የእርሻ ቴክኖሎጂን ለአካባቢው አርሶ አደሮች
በማስተዋወቅና የዞኑን የምርጥ ዘር እጥረት
ለመፍታት በትኩረት እየሠራ መሆኑን የደባርቅ
ዩኒቨርሲቲ አስታወቀ።
ዩኒቨርሲቲው የአካባቢውን ፀጋዎች በጥናት
በመለየት በግብርና፣ በትምህርትና በቱሪዝም
ዘርፎች የማሕበረሰቡን ኑሮ ለማሻሻል ትኩረት
ሰጥቶ እየሠራ እንደሚገኝ ነው ያስታወቀው።
በተለይ በግብርናው ዘርፍ የአካባቢውን
የምርጥ ዘር ችግር ለመፍታትና ዘመናዊ የእርሻ
ቴክኖሎጂን ወደ አርሶ አደሩ ለማድረስ እየሠራ
መሆኑን የዩኒቨርሲቲው የጥናትና ምርምር
ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አወቀ ዋሴ ገልፀዋል።
በአካባቢው ያሉ አርሶ አደሮች ዘመናዊ የአስተራርስ
ዘዴዎችንና የሰብል አሰባስብ መንገዶችን
እንዲያውቁ እየተደረገ መሆኑንም ተናግረዋል።
ዳይሬክተሩ እንዳሉት በ2015/2016 የምርት
ዘመን አራት የእርሻ ትራክተር በመግዛት ለአርሶ
አደሩ አስተዋውቀዋል፣ በተመጣጣኝ ዋጋ
በማከራየትና እንዲዋሱ በማድረግ ተጠቃሚ
ሆነዋል። በዚህም ዩኒቨርሲቲው በሚገኝበት
አካባቢ ለሚገኙ አርሶ አደሮች (የሰሜን ጎንደር ዞን)
የምርጥ ዘር ብዜት ሥራዎችን እያከናወነ መሆኑን
አብራርተዋል። ይህም ምርታማነትን ለማሳደግ
እንደሚያስችል ጠቁመዋል።