የ2024 የዓለማችን ስጋቶች

0
218

በያዝነው የአዉሮፓዊያን ዘመን (በ2024) ወደ 300 ሚሊዮን የሚጠጉ ሰዎች ሰብአዊ እርዳታ እና ጥበቃ ያስፈልጋቸዋል ተብሏል። የተባበሩት መንግሥታት እና አጋር ድርጅቶች በ72 ሀገሮች ውስጥ በጣም የተቸገሩ 181 ሚሊዮን ሰዎችን ለመርዳት ዓላማ እንዳላቸው ከሰሞኑ አስታውቀዋል::  ድርጅቶቹ እንዳስታወቁት ምሥራቅ እና ደቡብ አፍሪካ ከፍተኛ የተቸገሩ ሰዎች ቁጥር ያሉባቸው ቀጣናዎች ናቸው። ሪሊፍ ዌብ ላይ ያገኘነው መረጃ እንደሚያትተው ደግሞ እነዚህን የተቸገሩ ሰዎች ለመርዳት 46 ነጥብ አራት ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር ያስፈልጋል።

ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ግጭቶችና ሰብዓዊ ቀውሶች እየበዙና እየጠነከሩ መጥተዋል። እ.አ.አ. በ2023 የሰብአዊ መብቶች እና የሰብአዊ ሕግ ጥሰቶች ተባብሰዋል። በመሆኑም በሚቀጥሉት ዓመታት ግጭቶች፣ የአየር ንብረት ቀውሱ ተፅዕኖ እና የምጣኔሀብት ፍትሃዊነት ጥያቄዎች ለሰብአዊ መብቶች ችግር መባባስ ዋና መንስኤ ሆነው ይቆያሉ። እነዚህ መንስኤዎችም የመፈናቀል ማዕበልን ይቀሰቅሳሉ። የገቢ እና አስፈላጊ አገልግሎቶችን እንደ ጤና እና ውኃ ያሉ ተደራሽነትን ይቀንሳልም ነው የተባለው።

የግጭት ጥንካሬ ከጊዜ ወደ ጊዜ እንደጨመረ የተገለጸ ሲሆን በተያዘው የአውሮፓዊያን የዘመን ቀመር አሃዙ በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ፣ በፍልስጤም፣ በሳህል እና በሱዳን ግጭቶች ምክንያት የበለጠ አሳሳቢ ይሆናል። እነዚህ የትጥቅ ግጭቶች ከዚህ ቀደም ታይቶ በማይታወቅ ደረጃ የተጋላጭነት እና የሰው ልጅ ስቃይ እየፈጠሩ ነው።

ሰብዓዊ እርዳታ እና ጥበቃ ያስፈልጋቸዋል ተብለው ከተለዩት መካከልም 53 ነጥብ ስምንት ሚሊዮን ሰዎች በመካከለኛዉ ምሥራቅ እና በሰሜን አፍሪካ  እርዳታ ያገኛሉ። 74 ነጥብ አንድ ሚሊዮን ሰዎች ደግሞ በምስሥቅ እና በደቡብ አፍሪካ የሚገኙና ሰብዓዊ እርዳታ ያሚያስፈልጋቸው ናቸው። በሱዳን ያለው ቀውስ ከዚህ አጠቃላይ 40 በመቶውን ይይዛል።

በሶሪያ እና በአጎራባች ሀገሮች 32 ነጥብ አምስት ሚሊዮን ሰዎች እርዳታን ይሻሉ። በእስያ እና በፓስፊክ ውቅያኖስ ውስጥ 50 ነጥብ ስምንት ሚሊዮን ሰዎች የተቸገሩ ሲሆን ከእነዚህ ውስጥ 30 ነጥብ ስድስት ሚሊዮን የሚሆኑት በአፍጋኒስታን ቀውስ ምክንያት ለችግር የተጋለጡ ናቸው።

እንደ ሪሊፍ ዌብ መረጃ በ2023 አጋማሽ ከ110 ሚሊዮን በላይ ሰዎች በግጭት በግዳጅ ተፈናቅለዋል። 57 በመቶ የሚሆኑት በተለያዩ ሀገራት የሀገር ውስጥ ተፈናቃይ ናቸው።

በሱዳን ብቻ ጦርነቱ ከተጀመረበት እ.አ.አ. ሚያዚያ 2023 ጀምሮ ከስድስት ሚሊዮን በላይ ሰዎች በግጭቱ ተፈናቅለዋል:: ይህም በዓለም ላይ ትልቁ የሀገር ውስጥ የመፈናቀል ቀውስ ነው።

ከግጭት እና ከሁከት በተጨማሪ የተፈጥሮ አደጋዎችም ለውስጥ መፈናቀል ምክንያት ሆነዋል። ለአብነትም እ.አ.አ. በ2022 በተፈጥሮ አደጋ ምክንያት 32 ነጥብ ስድስት ሚሊዮን የሀገር ውስጥ መፈናቀል ስለመከሰቱ ሪፖርት ተደርጓል::

ይህ በእንዲህ እንዳለ እነዚህን ችግሮች ለመፍታት የሚሠራው ሥራ አጥጋቢ አይደለም ነው የተባለው:: የሰብዓዊ እርዳታ ሠራተኞች ተደራሽነታቸው እየቀነሰ ነው:: የእርዳታ ሥራቸውን በሚያከናውኑበት ጊዜም ሁከት እና የደህንነት እጦት ይገጥማቸዋል:: ይህ ሁኔታ ለሰብዓዊ ሥራዎች የሚያስፈልገውን ወጪ ከፍ አድርጎታል። ተጋላጭ የሆኑትን ሕዝቦች ለመድረስም አስቸጋሪ ሆኗል::

ለጋሾች በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የተገለጹትን ፍላጎቶች ለማሟላት የሚያስፈልጋቸውን ሀብት ማቅረብ አልቻሉም:: ይህም ግጭቶችና አደጋዎች እየተባባሱ ከመሄዳቸው ጋር ተዳምሮ በምግብ ወይም በመጠጥ ውኃ እጦት ምክንያት ሕዝቡ ለበሽታ እና ለረሃብ አደጋ ተጋላጭነቱ የመባባስ ስጋቱ ከፍ ብሏል። የበለጠ ከባድ መዘዝ ሊከተልም ይችላል።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ ጉዳዮች ምክትል ዋና ፀሐፊ እና የአደጋ ጊዜ እርዳታ አስተባባሪ ማርቲን ግሪፊዝ የ2024 የዓለም የሰብዓዊነት ዕይታን ይፋ ባደረጉበት ወቅት እንደተናገሩት የተባበሩት መንግሥታት እና የሰብዓዊ ድርጅቶች በ2024 ወደ 300 ሚሊዮን የሚጠጉ ሰዎች ሰብዓዊ እርዳታ ይፈልጋሉ። ከዚህ  ውስጥ 181 ሚሊዮን የሚሆኑትን ለመርዳት ዕቅድ እንዳላቸው አስታውቀዋል።

የትጥቅ ግጭት ለከፍተኛ ረሃብ፣ የምግብ ምርት መቋረጥ፣ አስፈላጊ መሠረተ ልማቶች እና አገልግሎቶች እንዲሁም የገቢ ተደራሽነትን በመግታት ለችግሩ መባባስ ግንባር ቀደም መንስኤ ናቸው። እ.አ.አ.  በ2024 በተለይ አምስት ሀገሮች (ቡርኪናፋሶ፣ ማሊ፣ ፍልስጤም ራስ ገዝ አስተዳደር፣ ደቡብ ሱዳን እና ሱዳን) ተጋላጭ ተብለው ተለይተዋል::

በተባበሩት መንግሥታት የሰብአዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ፅሕፈት ቤት የኦፕሬሽን ዳይሬክተር ኤደም ዎሶርኑ በሁሉም እርምጃዎች  የሰብአዊ ፍላጎቶች መጠን፣ የተፈናቀሉ እና ረሃብን የተጋፈጡ ሰዎች ቁጥር ሱዳንን በቅርብ ጊዜ ከሚታወሱት አስከፊ ሰብአዊ አደጋዎች ከተከሰቱባቸው አንዷ አድርጓታል ብለዋል:: ግጭቱ “በቀላሉ የሱዳንን ሕዝብ እያሳጣን ነው” ሲሉ የሕዝቡን ተስፋ መቁረጥ ገልጸዋል።

አልጀዚራ እንደዘገበው ከሆነ በሱዳን እየተካሄደ ያለው የእርስ በእርስ ጦርነት ተባብሶ ቀጥሏል። በመጋቢት ወር መጀመሪያ ላይ የፀጥታው ምክር ቤት በረመዳን ጾም ወቅት አፋጣኝ የተኩስ ማቆም ጥሪ አቅርቦ ነበር። እንዲሁም በዚህ ተኩስ የማቆም ጥሪ ዜጎች የተሻለ ሰብዓዊ እርዳታ ማግኘት እንዳለባቸው አሳስቦ ነበር።

ሆኖም በተፋላሚ ወገኖች መካከል በተፈጠረ አለመግባባት የተኩስ አቁም ስምምነቱ እውን ሊሆን አልቻለም። አልጀዚራ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትን ዋቢ አድርጎ እንደዘገበው በሱዳን ጦርነት ከ18 ሚሊዮን በላይ ሱዳናውያን ለከፋ የምግብ ዋስትና እጦት ተዳርገዋል:: 730 ሺህ ሱዳናውያን ህጻናትም በከፍተኛ የምግብ እጥረት እየተሰቃዩ ነው።

በተመሳሳይ እስራኤል – ሃማስ ጦርነት  በጋዛ የሚገኙ ፍልስጤማዊያን ለከፍተኛ ረሃብ እንዳጋለጣቸው የዓለም ጤና ድርጅት አስታውቋል:: ጦርነቱ ተባብሶ የመቀጠል ምልክቶች እያሳየ ሲሆን እስራኤል በዓለም አቀፍ የአቅርቦት ሰንሰለት ውስጥ ትልቅ ሚና ትጫወታለች። በመካከለኛዉ ምሥራቅ ወሳኝ የንግድ ማዕከል በመሆኗም ጦርነቱ እያሳደረ ያለው አሉታዊ ተጽዕኖ እየበረታ ነው። በንግድ መረቦች እና በሸቀጦች ገበያዎች በኩልም በዓለም ምጣኔሀብት ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ አሳድሯል::

በእስራኤል ዙሪያ ያለው የባሕር ዳርቻ አስፈላጊ የዓለም የንግድ መስመር ነው። የግጭቱ ቀጣይነት ታዲያ በባሕር ዳርቻ ትራንስፖርት ላይ የመስተጓጎል ስጋትን ከፍ እንደሚያደርግ እና የመርከብ ወጪን ማሳደጉ አይቀሬ ነው።

መካከለኛው ምሥራቅ ከዓለም የነዳጅ አቅርቦት ምንጮች አንዱ ነው። ጦርነቱ ታዲያ በቀጣናው  የነዳጅ ምርት እንዲስተጓጎል እና የዓለም የነዳጅ አቅርቦትን በመቀነስ ለነዳጅ  ዋጋ ንረት ሊዳርግ ይችላል ሲል ከዩሮፓርል (www.europarl.europa.eu) ድረ ገጽ ያገኘነው መረጃ ያትታል::

ሌላው በ2024 ዓለማችንን ይፈትናታል ተብሎ የሚጠበቀው እና እየፈተናት የሚገኘው የቀይ ባሕር ውጥረት ነው:: እንደ ኦፍሾር ቴክኖሎጂ (offshore.com) መረጃ ከሆነ የዓለማችን ትላልቅ የመርከብ አጓጓዥ ድርጅቶች ሀውቲ በተሰኘው የየመን ታጣቂዎች የሚያደርሱትን ጥቃት ተከትሎ በቀይ ባሕር ላይ የሚያደርጉትን ጉዞ እያቋረጡ ይገኛሉ:: ወደ እስራል  ያቀናሉ ብለው ያመኑባቸው መርከቦች ላይም ጥቃት እየፈጸሙ ነው::

የእስያን፣ የአውሮፓን እና የአፍሪካ አሕጉራትን በዋነኛነት የሚያስተሳስረው ቀይ ባሕር በየዓመቱ በቢሊዮን ዶላር የሚያወጡ ሸቀጦችን እና የነዳጅ አቅርቦትን ያስተናግዳል። ከ12 በመቶ በላይ የዓለም ንግድ የሚካሄድበት ቀይ ባሕር ኢትዮጵያን ጨምሮ ለበርካታ ሀገራት የደም ሥር ነው::

ይህ ሰርጥ በአሁኑ ወቅት የዓለም የፖለቲካ ትኩሳት ሆኗል:: እ.አ.አ. ጥቅምት 7 ቀን 2023 የጀመረው የእስራኤል – የሀማስ ጦርነት በአካባቢው የሚገኙ ሀገራት ታጣቂ ኃይሎች  በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ  መንገድ እንዲሳተፉ አድርጓቸዋል:: ከተሳታፊ ኃይሎች መካካልም የሊባኖሱ ይዝቦላህ እና በኢራን የሚደገፈው የየመኑ ታጣቂ ኃይል የሀውቲ ቡድን ይገኙበታል:: የየመኑ የሀውቲ ታጣቂዎች ካለፈው ሕዳር ወር ጀምሮ በቀይ ባሕር የሚመላለሱ የዕቃ እና የነዳጅ ጫኝ መርከቦች ላይ ጥቃት በማድረስ ጉዳት እያደረሱ ይገኛሉ።

በየመን ሀውቲዎች በተቀሰቀሰው የቀይ ባሕር ውጥረት ምክንያት አሜሪካ እና እንግሊዝ በታጣቂዎች ላይ የአጸፋ እርምጃ እየወሰዱ ነው። በዚህም ምክንያት ኩባንያዎች መርከቦችን ወደ ሌላ አቅጣጫ ቀይረው የመላክ ሥራ ጀምረዋል።

በቅርብ ጊዜ በቀይ ባሕር ውስጥ ያለው ውጥረት በዓለም የነዳጅ እና የጋዝ እንዲሁም የመርከብ ገበያ ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ አሳድሯል:: የማጓጓዣ ወጪም ጨምሯል:: እንዲሁም ሸቀጦች ዘግይተው እንዲደርሱ አድርጓል።

መርከቦች ቀይ ባሕርን ከማለፍ ይልቅ አሁን በአፍሪካ እና በኬፕ ኦፍ ጉድ ሆፕ ዙሪያ ረዘም ያለ መንገድን ይጓዛሉ:: ይህም በጉዞ ጊዜያቸው ከበፊቱ ከሰባት እስከ 20 ቀናት ይጨምራል::

ሌላው ዓለማችንን የሚያሰጋት የአየር ንብረት ቀውስ እንደሆነ ሪሊፍ ዌብ ያትታል:: እንደ ጎርፍ፣ ድርቅ እና አውሎ ነፋስ ያሉ አስከፊ የአየር ሁኔታ ክስተቶች ጉዳታቸው የሚያይለው በድሃ ሀገራት ውስጥ ባሉ ሕዝቦች ነው። የአየር ንብረት ቀውስ የሰብአዊ ፍላጎቶችን ያባብሳል:: የግጭት አደጋን ይጨምራል:: መፈናቀልን ያስከትላል፤ የምግብ ዋስትና እጦትን ያባብሳል። የሕዝብ ጤናን አደጋ ላይ ይጥላል። ድርቅ እና የጎርፍ መጥለቅለቅን ሊያስከትል ይችላል።

ከባድ የአየር ሁኔታ ክስተቶች እንደ ተቅማጥ እና ኮሌራ ያሉ ተላላፊ በሽታዎች እንዲስፋፉ በማድረግ የውኃ እጥረት፣ የአካባቢ ጽዳትና የግል ንፅህና አጠባበቅ ሥርዓትን ያስተጓጉላሉ። ለአብነትም ከኮሌራ ጋር በሚደረገው ትግል ከዐሥር ዓመታት በኋላ በሽታው እያገረሸ ነው። ባለፉት ሁለት ዓመታት ገዳይ ወረርሽኞች መከሰታቸውም ተጨማሪ ማሳያ ነው።

ኤልኒኖ በብዙ የዓለም ክፍሎች የግብርና ምርትን ይቀንሳል ተብሎ ይጠበቃል። ይህ ደግሞ የምግብ እና የተመጣጠነ ምግብ እጥረት በመጨመር በሽታን የመከላከል አቅምን በማዳከም ሰዎችን ለበሽታ ተጋላጭ ያደርጋል።

(ሳባ ሙሉጌታ)

በኲር መጋቢት 16 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here