የፍሎረንቲኖ ፔሬዝ አዲሱ የዝውውር ዕቅድ

0
90

ሪያል ማድሪድ ከዓለማችን ታላላቅ ክለቦች መካከል ቀዳሚውን ስፍራ ይይዛል። የስፔኑ ኃያል ክለብ ስኬታማ እና ዝነኛ ከሆኑ የምድራችን የእግር ኳስ ክለቦች ውስጥም ቀዳሚው ነው። በዚህ ኃያል ክለብ ታላላቅ የእግር ኳስ ኮከቦች ተጫውተው አልፈዋል፤ እየተጫወቱም ነው። ክለቡ የብዙ እግር ኳስ ታዳጊዎች ህልም እና መዳረሻ ጭምር ነው። በሳንቲያጎ ቤርናቢዮ የማይቋረጥ የእግር ኳስ ሌጋሲ መኖሩ እና ተጫዋቾች በግላቸውም ሆነ በቡድን በርካታ ክብሮችን ለመቀዳጀት ትክክለኛው ቦታ መሆኑ ክለቡን በባለተሰጥኦ ተጫዋቾች ዘንድ ተመራጭ አድርጎታል።

ሪያል ማድሪድ የአውሮፓ ንጉሥ ክለብ ነው፤ 14 የሻምፒዮንስ ሊግ ዋንጫዎችንም በማንሳት ባለክብረወሰን ክለብ ነው። በክለቡ ክርስቲያኖ ሮናልዶ፣ ዚነዲን ዚዳን፣ ራኡል እና የመሳሰሉት በረካታ ባለተሰጥኦ የእግር ኳስ ተጫዋቾች ተጫውተው አልፈዋል። ዛሬም የእነርሱን እግር ተከትለው በሳንቲያጎ ቤርናቢዮ ሰማይ ስር እያንፀባረቁ ያሉ በርካታ ኮከቦች አሉ። ተጫዋቾች በሳንቲያጎ ቤርናቢዮ ራሳቸውን ካሳዩ በትልቁ የተጫዋቾች ሽልማት ባሎን ዶር የመታጨት እና የመሸለም እድላቸው ከፍተኛ እንደሚሆን ይታመናል። ታዲያ የልጅነት ህልማቸውን ለመኖር መዳረሻቸውን ቤርናቢዮ እንደሚያደርጉ መረጃዎች አመልክተዋል፡፡

የሪያል ማድሪዱ ፕሬዝዳንት ፍሎረንቲኖ ፔሬዝ ወደ ስልጣን ከመጡ በኋላ በተለያየ ጊዜ የጋላክቲኮን (የኮከቦችን) ስብስብ በመፍጠር የተጫዋቾችን እና የክለቡን ህልም አሳክተዋል። የመጀመሪያው የጋላክቲኮ ስብስብ ሊዊስ ፊጎን፣ ዚነዲን ዚዳንን እና ዴቪድ ቤካምን የያዘ ሲሆን ከፈረንጆች ሚሊኒየም ጀምሮ እስከ 2006 እ.አ.አ ድረስ ቆይቷል። ሁለተኛው የጋላክቲኮ ስብስብ ክርስቲያኖ ሮናልዶን፣ ካሪም ቤንዜማን፣ ጋሪዝ ቤልን፣ ሉካ ሞድሪችን፣ ቶኒ ክሩስን እና የመሳሰሉትን የያዘ እንደነበር አይዘነጋም። ይህ ስብስብም ከ2009 እ.አ.አ ጀምሮ ለዘጠኝ ዓመታት ቆይቷል።

ፕሬዝዳንት ፍሎረንቲኖ ፔሬዝ አዲሱን እና ሦስተኛውን የጋላክቲኮ ስብስብ “ቤቢ ጋላክቲኮ” ብለው ይጠሩታል። እ.አ.አ ከ2020 ጀምሮ ተግባራዊ እየሆነ ሲሆን በወጣት ኮከቦች የተሞላ ስብስብ ነው ። ፕሬዝዳንቱ የመጀመሪያውን እና ሁለተኛውን የጋላክቲኮ ስብስብ ሲፈጥሩ በርካታ ሚሊዮን ዩሮዎችን አውጥተዋል። ለአብነት ፖርቹጋላዊውን ኮከብ ክርስቲያኖ ሮናልድን በወቅቱ የፕላኔታችን ክብረወሰን በሆነ ዋጋ ካማንቸስተር ዩናይትድ ማስኮብለላቸው የሚታወስ ነው። ለዚዳን እና ለቤካም ዝውውርም ከፍተኛ ገንዘብ ማውጣታቸውን ዋን የፕላኔት መረጃ አመልክቷል።

የሳንቲያጎ ቤርናቢዮ ፈላጭ ቆራጩ ፕሬዝዳንት ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በተጫዋች ዝውውር ላይ አዲስ ፖሊሲ በመቅረጽ ያለምንም ገንዘብ በነጻ ተጫዋቾችን ወደ ቤርናቢዮ እያስኮበለሏቸው ይገኛሉ።  የተጫዋቾችን ፍላጎት እና ህልም ጠንቅቀው የሚረዱት ፍሎረንቲኖ ፔሬዝ እነርሱን ለማስፈረም ከቀድሞ ክለባቸው ጋር ያለው የውል ስምምነት እስኪጠናቀቅ በትዕግስት ይጠባበቃሉ። እስከዚያው ግን ተጫዋቾችን በማማለል የተለያዩ ንግግሮችን ሲያደርጉ ይቆያሉ።

ጊዜው ሲደርስም ለዝውውሩ ምንም ዓይነት ገንዘብ ሳያወጡ በነጻ ዝውውር ወደ ቤርናቢዮ እንዲመጡ ያደርጋሉ። በዚህ መንገድ ባለፉት አምስት ዓመታት ባለተሰጥኦ የእግር ኳስ ተጫዋቾችን በነጻ በማዘዋወር ብቃታቸውን አሳይተዋል፡፡ ፍሎረንቲኖ ፔሬዝ ቢያንስ በየዓመቱ አንድ የእግር ኳስ ኮከብ በነጻ ዝውውር እንደሚያስፈርሙ የዋን ፕላኔት መረጃ ያመለክታል። ዘንድሮ እንግሊዛዊውን የቀኝ ተመላላሽ ትሬንት አሌክስአንደር አርኖልድን በቅርቡ ማስፈረማቸው ይታወሳል። አርኖልድ ከመርሲሳይዱ ክለብ ጋር ያለው የውል ስምምነት መጠናቀቁን ተከትሎ ነው በነጻ ዝውውር ሎስብላንኮዎችን የተቀላቀለው። በቤርናቢዮም አምስት ዓመታት የሚያቆየውን የውል ስምምነት ነው የፈረመው።

አርኖልድ በፕሪሚየር ሊጉ ከታዩ ምርጥ የኋላ ተመላላሾች ከቀዳሚዎች ውስጥ ይጠቀሳል። የተሳኩ ኳሶችን በማቀበል፣ የቆሙ ኳሶችን በማሻማት እና በማጥቃት ረገድ የተዋጣለት ተከላካይ ነው። የ26 ዓመቱ ሁለገብ ተጫዋች ለመርሲሳይዱ ክለብ እና ለእንግሊዝ ብሄራዊ ቡድን በአማካይ ቦታም ሲያገለግል እንደበር አይዘነጋም።

አርኖልድ በ2018/19 እ.አ.አ 12 ግብ የሆኑ ኳሶችን አመቻችቶ በማቀበል ቀዳሚው ተከላካይ ነው። አርኖልድ ከሊቨርፑል ጋር ሁለት የፕሪሚየር ሊግ እና አንድ የሻምፒዮንስ ሊግ ዋንጫን ካሳካ በኋላ ነው ከ21 ዓመታት በኋላ ያደገበትን ክለብ ለቆ ማድሪድን የተቀላቀለው። በሎስብላንኮዎች ቤትም ከዳኒ ካርቫል ጋር በቦታው የሚፎካከር ይሆናል።

ኬሊያን ምባፔ ባሳለፍነው የክረምቱ የተጫዋቾች የዝውውር ወቅት ሳንቲያጎ ቤርናቢዮ በመድረስ ለሪያል ማድሪድ የመጫወት ህልሙን አሳክቷል። ፈረንሳያዊው አጥቂ የፓሪሱን ሀብታም ክለብ ፓሪሴን ዥርሜንን ለቆ ነው በነጻ ዝውውር ሪያል ማድሪድን የተቀላቀለው። ለዓመታት ሲፈላለጉ የነበሩት ምባፔ እና ሪያል ማድሪድ በ2024 እ.አ.አ የክረምቱ የተጫዋቾች ዝውውር ወቅት ጊዜው ደርሶ ተገናኝተዋል።

የ26 ዓመቱ ምባፔ አርአያው ክርስቲያኖ ሮናልዶ በሄደበት መንገድ በመጓዝ አልጋወራሽ መሆን የሚፈልግ ተጫዋች ነው። ህልሙን ለማሳካት ደግሞ ትክክለኛው ቦታ ፓርክ ደ ፕሪንስ ሳይሆን ቤርናቢዮ እንደሆነ ያምናል። ታዲያ ህልሙን ለመኖር ነበር ከሀብታሙ የፈረንሳይ ክለብ እና ከሳውዲ የተለያዩ ክለቦች የቀረበለትን አማላይ ጥቅማጥቅም እና ረብጣ ሚሊዮን ዶላሮች በመግፋት መዳረሻውን ማድሪድ ያደረገው።

ፈረንሳያዊው ባለተሰጥኦ ከሀገሩ ክለብ ጋር ያለው የውል ስምምነት ባይጠናቀቅ ሪያል ማድሪድ በርካታ ሚሊዮን ዶላሮችን ያወጣ እንደነበር አያጠያይቅም። ነገር ግን ምስጋና ለፕሬዝዳንት ፔሬዝና አዲስ የዝውውር ፖሊሲ ሪያል ማድሪድን ከብዙ ወጪ አድኖታል።

ሪያል ማድሪድን በነጻ ዝውውር የተቀላቀለው ተጫዋች ሌላኛው ተከላካይ አንቶኒዮ ሩዲጊር ነው። ጀርመናዊው ተከላካይ በኃይል አጨዋወቱ የሚታወቅ የመሀል ተከላካይ ነው። የ31 ዓመቱ ተከላካይ ከምዕራብ ለንደኑ ክለብ ጋር አምስት ዓመታትን ካሳለፈ በኋላ ነበር በ2022 እ.አ.አ በነጻ ወደ ሪያል ማድሪድ ያቀናው።

ግዙፉ ተከላካይ ከሰማያዊ ለባሾች ጋር የሻምፒዮንስ ሊግ እና የኢሮፓ ሊግ ዋንጫዎችንም ማሳካቱ አይዘነጋም። ከነጭ ለባሾች ጋር ደግሞ የላሊጋን እና የሻምፒዮንስ ሊግ ዋንጫን ማሳካቱን የግል የታሪክ ማህደሩ ያሳያል። ሩዲጊር ቤርናቢዮ ከደረሰ በኋላ የኋላ ክፍሉ የጀርባ አጥንት በመሆን እያገለገለ ይገኛል። ከሌላኛው ኦስተሪያዊ ተከላካይ ዴቪድ አላባ ጋርም አስደናቂ ጥምረት በመፍጠር የተከላካይ ክፍሉን አስፈሪ አድርገውታል። ተጫዋቹ ከቀድሞ ክለቡ ቸልሲ ጋር ያለው የውል ስምምምነት ሲጠናቀቅ በነጻ የማስፈረምን (የቦስማን ሕግን) ተግባራዊ በማድረግ ነው ሪያል ማድሪድ ያስፈረመው።

ሌላው ሪያል ማድሪድ በነጻ ካስፈረማቸው ድንቅ ተጫዋቾች መካከል ተከላካይ ዴቪድ አላባ ነው። አላባ በትውልዱ ካሉ ሁለገብ ተከላካዮች ውስጥ አንዱ ነው። በቴክኒክ ክህሎቱ የላቀ መሆኑንም ብዙዎች ይመሰክሩለታል። የሰርጂዮ ራሞስን እና ራፋኤል ቫራንን መልቀቅ ተከትሎ ነበር ማርጌዎች ቤት የደረሰው፡፡ አላባ የኋላ ክፍሉን በመምራት የተዋጣለት መሆኑን በተደጋጋሚ አስመስክሯል።

በ2021 እ.አ.አ ነው 13 ዓመታት የቆየበትን አሊያንዝ አሬናን በመልቀቅ ቤርናቢዮ የደረሰው የባቫሪያኑ ክለብ አዲስ የውል ስምምነት ቢያቀርብለትም አዲስ ፈተና ለመጋፈጥ ክለቡን ለቋል። ኦስትሪያዊው ተከላካይ የላቀ የቲክኒክ ክህሎት ባለቤት በመሆኑ ለሀገሩ ብሄራዊ ቡድን በአማካይ ስፍራ ጭምር እንደሚጫወት የዋን ፕላኔት መረጃ አስነብቧል። ባሳለፍነው ዓመት በጉዳት ምክንያት ረዘም ላለ ጊዜ ከሜዳ የራቀው ዴቪድ አላባ  ባለመኖሩ የስፔኑ ኃያል ክለብ በአውሮፓ መድረክ በግማሽ ፍጻሜ ብዙ ግቦች ተቆጥረውበት በጊዜ ተሰናብቷል።

የአውሮፓው ንጉሥ ክለብ ከዚህ በፊትም በርካታ ባለተሰጥኦዎችን በነጻ ማዘዋወሩን መረጃዎች ያስታውሱናል። እንግሊዛዊው የቀድሞው የክንፍ ተጫዋች ስቴቭ ማክማንማን በ1999 እ.አ.አ ቀዮችን ለቆ በነጻ ሪያል ማድሪድን ተቀላቅሏል። ፍሎረንቲኖ ፔሬዝ ፕሬዝዳንት ከመሆኑ በፊት እ.አ.አ በ1997 አጥቂው ፈርናንዶ ሞሬንተስ ከሞናኮ በነጻ ነጭ ለባሾች ቤት መድረሱን መረጃዎች አመልክተዋል።

በርንድ ሹስተር እና ሚካኤል ላውድሮፕን ከባርሰሎና በነጻ ዝውውር ካስፈረሟቸው መካከል ይጠቀሳሉ። ጀርዚ ዱዴክም በነጻ ዝውውር ማድሪድ የደረሰ ብቸኛው ግብ ጠባቂ መሆኑን የዋን ፕላኔት መረጃ ያሳያል። ካባየር ሊቨርኩሰን ጋር በውድድር ዘመኑ መጨረሻ የውል ስምምነቱ የተጠናቀቀው አሰልጣኝ ዣቢ አሎንሶም በነጻ የካርሎ አንቸሎቲን መልቀቅ ተከትሎ አዲሱ የቤርናቢዮ አለቃ ሆኖ መሾሙ የሚታወስ ነው።

ሪያል ማድሪድ በቀጣይም ውላቸው እስከሚጠናቀቅ በጉጉት የሚጠብቃቸው በርካታ ኮከቦች መኖራቸውን መረጃው ይጠቁማል። ከእነዚህ መካከል የ18 ዓመቱ ግራ ተከላካይ ሊዊስ ስኬሊ አንዱ ነው። ፈረንሳያዊው የመሀል ተከላካይ ዊሊያም ሳሊባንም ሪያል ምድሪድ በነጻ ለማዘዋወር የውል ስምምነቱን በጉጉት የሚጠባበቀው ሌላኛው ተከላካይ ነው። በኤምሬትስ የሁለቱ ተጫዋቾች ውል የሚጠናቀቀው በ2026 ሲሆን በመድፈኞች ቤት ውላቸውን ለማራዘምም እየተነጋገሩ ነው መባሉ  ለፕሬዝዳንት ፔሬዝ መጥፎ ዜና ተብሏል። ታዳጊውን አብደላህ ኡዛኔ ከአያክስ፣ አይመሪክ ላፖርትን ከአል ናስር እና ሰርጂዮ ሬጉይሎን ከቶትንሀም ሆትስፐርስ ሪያል ማድሪድ በዚህ ክረምት በነጻ ለማስፈረም ዐይኑን የጣለባቸው ተጫዋቾች መሆናቸውን የዋን ፕላኔት መረጃ ያመለክታል፡፡

(ስለሺ ተሾመ)

በኲር የሰኔ 9 ቀን 2017 ዓ.ም  ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here