የፍትሕ ሚኒሥቴር ሥልጣን እና ተግባር

0
139

የፍትሕ ሥርዓቱን በማጎልበት ረገድ ሁሉም የመንግሥት አካላት እና ኅብረተሰቡ የሚጫወቱት ሚና የማይናቅ ቢሆንም በዋነኛነት ግን ፍርድ ቤት፣ ዐቃቤ ሕግ እና ፖሊስ በዚህ ረገድ ዋናውን ድርሻ ይይዛሉ፡፡ አስፈፃሚ አካል የሆኑት የፍትሕ  እና የፖሊስ ተቋማት ሥልጣንና ተግባር የሚመነጨው ሕገ መንግሥቱን መሰረት አድርገው  የአስፈፃሚ አካላትን ሥልጣንና ተግባር ለመወሰን ከተደነገጉ አዋጆችና ተቋማቱን ለማቋቋም ከወጡ የማቋቋሚያ አዋጆች ነው፡፡ በዚህም እያንዳንዳቸው የየራሳቸው የሆነ ሥልጣን እና ኃላፊነት ተሰጥቷቸዋል፡፡

በኵር በዚህ እትም የፍትሕ ሚኒሥቴር ሥልጣን እና ተግባር ምንድን ነው? ለሚለው ምላሽ ይዛለች፡፡

በአዋጅ ቁጥር 943/2008 አንቀፅ ስድስት ንኡስ አንቀፅ ሁለት መሰረት ፍትሕ ሚኒሥቴር በሕግ ጉዳዮች የፌዴራል መንግሥት ዋና አማካሪና ተወካይ ሆኖ የመሥራት ሥልጣን አለው፡፡ ከዚህ በተጨማሪ   በወንጀልና ፍትሐብሔር ጉዳዮች፣ በሰብአዊ መብት፣ በሕግ ማርቀቅና ማስረፅ እንዲሁም በተለያዩ ሕግ ነክ ጉዳዮች ዝርዝር ሥልጣንና ተግባራት ተሰጥተውታል፡፡

  • የወንጀል ጉዳዮች፦

የወንጀል ሕግ በዋነኛነት የሀገርንና የሕዝብን ሰላምና ደህንነት ለመጠበቅ የሚወጣ ሆኖ እንደ ወንጀል የሚቆጠሩ ድርጊቶችን የያዘ እና ድርጊቶቹ ተፈፅመው በተገኙ ጊዜም የሚያስከትሉትን ቅጣቶች የሚደነግግ ሕግ ነው፡፡ ከዚህ አንፃር የፍትሕ ሚኒሥቴር የወንጀል ፍትሕ ሥርዓቱ የሚፈልገውን ዓላማ እና ግብ ለማሳካት የሚያስችሉ የተለያዩ ሥልጣንና ተግባራት ተሰጥተውታል፡፡

 

ይህም በሌሎች ሕጎች ለፖሊስ የተሰጠው ሥልጣን እንደተጠበቀ ሆኖ በፌዴራል ፍርድ ቤት ሥልጣን ስር የሚወድቅ የወንጀል ምርመራ እንዲጀመር፣ በተጀመረ የወንጀል ምርመራ ላይ የክትትል ሪፖርት እንዲቀርብ፣ በምርመራ ሂደት ላይ ለመርማሪ ፖሊስ አስፈላጊውን ድጋፍና ክትትል መረጉን ማረጋገጥ አለበት፡፡

በመጨማሪም  የወንጀል ምርመራዎች በሕጉ መሰረት መከናወናቸውን ማረጋገጥ እና አስፈላጊውን ትእዛዝ መስጠት፣ የተጠናቀቁ የምርመራ መዝገቦችን ከሕግና ከማስረጃ አንፃር መርምሮ ያስከስሳል ወይም አያስከስስም ውሳኔ የመስጠት፣ የጥፋተኝነት ድርድር የመወሰን፣ ድርድር የማድረግ፣ አማራጭ የመፍትሔ ርምጃ እንዲወሰድ የመወሰን እና ተግባራዊነቱን የመከታተል፣ የፌዴራል መንግሥትን በመወከል የወንጀል ጉዳዮች ክስ የመመስረት፣ ለሕዝብ ጥቅም አስፈላጊ ሆኖ ሲያገኘው ክስ የማንሳት፣ የተነሳ ክስ እንዲቀጥል የማድረግ፣ ፍርድ ቤቶች በወንጀል ጉዳይ የሚሰጧቸው ውሳኔዎችና ትእዛዞች የመፈፀምና መከበራቸውን የመከታተል፣ ካልተፈፀሙ ወይም አፈፃፀማቸው ሕግን ያልተከተለ ከሆነ ለፍርድ ቤት በማመልከት የእርምት ርምጃ እንዲወሰድ የማድረግ ኃ ላፊነትም የፍትሕ ተቋማት ተግባርና ኃላፊነት ነው፡፡

በፍርድ ቤት የሚወሰኑ የወንጀል ቅጣቶች በአግባቡ እንዲፈፀሙ ለማድረግ የሚያስችሉ  በፍርድ ቤት የተሰጡ የሞት ቅጣት ውሳኔዎችን ለኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ፕሬዚዳንት የማቅረብ እና አፈፃፀሙን የመከታተል ኃፊነቶችን የሚያካትት መሆኑንም ከአዋጅ ቁጥር 943/2008 አንቀፅ 6 ንኡስ አንቀፅ ሦስት መመልከት ይቻላል፡፡

  • ሰብአዊ መብት፦

በአዋጁ አንቀፅ ስድስት ንኡስ አንቀፅ ስምንት መሰረት የሰብአዊ መብቶች ከማክበርና ከማስከበር አንፃር ፍትሕ ሚኒሥቴር  በፖሊስ ጣቢያና በማረሚያ ቤት ቁጥጥር ስር ያሉ ሰዎችን የመጎብኘት፣ አያያዛቸውና ቆይታቸው በሕጉ መሰረት መፈፀሙን የማረጋገጥ፣ ሕገ ወጥ ተግባር እንዲታረም ሕጋዊ እርምጃ የመውሰድ ወይም እንዲወሰድ የማድረግ ኃላፊነት ተጥሎበታል፡፡

ከዚህ በተጨማሪ   ኢትዮጵያ ያፀደቀቻቸውን ወይም የተቀበለቻቸውን ዓለም አቀፍና አህጉራዊ የሰብአዊ መብት ስምምነቶች አፈፃፀም የመከታተል፣ ነፃ የሕግ ድጋፍ አሰጣጥ ስትራቴጂዎችን የመቅረፅ፣   ብሔራዊ የሰብአዊ መብት የድርጊት መርሀ ግብርን ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን የማዘጋጀት፣ በሀገር አቀፍ ደረጃ የሚመለከታቸውን አካላት የማስተባበር፣ የሰብአዊ መብት ትምህርት እና የንቃተ ሕግ ለማዳበር በተለያዩ ዘዴዎች ትምህርት የመስጠት እና በዘርፉ የተሰማሩ የሚመለከታቸው አካላትን የማስተባበር ኃላፊነት ተጥሎበታል፡፡

  • የፍትሐብሔር ጉዳዮች፦

በአዋጁ አንቀፅ ስድስት ንኡስ አንቀፅ አራት  መሰረት በፍትሐብሔር ጉዳዮች ረገድ ፍትሕ ሚኒስቴር በፌዴራል የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች የሕዝብ እና የፌዴራል መንግሥት መብትና ጥቅም ወኪል ሆኖ የመከራከር፣ የማስከበር፣ እንዲከበሩ የማድረግ፣ የመከታል እና የመቆጣጠር፣ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን በግዙፍ የመንግሥት ፕሮጀክቶች የውል ዝግጅት እና ድርድር የማድረግ፣ የሕዝብና የፌዴራል መንግሥት መሥሪያ ቤቶች ጥቅም ይጎዳል ብሎ ሲያምን በሌሎች ጉዳዮች የውል ዝግጅትና ድርድር የማድረግ ወይም የሚመለከታቸውን አካላት የማማከር ኃላፊነት አለው፤፤

የፌዴራል መንግሥት መሥሪያ ቤትን በመወከል የፍትሐብሔር ክስ የመመስረት፣ በከሰሱበት ወይም በተከሰሱበት የፍትሐብሔር ጉዳዮች ላይ ክርክር የማድረግ፣ በክርክር አመራር ላይ ለመሥሪያ ቤቶች አቅጣጫ የመስጠትና በሕግ መሰረት ፍርድን የማስፈፀም ተግባር እና ኃላፊነትም ተጥሎበታል፡፡

ከዚህ በተጨማሪ    በፌዴራል ፍርድ ቤቶች የፍትሐብሔር ክስ ለመመስረት የገንዘብ አቅም የሌላቸውን ዜጎች በተለይም ሴቶችን፣ ሕፃናትን፣ አካል ጉዳተኞችን እና አረጋውያንን ወክሎ የመከራከር፣  የኢፌዲሪ መንግሥት በዓለም አቀፍ የዳኝነትና ከፊል ዳኝነት አካላት በሚከስበት ወይም በሚከሰስበት ጉዳይ መንግሥትን በመወከል እና ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመመካከር ክርክር የማድረግ፣ ድርድር የማካሄድ እና ውሳኔውንም የማስፈፀም ኃላፊነት ተጥሎበታል፡፡

  • ሕግ ማርቀቅ እና ማጠቃለል፦

ፍትሕ ሚኒስቴር  በፌዴራል መንግሥት ለሚወጡ ሕጎች የሕግ ረቂቅ ዝግጅት መሥራት፣ የመንግሥት አካላት የሚያዘጋጁት ረቂቅ ሕግ ከሕገ መንግሥቱና ከፌዴራል ሕጎች ጋር የተጣጣመ መሆኑን ማረጋገጥ፣ ለሚመለከታቸው ክፍሎችም አስተያየት ማቅረብ፣ በክልሎች ጥያቄ ሲቀርብለት የሕግ ረቂቆችን በማዘጋጀት መርዳት፣ የሕግ ማሻሻያ ጥናቶችን እንዲሁም  የፌዴራል ሕጎችን የማሰባሰብና ማጠቃለል ሥራ መሥራት፣ የክልል ሕጎችን በማሰባሰብ እንደ አስፈላጊነቱም እንዲጠቃለሉ ማድረግ፤ ኢትዮጵያ የምትፈርመው ወይም የምትቀበለው ዓለም አቀፍ ስምምነት ሕገ መንግሥቱን እና የሀገሪቱን ሌሎች ሕግጋት ያገናዘበና ከብሔራዊ ጥቅም አንፃር ተቀባይነት ያለው መሆኑን የማረጋገጥ ኃላፊነት እንዳለበት በአዋጁ አንቀፅ ስድስት ንኡስ አንቀፅ አምስት ተደንግጓል፡፡

በተጨማሪም በአዋጁ አንቀፅ ስድስት ንኡስ አንቀፅ ስድስት  መሰረት ፍትሕ ሚኒሥቴር የፌዴራል መንግሥቱ ሕጎች ተግባራዊ መደረጋቸውን እና አተገባበራቸው ወጥነት ያለው መሆኑን የማረጋገጥ እና የፌዴራል መንግሥት መሥሪያ ቤቶች ሥራቸውን በሕጉ መሰረት ማከናወናቸውን የማረጋገጥ ኃላፊነት ተጥሎበታል፡፡

  • የሕግ ጥናትና ሥልጠና፦

በአዋጁ አንቀፅ ስድስት ንኡስ አንቀፅ ዘጠኝ መሰረት ፍትሕ ሚኒሥቴር  አሠራሩን ውጤታማና ቀልጣፋ ለማድረግ ጥናትና ምርምር በማድረግ የወንጀል ፍትሕ መረጃዎችን ለማሰባሰብ፣ ለማደራጀት፣ ለመተንተን እና ለማሰራጨት የሚያስችል ሥርአት የመዘርጋትና የማስፈፀም ኃላፊነት ተጥሎበታል፡፡

ዐቃቢያነ ሕግ ስለ ሥራቸው ያላቸውን አመለካከት፣ እውቀትና ክህሎት በተከታታይ እና በየደረጃው ለማሳደግ ሥልጠና የመስጠት ወይም ሥልጠና እና ትምህርት እንዲሰጣቸው የማድረግ ኃላፊነት ያለበት ከመሆኑም በተጨማሪ በአዋጁ አንቀፅ ስድስት ንኡስ አንቀፅ ሰባት መሰረት ለፌዴራል መንግሥት ባለሥልጠናት፣ሹመኞች፣ተመራጮች፣ ሠራተኞች እና ለግሉ ዘርፍ ተሳታፊዎች እንደ አስፈላጊነቱ የሕግ ሥልጠና የመስጠትና እንዲሰጥ የማድረግ ኃላፊነትም እንዳለው ሰፍሯል፡፡

ሌሎች ኃላፊነቶችን በተመለከተ  በአዋጁ አንቀፅ ስድስት ንኡስ አንቀፅ 11 መሰረት በፌዴራል ፍርድ ቤት ደረጃ የጥብቅና አገልግሎት ለሚሰጡ ጠበቆች በሕጉ መሰረት ፈቃድ መስጠት፣ ማደስ፣ ማገድ፣ መሰረዝ፣ ጠበቆችንና የጥብቅና አገልግሎትን ማስተዳደርና መቆጣጠር እንዲሁም በአዋጁ አንቀፅ ስድስት ንኡስ አንቀፅ 12 መሰረት በሌሎች ሕጎች ለውጪ ጉዳይ ሚኒሥቴር የተሰጠው ኃላፊነት እንደተጠበቀ ሆኖ በወንጀልና በፍትሐብሔር ጉዳይ ዓለም አቀፍ ግንኙነቶችንና ትብብሮችን ማድረግ በአዋጁ ለፍትሕ ሚኒሥቴር የተሰጡት ተግባራት ናቸው፡፡

ሚኒሥቴሩ ከላይ ከተጠቀሱት ሥልጣንና ተግባራት በተጨማሪ የኢፌዲሪ ፍትሕ ሚኒሥቴር በተለያዩ ጊዜያት በወጡ ሌሎች ሕጎች ለምሳሌ በንግድ ሕግ፣ በተሻሻለው የፌዴራል የቤተሰብ ሕግ፣ በፌዴራል ጥብቅና አገልግሎት ፈቃድ አሰጣጥና አስተዳደር አዋጅ፣ በፌዴራል አስተዳደር ሥነ ሥርአት አዋጅ እና መሰል ሌሎች ሥልጣንና ኃላፊነቶች ያሉት መሆኑን የፌዴራል ፍትሕ ሚኒሥቴር በድረ ገፁ ካዘጋጀው  ንቃተ ሕግ ፅሁፍ  መረዳት ይቻላል፡፡

(ማራኪ ሰውነት)

በኲር የመጋቢት 8 ቀን 2017 ዓ.ም  ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here