የፍቺ ቀውስ

0
274

ሼሪፍ ግሪስ፣ ራየን ኤርሰን  እንዲሁም ሮበርት ጆርጅ የተባሉ የሕግና የማህበራዊ ሳይንስ ምሁራን ኢ ካውንትር በተባለው መጽሐፋቸው “ጋብቻ ማለት በስነ ልቦና፣ በስነ አዕምሮ እና በአካላዊ ጥምረት ቤተሰብ ለማስተዳደር ወይም ለመምራት አንድ ወንድ እና አንዲት ሴት ባልና ሚስት ሆነው የሚጣመሩበትና ያዳበሩዋቸውን ማህበራዊ ዕሴቶች በሕግ አግባብ የሚተገብሩበት ሂደት ነው” ሲሉ ይተረጉሙታል፡፡

ዲክሽነሪ ዶት ኮም የተባለው ድረ ገጽ ደግሞ ጋብቻን በሁለት መንገድ ተርጉሞታል::በአንድ በኩል “ጋብቻ አንድ ወንድና አንዲት ሴት ባልና ሚስት ሆነው ለመኖርና የሕግ፣ የሃይማኖታዊና ማህበራዊ ኃላፊነትን ለመውሰድ ተስማምተው የሚመሰርቱት ግንኙነት ነው” የሚል  ትርጉም ሰጥቶታል::በሌላ በኩል ደግሞ  “ጋብቻ በተለያየ የስርዓት አይነት ቤተሰባዊ ትስስር ለመፍጠር በሕግ ዕውቅና የተሰጠውና የጋራ ጥቅም፣ ኃላፊነትና ግዴታ የሚያስከትል  ግንኙነት ነው” ሲል ይገልጸዋል::በአጠቃላይ  “ጋብቻ በማህበረሰቡ መካከል ትስስር የሚፈጥር ሕጋዊ፣ ማህበራዊ እና ሃይማኖታዊ ኃላፊነት እና ግዴታን የሚያስከትል ግንኙነት ነው“ የሚል ግንዛቤን (ትርጓሜን) ይሰጣል::

ከሳቴ ብርሐን ተሰማ ኃብተሚካኤል አግደው በ1951 ዓ.ም ለመጀመሪያ ጊዜ ባሳተሙትና በ2002 ዓ.ም በድጋሚ በታተመው የአማርኛ መዝገበ ቃላት  ውስጥ “ትዳር (ሀደረ) ወይም (አደረ) ከሚለው የግእዝ ቃል የተወሰደ ሲሆን የሚሰጠውም የአማርኛ ትርጉም “ሰው ሁሉ ባለፀጋም ሆነ ድሃ ንብረቱን የሚያስተዳድርበት የቤት ሥራ ነው“ የሚል ትርጉም ተሰጥቶታል::ታዲያ ይሄ የጋራ የቤት ሥራ እና ማህበር በተለያዩ ምክንያቶች ለመበተን እና ለመለያት ሲዳረግ ደግሞ ፍቺ ይባላል፡፡

ቢቢሲ እ.አ.አ 2022 እንደዘገበው ትክክለኛው የፍቺ መጠን በቁጥር ተሰልቶ ባይታወቅም ጉዳቱ ግን ከጊዜ ወደ ጊዜ  እየጨመረ መጥቷል::የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ደግሞ በአዲስ አበባ እና በሌሎች ከተሞች የፍቺ ቁጥር መጨመሩ እንዳሳሰበው በድረ ገፁ ላይ አስፍሮ  ነበር።

አንዳፍታ ዶት ኮም በአዲስ አበባ ከተማ በ2016 ዓ/ም ግማሽ ዓመት 2 ሺህ 813 ፍቺ መፈጸሙን የከተማ አስተዳደሩ የሲቪል ምዝገባ እና የነዋሪነት አገልግሎት ኤጀንሲን ዋቢ አድርጎ ገልጿል:: በስድስት ወራት የተመዘገበው ፍች ከ2015 ዓ.ም ጋር ሲነጻጻር  በ106 ነጥብ 7 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል::በተያዘው የኢትዮጵያውያን 2018 ዓ.ም ሩብ ዓመት በመዲናዋ አዲስ አበባ ከተፈፀሙ 10 ሺህ ጋብቻዎች  ሦስት  ሺህ አካባቢ የሚደርስ ፍቺ ተፈጽሟል፡፡

የአማራ ክልል የሲቪል እና ቤተሰብ ምዝገባ አገልግሎት መረጃ እንደሚያመላክተው ደግሞ  በ2017 ዓ.ም በክልሉ 2 ሺህ 752 ፍቺ ተመዝግቧል::በሁለት ግለሰቦች ስምምነት እና ፍቃድ ይመሰረታል የተባለው ትዳር በፍቺ ሲጠናቀቅ  ከተጋቢዎቹ በበለጠ የሚጎዱት በመካከል የተፈጠሩት ልጆች እንደሆኑ  ላለፉት 20 ዓመታት በባሕር ዳር ከተማ በአፀደ ሕፃናት መምህርነት ሲያስተምሩ የቆዩት ወ/ሮ ዕፀሕይወት አለባቸው ናቸው::

ወ/ሮ ዕፀሕይወት ከአራት  እስከ ሰባት ዓመት ያሉ ሕፃናትን እንደሚያስተምሩ ገልፀው ምንም እንኳን ሕፃናቱ ምንም እንደማያውቁ ቢገመትም  ከወላጆቻቸው አንዳቸው  ገና  ከቤት      ሲወጡ ጀምረው የባህሪ ለውጥ እንደሚታይባቸው ይገልፃሉ፡፡

መምህር ዕፀሕይወት የባህሪ ለውጣቸውን ሲያብራሩ ትምህርት ቤት መምጣት አለመፈለግ፣ የምግብ ፍላጎት መቀነስ፣ ወላጆቻቸው አብረው እንደማይኖሩ ባገኙት አጋጣሚ ማውራት  መፈለግ፣ በምን እንደሆነ ለማያውቁት ፍቺ ራሳቸውን ተጠያቂ ማድረግ፣ አባት ከቤት ከወጣ “አባቴ እኮ አይወደኝም ጥሎን ሄዷል!“ እንዲሁም  እናት ከሄደች ደግሞ “እናቴ እንኳን አትወደኝም ጥላኝ ሄዳለች” ማለት፣  አባቱ ያልገዛለትን እቃ ሁሉ ሳይጠየቅ “አባቴ ገዝቶልኝ“ …ማለት፣ መፍዘዝ ፣ከየትኛውም ቤተሰብ ጋር መሆን እንደሚፈለጉ አለማወቅ እና ግራ የመጋባት ባህሪ ያሳያሉ::

ለዚህ እንደ ማሳያ ያነሱት  ባለፈው ዓመት ተማሪያቸው የነበረ የአምስት ዓመት ልጅ ወላጆቹ አንድ ላይ እያሉ የሚተኛው ከአባቱ ጋር ስለነበረ እናትና አባት ተለያይተው ከእናቱ ጋር ሌላ ቦታ ሲሄድ መተኛት ባለመቻሉ አባቱ ይዞት መመለሱን ነው:: በወቅቱም ልጁ አባቱ ጋር መሆኑን ይፈልጋል፤ እናቱ ስታወራው ደግሞ ያለቅሳል::ልጁ በመካከል ምን አይነት ጫና ውስጥ እንዳለ እንደ ሦስተኛ ወገን መመልከት ልጆች ገና ከሕፃንነታቸው ጀምሮ በፍቺ ምክንያት የሚሸከሙት ጫና ከባድ እንደሆነ በመገንዘብ ቤተሰብ ችግሩን በማስተዋል ሊፈታው  እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

በቅዱስ ጴጥሮስ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የአዕምሮ ህክምና ስፔሻሊስት ሀኪም ዶ/ር ይቅናሸዋ ሰለሞን ፍቺ ዘርፈ ብዙ ማህበራዊ ቀውሶች እንደሚኖሩት አንስተዋል::ይህም እንደ ግለሰብ ቤተሰብን ፤ ቤተሰብ ደግሞ ማህበረሰብን ስለሚሠራ ማህበረሰብን ሊነካ የሚችል ችግር ይፈጥራል::

ፍቺ በተወሰነ ደረጃ በጣም አስቸጋሪ በሆነ ሁኔታ  ውስጥ የሚኖሩ  ከሆነ ካሉበት መጥፎ ሁኔታ ለመውጣት እና ጥሩ ሁኔታ ላይ እንዲኖሩ ሊረዳ ይችላል::እነዛ ሰዎች ደግሞ ችግሮችን ተቋቁመው የመኖር አቅማቸው ከፍተኛ ነው ፤ ነገር ግን ልጆች በፍቺ ምክንያት ለችግር ተጋላጭ እንደሚሆኑ ጠቁመዋል፡፡

እንደ ባለሙያው ማብራሪያ ፍች /የጋብቻ መፍረስ/  ውስጥ ካሉ ልጆች ይልቅ በትዳር ውስጥ የሚኖሩ /እናት አባት  /  ልጆች የተሻለ ተጠቃሚነት ይኖራቸዋል፡፡

በፍቺ የተለያዩ ሰዎች ልጆች በትዳር ውሥጥ ካሉት  በሁለት እጥፍ  ችግራቸው ይጨምራል::በተለይ ሕፃናት ሲሆኑ “በኔ ምክንያት ነው ወላጆቼ የተለያዩት“ ብለው በከፍተኛ ደረጃ ራሳቸውን መውቀስ፣በቃል መግለፅ ስለማይችሉ ለተለያየ ህመም መጠቃት፣ ፀፀት ፣ አብረዋቸው ያሉ ሰዎች እናታቸው ከሆነች ያለችው “እሷም አንድ ቀን ጥላኝ ትሄዳለች“ ብለው ከፍተኛ የመንፈስ ጭንቀት የመመግባት ችግር ይገጥማቸዋል::

ፍቺ በሚፈፀምበት ጊዜ  ልጆች ትልቅ ሆነውም ቢሆን በዙሪያቸው ባለውሉ  ማህበረሰብ ላይ ተፅዕኖ ይኖረዋል::የባህሪ እና የስሜት ችግሮች ሊኖርባቸው ይችላል ፤ ለምሳሌ ጭንቀት ፣ ድባቴ፣ ለራስ ዝቅተኛ ግምት መስጠት፣ ኀይለኛ ቁጡ መሆን፣ ከልጆች ጋር መደባደብ፣ በትምህርታቸው ውጤት መቀነስ እንዲሁም አድገው በግንኙነታቸው ውስጥ ሰውን ባለማመን ትተውኝ የሄዳሉ ብሎ ማሰብ…ይከሰታል::በዚህም ምክንያት ልጆች አድገው  ትዳር ቢመሰርቱ እንኳ  በጥርጣሬ የተሞላ ይሆናል::

ባለሙያው ጥናቶችን ጠቅሰው እንዳሉት በፍቺ ውስጥ  ያለፉ ልጆች እነሱም አድገው ትዳር ሲመሰርቱ    ለፍቺ የመጋለጥ እድላቸው ከፍተኛ ነው::አድገውም ቢሆን ለወላጆቻቸው ያላቸው ፍቅር፣ አክብሮት እና ግንኙነት ይላላል፡፡

ቤተሰብ በፍቺ ሲለያዩ ልጆች የለመዷቸው  አያቶቻቸው፣ ጎረቤቶቻቸው ፣ ሰፈር ፣ትምህርት ቤት፣ አብሮ የሚኖር ሰው ፣ ጓደኛ… ይቀየራል::የለመዱት  አብሮ መብላት፣ መዝናናት… ሁሉ ሲቀየር አብሮ የባህሪ ለውጥ ይመጣል::ይህን ተከትሎም  አደገኛ የሆኑ ነገሮችን ሁሉ በመሞከር ወደ ሱስ መግባት፣ ያለዕድሜ ፆታዊ ግንኙነት መጀመር፣ አንዳንዴ ወላጆች ሌላ ትዳር ሲመሠርቱ ደግሞ በዛ ሰው  ጥቃትን ማስተናገድ ይጀምራሉ::ይሄ በራሱ ደግሞ የሚያመጣው ከፍተኛ የአዕምሮ ጤና መዘዝ ይኖራል::

እንደ ዶ/ር ይቅናሸዋ ገለፃ  ልጆች አድገውም ራሳቸውን ከማህበረሰቡ የሚያገሉ፣ በጣም ብቸኛ፣ በትምህርትም ሆነ በሥራ  ትኩረታቸውን መሰብሰብ ስለማይችሉ  ውጤታማ አለመሆን፣ በገንዘብ መቸገር፣ እናት ጋር ወይም አባት ጋር ሁነው በሚገጥማቸው ችግር ራስን እስከ ማጥፋት ድረስ መሄድ ይፈጠራል::በአካላዊ  ሁኔታ መታወክ ለግፊት ፣ ለልብ ህመም፣ ለአንቅልፍ መረበሽ ችግር ይጋለጣሉ፡፡

እንደ ማህበረሰብ  ቤተሰብ ሲፈርስ የማህበረሰብ ትስስር እየላላ እንደሚሄድም ባለሙያው ጠቁመዋል::ብዙ ፍቺ ባለበት አካባቢ ልጆች ነጭናጫ፣ ቁጡ…ስለሚሆኑ ወንጀል የበዛበት ማህበረሰብ ይፈጠራል::ብዙዎቹ ፍቺው ሲመጣ የሚያልፉበት መንገድ በራሱ ልጆች ፊት አንዱ ሌላውን እየሠደበ፣ እያዋረደ… ስለሚሆን ተፅዕኖው ልጆች ላይ ያርፋል::አንዳንድ ጊዜ ወላጆች በፍቺ ከተለያዩ በኋላ የገጠማቸውን ችግር ተቋቁመው የወደፊት ሁኔታን ታሳቢ ያደረገ ሂደት ሲኖር  ውጤታማ እንደሚሆን ዶ/ር ይቅናሸዋ አስረደረተዋል፡፡

“በብዙ ችግሮች ምክንያት ፍቺ የሚመከር አይደለም:: የማይቀር ከሆኖ እንኳ  እናትም ለልጆቿ እናት፣  አባትም አባት ስለሆኑ በልጆች ፊት አለመሰዳደብ የነሱ ችግር አለመሆኑን መንገር እና የለመዱትን ነገር ማስቀጠል ይገባል::ልጆች ከተቀጡ ወደ ሌላ ቦታ ይሄዳሉ ብሎ ባለማሰብ በሥርዓት ማሳደግ፣ ሕግ ማውጣት፣ ፍቅር መሥጠት ፣ጥያቄያቸውንም በመረዳት  መመለስ ያስፈልጋል“ በማለት መክረዋል፡፡

 

(ማራኪ ሰውነት)

በኲር የህዳር  1  ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here