ያለ ሰላም ልማት፣ ያለ ውሀ አሳ ማርባት

0
222

የየትኛውም ሀገር የስልጣኔ እና ዕድገት መሰረቱ  የውስጣዊ እና ውጫዊ ሰላም መኖር ነው።  ሀገራት ከዕድገት እና ሥልጣኔ ወጥተው ወደ ኋላ ቀርነት የተመለሱት፣ ከዚህም አልፎ ተርፎ ኅልውናቸውን ያጡት፣ ዜጎች በገፍ የተገደሉት፣ ከሞት የተረፉትም ለስደት እንዲሁም እንግልት የተዳረጉት በሰላም እጦት ምክንያት መሆኑም ግልፅ ነው።

የሰላም እጦት ሲባል የግድ የመሳሪያ ድምፅ መሰማት  ማለት  አይደለም። ይልቁንም የሰላም እጦት   ጥርጣሬ፣ ፍረጃ፣ አለመስማማት፣ የፍትሕ እጦት፣ የግልፀኝነት እና የተጠያቂነት አሰራር አለመኖርም አካላዊ ግጭት ባይኖር እንኳ እንደ ሰላም እጦት ሊቆጠር ይችላል። በመሆኑም ሰላም ሲባል ግጭት አለመኖር ብቻ ሳይሆን የፍትሕ   መኖር እና የሕዝብ ጥያቄዎች ምላሽ ማግኘትን የሚመለከት ነው። በአጭር አነጋገር ሰላም ማለት የሰዎች  እርካታ፣ ዋስትና እና መተማመንን ማግኘት ማለት ነው። ስለዚህ  ይሄ ሰላም ካለ ምቹ የስራ ሁኔታ፣ ነፃ እንቅስቃሴ፣ አድሎ የሌለበት   አሰራር ይኖራል ማለት ነው። ባንጻሩም ያለ ሰላም ስለ ልማት ማውራት ያለ ውሀ አሳ ከማርባት ተለይቶ የሚታይ አይደለም፡፡

በመሆኑም ለሰላም መስፈን የቅድሚያ ቅድሚያ ትኩረት ልንሰጥ ያሻናል፡፡ ሰላምን ለማምጣት ፍትሐዊ አስተዳድር፣ ሕዝብ አለቃ የሚሆንበት መንግሥታዊ ውቅር፣  አካታች እና አሳታፊ ሥነ መንግስት፣ አለመግባባቶችን በፖለቲካዊ ውይይት መፍታት የግድ ይላል። ይህ ሲሆን ሰላም ይኖራል፣ የሰላም መኖር ደግሞ ልማትን ወይም የመዋዕለ ነዋይ ፍሰትን ( ኢንቨስትመንት) እና ፈጠራን  ያሳድጋል።  ኢንቨስትመንት በተስፋፋ ቁጥር ዜጎች ውሏቸው ሥራ ላይ ስለሚሆን ፈጠራ ይዳብራል፤ ፆም አደርነት ይጠፋል፤ ስልጣኔ ይሰፋል፤ ዕድገት ብልጽግና ይደረጃል።

ስለዚህ ለኢንቨስትመንት እና ጠቅላላ ልማት፣ ለዜጎች ደኅንነት፣ ለሀገር ሉዓላዊነት እና ፍቅር  ሰላም  መሰረት ነው። በርስ በርስ ጦርነት ውስጥ ተሁኖ  የሀገር ፍቅርን ማምጣትም ሆነ የሥራ ምቹ ሁኔታን መፍጠር አይቻልም። ዜጎች የሚተማመኑበት ሀገር እና ሥርዓት ይኖራቸው ዘንድ  ሰላም ዋነኛ ጉዳይ ነው።

ፍልሰትን፣ ጥርጣሬን፣ ስጋትን ለማራቅ ነፃ እና ገለልተኛ ተቋማት፣ የግልፀኝነት እና የተጠያቂነት አሰራር  በእጅጉ ያሻል። ይሄ ሲሆን የሥራ ተነሳሽነት ይኖራል፣ ልማትም ይፋጠናል። ሰላም የልማት ነፍስ ነው፤ ሰላም በሌለበት ልማት የየብስ ላይ ዓሳን እንደ ማርባት አይነት ጉም የመጨበጥ አይነት  ተስፋ ይሆናል። ሰላም የልማት፣ የመኖር፣ የመዋደድ፣ የስኬት ወዘተ. ሁሉ መሰረት ነው። ስለሆነም ሰላምን ልንፈልገው ይገባል፡፡  እርግጥ ነው፤ ሰላምን የማይፈልግ ማንም የለም። ትልቁ ጉዳይ ሰላምን ከልብ መሻት እና ሰላምን ለማምጣት በቁርጠኝነት መነሳት ነው፡፡ ሰላምን ለማምጣት ቁርጠኛ ከመሆን በመለስ ለሰላም መረጋገጥ ከኔ ወይም ከኛ የሚጠበቀው ምንድነው በሚል መለየትና ለሰላም መስፈን የሚጠበቅብንን  ሁላችንም ካደረግን ሰላምን በእርግጥም ማስፈን አይሳነንም፡፡ በጥቅሉ  ሰላምን ማስፈን ጠቀሜታው ለሁላችንም  መሆኑን ተገንዝበን ለሰላም  የሚጠበቅብንን ሁሉ ልናደርግ ይገባናል!

(የሺሃሳብ አበራ)

በኲር ሚያዝያ 28 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here