በአማራ ክልል ያለውን የፍትሕ ሥርዓት በመሰረታዊነት ለመለወጥ የተቋማት ግንባታ ተጀምሯል፡፡ ለተቋማቱ መሻሻልም የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት እና በክልሉ በሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች የሚገኙ የሕግ ትምህርት ቤቶች በጋራ ለመሥራት በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ ከሰሞኑ በባሕር ዳር ከተማ ጥምረት ፈጥረዋል፡፡
ጥምረቱ እስካሁን የነበረውን የክልሉን የፍትሕ ሥርዓት በማሻሻል ዩንቨርሲቲዎች የበኩላቸውን ድርሻ እንዲወጡ የሚያስችል እንደሆነ ነው ከደብረብርሐን ዩንቨርሲቲ የሕግ ክፍል የመጡት አቶ ሆነልኝ ኀይሉ የገለጹት፡፡ ባለሙያው እንደሚሉት ከዚህ በፊት በተበታተነ መልኩ ይከናወኑ የነበሩ ተግባራት ከክልሉ የፍትሕ እና ከየዩንቨርሲቲዎች የሕግ ተቋማት ጋራ በጋራ ለመሥራት የሚያስችል መንገድ ነው የተፈጠረው፡፡ በቀጣይ የሚደረገው ስምምነትም በተለይ ዋና ሥራቸው ሥልጠና እና ምርምር ለሆነው ከፍተኛው የትምህርት ተቋማት ለክልሉ ፍትሕ ሥርዓት መሻሻል የበኩላቸውን አስተዋጽኦ የሚያደርጉበት እድል ይፈጥርላቸዋል፡፡
የጎንደር ዩንቨርሲቲ የሕግ ትምህርት ክፍል ዲን አቶ መብራት ጥላሁን በበኩላቸው የፍትሕ ሥርዓት በአንድ አካል ብቻ ስለማይቃና የሁሉንም የፍትሕ አካላት ጥምረት እንደሚጠይቅ ነው የተናገሩት፡፡
አቶ መብራት ጥላሁን እንዳሉት በክልሉ ለፍትሕ ስርዓት መረጋገጥ ትምህርት ቤቶች ደጋፊ ሃሳብን በመቀባበል ወደ ፊት እቅዶችን በጋራ በማውጣት በሕግ ሥርዓቱ ለክልሉም ሆነ ለሀገሪቱ የራሳቸውን አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ ያስችላቸዋል፡፡
የሕግ ትምህርት ቤቶች ጥራት ያለው ባለሙያ በብቃት ከማፍራት በተጨማሪ በማህበራዊ አገልግሎት /በነፃ ድጋፍ በመስጠት/ እና በምርምር በሁሉም በኩል ለፍትሕ መረጋገጥ የበኩላቸውን ማድረግ ይጠበቅባቸዋል፡፡
የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት ዓለምአንተ አግደው እንደገለፁት በክልሉ የሚገኙ ፍርድ ቤቶች በሚቀርቡላቸው የጉዳይ ብዛት ከሌሎች ክልሎች ሲነፃፀር ከፍተኛ ነው፡፡ በመሆኑም በቀጣይ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት በተለይም የሕግ ትምህርት ቤቶች በሀገሪቱ እና በክልሉ የፍትሕ ሥርዓቱን ውጤታማ፣ ቀልጣፋ እና ተደራሽ ለማድረግ ድርሻቸው የላቀ ነው።
የክልሉን የዳኝነት ሥርዓት ለመለወጥም መሰረታዊ የተቋም ግንባታ መጀመሩን የጠቆሙት ፕሬዝዳንቱ በተለይም የአሠራር ሥርዓቶችን፣ አደረጃጀቶችን እና የሕግ ማዕቀፎችን ለማሻሻል ከሕግ ትምህርት ቤቶች ጋር በትብብር መሥራት በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ ሰፊ ውይይት ተደርጓል፡፡ በቀጣይም በፍትሕ ተቋማት የሰው ኀይል አቅም መገንባት የመጀመሪያ ሥራ ይሆናል፡፡
ዩኒቨርሲቲዎች በንድፈ ሀሳብ የሚሰጡትን ትምህርት በተግባር እንዲደገፉ ከፍትሕ ተቋማት እና ከሕግ ምርምር ኢንስቲትዩቱ ጋር ተቀናጅተው እንደሚሠሩም ነው ፕሬዝዳንቱ ያስገነዘቡት።
ፍርድ ቤቱ በሕግ ምርምር፣ በጥናት እና በረጅም ብሎም በአጫጭር ሥልጠናዎች እና በአማራጭ የሙግት መፍቻ ሥርዓት ላይ በጋራ እንደሚሠራም ጠቁመዋል። በዚህ ዓመት የአማራ ክልል የባሕል ፍርድ ቤቶች ማቋቋሚያ አዋጅ መውጣቱን ፕሬዝዳንቱ ገልጸዋል፡፡ ሀገር በቀል ዕውቀት ላይ ከሚሠሩ ዩኒቨርሲቲዎች ጋርም በቀጣይ በቅንጅት ይሠራል።
የፍርድ ቤት አስማሚነት፣ የግልግል ዳኝነት፣ በየአካባቢው የባሕላዊ የፍትሕ ሥርዓቶችን አጥንቶ መጀመር፣ ዜጎች ያለምንም እንግልት ባሉበት ሆነው እንዲገለገሉ እና ሌሎች ጉዳዮች ላይ በክልሉ ከሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች እንዲሁም ከሕግ ትምህርት ቤቶች ጋር በመተባበር እንደሚሠራም አስገንዝበዋል።
በሕዝቡ ውስጥ ያለውን ሕግ የማክበር ሥርዓትን በመመለስ፣ በመጠበቅ፣ በማዳበር… እሴቱ እንዲመለስ ማጥናት እና ተግባራዊ ማድረገግ እንደሚገባም ነው ፕሬዝዳንቱ የገለጹት፡፡
አጠቃላይ በክልሉ የተጀመሩ የዳኝነት እና የፍትሕ ዘርፍ ማሻሻያዎችን (ሪፎርም) በሚገባ ተግባራዊ ለማድረግ ከተፈለገ የሚመለከታቸውን አካላት ማሳተፍ አስፈላጊ ነው፡፡ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማትም ባሉበት አካባቢ የማህበረሰብ አገልግሎት የመስጠት ግዴታ አለባቸው፡፡ አሁን የተመሠረተው ትብብር ደግሞ በክልሉ ላይ የሚሠጡ የለውጥ ስራዎችን የሚያግዙ መሆናቸውም ተጠቁሟል፡፡
እንደ ፕሬዝዳንቱ ማብራሪያ ዩኒቨርሲቲዎች በንድፈ ሃሣብ ላይ ሥልጠና ይሠጣሉ፡፡ በተግባር ደግሞ ያለውን አፈፃፀም በፍርድ ቤቶች መተግበር ከቻሉ ደግሞ የፍትሕ አገልግሎት አሰጣጡ ከፍተኛ ለውጥ ይኖረዋል፡፡ በተለይ እንደ ክልል የዳኝነት እና የፍትሕ አገልግሎት አሠጣጥ ላይ ያለውን ችግር ለመፍታት ለዳኞች ፣ ለዐቃቢ ሕግ ባለሙያዎች እና ለመርማሪ ፖሊሶች የአጭር ጊዜ ስልጠና እና የትምህርት ዕድል መስጠት የሚያስችል ነው፡፡ ጥምረቱ በቀጣይ ችግር ፈች ሰፊ የምርምር ሥራዎችንና ሥልጠናዎችን በመስጠት ሥራውን ይጀምራል፡፡
(ማራኪ ሰውነት)
በኲር የግንቦት 18 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም