የጋራ እርምጃ እንዲወሰድበት ጥሪ የቀረበበት የፕላስቲክ ብክለት በዘንድሮው የዓለም የአካባቢ ቀን ሲከበር ዋና አጀንዳ ነበር። የፕላስቲክ ብክለት በአካባቢ ውስጥ የፕላስቲክ ዕቃዎች እና ቅንጣቶች መከማቸት ሲሆን ይህም በሰዎች፣ በዱር እንስሳት እና በመኖሪያ አካባቢዎች ላይ አሉታዊ ተጽዕኖን ያሳድራል፡፡ ለብዝኃ ሕይወት መጥፋት፣ ለስነ – ምህዳር መራቆት እና ለአየር ንብረት ለውጥ መንስኤ ነው። የፕላስቲክ ቆሻሻ የውኃ ውስጥ ስነ-ምህዳሮችን በመበከል በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎችን ጤና ያውካል፣ የምግብ ምርትን ይጎዳል።
የፕላስቲክ ብክለትን በማስወገድ ላይ ያተኮረው የዘንድሮው የዓለም የአካባቢ ቀን ደቡብ ኮሪያ እ.አ.አ ሰኔ 5 ቀን 2025 አስተናግዳለች። ባለፉት 28 ዓመታት ሀገሪቱ የውኃና የአየር ጥራትን በማሻሻል፣ ኬሚካሎችን በኃላፊነት በመቆጣጠር እንዲሁም ሥነ-ምህዳሮችን በመጠበቅ ረገድ ጉልህ መሻሻል አሳይታለች። ለዚህም ነው የዘንድሮውን የአከባቢ ቀን እንድታዘጋጅ የተመረጠችው፡፡
በአሁኑ ጊዜ ደቡብ ኮሪያ ቆሻሻን በማስወገድ ረገድ ግንባር ቀደም ከሆኑት ሀገሮች መካከል ትጠቀሳለች። የዓለም የአካባቢ ቀንን ስታዘጋጅም ይህ ለሁለተኛ ጊዜ ነው። እ.አ.አ በ1997 “በምድር ላይ ላለ ሕይወት” በሚል መሪ ሃሳብ በዓሉን ለመጀመሪያ ጊዜ አስተናግዳለች። የዘንድሮው የዓለም የአካባቢ ቀን የፕላስቲክ ብክለትን ማስወገድ (Beat Plastic Pollution) በሚል ጭብጥ ላይ ሲያተኩር ይህ ለሦስተኛ ጊዜ ነው።
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ በዓሉ ሲከበር ባስተላለፉት መልዕክት “የፕላስቲክ ቆሻሻ የወንዞችን ፍሰት ይዘጋል፣ ውቅያኖስን ይበክላል፤ የዱር አራዊትንም አደጋ ላይ ይጥላል። በተጨማሪም ወደ ትናንሽ ቁርጥራጮች ሲከፋፈል ወደ ሁሉም የምድር ክፍሎች ዘልቆ ይገባል፡፡ በመሆኑም ለአስቸኳይ ለውጥም እንቅስቃሴ እየተደረገ ነው። ሕዝባዊ ተሳትፎን እያየን ነው፣ … ፕላስቲኮችን ለመቀነስ እና የቆሻሻ አያያዝን ለማሻሻል ፖሊሲዎች ያስፈልጋሉ። እኛ ግን የበለጠ በፍጥነት መሄድ አለብን” ነው ያሉት።
በኮሪያ ሪፐብሊክ ጄጁ ከተማ በተካሄደው የዓለም የአካባቢ ቀን ይፋዊ ሥነ-ሥርዓት ላይ የፕላስቲክ ብክለትን ለማስቆም ፍጥነት እንደሚያስፈልግ አጽንኦት ተሰጥቶበታል፤ የሀገሪቱ የአካባቢ ጥበቃ ምክትል ሚኒስትር ሊ ቢዩንግዋ በጄጁ በተካሄደው መታሰቢያ ላይ “መንግሥታት፣ የንግዱ ማሕበረሰብ፣ ዜጎች እና ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የክብ (ፕላስቲክን ማምረት እና እንደገና መጠቀም) ምጣኔ ሀብቱን ዕውን ለማድረግ ሁሉም ቁልፍ ተዋናዮች ናቸው። የፕላስቲክ ብክለት እኛን ከመጨረሱ በፊት የፕላስቲክ ብክለትን እኛ ልንጨርሰው ይገባል” ነው ያሉት። ምክትል ሚኒስትሩ አክለውም “ምቾትን ወደ ጎን ትተን በትንሽ ተግባራት አንድ ላይ እንጀምር፤ ሁሉም ሰው ሢሠራ ለውጥ ይከሰታል” በማለት የችግሩን አሳሳቢነት በማንሳት አሳስበዋል፡፡
የተባበሩት መንግሥታት የአካባቢ ጥበቃ ፕሮግራም (ዩ ኤን ኢ ፒ) ዋና ዳይሬክተር ኢንገር አንደርሰን በጄጁ በተከበረው በዓል ላይ እንደተናገሩት የፕላስቲክ ብክለትን ማቆም ለሰው ልጅ፣ ለፕላኔቶች፣ ለኢኮኖሚያዊ እና ለንግድ ጤና አስፈላጊ ነው፡፡
የዓለም የአካባቢ ቀንን ምክንያት በማድረግ ከ2
ሁለት ሺህ 500 በላይ ዝግጅቶች በሁሉም የዓለም ክፍሎች ተካሂደዋል፡፡ ታዋቂ ዓለም አቀፍ ሰዎችን ጨምሮ በሚሊዮን የሚቆጠሩ የተለያዩ ሀገራት ዜጎች በዓለም አቀፍ ደረጃ ስለ ፕላስቲክ ብክለት ድምፃቸውን አሰምተዋል፡፡
በውቅያኖስ ውስጥ ያለውን ፕላስቲክ ስናስብ ወደ አዕምሯችን ቀድሞ የሚመጣው ምናልባትም በውኃው ላይ የሚንሳፈፉ የፕላስቲክ ጠርሙሶችና ዕቃዎች ሊሆኑ ይችላሉ። ይህ ዓይነቱ ብክለት በእርግጥ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ቢሆንም በባሕር ሥነ-ምህዳር ላይ ከፍተኛ ስጋት ሊፈጠር የሚችለው የማይክሮፕላስቲኮች (እጅግ እኑስ ፕላስቲኮች) ጉዳይ ነው። ፕላስቲክ በጊዜ ሂደት ተሰባብሮ ወደ ትናንሽ ቁርጥራጮች ይቀየራል። እነዚህ ቁርጥራጮችም ማይክሮ ፕላስቲክ ይባላሉ፡፡ የፕላስቲክ ቁርጥራጮች ከአምስት ሚሊ ሜትር ያነሱ ጥቃቅን የፕላስቲክ ቅንጣቶች ናቸው፡፡
ማይክሮፕላስቲኮች የሚያስከትሉትን የጎንዮሽ ጉዳት በተመለከተ ጥናት እየተደረገባቸው ነው፡፡ እስካሁን በተደረጉ ጥናቶች ጉዳት እያስከተሉ ስለመሆኑ ተመላክቷል፡፡ ዓሳዎች እነዚህን ጥቃቅን የፕላስቲክ ቅንጣቶች ይመገባሉ፤ እነዚህን ዓሳዎች ደግሞ ሰዎች ሊመገቧቸው ይችላሉ። ይህም የጤና ቀውስን ያስከትላል፡፡
በውቅያኖሶች ውስጥ ያለው የፕላስቲክ ብክለት ቀውስ በየዓመቱ እየተባባሰ ነው። በአንድ ሳይንሳዊ ጥናት ላይ የተገኘ ውጤት እንደሚያሳየው በዓለም ውቅያኖሶች ውስጥ ከዐሥራ አምስት እስከ ሃምሳ አንድ ትሪሊዮን የሚደርሱ ማይክሮፕላስቲኮች አሉ፡፡ በየዓመቱ ስምንት ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን ፕላስቲክም ወደ ውቅያኖስ ይገባል።
የፕላስቲክ ብክለት ፕላኔታችን እና የሰውን ደኅንነት አደጋ ላይ የሚጥል እየጨመረ የመጣ ቀውስ ነው፡፡ እ.አ.አ በ2025 ብቻ ዓለም አምስት መቶ ዐሥራ ሚሊዮን ቶን ፕላስቲኮችን ታስተናግዳለች ተብሎ ይጠበቃል። በየዓመቱም ወደ ዐሥራ ሦስት ሚሊዮን ቶን የሚጠጋ ፕላስቲክ በአፈር ውስጥ ይከማቻል። በጣም የሚያስደነግጠው ደግሞ ማይክሮፕላስቲክ በሰው ደም ወሳጅ ቧንቧዎች፣ ሳንባዎች፣ አዕምሮ እና በእናት ጡት ወተት ውስጥ ሳይቀር መገኘቱ ነው። ይህ ጉዳይ የዓለማችንን እና የሕይወታችንን ክፍል ሁሉ ይነካል። በዚህ ምክንያትም የፕላስቲክ ብክለት በጊዜያችን ካሉት አሳሳቢ የአካባቢ ተግዳሮቶች አንዱ ሆኗል።
እ.አ.አ. በ2040 በፕላስቲክ የተሞሉ አከባቢዎች በሃምሳ በመቶ እንደሚያድጉ የተተነበየ ሲሆን ይህም ከፍተኛ ብክለት በማስከተል በምንመገበው ምግብ፣ በምንጠጣው ውኃ እና በምንተነፍሰው አየር ወደ ሰውነታችን ዘልቆ ይገባል። ውጤቱም ለጤና ቀውስ መዳረግ ነው፡፡
ትልቁ ችግር ፕላስቲክ እጅግ በጣም ጠንካራ በመሆኑ እንደሌሎች ቆሻሻዎች ተቃጥሎ የሚጠፋ ወይም የሚበሰብስ አለመሆኑ ነው፡፡ ፕላስቲክ ለፀሐይ ብርሃን ሲጋለጥ በጊዜ ሂደት ቢፈራርስም ሙሉ በሙሉ አይጠፋም። ከዚህ ይልቅ ቅንጣቶቹ በአጉሊ መነጽር ብቻ እስኪታዩ ድረስ ትናንሽ ቁርጥራጮች ይሆናሉ። እስከ ዛሬ ድረስ የሚመረተው እያንዳንዱ የፕላስቲክ ቁርጥራጭም አሁንም በዓለም ላይ ይገኛል። በተለይም ከቅሪተ አካል ነዳጆች የተሠሩ ፕላስቲኮች ከመቶ ዓመት በላይ ዕድሜ አላቸው።
ፕላስቲኮች ብዙ ጊዜ ጠንካራ፣ ተለዋዋጭ እና ዘላቂ የሚያደርጋቸው ተጨማሪ ነገሮችን ይይዛሉ። ታዲያ እነዚህ ነገሮች የፕላስቲክ ምርቶችን ዕድሜን ሊያራዝሙ ይችላሉ፡፡ አንዳንድ ግምቶች እንደሚያሳዩት ቢያንስ 400 ዓመታት ሊቆዩ ይችላሉ፡፡
የፕላስቲክ ቅንጣቶች ዘላቂ፣ ጎጂ ኬሚካሎችን እና መርዛማ ንጥረ ነገሮችን ስለሚለቁ በአካባቢ ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ያሳድራሉ። የፕላስቲክ ምርት በቅሪተ አካል ነዳጆች ላይ የተመሠረተ ነው፡፡ ይህም ለግሪንሃውስ ጋዝ ልቀት እና ለዓለም ሙቀት መጨመር አስተዋፅኦ አለው፡፡ እንዲሁም ፕላስቲክን ማቃጠል የአየር ንብረትን የሚቀይሩ ጋዞች እንዲወጡ ያደርጋል።
ማይክሮፕላስቲክ የአልጌዎችን ዕድገት እና በጸሐይ ብርሃን ምግብ የማዘጋጀት ሂደትን (ፎቶሲንተሲስ) ቅልጥፍናን በመቀነስ የውቅያኖስ ካርቦንዳይኦክሳይድን የመሳብ ችሎታ ላይ ተጽዕኖ ያሳድራል።
በዓለም አቀፍ ደረጃ በየዓመቱ 11 ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን የሚመዝን የፕላስቲክ ቆሻሻ ወደ ውኃ ስነ ምህዳር ይገባል። በፕላስቲክ ብክለት ምክንያት በየዓመቱ የሚወጣው ማሕበራዊ እና አካባቢያዊ ወጪ ከ300 ቢሊዮን እስከ 600 ቢሊዮን ዶላር እንደሚደርስ ይገመታል።
በውቅያኖስ ውስጥ ያለው የፕላስቲክ ብክለት ጉዳይ እየተሻሻለ አይደለም፡፡ እንዲያውም ይህ ሁኔታ በከፍተኛ ሁኔታ እየተባባሰ ነው፡፡ ምክንያቱም የከርሰ ምድር ነዳጅ አውጪ ኩባንያዎች የፕላስቲክ ምርታቸውን ለማሳደግ በቢሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ ፈሰስ እያደረጉ ነው። በፋብሪካዎች ፕላስቲክ ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ በፍጥነት እና ርካሽ በሆነ መንገድ እየተመረተ ነው።
በአከባቢ ጥበቃ ዙሪያ ላይ የሚሠራ ኤለን ማካርቻርት የሚባለው ፋውንዴሽን እንዳለው ከሆነ የፕላስቲክ ምርት እ.አ.አ በ1960ዎቹ ከ15 ሚሊዮን ቶን በ2014 ወደ 311 ሚሊዮን ቶን ጨምሯል። በ2050 ደግሞ በሦስት እጥፍ እንደሚጨምር ይጠበቃል። ምንም ዓይነት እርምጃ ካልተወሰደ በ2050 በውቅያኖስ ውስጥ ያለው ፕላስቲክ በሙሉ ክብደቱ በውቅያኖስ ውስጥ ካለው ዓሳ ይበልጣል።
በውቅያኖሶች ውስጥ ከሚገኘው ፕላስቲክ ውስጥ ስልሳ ከመቶ የሚሆነው ከቻይና፣ ከኢንዶኔዥያ፣ ከፊሊፒንስ፣ ከታይላንድ ወይም ከቬትናም ተመርተው የተጣሉ ናቸው። እነዚህ አምስት ሀገሮች በፍጥነት በማደግ ላይ በመሆናቸው በከፍተኛ ሁኔታ ፕላስቲክን ያመርታሉ፡፡
በአሁኑ ጊዜ ቻይናዊያን ከዓለም በከፍተኛ ሁኔታ የታሸገ ውኃ ሸማቾች ናቸው። ይሁን እንጂ በእነዚህ ሀገሮች ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት ቢኖርም የቆሻሻ ማስወገጃ ቴክኖሎጂያቸው ደካማ በመሆኑ ፕላስቲክን ከተጠቀሙ በኋላ ወደ ባሕር ዳርቻዎች ነው የሚጥሉት። በዚህ ድርጊታቸውም ምክንያት የአካባቢ ስነ – ምህዳርን እየጎዱ ነው።
እንደ ፕላስቲክ ከረጢቶች እና የምግብ መጠቅለያዎች ያሉ አብዛኛዎቹ መሰል ምርቶች ከደቂቃዎች እስከ ሰዓታት የሚቆይ የሕይወት ጊዜ አላቸው። ነገር ግን በአካባቢው በመቶዎች ለሚቆጠሩ ዓመታት ሊቆዩ ይችላሉ።
ለዚህም ነው አንዳንድ መንግሥታት የፕላስቲክ ከረጢቶችን ለመገደብ ወይም ለማገድ እርምጃ የወሰዱት። ለአብነትም ከሰሞኑ የኢትዮጵያ መንግሥት በመዲናዋ አዲስ አበባ የፕላስቲክ ምርቶች አገልግሎት ላይ እንዳይውሉ የሚያስችል አዋጅ አጽድቋል፡፡ የአሜሪካዋ የካሊፎርኒያ ግዛትም እ.አ.አ በ2026 ሁሉንም የፕላስቲክ ከረጢቶች የሚከለክል ሕግ አውጥታለች። የሜክሲኮ ፕሬዘዳንት ክላውዲያ ሺንባም መቶ በመቶ የፕላስቲክ ቆሻሻን ከሀገሪቱ የባሕር ዳርቻዎች በአምስት ዓመታት ውስጥ (ከ2025 – 2030) ለማስወገድ የሚያስችል የባሕር ዳርቻ ጽዳት እና ጥበቃ ብሄራዊ ስትራቴጂ ጀምረዋል።
ምንጭ:-
www.worldenvironmentday.global፣
(https://www.unep.org)፣
https://globalplasticshub.org/)
(ሳባ ሙሉጌታ )
በኲር የሰኔ 9 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም