የፕሬዝዳንቱ ሞት

0
161

ግንቦት 19 ቀን 2016 ዓ.ም

የኢራኑ ፕሬዝዳንት ተሳፍረውበት የነበረው ሄሊኮፕተር ባጋጠመው የቴክኒክ ብልሽት በመከስከሱ   ፕሬዝዳንቱን ጨምሮ የስምንት ሰዎች ሕይወት ማለፉን የኢራን መንግሥት የዜና አገልግሎት ዘግቧል።

የ63 ዓመቱ ሚስተር ራይሲ እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሆሴን አሚር አብዶላሂን ባለፈው እሁድ በሄሊኮፕተር አደጋ መሞታቸው ነው የተረጋገጠው፡፡

እንደ ፕረስ ዘገባ በኢራን እና በአዘርባጃን ድንበር አቅራቢያ  የተሠሩ ሁለት ግድቦችን ከከፈቱ በኋላ ሄሊኮፕተራቸው በጆልፋ ከተማ አቅራቢያ በሚገኝ ተራራማ አካባቢ ተከስክሷል። የአሰሳ እና የነፍስ አድን ቡድኖች የአደጋውን ቦታ ከማግኘታቸው በፊት ለሰዓታት ያህል በዝናብ እና በጭጋግ ጥቅጥቅ ባለው ደን ያለውን ወጣ ገባ ቃኝተዋል። ሆኖም በሕይወት የተረፉ ሰዎች አልነበሩም።

የኢራን የበላይ መሪው አያቶላ አሊ ካሜኔ በመንግሥት ሥራ ላይ “ምንም አይነት መስተጓጎል አይኖርም” ያሉ ሲሆን ፕሬዝዳንቱ ሞታቸው ከተረጋገጠ በኋላ በፍጥነት ነበር  ተቀዳሚ ምክትል ፕሬዝዳንት መሀመድ ሞክበር የተጠባባቂ ፕሬዝዳንትነት ሚና እንደሚጫወቱ የተወሰነው፡፡ ምክትል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አሊ ባገሪ ካኒንን ደግሞ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አድርጎ ሾሟል።

የአያቶላ ካሜኔን ተተኪ ሊሆን ይችላል ተብሎ የተገመተው የወግ አጥባቂው  ራይሲ ሞት የተከሰተው ቴህራን ከእስራኤል እና ከዩናይትድ ስቴትስ ጋር ግጭት ለመፍጠር ከተቃረበች ሳምንታት በኋላ ነው። ኢብራሂም ራይሲ በኢራን የፖለቲካ መዋቅር ውስጥ ከአቶ ካሜኒ ቀጥሎ ሁለተኛው በጣም ኃይለኛ ግለሰብ ነበሩ ሲል ኒውዮረክ ታይምስ ዘግቧል፡፡

እ.አ.አ. በ2021 ወደ ፕሬዝዳንትነት መውጣታቸውን ተከትሎ ራይሲ ስልጣናቸውን በማጠናከር የለውጥ አራማጆችን አግልለዋል። በእስራኤል እና በአሜሪካ ላይ ጥቃት ያደረሱትን በመካከለኛው ምሥራቅ የሚገኙ አማጽያንን በመደገፍ የኢራንን ክልላዊ ተጽእኖ ማስፋፋቱን ቀጥለው ነበር፤ እንዲሁም በሀገር ውስጥ ተቃዋሚዎች በተለይም በአብዛኛዎቹ ሴቶች እና ወጣቶች ላይ ሞትን ያካተተ እርምጃ ወስደዋል።

አልጀዚራ እንደዘገበው ራይሲ እ.አ.አ. በ1988 ለአምስት ወራት ያህል በፖለቲካ እስረኞች ላይ የሚፈጸሙ ግድያዎችን የሚከታተል ኮሚቴ አባል ሆነው ነበር፡፡ ይህም ያለፈው ታሪካቸው በኢራን ተቃዋሚዎች ዘንድ ተቀባይነት እንዳይኖራቸው ያደረገ እና አሜሪካ ማዕቀብ እንድትጥል አድርጎታል።

እንደሚታወቀው ሐማስ እ.አ.አ ጥቅምት 7 2023 እስራኤል ላይ ድንገተኛ ጥቃት አድርሷል፡፡ ይህን ተከትሎ እስራኤል  በጋዛ አጸፋዊ እርምጃ ከጀመረች በኋላ ኢራን ከእስራኤል ጋር የነበራት ድብቅ ጦርነት ወደ አደባባይ ወጥቷል። ባለፈው ሚያዝያ ወር እስራኤል በሶሪያ በሚገኘው የኢራን ኤምባሲ ግቢ ውስጥ በሚገኝ ህንፃ ላይ የአየር ድብደባ ካደረገች በኋላ ግጭቱ ይበልጥ ጎልቶ ታይቷል። በወቅቱ ኢራን ከአስርት ዓመታት ጠላትነት በኋላ የመጀመሪያውን ቀጥተኛ ጥቃት በእስራኤል ላይ ወስዳለች፡፡ ሁሉም ጉዳት ሳያስከትሉ ቢከሽፉም ከ300 በላይ ሰው አልባ አውሮፕላኖችን እና ሚሳኤሎችን ወደ እስራኤል ተኩሳለች፡፡

ኒውዮረክ ታይምስ እንደሚለው ራይሲ ይመሯት የነበረው ኢራን ሙስና እና ዓለም አቀፍ ማዕቀቦች ምጣኔ ሀብቷን አሽመድምደውባታል። ባለፉት ሁለት ዓመታት ሀገሪቱ በሀገር ውስጥ ህዝባዊ አመጽ ስትታመስ ቆይታለች፤  ምንዛሪዋም  አሽቆልቁሏል፡፡ በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት የውኃ እጥረቱ ከፍተኛ ነው፤ እንዲሁም በ1979 ኢስላማዊ ሪፐብሊክ ከተመሠረተ በኋላ ከፍተኛ ገዳይ የሽብር ጥቃት በሀገሪቱ ተባብሷል፡፡

በእንቅርት ላይ እንዲሉ የኢራን ፕሬዝዳንት እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በሄሊኮፕተር አደጋ መሞታቸው የሚገልጸው ዜና ሀገሪቱ ወደፊት ምን እንደሚፈጠር ድንጋጤ እና ስጋትን ፈጥሯል፡፡ ሆኖም ኢራን በሰኔ 28 ቀን ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ እንደምታካሂድ አስታውቃለች፡፡ የኢራን ተንታኞች እንዳሉት ምንም እንኳን የኢስላሚክ ሪፐብሊክ አገዛዝ መረጋጋት እና ህልውና አደጋ ላይ ባይሆንም ብዙዎች ቀጣዩ ፕሬዝደንት ማን ይሆን? በሚል ስጋት ውስጥ ገብተዋል።

ከሦስቱ የኢራን መንግሥት ዋና ዋና ቅርንጫፎች ሁለቱ ማለትም ፕሬዚዳንቱ እና ፓርላማ ያለ መሪ ናቸው፡፡ ሁለተኛ ዙር የፓርላማ ምርጫ ባለፈው ሳምንት ተካሂዶ የነበረ ቢሆንም አዲስ የፓርላማ አፈ-ጉባዔ አልተወሰነም። የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ሆሴን አሚር አብዶላሂን መሞታቸውም ኢራን ከአካባቢው አረብ ሀገራት ጋር የቅርብ ግንኙነት ለመፍጠር፣ ከእስራኤል ጋር ያለውን ሰፊ ግጭት ለመቆጣጠር እና ከአሜሪካ ጋር ቀጥተኛ ያልሆነ ውይይት ለማድረግ የጀመረችውን የዲፕሎማሲ እንቅስቃሴ ይረብሸዋል ተብሏል።

ሟቹ ፕሬዝደንት ራይሲ የአያቶላህ ካሜኔይ ተተኪ ለመሆን ከቀደሙት እጩዎች እንደ አንዱ ተደርገው ይወሰዱ ነበር፡፡ ስማቸው በጥሩ በማይነሳው  ራይሲ በርካቶች ጭካኔ የተሞላበት ግፍ እና የጭቆና ፖሊሲዎች ሰለባ ሆነዋል። የቀድሞ የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ከፍተኛ ባለስልጣን የነበሩት ዶ/ር ሞህሰን አሳዲ-ላሪ የሳቸው የጭካኔ ሰለባ ከሆኑት መካከል አንዱ ናቸው፡፡ ከራይሲ ሞት በኋላም “አንዳንድ ጊዜ አምላክ እንዲበቀልልህ መጠበቅ አለብህ” የሚል መልእክት በኢንስታግራም ገጻቸው ላይ አስፍረዋል።

የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ቃል አቀባይ ማቲው ሚለር በኢራን የአቪዬሽን ኢንዱስትሪ ላይ የተጣለው ማዕቀብ ለአደጋው ተጠያቂ መሆኑን የቀድሞ የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ያቀረቡትን ሀሳብ ውድቅ አድርገውታል።

ሚለር ለጋዜጠኞች እንደተናገሩት “በመጨረሻም የ 45 ዓመት ዕድሜ ያለው ሄሊኮፕተር ደካማ የአየር ሁኔታ ተብሎ በተገለጸው ጊዜ እንዲበር በተወሰነው ውሳኔ ተጠያቂ የሚሆነው የኢራን መንግሥት ነው” ሲሉ ለጋዜጠኞች ተናግረዋል።

እ.አ.አ. ከመስከረም 2022 ጀምሮ ሴቶች በጨዋነት እንዲለብሱ እና የራስ መሸፈኛ እንዲለብሱ የሚደነግገውን የሞራል ሕግ በመቃወም “ሴት ፣ ሕይወት ፣ ነፃነት” በሚል ኢራንን ለወራት ያመሰውን  የተቃውሞ እንቅስቃሴን ለማፈን ሞክረው  ነበር ። የራይሲ መንግሥት ተቃውሞውን በእስር እና በኃይል አፍነዋል። በሰልፉ ወቅት የመብት ቡድኖች በጥይት ተመትተው ተገድለዋል፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ የኢራን ጠቅላይ መሪ አያቶላ አሊ ካሜኒ የሀገሪቱ ፕሬዝዳንት ኢብራሂም ራይሲን ህልፈት ተከትሎ ለአምስት ቀናት የሚቆይ የሃዘን ቀን አውጀዋል። ቢቢሲ እንደዘገበው የ63 ዓመቱ ራይሲ ጠንካራ መስመር ያላቸው ሙስሊም ነበሩ፡፡ እ.አ.አ. በ2021 ፕሬዝዳንት ሆነው መመረጣቸው የወግ አጥባቂዎችን ቁጥጥር በሁሉም እስላማዊ ሪፐብሊክ ክፍል ላይ አጠናክሯል።

የፕሬዚዳንት ራይሲን ሞት ተከትሎ በርካታ ሀገራት ሀዘናቸውን የገለፁ ሲሆን የፓኪስታን ጠቅላይ ሚኒስትር ሼህባዝ ሻሪፍ ብሄራዊ የሀዘን ቀን በማወጅ  ራይሲን እና  አሚር አብዶላያንን “ ጥሩ ጓደኞች” ሲሉ ገልጸዋቸዋል።

የሕንድ ጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲ በማህበራዊ ሚዲያ ላይ  በሞቱት ሰዎች በጣም ማዘናቸውን እና መደናገጣቸውን ተናግረዋል። የቱርክ ፕሬዝዳንት ሬሲፕ ጣይብ ኤርዶጋን መንግሥታቸው ከኢራን ባለስልጣናት ጋር ሙሉ ግንኙነት እና ቅንጅት እያደረገ  እና አስፈላጊውን ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል።

የሩሲያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌ ላቭሮቭ ሀዘናቸውን ገልፀው ፕሬዚዳንቱ እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ እውነተኛ እና ታማኝ የሀገራችን ወዳጆች ናቸው” ሲሉ የቻይናው ፕሬዝዳንት ዢ ጂንፒንግ በበኩላቸው “ራይሲ ለኢራን ደኅንነት እና መረጋጋት አስተዋፅኦ አድርገዋል” ብለዋል። የአውሮፓ ኅብረት ልባዊ ሀዘኑን በአውሮፓ ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ቻርልስ ሚሼል በኩል ገልጿል፡፡

ሐማስ ሚስተር ራይሲን ለፍልስጤም ቡድን ጠንካራ ድጋፍ የያደርጉ እንደነበር የገለጸ ሲሆን በሊባኖስ የሚገኘው በቴህራን የሚደገፈው የሂዝቦላህ ንቅናቄ ሃዘን ላይ መሆኑን አሳውቋል። ሆኖም ኋይት ሀውስ ሟቹ ፕሬዝዳንት  ለአካባቢው የሽብር ኔትዎርኮች ድጋፍ በማድረግ ተጠያቂ እንደነበሩ እና ብዙ ደም በእጃቸው ላይ እንዳለ ተናግሯል።

የዋይት ሀውስ የብሄራዊ ደኅንነት ቃል አቀባይ ጆን ኪርቢ እንደተናገሩት የኢራኑ መሪ በገዛ ሀገራቸው ለደረሰው አሰቃቂ የሰብአዊ መብት ጥሰት ተጠያቂ ናቸው። “ለአብነትም  በመቶዎች በሚቆጠሩ ተቃዋሚዎች ላይ ለተፈፀመው እስር እና አካላዊ ጥቃት” ሲሉ  ኪርቢ ተናግረዋል።

በተያያዘም የፕሬዚዳንት ኢብራሂም ራይሲ ሄሊኮፕተር በሰሜን ምዕራብ ኢራን የመከስክስ ዜና ከተሰማ በኋላ አብዛኞቹ ኢራናውያን በማህበራዊ ሚዲያ ላይ  የድንጋጤ እና የአለማመን  ስሜቶች ነበሯቸው። እንዲሁም መሞታቸው ከተረጋገጠ በኋላ ተቃዋሚዎች የራይሲን ሞት “የምስራች” ብለው አከበሩ። እ.አ.አ. በ2022 “ሴት ፣ ሕይወት ፣ ነፃነት” የተቃውሞ እንቅስቃሴን በኃይል በማፈን እና እ.አ.አ በ1980ዎቹ መገባደጃ ላይ በፖለቲካ እስረኞች ላይ በተፈጸመው የጅምላ ግድያ ውስጥ በመሳተፋቸው በብዙዎች ተተችተዋል።

በፋርስ ማህበራዊ ሚዲያ ብዙ ቀልዶች እና አሽሙር አዘል አስተያየቶች እንዲሁም ከሁለት ዓመት በፊት የተገደሉ ወይም የተጎዱ ተቃዋሚዎች ፎቶግራፎች ሲንሸራሸሩ ነበሩ። አንዳንዶች ደግሞ ዜናውን በአደባባይ የሚያከብሩትን ለማውገዝ አልፎ ተርፎም ለማስፈራራት በማህበራዊ ሚዲያ ቀርበው ነበር።

የኢራን ጠንካራ ፕሬዝዳንት እጣ ፈንታ የኢራንን ፖሊሲ አቅጣጫ ያደናቅፋል ወይም እስላማዊ ሪፐብሊክን በማንኛውም ምክንያት ያደናቅፋል ተብሎ አይጠበቅም።

ነገር ግን  ወግ አጥባቂ ጽንፈኞች ሁሉንም የስልጣን ቅርንጫፎች የተመረጡ እና ያልተመረጡትን የሚቆጣጠሩበትን ስርዓት ይፈትናል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ በርካታ ሀገራት በፕሬዝዳንቱ እና በውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ሥርዓተ ቀብር ላይ ተወካዮቻቸውን ልከዋል፡፡ አንዳንዶች እጃቸውን ወደ አሜሪካ እና እስራኤል እየጠቆሙ ባሉበት ሰዓት ኢራን አደጋው እንዴት ሊደርስ እንደቻለ የማጣራት ሥራ ጀምራለች፡፡

(ሳባ ሙሉጌታ)

በኲር ግንቦት 19 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here