ግንቦት 19 ቀን 2016 ዓ.ም
የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ባልተጠበቁ ሁነቶች እና ድራማዊ ክስተቶች ታጅቦ ዓመቱ ተደምድሟል። የማንቸስተር ከተማ በተከታታይ ለአራተኛ ጊዜ ውኃ ሰማያዊ ቀለም የሆነችበት፣ በሚኬል አርቴታ የሚመራው ሠራዊት ከእልህ አስጨራሽ ትግል በኋላ ልምድ ባለው ጓርዲዮላ ድጋሚ የተበለጠበት፣ ሊቨርፑላውያን በካራባው ዋንጫ ብቻ አሰልጣኛቸውን የሸኙበት፣ በስታንፎርድ ብሪጅ የቶድ ቦህሊ ረብጣ ቢሊዮን ፓውንድ ዕቅድ የከሸፈበት እንዲሁም ማንቸስተር ዩናይትድ እንደ ታሪኩ ማደር ተስኖት በልኩ ያልተገኝበት ዓመት ነበር – የ2023/24 የውድድር ዘመን።
በአራቱም የዓለም ማዕዘን የሚገኙ የእግር ኳስ ደጋፊዎች እና ተመልካቾች ለአፍታ እንኳ ትኩረት የማይነፍገው ነው የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ። ለ38 ሳምንታት ሲተወን የነበረው አጓጊው የፕሪሚየር ሊጉ ድራማ በማንቸስተር ሲቲ አሸናፊነት ተደምድሟል።
በሼክ መንሱር ረብጣ ቢሊዮን ዶላር የሚዘወረው ማንቸስተር ሲቲ ለተከታታይ አራተኛ ጊዜ ዋንጫውን በማንሳት አዲስ ክብረ ወሰን አስመዝግቧል። አሰልጣኝ ፔፕ ጓርዲዮላ ኢትሀድ ከደረሰበት እ.አ.አ 2016 ጀምሮ ባለፉት ስምንት ዓመታት ስድስት የፕሪሚየር ሊጉን ዋንጫ ማሳካት ችሏል። ይህ መረጃ እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስ በአጠቃላይ 17 ዋንጫዎችንም ማሳካት ችሏል ፔፕ ጓርዲዮላ።
እስከ መጨረሻው ሽርፍራፊ ሴኮንድ ልብን በሚያሞቅ እና ትንፋሽን በሚያስውጥ ፉክክር ውስጥ የነበረው የሰሜን ለንደኑ ክለብ አርሴናል ልክ እንደ አምናው ሁለተኛ ደረጃን ይዞ አጠናቋል። በውድድር ዘመኑ የሠራቸው ጥቃቅን ስህተቶች በመጨረሻ ዋጋ አስከፍሎት ማንቸስተር ሲቲን አጅቦ እንዲያጠናቅቅ አድርጎታል።
የመርሲሳይዱ ክለብ ሊቨርፑል ሦስተኛ ደረጃን ይዞ ባጠናቀቀበት የውድድር ዘመን አሰልጣኝ የርገን ክሎፕ ከዘጠኝ ዓመታት ቆይታ በኋላ ከአንፊልድ ሮድ ተሸኝቷል። የኡናይ ኤምሪው አስቶንቪላ ከ41 ዓመታት በኋላ በአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ መድረክ መሳተፍ የሚያስችለውን ውጤት አስመዝግቧል።
ሁለቱ የለንደን ከተማ ክለቦች ቶተንሃም እና ቼልሲ ደግሞ በቅደም ተከተል ኢሮፓ ሊግ እና ኮንፍረንስ ሊግ የሚያሳትፋቸውን ውጤት ይዘው ዓመቱን ጨርሰዋል።
የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ከየትኛውም የአምስቱ ታላላቅ ሊጎች የበለጠ ጠንካራ ፉክክር የሚስተዋልበት ሊግ ነው። ዋንጫውን ለማንሳት፣ የአውሮፓ መድረክ ተሳትፎን ለማረጋገጥ ከሚደረገው ትንቅንቅ ባልተናነሰ ላለመውረድ የሚደረገው ፉክክር እጅግ አጓጊ ነበር። ሉተን ታውን፣ ሼፊልድ ዩናይትድ እና በርንሌይ ሊጉን መቋቋም ተስኗቸው በመጡበት ዓመት ወደ ሻምፒዮን ሺፑ የወረዱ ክለቦች ሆነዋል። እስከ መጨረሻው የሊጉ መርሐ ግብር ላለመውረድ ሲታገል የነበረው ሉተን ታውን ጥረቱ እውን ሳይሆን ቀርቷል።
በ38ኛ ሳምንት የፕሪሚየር ሊጉ ጨዋታ ተአምር መሥራት ቢጠበቅበትም ሳይሆን ቀርቶ በርንሌይን እና ሼፊልድን ተከትሎ ወደ ታችኛው የሊግ እርከን ወርዷል። 139 ዓመታትን እድሜ ያስቆጠረው ሉተን ባሳለፍነው ዓመት ነበር ለመጀመሪያ ጊዜ ፕሪሚየር ሊጉን የተቀላቀለው።
በቪንሰንት ኮምፓኒ ሲመራ የነበረው በርንሌይም ከአስከፊ የአንድ ዓመት የፕሪሚየር ሊጉ ቆይታ በኋላ ወደ መጣበት ተመልሷል። በደረጃ ሰንጠረዡ ግርጌ ላይ ሆኖ የጨረሰው ሌላኛው ክለብ ሼፊልድ ዩናይትድ በፕሪሚየር ሊጉ ታሪክ አስከፊውን የውድድር ዘመን በማሳለፍ አዲስ መጥፎ ክብረ ወሰን በማስመዝገብ ጭምር ነው የተሰናበተው -ከፕሪሚየር ሊጉ።
በፕሪሚየር ሊጉ አነስተኛ ግቦችንም ያስቆጠረ ሲሆን በሊጉ ታሪክ በርካታ ግቦች የተቆጠሩበት የመጀመሪያ ክለብም ሆኗል። ይህም እ.አ.አ በ1993/94 የውድድር ዘመን በወቅቱ በፕሪሚየር ሊጉ ይሳተፍ ከነበረው ስዊንደን ታውን ከተቆጠረበት 100 ግቦች የበለጠ ሼፊልድ ዘንድሮ ተቆጥሮበታል።
በወረዱት እነዚህ ክለቦች ምትክ ደግሞ ሦስት ክለቦች በፕሪሚየር ሊጉ የሚሳተፉ ይሆናል። ይህ መረጃ እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስ ሌስተር ሲቲ እና ኢፕስዊች ታውን ወደ ፕሪሚየር ሊጉ ያደጉ ክለቦች ናቸው።
አንደኛው ክለብ ደግሞ በደረጃ ሰንጠረዡ ከሦስተኛ እስከ ስድስተኛ የተቀመጡ ክለቦች በሚያደርጉት የእርስ በእርስ ጨዋታ (በጥሎ ማለፍ) ተለይቶ የሚታወቅ ሲሆን የሊድስ ዩናይትድ እና የሳውዝ አምፕተን አሸናፊ ሦስተኛው ክለብ ሆኖ ፕሪሚየር ሊጉን ይቀላቀላል።
ሌስተር ሲቲዎች 97 ነጥቦችን በመሰብሰብ ነው ከአንድ ዓመት የሻምፒዮን ሺፕ በኋላ ድጋሚ ወደ ፕሪሚየር ሊጉ የተመለሱት። ቀበሮዎቹ የፕሪሚየር ሊጉን ዋንጫ በማንሳት ስማቸው በክብር መዝገብ ከሰፈሩት ክለቦች መካከል ይገኙበታል።
አንጋፋው ክለብ ሌስተር ሲቲ ሁለተኛ ደረጃን ይዞ ካጠናቀቀበት እ.አ.አ 1928/29 የውድድር ዘመን በኋላ አስደናቂ አቋም በማሳየት ዋንጫውን ያነሳው በ2015/16 የውድድር ዘመን እንደነበረ አይዘነጋም። በወቅቱ በአሰልጣኝ ክላውዲዮ ራኔየሪ እየተመራ የሊጉ ሻምፒዮን መሆኑ ይታወሳል። ቀበሮዎቹ በ2020/21 የውድድር ዘመንም የኤፍ ኤ (FA Cup ) ዋንጫን አሳክተዋል። ክለቡ የኤፍ ኤ ዋንጫውን ባነሳበት ማግስት ግን በውጤት ማጣት እና በገንዘብ እጥረት ምክንያት በእጅጉ ተፈትኗል።
የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ሌስተር ሲቲን ክፉኛ የኢኮኖሚ ቀውስ ውስጥ እንዲገባ አድርጎታል። በዚህ ምክንያት ክለቡን ከገባበት አጣብቂኝ ለማውጣት ወሳኝ የቡድኑ ተጫዋቾችን መሸጡን መረጃዎች አመልክተዋል። በእነዚህ ሁሉ ችግሮች የተፈተነው ሌስተር ሲቲ በ2022/23 የውድድር ዘመን መጨረሻ ወደ ሻምፒዮን ሺፑ ወርዷል። ወደ ታችኛው የሊግ እርከን ሲወርድ አብረው በመውረድ እና በኋላም ወደ ላይኛው የሊግ እርከን እንዲመጣ ትልቅ አስተዋጾ ያደረጉ ተጫዋቾች መኖራቸውም ተዘግቧል።
ጂሚ ቫርዲ፣ ዌስ ሞርጋን፣ዊልፍሪድ ኒዲዲ እና ኬሌቺ ኢንሀቾ የመሳሰሉት ታማኝ ተጫዋቾች አብረክቶ የማይዘነጋ መሆኑን የክለቡ ድረ ገጽ መረጃ ያሳያል። በተለይ ደግሞ የእንግሊዛዊው አጥቂ ጂሚ ቫርዲ ሚና ላቅ ያለ መሆኑ በመረጃው ተጠቅሷል።
የ37 ዓመቱ አጥቂ በ2012 እ.አ.አ ነበር ኪንግ ፓወር የደረሰው። ባለፉት 12 ዓመታትም 405 ጨዋታዎችን በማድረግ 174 ግቦችን ከመረብ አገናኝቷል። በተጠናቀቀው የውድድር ዘመን ሌስተር ሲቲ ወደ ፕሪሚየር ሊጉ ሲያድግ 18 ግቦችን ከመረብ በማሳረፍ የላቀ አስተዋጽኦ ካደረጉት ውስጥ ቀዳሚው ተጫዋች ነው። ቀበሮዎቹ ከፕሪሚየር ሊጉ አምስት ጊዜ በመውረድ እና በማደግ የሚታወቁ ናቸው። ዌስትብሮም አልቢዮን እና ኖርዊች ሲቲም በተመሳሳይ የዚህ ታሪክ ተጋሪ መሆናቸውን መረጃው ያመለክታል።
ሌላው ከ22 ዓመታት በኋላ ፕሪሚየር ሊጉን የተቀላቀለው ኢፕስዊች ታውን ነው። ኢፕስዊች ታውን በ96 ነጥቦች ሌስተር ሲቲን በመከተል ቀድሞ ወደ ፕሪሚየር ሊጉ መቀላቀሉን ያረጋገጠ ክለብ ነው። ሰማያዊ ለባሾቹ በእንግሊዝ እድሜ ጠገብ ከሚባሉ ክለቦች ውስጥ የሚጠቀሱ ናቸው።
ባለፉት ሁለት ዓመታትም ጠንካራ እና ድንቅ የውድድር ጊዜ አሳልፈዋል። በአጭር ጊዜ ውስጥ ሁለት የእንግሊዝ ሊግ እርከኖችን በመሻገር ጠንካራ መሆናቸውን አስመስክረዋል። እ.አ.አ በ2022/23 የውድድር ዘመን ኢፕስዊች ታውን በሊግ አንድ ይጫወት እንደነበር የቅርብ ጊዜ ትዝታ ነው። በሊግ አንድ የመጀመሪያው ዓመት ወደ ሻምፒዮን ሺፕ በመሸጋገር ብዙዎቹን አጃኢብ አሰኝቷል።
የክለቡ አስደናቂ ገድል አሁንም በዚህ ሳይጠናቀቅ በተጠናቀቀው የውድድር ዘመን ደግሞ ሳይጠበቅ ፕሪሚየር ሊጉን በመቀላቀል ብዙዎቹን አስደንቋል። ኢፕስዊች ታውን በ1980ዎች መጀመሪያ ጠንካራ ከሚባሉ ታላላቅ ስድስት የፕሪሚየር ሊጉ ክለቦች አንዱ እንደነበር የታሪክ ማህደሩ ያመለክታል።
በኃያላኖቹ የአውሮፓ መድረክ በሜዳው የሚያደርጋቸውን ጨዋታዎች ባለመሸነፍም ይታወቃል። ሪያል ማድሪድን፣ ባርሰሎናን፣ ኤስሚላንን፣ ኢንተርሚላን እና ላዚዮን በሜዳው ማሸነፉም ይነገራል። በዚህ አስደናቂ አቋማቸውም በ1978 እ.አ.አ የኤፍ ኤ ዋንጫ እና በ1981 ደግሞ የአውሮፓ ዋንጫን (የአሁኑ ሻምፒዮንስ ሊግን) ማሸነፋቸው በታሪክ መዝገባቸው ተቀምጧል። ይሁን እንጂ ከዚህ ሁሉ ዝና እና ክብር በኋላ ወደ ታችኛው ሊግ ወርደዋል። ላለፉት ሁለት አስርት ዓመታትም ወደ ላይ ከፍ ማለት ተስኗቸው በታችኛው ሊግ አሳልፈዋል።
ኢፕስዊች ታውን ባለፉት ሁለት ዓመታት ወደ ቀድሞ ከፍታው እየተንደረደረ መሆኑን ሜዳ ላይ አሳይቷል። ከፈረንጆች 2021 ጀምሮ በአዲስ ባለ ሀብቶች መመራቱ ደግሞ በክለቡ አዲስ የእግር ኳስ አቢዮት እንዲፈጠር አድርጓል። ይህ ደግሞ በፍጥነት ፍሬ ማፍራቱን መረጃዎች አመልክተዋል።
በ11 ዓመታት የእንግሊዝ ሊግ ታሪክ በአጭር ጊዜ ሁለት የሊግ እርከኖችን በመሻገር ከሊግ አንድ ፕሪሚየር ሊጉ የደረሰ ብቸኛው ክለብ መሆኑን የቢቢሲ መረጃ ያስነብባል።
በተመሳሳይ ሌስተር ሲቲን እና ኢፕስዊች ታውንን ተከትሎ ወደ ላይኛው የሊግ እርከን የሚያልፈውን ቡድን ለመለየት ሊድስ ዩናይትድ፣ ሳውዝ አምፕተን፣ ዌስትብሮምዊች አልቢዮን እና ኖርዊች ሲቲ ተፋጠው እንደነበረ አይዘነጋም።
የበረቱት ሊድ ዩናይትድ እና ሳውዝ አምፕተንም የመጨረሻው ምዕራፍ ላይ የደረሱ ሲሆን አሸናፊው ክለብም ሦስተኛው ክለብ ሆኖ ፕሪሚየር ሊጉን የሚቀላቀል ይሆናል።
ቢቢሲን ስፖርትን የሌስተር ሲቲ ይፋዊ ደረ ገጽን እና ዘ ቴሌግራፍን በመረጃ ምንጭነት ተጠቅመናል።
(ስለሺ ተሾመ)
በኲር ግንቦት 19 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም