“ጎበዝ ተማሪ ባልሆንሁ ኖሮ እላለሁ” በሚል ከሰሞኑ ቢቢሲ አማርኛው ክፍል ‘የፒኤች ዲ’ ትምህርት በመከታተል ላይ ያሉ የዩንቨርሲቲ መምህራንን የድህነት አኗኗር አስነብቧል። ሮበርት ኪዮሳኪ ኤ ውጤት ያላቸው ለምን ‘ሲ’ ውጤት ባላቸው ተቀጣሪ ይሆናሉ በሚል መጽሐፍ ጽፏል። በሌላ አገላለጽ ሰነፉ የጎበዙ ቀጣሪ የሆነው ለምንድን ነው እንደማለት ነው።
በዓለማችንም ይሁን በሀገራችን ሀብት እና ጸጋ ያለው በትምህርታቸው ሰነፍ በሚባሉ ወይም ባልተማሩ ሰዎች እጅ ነው። ዶክተሩ እና ፕሮፌሰሩ የቤት ኪራይ መክፈል ይቸገራል። እንኳን የማህበረሰብ እና የሀገር ችግር ለመፍታት ቀርቶ ምሁራን የራሳቸውን ችግር መቅረፍ ሲሳናቸው እያየን ነው። ለምን?
አንዲት ባልደረባዬ ከዓመት በፊት ያጫዎተችኝ ነው። “ወደ ቢሮ ስገባ አንድ መኪና ድንገት ከፊቴ ቆመ። ‘እትዬ’ ብሎኝ አንድ ወጣት ለምስጋና ከመኪናው ወረደ። ‘እትዬ ያን ጊዜ የቤት ሥራ አልሠራህም ብለሽ ባታባርሪኝ ኖሮ እዚህ አልደርስም ነበር፤ አመሰግናለሁ’ ብሎኝ አቀፈኝ” ብላ አጫዎተችኝ። ከዓመታት በፊት በስንፍናው ከክፍል ያባረረችው ልጅ ነው ዛሬ አድጎ፤ የገንዘብ ነጻነቱን አረጋግጦ ያመሰገናት። ሰነፉ ተማሪ የሚሠራለትን የገንዘብ መንገድ ተጠቅሞ ጥሩ ኑሮ መኖር ችሏል። እንዴት? የሮበርት ኪዮሳኪን መጽሐፍ ትኩረት አድርገን እንነጋገርበት።
ሮበርት ይህንን መጽሐፍ ለማዘጋጀት ሲያስብ ወደ አዕምሮው ደጋግሞ የሚመላለስ ሐሳብ ነበር። “በትምህርት ቤት ቆይታችን ለምንድን ነው ስለገንዘብ ያልተማርነው፤ “መምህራችን ሥራ ለማግኘት መማር አለባችሁ። ካልተማራችሁ ጥሩ ሥራ አታገኙም’ በማለት በተደጋጋሚ ይነግረን ነበር” በማለት ሮበርት ያስታውሳል። ጉዳዩ ሥራ ለማግኘት ከሆነ ለምንድን ነው ስለ ገንዘብ በቀጥታ የማይነገረን ሲል ይጠይቃል። አሜሪካዊያን አሁን ሥራ ፈጣሪዎች መሆን ነው የሚፈልጉት።
የዓለም ትምህርት ሥርዓታችን ግን ልጆችን ተቀጣሪ ስለ ማድረግ ነው የሚያስበው። ለዚህ ነው መምህራንም ልጆችን “ጥሩ ሥራ ማግኘት ከፈለጋችሁ ወደ ትምህርት ቤት ሂዱ” የሚሉት ይላል። ሥራ ፈጣሪ ለመሆን የሚያስችሉ ክህሎቶችን የትምህርት ተቋማት አያስተምሩም።
ይልቁንስ ተቀጣሪ መሆን የሚያስችሏቸውን ተመሳሳይ እውቀቶች ይሰጧቸዋል እንጂ። ሮበርት የሰዎች የሥራ ፈጣሪነት እና ተቀጣሪነት እሳቤ መነሻው የገንዘብ እውቀት ማጣት ነው ይላል። ብዙዎች የገንዘብ እውቀት ስለሌላቸው መቀጠርን ይመርጣሉ። ሥራዬን ባጣስ የሚል ፍርሀት ውስጥ ይወድቃሉ ብሏል። በዚህም ሥራ ፈጠራን ሲያስቡ ገና መፍራት ይጀምራሉ።
የቢዝነስ አስተዳደር ምሁራን “አንድን ትልቅ ተቋም እንዴት ማስተዳደር ትችላላችሁ የሚለውን እንጂ ከምንም ተነስታችሁ የግላችሁን ድርጅት እንዴት መመስረት እንደምትችሉ አያስተምሯችሁም” ይላል።
የትምህርት ሥርዓቱ ልጆች አካዳሚሽያን እና የቢሮ ሠራተኞች እንዲሆኑ እንጂ ካፒታሊስት (ሥራ ፈጣሪዎች) እንዲሆኑ አያስተምራቸውም ነው የሚለው ሮበርት። በካፒታሊዝም የእሳቤ ብርሃን አልፈው ሥራ የሚፈጥሩት ሰነፍ ተማሪዎች ‘C’ ውጤት ያላቸው ቢሆኑም እንኳን ትምህርቱ ግን ተቀጣሪ ማፍራት ላይ ትኩረት ያደረገ ነው። ስቲቭ ጆብስ፣ ቶማስ ኤዲሰን፣ ዋልት ዴስኒ፣ ማርክ ዙከርበርግ ሥራ ፈጣሪዎች ናቸው። ኤዲሰን እና ዴስኒ ከፍተኛ ትምህርት እንኳን አላጠናቀቁም። ጆብስ እና ዙከርበርግ ደግሞ ኮሌጅ አላጠናቀቁም። ከስመ ጥር ኮሌጆች እና ዩኒቨርሲቲዎች የሚመረቁ ‘A’ ውጤት ያላቸው ተማሪዎች ግን የሚቀጠሩት ትምህርታቸውን ባላጠናቀቁ ሥራ ፈጣሪዎች ድርጅት ውስጥ ነው። ሰነፍ ተማሪዎች ጎበዝ ተማሪዎችን የሚበልጧቸው ለምን ነው? ጎብዞች የማያደርጉትን በማድረግ ነው። ሮበርት ዓለም የገጠማት የገንዘብ ቀውስ አይደለም ይልና ቀውሱ የገንዘብ ትምህርት ማጣት ቀውስ ነው ይላል። “ቀውሱም ልጆች ትምህርት ቤት ሲገቡ፤ ዓመታትን ሲያሳልፉ፤ ምናልባትም አሥርት ዓመታትን ፤ስለ ገንዘብ እውቀት ያለው ሰው ሳያስተምራቸው መቀጠላቸው ነው። መምህራን የኀጢዓት ሁሉ ስር ገንዘብ መውደድ ነው ብለው የሚያምኑ ናቸው። “ሕዝብ የገንዘብ እውቀት ከማጣት የተነሳ እየጠፋ ነው” ይላል ሮበርት ኪዮሳኪ። የትምህርት ሥርዓቱ ልጆች ገንዘብ እንዲሰሠሩ ከማድረግ ይልቅ እንዲያገኙ፤ ከሀብታም ወስዶ ለደሀ እንደ መስጠት ያለ ስለመሆኑ ጽፏል። ይህም በውጤቱ እጅ ጠባቂ እና በርካታ ቁጥር ያለው ደሀ ሕዝብ እንዲፈጠር አድርጓል።
የዘመን ለውጥ በገንዘብ አረዳዳችን ላይ መከሰቱን አልተረዳንም የሚለው ሮበርት በቀደመው ዘመን መማር፣ ሥራ መያዝ፣ ጠንክሮ መሥራት እናም ጡረታ መውጣት የተለመደ እንደነበር ይናገራል። ቤት ሠርቶ በቀላሉ መኖር ይቻል ነበር። አሁን ግን ይሕ ተረት ሆኗል። አሁን የትምህርት ዋጋው ከብዷል፣ ሥራ ማግኘት ራስ ምታት ሆኗል፣ በአንድ ደመወዝ መኖር አይቻልም። ቤት መሥራት የብዙዎች የሕይወት ዘመን ግብ ሆኗል።
የወጣት ምሩቃን ሥራ አጥነት ዓለም አቀፍ ጉዳይ ነው። ሮበርት የትምህርት አረዳዳችን መለወጥ አለበት በማለት ኮሌጅ ያላጠናቀቁ ዓለምን የቀየረ ፈጠራ ያበረከቱ 50 ሰዎችን ዝርዝር አስቀምጧል። እነዚህ ሰዎች ማህበረሰቡ ትክክል ብሎ ከሚያምንበት ትምህርት ሥርዓት በመውጣት በግላቸው ተጉዘው ለውጤት የበቁ የላቀ አዕምሮ ያላቸው ናቸው። የአሜሪካው ፕሬዝደንት ጆርጅ ዋሽንግተን፣ አብርሃም ሊንከን፣ የእንግሊዙ ጠቅላይ ሚኒስትር ዊንስተን ቸርችል፣ ራይ ክሮክ የማክዶናልድ በርገር መስራች፣ የሲኤንኤን ሚዲያ መሥራች ቴድ ቴርነር፣ የዓለም አሳሹ ክርስቶፈር ኮለምበስ፣ የፌራሪ መኪና መስራች ኤንዞ ፌራሪ፣ የፎርድ መኪና አምራች ባለቤት ሄነሪ ፎርድ፣ የአፕል መስራች ስቲቭ ጆብስ፣ የፌስቡክ ባለቤቱ ማርክ ዙከርበርግ እና የማይክሮሶፍት ባለቤቱ ቢልጌትስን በማሳያነት ይጠቅሳል።
“ትምህርት አይጠቅምም አይደለም የምላችሁ። ምን ዓይነት ትምህርት ነው የምትማሩት? የልጆቻችሁ ትምህርት የት ነው የሚያደርሳቸው፤ ለወደፊት ሕይወት የሚያዘጋጃቸው ነው ወይ፤ የገንዘብ ዋስትና በሌለበት ዓለም የሚኖረው ልጃችሁን የሚያግዝ ትምህርት እያገኘ ነው ወይ ነው? የምላችሁ” ሲል ሮበርት ይጠይቃል።
የሮበርት መጽሐፍ ልጆች በመንግሥት ጡረታ መተማመን እንዳይጀምሩ፣ ትምህርት ቤት የማይማሩትን የገንዘብ እውቀት ስለ መስጠት ነው። ለባለሀብቶች ተቀጥረው ከመሥራት ይልቅ በራሳቸው ባለሀብት መሆን ስለሚችሉበት ጥበብ ነው የሚያወራው።
በቀደመው ዘመን ሁለት ዓይነት ትምህርቶች ነበሩ የሚለው ሮበርት አካዳሚያዊ እና ሙያዊ ትምህርቶችን ይጠቅሳል። አካዳሚያዊ ትምህርት ማንበብ፣ መጻፍ፣ ሒሳብ መሥራት የመሳሰሉ አጠቃላይ ክህሎቶችን ለማስጨበጥ ይሰጣል። ሙያዊ ትምህርት ደግሞ ለመኖር የሚያስችሉ ክህሎቶችን የሚሰጥ ነው። በዚህ ያለፉ ጎበዝ ተማሪዎች ዶክተር፣ አካውንታንት፣ ኢንጅነር፣ ጠበቃ፣ የቢዝነስ ሥራ አስፈጻሚዎች ሆነው ይቀጠራሉ።
ሮበርት በትምህርት ሥርዓታችን ውስጥ የለም የሚለውን አዲስ የትምህርት ዓይነት “የገንዘብ ትምህርት” ዓይነት ሲል በሦስተኛነት አስቀምጦታል። የወደፊቱ የትምህርት ዓይነትም ይህ ነው ይላል። ወላጆች ገንዘብን በቤታቸው ውስጥ የመነገገሪያ አጀንዳ ሊያደርጉት እና በሕይወት ላይ ያለውን ሚና ለልጆች ማሳየት አለባቸው ይላል። ‘ኤ’ ውጤት ያላቸው ተማሪዎች ምርጥ ሥራዎችን ለማግኘት ጥረት ያደርጋሉ።
በውጤታቸው ተመርጠው፣ ተወዳድረው ይቀጠራሉ። ’ሲ’ ዎቹ ደግሞ ውጤታቸው አሪፍ ሥራ ለመቀጠር አያስችላቸውም። ምርጫ የላቸውም። በራሳቸው ተጣጥረው ሥራ ፈጥረው መኖር አለባቸው። ’ኤ’ ተማሪዎች በትምህርት ሥርዓቱ ተቀርጸዋል። ሥርዓቱን ይቀበሉታል። አንድ ነገር ላይ ትኩረት አድርጉ ይላቸዋል። ዶክተር ወይም ጠበቃ እሆናለሁ ብለው ያድጋሉ። አንድ መስመርን ተከትለው ይማራሉ። የትምህርት ቤቱ ሥርዓት ጋር ስምሙ ናቸው። ለመቀጠር ራሳቸውን ያዘጋጃሉ። የ’ሲ’ ተማሪዎች የትምህርት ሥርዓቱ የሚላቸውን አይቀበሉም። አንድ ነገር ላይ ትኩረት አያደርጉም። ውጤታቸው አናሳ ነው። ጠበኞች ናቸው። የሚሏቸውን አይቀበሉም። በራሳቸው ፈጠራ መኖርን ይመርጣሉ። የ ’ሲ’ ውጤት ተማሪዎች በሥራ ፈጠራ እና ሥርዓት መፍጠር ያምናሉ። በሂደቱም የ’ኤ’ ተማሪዎችን መቅጠር የሚችሉበትን ሥራ እና ሥርዓት ይፈጥራሉ።
የ ‘ኤ’ ውጤት ተማሪዎች በትምህርት ቤት ቆይታቸው ምርጥ ሊሆኑ ይችላሉ። የግላቸውን ሥራ ለመጀመር ግን ወኔ እና ፍላጎት የላቸውም። ትምህርት ቤት የሚሄዱት በአንድ ጉዳይ ላይ ስፔሻላይዝ ለማድረግ ነው። ሽያጭ፣ ሕግ፣ ሕክምና፣ ግብይት፣ አካውንቲንግ እና መሰል ሙያዎችን በልዩነት ያጠናሉ።
ለደሞዝ መሥራትን ያውቁበታል። ገንዘብ የሚያስገኝላቸውን ሥራ በግላቸው መሥራት አይችሉም። ጥሩ አዕምሯ ቢኖራቸውም እንኳን ልባቸው እሽ አይላቸውም። ኀላፊነትን ለመውሰድ በጣም ይፈራሉ። ካልከፈሏቸው አይሠሩም። ተጨማሪ ሥራ ሲሠሩ ተጨማሪ ገንዘብ የሚጠይቁ ናቸው። ክፍያ ካልሰጧቸው እረፍት ይጠይቃሉ። ነገሮችን በለመዱት መልኩ መከወንን ይመርጣሉ። መሳሳትን አይመርጡም፤ ቢሳሳቱ እንኳን ለውድቀታቸው ኀላፊነትን አይወስዱም። ሌሎችን ተጠያቂ ማድረግ ይቀናቸዋል። የተቀጠሩበት ድርጅት ቢከስር፣ እዳ ውስጥ ቢገባ፣ ቢመሰቃቀል፣ ቢዘጋ ብዙ አይጨነቁም። ሌላ ተቋም ውስጥ ለመቀጠር ሥራ መፈለግ ይጀምራሉ። በ’ኤ’ እና ‘ሲ’ ተማሪዎች መካከል ያለው ልዩነት ይህ ነው የሚለው ሮበርት፤ የ’ቢ’ ውጤት ተማሪዎች በመንግሥት ተቋማት እና አሠራሮች ውስጥ የሚቀጠሩ ናቸው ብሏል። በፓለቲካው ዘርፍ በልማት ድርጅቶች ውስጥም አሉ ይላል።
’ኤ’ እና ’ቢ’ ውጤት ያላቸው ተማሪዎች ኢንቨስትመንት እና ታላላቅ ኩባንያዎች ባሉበት አደጋዎች በሚጠበቁበት እና ኀላፊነቶችን መውሰድ በሚያስፈልግባቸው ሁኔታዎች ውስጥ መሥራትን አይመርጡም። ፈጣን እና ተለዋዋጭ አደጋዎችን ለመመከት ኀላፊነትን ለመውሰድ ይፈራሉ። የሥራ ዋስትና እና ቋሚ ደሞዝ ክፍያ ማግኘትን እንደ ትልቅ ቁም ነገር ይቆጥሩታል። የኮሌጅ ወይም የዩንቨርሲቲ ዲግሪ አላቸው። ግን ምንም ሀብት የላቸውም። ንብረት እና ምርት አይኖራቸውም። ዋስትና፣ ጥቅማ ጥቅም እና የጡረታ ዘመን እቅድ ቢኖራቸው አይፈረድባቸውም ይላል ሮበርት።
ሮበርት በተደጋጋሚ የሚኮንነው የደሀ አባት ምክር የሚለውን ሐሳብ ነው። ደሀ አባቶች በቢዝነስ አስተዳደር ማስተርስ ዲግሪ አላቸው።
ትምህርት እና እውቀት አያንሳቸውም። ነገር ግን መነሻቸው ትምህርት እና መዳረሻቸው ደግሞ ተቀጣሪነት ወይም አነስተኛ ከእጅ ወደ አፍ የግል ሥራ ነው። በአንጻሩ ሀብታም አባቶች በቀናት ስልጠና ክህሎት ቀስመው የትላልቅ ኩባንያዎች መስራች ወይም ኢንቨስተሮች ይሆናሉ። ‘ኤ’ እና ’ቢ’ ዎች አሠራሮችን ይቀበላሉ። ጠንካራ ሠራተኞች ናቸው። ቶሎ ለመማር አይቸገሩም። ከተዘረጋላቸው መስመር መውጣት አይችሉም። በተሠራ ሲስተም ውስጥ ጠንካራ ሠራተኞች ናቸው። ከሲስተም ውጪ መስራትም ሆነ ማሰብ አይችሉም። ሲስተሙንም መለወጥ አይችሉም።
… ይቀጥላል
(አቢብ ዓለሜ)
በኲር ጥቅምት 11 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም