በኢትዮጵያ የቤተሰብ ሕግ ጋብቻ መፈፀም ያለበት ከ18 ዓመት በላይ በሁለቱም ተጋቢዎች ፈቃድ ብቻ እንደሆነ ይደነግጋል:: ያለእድሜ ጋብቻ ሲባል ግን ሕግ ከሚደነግጋቸው የእድሜ ክልል በታች የሆኑ ልጆች ተጋብተው ትዳር እንዲመሰርቱ የሚደረግ ሥርዓት ነው:: በአብዛኛውም የሚፈፀመው ከ10 እስከ 15 ዓመት ባሉ የእድሜ ክልሎች ሲሆን አንዳንድ ጊዜ ከዚህ በታች በሆኑ ሕፃናት ላይም ሊፈፀም ይችላል::
በፈረንጆቹ 2011 የአለም ጤና ድርጅት የወጣ አንድ ጥናት ኢትዮጵያ ውስጥ ለሴቶች አማካይ የጋብቻ ዕድሜ 16 ዓመት ከአምስት ወር እንደሆነ ያመላክታል። ይህ ጥናት አክሎም በሀገሪቱ ካሉ ሴቶች 40 በመቶው ከ20ዎቹ ዕድሜያቸው በፊት ጋብቻ መፈፀማቸውን አስቀምጧል።
የተባበሩት መንግሥታት የሕፃናት መርጃ (ዩኒሴፍ) በፈረንጆቹ 2016 ባወጣው ዘገባ ደግሞ የኢትዮጵያ መንግሥት ያላቻ ጋብቻን በአሥር ዓመት ሊያጠፋ አቅዷል ብሎ ነበር። የአማራ ክልል ሴቶች፣ ሕፃናት እና ማኀበራዊ ጉዳይ ቢሮ የሴቶች ንቅናቄ ተሳትፎ ማስፋፊያ ዳይሬክተር ወ/ሮ ደስታ ፈንታ ግን የዩኒሴፍን ዘገባ አስመልክተው “እውነታው ግን ያላቻ ጋብቻ ከመጥፋት አሊያም ከመቀነስ ይልቅ በሰው ሠራሽና ተፈጥሯዊ ቀውስ ታግዞ በተለይም በአማራ ክልል እየጨመረ መጥቷል:: አለመረጋጋት ከመከሰቱ በፊት የመንግሥት አካላት ያለእድሜ ጋብቻ እንዲቀንስ በየቀበሌው ይሠሩ ነበር፤ ፖሊስም ጥቆማ ሲደርሰው ሁኔታውን ይከላከል ነበር። ትምህርት ቤቶች፣ በየደረጃው የተቋቋሙ የሴቶች ጉዳይ ተቋማት የድርሻቸውን ይወጡ ነበር። በዚህም መልካም የሚባልም ለውጥ ነበር። አሁን ግን ተመልሶ በፊት ከነበረውም እየጨመረ ነው” የሚል አስተያየት ሰጥተዋል።
በየቦታው ካለው ግጭት የተነሳ ሕፃናት እና ታዳጊዎች ከቤት ወደ ትምህርት ቤት እየሄዱ ስላልሆነ ወደ ትዳር እንዲገቡ መገደዳቸውንም ወ/ሮ ደስታ ጠቁመዋል።
በ2016 የኢትጵያ ሥነ ሕዝብ እና ጤና ተቋም ባጠናው ጥናት መሰረት የጋብቻ ሁኔታ በክልል ደረጃ ያለበት ሁኔታ ላይ አማራ ክልል 42 ነጥብ 4 ከመቶ ሴቶች እንደሚዳሩ ያመለከተ ነበር:: በዚሁ ጥናት በኢትዮጵያ ከአምስት ሕፃናት ሁለቱ እድሜያቸው 18 ዓመት ሳይሞላቸው የልጅነት ጋብቻ ይፈፀምባቸዋል::
የልጅነት ጋብቻ መንስኤ
ስር የሰደደ እና የተዛባ የሥርዓተ ፆታ አመለካከት፣ ለሴቶች ትምህርት እና ለውጥ ዋጋ አለመስጠት፣ በዋናነት በግጭቱ ምክንያት ትምህርት ቤቶች በብዙ ቦታዎች መቋረጥ፣ ከጋብቻ ውጭ ልጅ ወልደው ያሳፍሩኛል በሚል ስጋት፣ በግጭቱ ምክንያት በተስፋፋው ድህነት እና የኑሮ ጫና የተሻለ ሕይወት ያመጣል ብሎ ማሰብ/ በተለይ ግለሰቡ ሃብት ካለው መሬት እና ከብት ይሰጣል ብሎ ቤተሰብ ማሰቡ/ እንደሆነ ባለሙያዋ ወ/ሮ ደስታ አንስተዋል:: ችግሩን በመንግሥት መዋቅር በኩል ለማስቆም የሚደረገው ጥረት ስኬታማ ያልሆነው ግጭቱ ባሳደረው ፍራቻ ወደ ታች ወርዶ እንዳይሠራ ማድረጉን ነው::
የልጅነት ጋብቻ ጉዳት
ያለእድሜ ጋብቻ ከሚያስከትላቸው ጉዳቶች ሴቶች ያለእድሜያቸው ልጅ እንዲወልዱ ማስገደዱ ነው:: በልጅነታቸው የሚያገቡ ሴቶች በቤታቸው ውስጥ ውሳኔ የመስጠት አቅማቸው በጣም አናሳ ነው:: በልጅነታቸው የሚዳሩ ሴቶች እድሜያቸው ከፍ ካለ በኋላ ከሚዳሩት ሴቶች ይበልጥ በቤት ውስጥ ለሚፈፀም ጾታዊ ትንኮሳ ተጋላጭ ናቸው:: መገለል፣ ፆታዊ ጥቃት እና ትንኮሳ ለጭንቀትና ለድብርት ሊዳርግ ይችላል::
ያለእድሜያቸው የሚዳሩ ሴት ልጆች በአካል እና በአእምሮ ዝግጁ ሳይሆኑ ልጅ ለመውለድ ይገደዳሉ::
እነዚህ ሴቶች የሥነ ተዋልዶ ትምህርት እና የጤና አገልግሎት ለማግኘት አነስተኛ እድል ያላቸው ሲሆን ብዙውን ጊዜም “የወሊድ መቆጣጠሪያ መንገዶችን እንጠቀም?” ለማለት አይደፍሩም::
የታዳጊ ሴቶች ሰውነት በቀላሉ ለአባላዘር በሽታዎች የመጋለጥ አጋጣሚው ከፍተኛ እንደሆነም መረጃው ያመላክታል::
ያለእድሜ ጋብቻ ለፊስቱላም ያጋልጣል:: በጣም ከባድ የጤና መቃወስ የሚያስከትለው የፊስቱላ በሽታ በተለይ በመራቢያ አካል አካባቢ በሚፈጠር ቀዳዳ ምክንያት ሽንትና ሰገራን መቆጣጠር እንዳትችል ያደርጋታል:: የፊስቱላ ችግር ያለባት ሴት ከማህበረሰቡም ሆነ ከባሏ ትገለላለች:: በልጅነታቸው የሚዳሩ ሴቶች ደግሞ ትምህርታቸውን ለማቋረጥ ይገደዳሉ::
አለመማሯ ደግሞ ከፍ ባለሥራ ተቀጥራ መብቷን እንዳትጠይቅ ያደርጋታል:: በአጠቃላይ ያለእድሜ ጋብቻ የሙሽራዋን ወላጆች ለኢኮኖሚያዊ ክስረት እንዲሁም የሚዳሩ ልጆችን ለሥነ ልቦና እና ለጤና ቀውስ ይዳርጋቸዋል:: ከዚህ ባለፈ ጋብቻው የፀና ስለማይሆን ቀጣይ ደስተኛ ሕይወት ለመምራት የሚያስችላቸው ውሳኔ ለመወሰን ከፍተኛ ተፅዕኖ ያሳድርባቸዋል:: በኢትዮጵያ ውስጥ ከአምስት ሕፃናት አንዷ ያለእድሜዋ ማግባቷ ይህንን ሁሉ ችግር እንድትቀበል ያስገድዳል::
በ2017 ዓ.ም የተፈፀመ የልጅነት ጋብቻ
በአማራ ክልል ባለፈው በጀት ዓመት/2017/ በደረሱ ጥቆማዎች 2 ሺህ 565 ሴቶች ያለእድሜያቸው ጋብቻ እንዲፈጽሙ ስምምነት መደረጉ ከየአካባቢዎች በደረሰ ሪፖርት ተረጋግ ጧል ::
ከዚህ ውስጥ በ699 ሴቶች ላይ ሊፈፀም የነበረው ያለእድሜ ጋብቻ በድርድር እንዲቋረጥ ተደርጓል:: 669 ሕፃናት ደግሞ ጋብቻውን እንዲፈጽሙ ተገደዋል::
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የባሕር ዳር ሀገረ ስብከት ዋና ጸሐፊ እና የአማራ ክልል የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ አባል መልአከ ብርሐን ፍሰሃ ጥላሁን በኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን አስተምህሮ የጋብቻ እድሜ በሄዋን የጋብቻ እድሜ ከተፈጠረችበት 15 ዓመት ላይ በገነት የቆየችበት ሰባት ዓመት ተደምሮ 22 ዓመት ስለሚሆን የጋብቻ እድሜው በቤተክርስቲያን 22 ዓመት መሆኑን ጠቁመዋል::
በልጅነት የሚጋቡ ልጆች ክፉና ደጉን ስለማያውቁ በቤተክርስቲያን ውስጥ ሥርአተ ጋብቻቸው አይፈፀምም፤ ቤተክርስቲያኗም ታወግዛለች:: በየቤቱ ለሚፈፀም ጋብቻም ቢሆን ተጋቢዎች ለጋብቻ ካልደረሱ የሃይማኖት አባት እንዳይባርክ መግባባት ላይ ተደርሶ እየተሠራ እንደሆነ ነው የገለፁት::
የአማራ ክልል እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት የትምህርት እና ዳዕዋ ዘርፍ ኃላፊ ሼህ ሙሐመድ ኢብራሂም በበኩላቸው ሸሪአው ማንኛውም ድርጊት ጎጂ ሆኖ ሲገኝ አንዱ ሌላውን የሚበድል ነገር ማስፈን ስለሌለበት ምግብ እንኳን ቢሆን መተው እንደሚገባው አስገንዝበዋል:: ሴቶችን እና ሕፃናትን የሚጎዳው ያለእድሜ ጋብቻንም አንዳቸውን የሚጎዳ ከሆነ እንደማይፈቅድ ነው ያነሱት::
የአማራ ክልል የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ጽሕፈጽ ቤት ኃላፊ አቶ ፋሲል ታዬ ሃይማኖት የእያንዳንዱን ሰው ክብር እንዲጠብቅ ያስተምራል:: የሕይወት ልምምድን ከሃይማኖት ሥርዓት ጋር ማስተሳሰር እንደማይገባ እና ለዚህ ደግሞ የሃይማኖት አባቶች እውነተኛ ተባባሪ በመሆን የድርሻቸውን እንዲወጡ አሳስበዋል::
ኦሊቪያ ስሚዝ
ስሚዝ ምንም እንኳን ማርሻል አርትን ጨምሮ በበርካታ ስፖርቶች ውስጥ የተሳተፈች ቢሆንም እግር ኳስ መጫወት የጀመችው ግን በሦስት ዓመቷ ነበር። በ2019 ለመጀመሪያ ጊዜ ለሀገሯ ብሔራዊ ቡድን በ15 ዓመቷ የመጀመሪያ ጨዋታውን ያደረገችው ሲሆን የካናዳ የዓመቱ ምርጥ ወጣት ተጫዋች በመባልም ተመርጣለች።
ካናዳዊቷ አጥቂ ኦሊቪያ ስሚዝ በሴቶች እግር ኳስ ታሪክ በተመዘገበ/ሪከርድ በሆነ/ አንድ ሚሊዮን ፓውንድ (ከ1 ነጥብ 3 ሚሊዮን ዶላር በላይ) የዝውውር ዋጋ ከሊቨርፑል በመልቀቅ ለአርሰናል ሴቶች ቡድን ፊርማዋን አኑራለች ሲል ቢቢሲ የዘገበው ፡፡
ለካናዳ ብሔራዊ ቡድን 18 ጨዋታዎችን አድርጋ አራት ግቦችን አስቆጥራለች። በፖርቹጋል ብሔራዊ የሴቶች ሻምፒዮና ውስጥ አስደናቂ የውድድር ዘመን ካሳለፈች በኋላ በ19 ዓመቷ ነው ሊቨርፑልን የተቀላቀለችው። 15 ዓመቷ የመጀመሪያዋን ኢንተርናሽናል ጨዋታ ሀገሯን በመወከል ያደረገችው የ20 ዓመቷ ወጣት ከሻምፒየንስ ሊጉ ባለቤት አርስናል ጋር የአራት ዓመት የውል ስምምነት ተፈራርማለች። በ18 ጨዋታዎች 13 ግቦችን በማስቆጠር 9 ለግብ የሚሆኑ ኳሶችን አመቻችታ በማቀበል የሊጉ ምርጥ ወጣት ተጫዋች ተብላም ተሸልማለች።
(ማራኪ ሰውነት)
በኲር የነሐሴ 5 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም