ዩኒየኖች በተራበዉ ገበያ ውስጥ

0
218

“ለልጆቼ የትምህርት ቤት የደንብ ልብስ/ዩኒፎርም/ መግዣ በማጣቴ በእነሱ እኩያ ያሉ ሌሎች ተማሪዎች  የሚተውትን እየለበሱ  እየተማሩ ናቸው” በማለት የኑሮ ውድነቱ ክፉኛ እየጎዳቸው መሆኑን የነገሩን የባሕር ዳር ከተማ ነዋሪዋ   ወ/ሮ እሰይ ተመስገን  ናቸው::

ወይዘሮዋ በከተማዋ መንገድ ዳር በጥቂቱ  ሎሚ፣ ዝንጅብል፣ ነጭ ሽንኩርት…  እየሸጡ ሦስት ልጆቻቸውን ያለ አባት ብቻቸውን እያሳደጉ   ነው:: “እንደ ቀደመው ጊዜ   ሽንኩርት እና ዘይት  ገዝቶ መጠቀም ቀርቷል” የሚሉት ወይዘሮ እሰይ  የዕለት ገቢያቸው ከቀን ዳቦ መግዣ ያልዘለለ በመሆኑ ቅን አሳቢ እና በጎ አድራጊ ወገኖች ከትምህርት ቤት የደንብ ልብስ ባለፈ ለልጆቻቸው ድጋፍ እያደረጉላቸው  በመሆኑ አመስግነዋል::

“ከኑሮ ውድነቱ ባሻገር የገጠመኝ የጤና እክል   ሌላ ፈተና ሆኖብኛል” የሚሉት ወ/ሮ እሰይ እስከ ልጆቻቸው ፆማቸውን የሚያድሩበት ቀን እንዳለም  ነግረውናል::

የወ/ሮ እሰይ ተመስገንን ፈታኝ ሕይወት አየን እንጅ ልክ እንደርሳቸው በኑሮ ውድነቱ እየተሰቃዩ የሚገኙ በርካቶች ናቸው:: የኑሮ ውድነቱ በኢትዮጵያ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየናረ መምጣቱ የዜጎችን ኪስ ከመፈታተን አልፎ የዘወትር ምሬት እየሆነ መጥቷል:: ኑሮው መሽቶ በነጋ ቁጥር አሳሳቢ እየሆነ ስለመምጣቱ የበርካቶች የዕለት ከዕለት አጀንዳ ከሆነ ሰነባብቷል::ይህም የማሕበረሰቡን የመኖር አቅም ከመፈታተን አልፎ እንደ ወ/ሮ እሰይ በርካቶች  የዕለት ጉርሳቸውን እንዳያገኙ አድርጓል::

በሰዓታት ልዩነት በምርቶች ላይ የሚታየው ከፍተኛ የዋጋ ጭማሪ በማሕበረሰቡ ዘንድ ጭንቀት ፈጥሯል:: የኑሮ ውድነቱ የአብዛኛውን ቤት አንኳኩቷል:: በተለይም ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው  የቀን ሠራተኞች እንዲሁም ቋሚ ደመወዝተኞች የችግሩ ገፈት ቀማሽ ናቸው ::

በክልሉ የተፈጠረው የሰላም እጦት እና አለመረጋጋት የኑሮ ውድነቱን በከፋ ሁኔታ እንዲባባስ አድርጎታል:: እንደ ወ/ሮ እሰይ ሁሉ ሌሎች ወላጆችም ልጆቻቸውን ለማስተማር እና መሰረታዊ ፍላጎታቸውን ለማሟላት ከፍተኛ ውጣ ውረድን እያሳለፉ ይገኛሉ::

በክልሉ የተከሰተውን የሰላም እጦት ተከትሎ የተፈጠረውን  የኑሮ ውድነት  ያረጋጋ ዘንድ የሸማች ሕብረት ሥራ ማሕበራት እና ዩኒየኖች አምራቹን ከሸማች ጋር በማገናኘት የላቀ ሚና ይጫወቱ  ዘንድ ተስፋ ተጥሎባቸዋል:: መሰረታዊ የፍጆታ ዕቃዎች በሚፈለገው መጠን እና ጊዜ አለመገኘታቸው የሚፈጥረውን የዋጋ ንረት ለመቆጣጠር ትልቅ ድርሻ ያላቸው ዩኒየኖች እና ሸማች ሕብረት ሥራ ማሕበራት ለተጠቃሚው ማሕበረሰብ በተመጣጣኝ ዋጋ የፍጆታ ዕቃዎችን እንዲያገኙም ይመኛሉ:: ይህን ከግምት ውስጥ በማስገባት ተጨማሪ ምርቶችን በዓይነት እና በመጠን በማቅረብ የገበያን ዋጋ ማረጋጋት እና የሸማቾችን ፍላጎት የማርካት ሥራም ይጠበቅባቸዋል::

በአማራ ክልል በተለያዩ አካባቢዎች የሚገኙ ዩኒየኖች ገበያን በማረጋጋት በኩል እየሠሩት ያለውን ሥራ በኲር ጋዜጣ አነጋግራለች:: አቶ ይሁኔ ዳኛው በማዕከላዊ ጎንደር ዞን የፀሐይ ሁለገብ የገበሬዎች ሕብረት ሥራ ማሕበራት  ዩኒየን ሥራ አስኪያጅ ናቸው:: ዩኒየናቸው ከመቶ ሚሊዮን ብር በላይ መድቦ  የግብርና እና የኢንዱስትሪ ምርቶችን ለሸማቹ ማሕበረሰብ በተመጣጣኝ ዋጋ እያቀረበ እንደሚገኝ ነግረውናል::

ዩኒየኑ ከሚያከናውናቸው ዋና ዋና ተግባራት መካከል አንዱ ገበያን ማረጋጋት እንደሆነም  ሥራ አስኪያጁ አስረድተዋል:: በዚህም  በ174 መሰረታዊ ማሕበራት 145 ሺህ አባል አርሶ አደሮችን ይዞ እየሠራ ይገኛል:: ለአብነት ዩኒየኑ በገነባው    የዘይት ፋብሪካ  የኑግ ዘይት፣   የግብርና እና የኢንዱስትሪ ምርቶችን  /ጤፍ፣ማሽላ፣ስኳር፣ዘይት፣ዱቄት እና ሌሎችን/  ለአካባቢው ማሕበረሰብ መተመጣጣኝ ዋጋ እያቀረበ እንደሚገኝ አቶ ይሁኔ ጠቁመዋል::

ዩኒየኑ ምርትን በበቂ እና በተመጣጣኝ ዋጋ ለሸማቹ በማቅረብ ገበያውን ለማረጋጋት በሚደረገው ጥረት የበኩሉን አስተዋጽኦ ከማበርከት ባለፈ ለመንግሥት ሠራተኛው ለሦስት ወር የሚቆይ ብድር በማመቻቸት ተጠቃሚ አድርጓል:: በተያዘው በጀት ዓመት ከሁለት መቶ ሺህ ሊትር በላይ የምግብ ዘይት በተመጣጣኝ ዋጋ እንደቀረበም ያስረዳሉ::

አባል አርሶ አደሮች በሕገወጥ ነጋዴዎች ተጭበርብረው ምርታቸውን በዝቅተኛ ዋጋ እንዳይሸጡ   ዩኒየኑ ልፋታቸውን በሚመጥን መልኩ  ግዥ መፈፀሙንም አንስተዋል:: ለኢንዱስትሪ ምርቶች ግብዓት እየሰበሰቡ የሚገኙትም በቀጥታ ከአርሶ አደሩ እንደሆነ አመላክተዋል::

ዩኒየኑ የተቋቋመበትን ዓላማ ሙሉ በሙሉ እንዳይተገብር መሰናክሎች መኖራቸውን  ሥራ አስኪያጁ አንስተዋል፤ ለአብነት በክልሉ የተፈጠረው የሰላም መደፍረስ ፤የፋይናንስ እጥረት እንዲሁም  የአበዳሪ ተቋማት ብድር ለመስጠት መቀዛቀዝ ተጠቃሾች ናቸው::

ከአርሶ አደሩ ወደ ዩኒየኑ በቀጥታ ምርቶችን ለማስገባት የመዘግየት ሁኔታ እንዳለም አመላክተዋል:: እንደ አቶ ይሁኔ ማብራሪያ በቀጣይ ክረምቱ ሲገባ የምርት እጥረት እንዳይከሰት ከወዲሁ እየሠሩ መሆኑን እና አርሶ አደሩም ምርታማነቱን እንዲያሳድግ አስፈላጊውን ድጋፍ ለማድረግ መዘጋጀታቸውን አስገንዝበዋል::

በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ የሚገኙትን የሕብረተሰብ ክፍሎች  ማዕከል ያደረገ ገበያ የማረጋጋት ሥራ እየተከናወነ  እንደሚገኝ የተናገሩት ደግሞ በአዊ ብሔረሰብ አስተዳደር የሚገኘው የአድማስ ሁለገብ የገበሬዎች ሕብረት ሥራ ማሕበራት  ዩኒየን ሥራ አስኪያጅ አቶ መሰረት ወርቄ ናቸው:: ዩኒየኑ የአባላትን ምርት በመሰብሰብ ገበያን አፈላልጎ በመሸጥ  የልፋታቸውን እንዲያገኙ እንዲሁም የግብይት ትስስር በመፍጠር ገበያን የማረጋጋት ሥራ እየሠራ ይገኛል::

ዩኒየኑ የሚሰበስባቸው ዋና ዋና ሰብሎችም ስንዴ፣ ነጭ እና ቀይ ሩዝ፣ የቢራ ገብስ፣  የቅባት እህሎች (ሰሊጥ፣ ኑግ፣ ጎመንዘር…) እንዲሁም የጥራጥሬ ሰብሎች (አተር፣ ባቄላ፣ ሽንብራ…) ናቸው:: ከዚህ በተጓዳኝ ለአባላት እና ለአካባቢው ማሕበረሰብ  የኢንዱስትሪ ውጤቶችን እና የፍጆታ ምርቶችን በተመጣጣኝ ዋጋ እያቀረበ ይገኛል:: በቀጣይ የሚያከናውናቸው ዋና ዋና ተግባራትም የዩኒየኑን ውስጣዊ የፋይናንስ አቅም ማጠናከር እና የግብርና እና  የኢንዱስትሪ ምርት የግብይት ድርሻዎችን ማሳደግ ናቸው::

አቶ መሰረት እንደሚሉት ዩኒየኑ ለአካባቢው ማሕበረሰብ በሸማቾች ሕብረት ሥራ አማካኝነት ምርት በተመጣጣኝ ዋጋ እያቀረበ ነው::  በተለይ ለመጭው ክረምት ወራት የሚሆን 70 ሺህ ኩንታል የበቆሎ ምርት በመሰብሰብ በመጋዘኑ እያስቀመጠ እንደሚገኝ ነግረውናል:: 30 ሺህ ኩንታል የበቆሎ ምርት ለተፈናቀሉ፣በድርቅ ለተጎዱ እና በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ለሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎች ይሆን ዘንድ ለብሔራዊ አደጋ መከላከል ኮሚሽን ለማቅረብ ዝግጅቱን እንዳጠናቀቀም ለበኩር ጋዜጣ  ተናግረዋል::

ዩኒየኑ ለሸማች ማሕበራት ሊቀርብ የሚችለውን የምርት ግብዓት የማቅረብ ተግባሩን እያከናወነ መሆኑንም አስረድተዋል:: በቀጣይ ሊከሰት የሚችለውን የምርት እጥረት ግምት ውስጥ በማስገባት ከአባላት ምርት የማሰባሰብ ሥራ እያከናወነ መሆኑን ነግረውናል::

በመጭው የክረምት ወራትም ዩኒየኑ  የዋጋ ንረትን  ለማረጋጋት የበኩሉን ድርሻ እንደሚወጣ አረጋግጠዋል:: ዩኒየኑ የተቋቋመበትን ዓላማ አርሶ አደሩ ያመረተውን ምርት በተገቢው መንገድ እንዲሸጥ፣ በወቅቱ ገንዘብ እንዲያገኝ ሳይንገላታ እና  ሳይጭበረበር ተጠቃሚ እንዲሆን ሥራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉም አስገንዝበዋል:: ከዚህ ጎን ለጎን አርሶ አደሩ የተሻለ ምርት እንዲያመርት በቂ ግብዓት  መቅረብ እንዳለበትም ጠቁመዋል::  የፀጥታ ችግሩን ተቋቁሞ በቀጣይ የተሻለ ሥራ እንደሚሠራም ነው አቶ መሰረት የተናገሩት::

የሕብረት ሥራ ማህበራት እና ዩኒየኖችን የገንዘብ አቅማቸውን በማሳደግ በተመጣጣኝ ዋጋ ምርትን ለሸማቹ ማሕበረሰብ ከማቅረብ ባሻገር እሴት ጨምረው ለገበያ የሚያቀርቡ ፋብሪካዎችን በማቋቋም የህብረተሰቡ ሕይወት ትርጉም ያለው መሻሻል እንዲያመጣ  በትኩረት  መሥራት እንዳለባቸው ይታመናል::

የአማራ ክልል ሕብረት ሥራ ማሕበራት ባለስልጣን ኃላፊ አቶ ጌትነት አማረ በበኩላቸው”ገበያን ለማረጋጋት ዩኒየኖች እና ሸማች ሕብረት ሥራ ማሕበራት ብቸኛ ተዋናይ አይደሉም:: በግብይት ሰንሰለቱ የተሰማሩ ሁሉ በኃላፊነት መሥራት ይገባቸዋል:: ለዚህ ተግባር  በመንግሥት በኩል ተዘዋዋሪ ብድር የማመቻቸት ሥራዎች እየተከናወኑ ናቸው” በማለት አስረድተዋል::

የሸማችን ፍላጎት አሟልቷል ማለት ባይቻልም የሚቻለው  ሁሉ ጥረት እየተደረገ ስለመሆኑም  ተናግረዋል:: የሚከሰቱ ችግሮችን ለማርገብ ሥራዎችን አጠናክረው እንደሚቀጥሉም ኃላፊው ቃል ገብተዋል::

አቶ ጌትነት እንዳሉት የወ/ሮ እሰይ  እና መሰሎቻቸው ችግር የሚፈታው ዩኒየኖች እና ሕብረት ሥራ ማሕበራት በሚያደርጉት ጥረት ብቻ ሳይሆን የሁሉንም ድጋፍ እንደሚጠይቅ የኛም አስተያየት ነው::

 

(መልካሙ ከፋለ)

በኲር ሚያዝያ 21 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here