብሔራዊ የመታወቂያ አገልግሎትን ባለፈው ዓመት መተግበር ጀምራለች፡፡ የአማርኛ ቋንቋዎች ጥናትና ምርምር ማዕከል በ2011 ዓ.ም ባሳተመው የአማርኛ መዝገበ ቃላት “ፋይዳ” ለሚለው ቃል ጥቅም፣ እርባና በማለት አቻ ትርጉሙን አስቀምጧል፡፡ “ፈየደ” ለሚለው ቃል ደግሞ ጠቀመ፣ ረባ ይላል፡፡
ፋይዳ ዲጅታል መታወቂያ ባዮሜትሪክ እና ዲሞግራፊክ መረጃን ከነዋሪዎች በመሰብሰብ አንድን ሰው ልዩ በሆነ ሁኔታ መለየት የሚያስችል፣ ለሁሉም አገልግሎት ሰጪዎች ማንነትን በማረጋገጥ እና በኤሌክትሮኒክ መልኩ ደንበኞቻቸውን ማወቅ የሚያስችል ታዓማኒነት ያለው የዲጂታል ማንነት ምዝገባ ሥርዓት ነው።
ፋይዳ ዲጂታል ብሔራዊ መታወቂያ ከሌላው የሚለይበት
አቶ ኦላና አበበ ፋይዳ የብሔራዊ መታወቂያ ከፍተኛ አማካሪ ናቸው፤ አማካሪው እንደሚሉት ፋይዳ ብሔራዊ መታወቂያን ከሌሎች ልዩ የሚያደርጉት መገለጫዎች አሉት፡፡ ለማሳያም አንድ ሰው አንድ መሆኑ የሚረጋገጥበት እና የፋይዳ ቁጥር የሚባለውን ዜጎች ባለ 12 እና 16 አሀዝ /ዲጂት/ መለያ ቁጥር በካርድ፣ በወረቀት ወይም በስልካቸው በማሳየት አገልግሎት ማግኘት የሚችሉበት ሥርዓት መሆኑ ነው፡፡
እንደ አቶ ኦላና ማብራሪያ ፋይዳ ብሔራዊ መታወቂያ በልዩ ፋይዳ ቁጥሩ ከተለያዩ ሴክተር መሥሪያ ቤቶች ጋር ለማስተዋወቅ፣ ከክልል ክልል ለማስተሳሰር ይረዳል፡፡ ለምሳሌ ባሕር ዳር ላይ ያለውን ሥርዓት አዳማ፣ አዋሳ፣ መቀሌ… ካለው ሥርዓት የሚያስተሳስር ወጥ የሆነ የግንኙነት መረብን ይፈጥራል፡፡
ግላዊ መረጃን ምስጢራዊ አድርጐ የሚጠብቅ መሆኑን ያነሱት ከፍተኛ አማካሪው አስተማማኝነቱም ከሌሎች መታወቂያዎች ልዩ እንደሚያደርገው ጠቁመዋል፡፡ እንደ ሀገር የግል መረጃ ጥበቃ አዋጅ ወጥቶ ተግባራዊ መሆኑ ይታወቃል፤ ዲጂታል መታወቂያም አዋጁን የጠበቀ፣ ያከበረና በዛ አግባብ የሚመራ ሥርዓት እንደሆነ አክለዋል፡፡
እንደ አቶ ኦላና ማብራሪያ ሰዎች ሲመዘገቡ የሰጡት ማስረጃ ባለቤትነቱ የተመዝጋቢው ነው፡፡ እያንዳንዱን መረጃ ማየት ሲፈለግም የመታወቂያው ባለቤት ተጠይቆ በፈቃዱ የሚያጋራው እንጅ ባለሙያ ምዝገባውን ካካሄደ በኋላ የመዘገበውን መረጃ የሚያይበት ሥርዓት አይደለም፡፡
ፋይዳ ብሔራዊ መታወቂያውን የሚያገኙ
ፋይዳ ብሔራዊ መታወቂያ አራት መርሆች እንዳሉትም አቶ ኦላና ይናገራሉ፡፡ አነዚህም አካታችነት፣ አስተማማኝነት፣ የተመጠነ መረጃ የሚወስድ እና ተናባቢ ስለመሆናቸው ጠቅሰዋል፡፡
መረጃዎችን ዋቢ አድርገው እንዳስገነዘቡት እንደ ሀገር ካለው ሕዝብ 40 በመቶው ራሱን የሚገልጽበት ምንም አይነት መረጃ ወይም ማስረጃ /መታወቂያ/ የለውም፡፡ ይህን አሳሳቢ ጉዳይ ግምት ውስጥ በማስገባት የተለያዩ 33 ማስረጃዎችን (የቀበሌ መታወቂያ፣ ፓስፖርት፣ የመኪና ባለቤትነት ማረጋገጫ /ሊብሬ/፣ የመሬት ይዞታ ማረጋገጫ ካርታ …) በማቅረብ መመዝገብ የሚቻልበት ሥርዓት ነው፡፡
ማስረጃዎች የሌላቸው በአብዛኛዎች ጐዳና ተዳዳሪዎች፣ በተለያዩ ማዕከላት የሚኖሩ አቅመ ደካሞች፣ ወላጆቻቸውን በሞት ያጡ ሕፃናት… ፋይዳ መታወቂያ ያላቸውን ሰዎች ምስክር በማድረግ፣ ባሉበት ተቋም ወይም እነዚህን ወገኖች ተደራሽ ለማድረግ ወይም አገልግሎት ለመስጠት ከተቋቋመ መስሪያ ቤት ጋር በመናበብ መታወቂያውን የሚያገኙበት ሥርዓት መሆኑንም ከፍተኛ አማካሪዉ ጠቁመዋል፡፡
ፋይዳ ብሔራዊ መታወቂያውን በዜግነት ኢትዮጵያዊ ሆነም አልሆነ በሀገሪቱ ነዋሪ እስከሆነ ድረስ የመኖሪያ ወይም የሥራ ፈቃዱን በማየት አገልግሎቱ ይፈቅድለታል፡፡
ከዕድሜ አኳያም ከተወለዱ ጀምሮ የምዝገባ ሥርዓቱ መዘጋጀቱን አቶ ኦላና ጠቁመዋል፡፡ እንደ ከፍተኛ አማካሪዉ ማብራሪያ ከዜሮ እስከ አምስት ዓመት ያሉ ሕፃናት በሥነ ሕዝብ /ዲሞግራፊ/ መረጃ ብቻ የምዝገባ አገልግሎት ያገኛሉ፤ ከአምስት ዓመት በላይ ያሉ ልጆች ደግሞ በሥነ ሕዝብ እና አካል ላይ ያሉ መረጃዎችን /ባዮሜትሪክ/ በመውስድ ይሰጣቸዋል፡፡ በአሁኑ ወቅትም በሀገሪቱ ከአምስት ዓመት ጀምሮ ያሉ ሕፃናትን ብቻ ተደራሻ ለማድረግ በትምህርት ቤቶች እና ከሁሉም አገልግሎት ሠጭ ተቋማት ጋር ትስስር በመፍጠር በ55 ተቋማት አገልግሎቱ እየተሰጠ መሆኑንም ነው ያነሱት፡፡
ከአምስት ዓመት ጀምሮ ላሉ ሕፃናት ብሔራዊ መታወቂያ ለመስጠት መሠረት የሚያደርገው አካላዊ የሆኑ የእጅ፣ የዐይን ብሌን እና የፊት ገጽታ አሻራዎችን ነው፡፡ ይህም በትምህርት ሥርዓቱ ከማጭበርበር ጋር ተያይዞ ሕፃናት በትክክል ዕድሜያቸው ለአቅመ ሔዋን እና ለአቅመ አዳም እስኪደርሱ አገልግሎቱ ወጥ እንዲሆን እና የትምህርት ሥርዓቱን በቁጥር የሚሠራ /ዲጂታላይዝድ/ ለማድረግ ትልቅ ጠቀሜታ እንዲኖረው ታስቦ መሆኑን አቶ ኦላና ጠቁመዋል፡፡ ልጆች ሀገር ተረካቢዎች መሆናቸውን ያነሱት አቶ ኦላና አድገው በትልልቅ ተቋማት ሲያገለግሉ ወይም ትምህርት ላይ እያሉ የውጭ የትምህርት ዕድል ካገኙ “የሥም እና የትውልድ ቀን ሥህተት እንዳይፈጠር ያደርጋል” ነው ያሉት፡፡
የብሔራዊ መታወቂያ/ፋይዳ/ ተጨማሪ አበርክቶዎች
ከፍተኛ አማካሪው እንዳሉት በተለያዩ ጊዜያት ሕዝብን ተጠቃሚ እና ተደራሽ ለማድረግ በርካታ ሥራዎች ሲከናወኑ ቆይተዋል፡፡ በዚህ አግባብ በግብርናው፣ በጤናው፣ በትምህርቱ… የሚከናወኑ ተግባራት በዲጂታል ሥርዓት ካልታገዙ ሥኬታማ የመሆን ዕድላቸው ጠባብ ነው፡፡ ይህን አገልግሎት በማሳለጥ ኅብረተሰቡን ተጠቃሚ ለማድረግ ደግሞ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን፣ በየተቋማቱ አገልግሎት ለማግኘት የሚገጥመውን እንግልት እና ምልልስ ማስቀረት ይገባል፤ ለዚህም የፋይዳ ብሔራዊ መታወቂያ ሥርዓት መሠረት ይሆናል ብለዋል፡፡
እንደ ሀገር ወደ ዲጂታሉ ዓለም ለመግባት አራት አስቻይ ነጥቦችን ላይ መሥራት ይገባል፡፡ ይህ ካልሆነ ዕድሉ ጠባብ ነው፡፡ እነዚህም ኢነርጅ (መብራት፣ ኀይል)፣ ዳታ (ኮሙኑኬሽን)፣ የክፍያ አፈፃፀም /ዲጅታል ፔይመንት/ እና አሁን በሀገሪቱ እየተተገበረ የሚገኘው ፋይዳ /ድጂታል መታወቂያ ናቸው፡፡
ከፍተኛ አማካሪዉ እንደሚሉት ሀገር ካላት ሀብት ዋናው ሕዝብ ነው፡፡ በመሆኑም እንደ ሀገር ያለውን ሀብት መዝግቦ እና አውቆ አገልግሎት መስጠት ይገባል፡፡ የፋይዳ መታወቂያ ደግሞ አንድ ሰው አንድ መሆኑ የሚረጋገጥበት ሥርዓት በመሆኑ ጥቅሙ የጎላ ነው፡፡
የፋይዳ መታወቂያ ሥርዓት ለሀገር በቀል ኢኮኖሚ አጀንዳም አንዱ ምስሶ /ፒላር/ ነው፡፡ በዚህም የተጀመረውን ተግባር (የኢኮኖሚ ማሻሻያ) ለማሳካት የሚያስችል መርሀ ግብር ነው፡፡ ይህን ብቻ በማሳካትም ሰባት በመቶ ዓመታዊ የነብስ ወከፍ ገቢ /ጂ ዲ ፒ/ እንደ ሀገር ማግኘት የሚያስችል ሥርዓት ነው፡፡
የፋይዳ መታወቂያ ምንነት እና መታወቂያ አዋጅ ቁጥር 1284/2015 ዋና ዋና ገጽታዎችን በተመለከተ በገጹ እንዳሰፈረው ደግሞ ዘመናዊ የመታወቂያ ሥርዓት በአንድ ሀገር ውስጥ ተግባራዊ ሲደረግ መሰረታዊ የሚባሉ ጠቀሜታዎች ይኖሩታል፡፡ ከነዚህ ጠቀሜታዎች መካከልም ሀገራዊ ልማትን በአግባቡ ለማቀድ፣ ምጣኔ ሃብታዊ ሽግግር ለመፍጠር፣ መልካም አስተዳደርን ለማስፈን፣ የሀብት ብክነትን ለመቀነስ፣ ወንጀልን ለመከላከል፣ ፖሊሲዎች ሲቀረጹ እና የልማት ሥራዎች ሲከናወኑ ድግግሞሽን ለመቅረፍ እና አካታችነትን ለማጎልበት የሚረዳ መሆኑ የተረጋገጠ ነው፡፡
በኢትዮጵያም በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የበለፀገ፣ ዘርፍ ተሻጋሪ፣ መሠረታዊ የዲጂታል መታወቂያ ሥርዓት መዘርጋት አስፈላጊ መሆኑ ታምኖበት የብሔራዊ መታወቂያ ፕሮጀክት ጽህፈት ቤት ተቋቁሞ ላለፉት ሁለት ዓመታት በግንባታ እና በሙከራ ሂደት ላይ ቆይቷል። በዚህ ሂደት ውስጥ ከተለያዩ የአገልግሎት ዘርፎች ጋር ለማስተሳሰር የሙከራ ትግበራ ሥራዎችን በማከናወን አሁን ነዋሪዎችን መዝግቦ የዲጂታል መታወቂያ ባለቤት ለማድረግ መቻሉን መረጃው ጠቁሟል፡፡
ምስጢራዊነቱ
የፋይዳ መታወቁያ ተጠቃሚ የሆኑ አንዳንድ ሰዎች መታወቂያ ካርዱን ለማግኘት ከጊዜ፣ ከእንግልት… አኳያ ቀልጣፋ ቢሆንም ሲታተም /ኮፒ ሲደረግ/ የጀርባው ምስጢር ይወጣል? የሚል ስጋት ያነሳሉ፤ ይህ ምን ያህል እውነት ነው? ስንል አቶ ኦላናን ጠይቀናቸው ነበር፤ አቶ ኦላና በምላሻቸውም ሁለት ቁጥር (የፋይዳ 12 እና 16 አሀዝ /ዲጂት/) እንደሚሰጥ ጠቁመው ተለዋጭ ቁጥር የሚባለው ባለ 16 ዲጂት ቁጥሩ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ይህን ቁጥርም ሰዎች ለአገልግሎት ሲሄዱ እንዲያጋሩ ይመከራል ብለዋል፡፡ የፋይዳ ቁጥሩን /12 ዲጂቱን/ ቢያጋሩም ምንም የሚፈጠር ችግር እንደሌለ ተናግረዋል፡፡ ለዚህ ደግሞ ጥበቃ የሚደረግበት አሠራር መኖሩን አቶ ኦላና አረጋግጠዋል፡፡
መታወቂያዉ በምን አይነተ መንገድ መያዝ ይኖርበታል?
ፋይዳ መታወቂያ በየቦታው ይሰጣል፤ ነገር ግን ሰዎች መውሰድ ያለባቸው ትክክለኛ ቦታ የት ነው? ስንልም ለከፍተኛ አማካሪው ተጨማሪ ጥያቄ አንስተን ነበር፤ አቶ ኦላና እንዳብራሩት “ምዝገባ ከተካሄደ በኋላ መታወቂያ ይሰጣል፤ ሥርዓቱ ዲጀታል ነው፡፡ በአዋጁ እንደተገለፀውም መታወቂያው ቁጥሩ ነው፡፡ የፕላስቲኩን መታወቂያ ካርድ ከፈለጉ ግን ጊዜያዊ ስምምነት የተፈጸመው ከኢትዮጵያ ቴሌኮም እና ከፓስታ ቤት ጋር በመሆኑ ከቅርንጫፎች በመሄድ አገልግሎቱን ማግኘት ይቻላል፡፡
ይሁን እንጂ ሰዎች በራሳቸው ፍላጐት ያስፈልገኛል ብለው ካሰቡ በዲጂታል ቅጅ /ኮፒ/ በቴሌብር እና በፋይዳ መተግበሪያ /አኘሊኬሽን/ በመግባት ፋይዳ ቁጥራቸውን በማስገባት ዲጂታል ቅጅውን /ኮፒውን/ ያገኛሉ፡፡ በተጨማሪም በወረቀት የትም ቦታ በማሳተም አገልግሎቱን ማግኘት እንደሚችሉ ጠቁመዋል፡፡
ሥርዓቱ አካላዊ መረጃ ላይ ተመስርቶ የሚሰጥ እና አንድ ሰው አንድ መሆኑን የሚያረጋግጥ ነው ያሉት አቶ ኦላና፤ አንድ ሰው ሁለትና ከዛ በላይ በተለያየ ሥም ማውጣት እንደማይችልም አረጋግጠዋል፡፡
ወጥነት
ፋይዳ /ብሔራዊ መታወቂያ/ ወጥነት ያለው ሀገራዊ፣ ዓለም አቀፍዊ መሆኑን አማካሪው ገልጸዋል፤ ከዚህ ጋር በተገናኘ አማራ፣ ትግሬ፣ ኦሮሞ… እያለ አድራሻን መግለጽ ለምን አስፈለገ? ስንል አቶ ኦላናን ጠይቀናቸዋል፤ “እኛ የምንወስደው የሥነ ሕዝብ ማስረጃዎች አምስት ብቻ ናቸው፡፡ ሥም፣ የትውልድ ቀን፣ የመኖሪያ አድራሻ /ጊዜያዊም ወይም አሁን ያለበት/፣ ዜግነት እና ፆታ ናቸው፡፡ የመኖሪያ አድራሻም አስፈላጊ ነው፡፡ የመኖሪያ አድራሻ ማለት ሰዎች አሁን ላይ የሚኖሩበትን የሚገልጽ ማስረጃ ብቻ ነው፡፡ ለአብነት እኔ ዛሬ ድሬዳዋ፣ ነገ ባሕር ዳር… ልኖር እችላለሁ፡፡ ለዚህም ሲባል ሰዎች ምዝገባውን የሚያካሂዱት ባሉበት አካባቢ ነው” በማለት አብራርተዋል፡፡
አቶ ኦላና በመጨረሻም “የፋይዳ ሥርዓት ሰው ተኮር ሆኖ ሰዎችን ከአገልግሎት ጋር በተያያዘ ተጠቃሚ ለማድረግ ያለውን እንግልት ለመፍታት የተዘጋጀ ኘሮግራም ነው፡፡ በተለይ አገልግሎትን ለማሳለጥ ከገቢዎች፣ ከመሬት ካርታ እና ፕላን… ከገንዘብ ጋር ተያይዘው የሚፈጠሩ ማጭበርበሮችን ያስቀራል፡፡ በቀጣይ ደግሞ ሰዎች ወደ ተቋማት ሳይሄዱ ከቤታቸው ወይም ባሉበት ቦታ ሆነው ሳይንገላቱ በስልክ አገልግሎት የሚያገኙበት ሥርዓት ነው፤ ስለሆነም ሁሉም የአገልግሎቱ ተጠቃሚ ይሁን” በማለት ጥሪ አስተላልፈዋል፡፡
(ሙሉ ዓብይ)
በኲር የግንቦት 25 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም