የአድዋ ተራሮች ስር ሀገርን ላለማስደፈር የተደረገውን ትንቅንቅ፣ የጦርነቱን ድባብ የጀግኖች አፅም ለአፍታ ህያው ሆኖ ታሪክ ቢነግሩን ምንኛ አሁን ከተደመምነው ይበልጥ ያስደምሙን። ይሁን ግዴለም ጀግኖቻችን ባሉበት በሰላም ይረፉ አልቀሰቅሳቸውም፣ ከመቃብር በላይ ህያው የሆነውን ደማቁን ታሪካቸውን እጠይቀዋለሁ።
ጥቁርነትን ንቆ፣ የሰውን መሬት ለመዝረፍ፣ በእብሪት የኢትዮጵያን ምድር ከምፅዋ ጀምሮ ቀስ በቀስ ሲንኳተት ኤርትራን አልፎ አድዋ ደረሰ። ትዕግስትን እንደ ፍርሃት ቆጠረው። አድዋ ሆ ብለው የወጡት የኢትዮጵያ ጀግኖች ወራሪውን ጣሊያን በአንድ ጀምበር አጠናቀቁት። የአድዋ ተራሮች በኢትዮጵያ አርበኞች ጀግንነት ተንቀጠቀጡ፣ ዘመናዊው የጣሊያን ጦር በአልበገሬዎች መግቢያ መውጫ ጠፍቶት ሲጨነቅ፣ የጣሊያን ጄኔራሎች ወደቁ።
የጣሊያንን መሸነፍ የሰማው የዓለም ሕዝብ እጁን በአፉ ጫነ። አፍሪካን ያዋረደው ቅኝ ግዛት በአድዋ ተዋረደ። አውሮፓውያን በአሳፋሪው የጣሊያን ሽንፈት አንገታቸውን ደፉ። የኢትዮጵያውያን ጀግንነት በዓለም ዝናው ናኘ፣ ጥቁሮች በኢትዮጵያ ድል ተነቃቅተው ለነፃነት ትግል እንዲፋለሙ ትልቅ የወኔ ስንቅ ሆነላቸው። ኢትዮጵያ ከዓለም ሀያላኑ ጋር ነፃ እና ሉዓላዊት ሀገር ሆና እውቅና በማግኘት በመንግሥታቱ ማህበር አባል ሆነች። ይህ ለጣሊያን እና ለአጋሮቿ ባይዋጥም እየመረራቸውም ቢሆን መቀበል ግዴታ ነበር።
አሳፋሪው የአድዋ ሽንፈቷ ጣሊያንን ለአያሌ ችግሮች ዳርጓታል። ሕዝባዊ ተቃውሞ አስነስቶ የወቅቱን ጠቅላይ ሚኒስትር ክሪስፒን ከመንበሩ አስወግዷል። ከሊቢያ ጋር የነበረው ጦርነት ትንፋሽ አሳጥቷታል። በኤርትራ እና ሶማሊያ የቅኝ ግዛት ይዞታዋ ብዙም የሚያስደስት ጥቅም አላገኘችበትም። ኢትዮጵያ በዓይናቸው ላይ ቀርታለችና አንድ ቀን የአድዋ ሽንፈታቸውን ተበቅለው ኢትዮጵያን ይዘው ከሰው እኩል ለመሆን ምኞት ነበራቸው።
በዚህ መካከል አፍሪካ ውስጥ ቅኝ ግዛት እንደሚሰጣት በቀድሞ ወዳጆቿ እንግሊዝ እና ፈረንሳይ ቃል በተገባላት ብዙም ሳይቆይ የመጀመሪያው የዓለም ጦርነት ተቀሰቀሰ። ሀገራት ወይ ከጀርመን ወይ ከሩሲያ ወገን ተለይ በሚሉበት ወቅት ቀድመው እንግሊዝ እና ፈረንሳይ ከሩሲያ ጎን ቆሙ። ስታወላውል ቆይታ ጣሊያንም ወደ ጦርነቱ ገባች። የተገባላት ቃል አለና። በዚህ መካከል ነበር ቤኒቶ ሞሶሎኒ የፋሺዝም ርዮተ ዓለምን ይዞ ብቅ ማለቱን ጥላሁን ብርሃኔ ሥላሴ የ20ኛው ክፍለ ዘመን ኢትዮጵያ በተሰኘው መፅሃፋቸው ገልፀውታል።
የኢትዮጵያ ታሪክ ከዐፄ ቴዎድሮስ እስከ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ፣ በተሰኘው መፅሃፋቸው ተክለ ፃዲቅ መኩሪያ እንደ ፃፉት ኢጣሊያንን ወደ ቀድሞው ዝናዋ እንደሚመልስ፣ ንጉሡም የቀድሞ የቄሳርነትን ክብርና ስም መልሶ እንደሚያጎናፅፍ ተስፋ አስደረገ። ይሁን እንጅ ከኢትዮጵያ ጋር ጦርነት አድርጎ ደም ከመፋሰስ በወዳጅነት ገብቶ የኢትዮጵያን ግዛት መውሰድ ይሻላል በሚል የፖለቲካ አካሄዱን ለመለወጥ ሞከረ።
ነገር ግን ኢጣሊያ በኢትዮጵያ፣ በተሰኘው መፅሀፋቸው ተድላ ዘዮሐንስ ዘውዴ እንደፃፉት አዲሱ የፋሽስት መንግሥት ልዩ ልዩ ችግሮች ተደቀኑበት። የሙሶሊኒ ቅዠት ያላማራቸው ተቃዋሚ ፓርቲዎችን ቁጥር እየበዙ መጡ። የማይታረቁ የአመለካከት ልዩነቶች ተፈጠሩ። የሕዝቡ ዲሞክራሲያዊና ፍላጎት እየጨመረ ሄደ። በኢንዱስትሪው የልማት ጉዞ ቀርፋፋ ሆነ። በዓለም መንግሥታት ያለው ንቀትም ሕዝቡን አናደደው።
በእነዚህ ሁኔታዎች ተቀስፎ የተያዘው ሙሶሎኒ ታዲያ አይነ ልቦናውን ኢትዮጵያ ላይ ጣለው። ኢትዮጵያን በቅኝ ግዛትነት መያዝ ብዙ ነገሮችን እንደሚተኩስለት ሆኖ ታየው። የአድዋን ሽንፈት መበቀል እና የጣሊያንን ክብር ማደስ፣ ሰፊ ለም መሬት ያለው ቅኝ ግዛት ይዞ የወደቀውን የሀገሩን ኢኮኖሚ መገንባት የሚችለው ኢትዮጵያን በቅኝ ግዛት በመያዝ መስሎ ተሰማው። በርዕዮተ ዓለም ረገድ ለተቅበጠበጠው የጣሊያን ሕዝብ አዲስ የሰፈራ ቦታ እና የስራ እድል መስጠት፣ በዓለም ፊት ሞገስ ማግኘት፣ የሕዝቡን ብሔራዊ ስሜት እና አንድነት ለማፅናት፣ የእርሱን የራሱን ክብር ከፍ ማድረግ እና የፋሽስት ፓርቲውን ርዕዮተ ዓለም መገንባት የሚችለው ኢትዮጵያን በመያዝ መሰለው።
ሕዝቡ ቀስ በቀስ በሙሶሎኒ የቅዠት ሰበካው እየሰጠመ፣ በቀድሞ የሀገሩ ታላቅነት ታሪክ ተቋጨ። እናም ከሙሶሊኒ ጋር ወደ ማያውቀው ነገ ለመትመም በስሜት ነጎደ። ንጉሡም ጳጳሱም ከሙሶሊኒ አቋም ጎን ሆኑ። ባቋቋመው የፋሽስት ርዕዮተ ዓለም ወጣቱን ሳበው። የሚቃወሙትን ሁሉ ሰብስቦ ዘብጥያ አወረዳቸው። ከጥቂቶች በስተቀር አብዛኛው ሕዝብ ሳይወድ በግድ፣ በሀይለኛ ፕሮፓጋንዳው ተደናግሮ ከጎኑ ቆመ።
ተክለ ፃዲቅ መኩሪያ እንደፃፉትም የጣሊያን መንግሥት የኢትዮጵያን ውስጣዊ ሁኔታ የሚያጠኑ ሰላዮችን በቆንስላው ስም በአውራጃ በወረዳ ሳይቀር አሰራጭቷል። እነዚህ ስላዮች ከሕዝቡም ከመኳንንቱም ጋር በእጅ መንሻ እየተወዳጁ የጣሊያን መንግሥት ደግነት ፕሮፓጋንዳ ይነዙ ነበር።
በሀገሪቱ ስድስት አካባቢዎች ቆንስላዎች ነበሩት። በትግራይ፣ ደሴ፣ ጎንደር፣ ጎጃም፣ ሸዋ እና አፋር የስለላ ቆንስላዎችን ከፍተው የተለያዩ እንቅስቃሴዎችን አድርገዋል። ዋና አላማው ሕዝቡ የኢትዮጵያን መንግሥት እንዲጠላ ማድረግ፣ ለጣሊያን መንግሥት ጥላቻውን እንዲቀንስ ማድረግ ነበር። በጎንደር በከፈቱት ቆንስላቸው በርካታ ሰላዮችን አሰማርተው ሕዝብን ከሕዝብ የመከፋፈል ሴራ ይጎነጉኑ ነበር። የጎንደር እና የሸዋን ሕዝብ ለማጣላት ይሰራ ነበር። በትግራይ ከዐፄ ዮሐንስ የልጅ ልጆች መንደር ገብተው ሀገር የማስካድ ስራዎችን ይሰሩ ጀመር። ከራስ ኃይለ ሥላሴ ጉግሳ ጋር ልዩ ወዳጅነት በመፍጠር መቀራረብ ፈጥረዋል። የዐፄ ዮሐንስ ዝና እንደገና ታድሶ ሊፈጠር የሚችለው በጣሊያን እርዳታ ብቻ እንደሆነ አታልለውሃል በሀገሩ ላይ ባንዳ አድርገውታል። በተቃራኒው ደግሞ ራስ ስዩም የጣሊያን ዋነኛ ጠላት ሆነው ሀገራቸውን በታማኝነት አገልግለዋል። ራሶችን እና የሀይማኖት አባቶችን በመደለል ከጣሊያን ጎን የማስቆም ስራ ሰርተዋል።
ዲፕሎማሲያዊ መንገድን እንደ ሽፋን ተጠቀመበት እንጅ የአድዋ ሽንፈቱን ለመበቀል በሚያስችለው መልኩ ውስጥ ውስጡን የሀገሪቱን ፋብሪካዎች ሌት እና ቀን ያለዕረፍት የጦር መሳሪያ እንዲያመርቱ ትዕዛዝ ተሰጥቷል። በሁለተኛው የዓለም ጦርነት የተጠቀመችባቸውን እጅግ ዘመናዊ የጦር መሳሪያዎች ለኢትዮጵያው ጦርነት ዝግጁ ሆኑ።
ተድላ ዘዮሐንስ ዘውዴ እንደፃፉት ሙሶሎኒ ዓላማውን ለማስፈፅም ልዩ ልዩ ዝግጅቶችን ማደረግ ነበር። ቀዳሚው ዝግጅት የጦር መሳሪያዎችን በማምረት፣ ማምረት ያልቻለውንም በመግዛት ላይ አተኮረ። በርካታ የጦር መሳሪያ ማምረቻ ፋብሪካዎችን አቋቋመ። በአድዋው ውጊያ ያልነበሩ አዳዲስ እና ዘመናዊ ጠብመንጃዎች ተመረቱ። ታንኮች፣ ተዋጊ ጀቶች እና የመርዝ ጋዝ ቦምቦች ጭምር ተዘጋጁ። በርካታ ወታደሮችን በማሰልጠን ወደ ኤርትራ እና ሶማሊያ ቅኝ ግዛቶቹ አጋዘ።
በኤምባሲዎቹ አማካይነት የኢትጵያን ወታደራዊ አቅም በሚገባ ሲሰልሉ ቆይተዋል። አርባ አመቱን በሚገባ ዝግጅት ሲያደርጉ የቆዩት ጣሊያኖች ከኢትዮጵያ ዝምታ ጋር ተዳምሮ የተሳካ ይመስል ነበር።
ይቀጥላል
(መሰረት ቸኮል)
በኲር ሚያዝያ 14 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም