የተረት አባቱ አበባ ተስፋዬ ሕጻናትን “የዛሬ አበባዎች፣ የነገ ፍሬዎች” ሲሉ ይጠሯቸዋል:: እርግጥ ነው ልጆች ዛሬ ላይ አበባ ናቸው፤ እንክብካቤ ካገኙ ለፍሬ በቅተው ለብዙዎች የመኖር ህልውና ይሆናሉ:: እንክብካቤ ከተነፈጋቸው ደግሞ ይጠወልጋሉ፣ ፍሬ ሳይሰጡ ደርቀው ይደርቃሉ፤ ሰው ተስፋ ያደረገው እንደ ጉም በኖ ይጠፋል:: ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በዓለም ላይ እየተስተዋለ ያለው ከዚህ የተለየ አይደለም::
ሕጻናት አበባነታቸውን ወደ ፍሬ እንዳይቀይሩ፣ ጣፋጭነታቸውን ለሚጓጉላቸው ወላጆቻቸው እና ድጋፋቸውን ለሚፈልጉ ሁሉ ላያቀምሱ ተከልክለዋል:: አበባ ወደ ፍሬ እንዳይለወጥ አፈሩን ያጠበው፣ የጸሐይ ብርሀንን የከለለው፣ ውኃውን ያነጠፈው ትልቁ ግንብ ደግሞ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የዓለም ሀገራት ገላጋይ ያጡበት ግጭት እና ጦርነት ነው::
የምናወራው የሕጻናት የነገ መዳረሻ መንገድ ስለሆነው ትምህርት ነው:: ሕጻናት ነገ ምን መሆን እንደሚፈልጉ ሲጠየቁ እርግጠኛ ሆነው የሚናገሯቸው የሕክምና ዶክተር፣ ተመራማሪ፣ አውሮፕላን አብራሪ (ፓይለት)፣ ምህንድስና፣ መምህር፣ ፖሊስ፣ መከላከያ እና ሌሎችንም መሆን ነው:: የልጅነት አዕምሯቸው አስቦ አፋቸው የሚያወጣቸው እነዚህ ህልሞች በዋናነት የማኅበረሰቡን ችግር ለመፍታት ካላቸው ጉጉት የመነጨ ነው::
በእርግጥም ትምህርት ድህነትን ለመዋጋት፣ ሰላም እና ደኅንነትን ለማረጋገጥ፣ ሀገርን በሁለንተናዊ ዕድገት ተራማጅ ለማድረግ ዋና መሳሪያ እንደሆነ ብዙዎች ይስማሙበታል:: ይሁን እንጂ የትምህርት ዘርፉ ዓለምን ለመለወጥ ካለው አቅም በተጻራሪ የቆሙ ተግዳሮቶች ግቡን እንዳይመታ እያደረጉት እንደሚገኝ የኮንሰርን ኒውስ መረጃ ዋቢ ነው:: ድረ ገጹ እ.አ.አ በወርሀ ነሐሴ 2024 ይፋ ባደረገው መረጃ መሠረት ዓለም የ250 ሚሊዮን ታዲጊዎቿ የነገ መዳረሻ መንገድ ተዘግቶባቸዋል::
ኮንሰርን ኒውስ የትምህርት ዘርፉን አሥር ፈተናዎች በጠቆመበት ጽሑፉ ቀዳሚ ያደረገው በትጥቅ የታገዙ ግጭቶች እና የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ናቸው:: ኮንሰርን ኒውስ የአሜሪካውን የተራድኦ ድርጅት (USAID) መረጃ ጠቅሶ በገጹ እንዳሰፈረው በዓለም ላይ ከትምህርት ውጪ ከሆኑ ሕጻናት ውስጥ 125 ሚሊዮን የሚሆኑት በግጭት ምክንያት ከትምህርት የራቁ ናቸው:: ይህ አኃዝ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የትምህርት፣ የሳይንስ እና የባህል ድርጅት (UNESCO) እ.አ.አ በ2013 በግጭት ምክንያት ከትምህርት የራቁ ናቸው ብሎ ይፋ ካደረጋቸው 50 ሚሊዮን ታዳጊዎች በ75 ሚሊዮን የሚልቅ ነው:: ይህም ዓለም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየገባችበት ያለው የርስ በርስ ግጭት ድንበር ዘለል ጦርነቶች የዓለም ሕዝብን ወደ ከፋ ማኅበራዊ መቃወስ እየዳረጉት መሆኑን የሚያረጋግጥ ተደርጎ ይወሰዳል::
በትምህርት ተቋማት ላይ የሚፈጸም ጥቃት እና ትምህርት ተቋማትን ለወታደራዊ ማዘዣነት የመጠቀም አዝማሚያው ከዓመት ዓመት እየጨመረ መምጣቱን ኮንሰርን ኒውስ በዘገባው አመላክቷል:: ትምህርትን እና የትምህርት ሥርዓቱን ለመጠበቅ በዓለም አቀፍ ደረጃ የተቋቋመው ጥምረት (GCPEA) እንዳስታወቀው በፈረንጆቹ 2022 እና 2023 በትምህርት ተቋማት ላይ የሚፈጸመው ጥቃት በፈረንጆቹ 2022 እና 2023 ከነበረበት 20 በመቶ መጨመሩን ማስታወቁ ደግሞ ዓለም አሁንም ከሰላም ይልቅ የኀይል አማራጭን ብቸኛ መንገድ አድርጋ እየተከተለች መሆኑን የሚያረጋግጥ ነው:: እንደ ጥምረቱ በተጠቀሱት ዓመታት ብቻ ትምህርት ተቋማት ላይ ያነጣጠሩ 6 ሺህ ጥቃቶች ተፈጽመዋል:: ከ10 ሺህ በላይ ተማሪዎች እና መምህራን ለሞት እና ለአካላዊ ጉዳት ተዳርገዋል::
ባለፉት ሁለት ዓመታት የትምህርት እንቅስቃሴውን ለማስተጓጎልም ሆነ ኢላማቸውን የሳቱ በየቀኑ ስምንት ጥቃቶች እየተፈጸሙ መሆኑን ዘገባው አመላክቷል:: ይህም ተማሪዎች ተረጋግተው ወደ ትምህርት ቤት እንዳይሄዱ፣ ትምህርታቸውንም እንዳይከታተሉ፣ መምህራን በነጻነት ጥራት ያለው ትምህርት በሕጻናት አዕምሮ ውስጥ እንዳያሰርጹ፣ የትምህርት መሰረተ ልማቶች እንዲወድሙ፣ የውስጥ ግብዓታቸው እንዲወድም አድርጓል:: ሌላው ቀርቶ በእስራኤል እና በጋዛ መካከል እየተደረገ ባለው ጦርነት ምክንያት በተለይ ከጥቅምት 2023 ጀምሮ ኮንሰርን ኒውስ ይህንን ዘገባ ይፋ እስካደረገበት እ.አ.አ ወርሀ ነሐሴ 2024 ድረስ ብቻ በጋዛ የሚገኙ ሁሉም ዩኒቨርሲቲዎች እና ከ80 በመቶ በላይ የሚሆኑ ትምህርት ቤቶች ለጉዳት እና ውድመት ተዳርገዋል::
ግጭቶች እና ጦርነቶች በትምህርት ተቋማት ላይ እያደረሱት ያለውን ጉዳት እና ውድመት ለመታደግ ግጭቶች ውስጥ ትምህርትን ለመጠበቅ የፖለቲካ ቁርጠኝነት ያስፈልጋል የሚለውን መግለጫ 120 ሀገራት እ.አ.አ በግንቦት 2024 የደገፉት ቢሆንም አሁንም መግለጫው ርባና ቢስ ሆኖ ቀጥሏል::
ማሊ፣ ኒጀር፣ ቡርኪናፋሶ፣ የመን፣ ቻድ፣ ጊኒ፣ ሴኔጋል፣ ጅቡቲ፣ ሴራሊዮን፣ አፍጋኒስታን፣ ኢትዮጵያ ፣ ደቡብ ሱዳን፣ ሱዳን፣ ጋምቢያ እና መካከለኛው አፍሪካ ሪፐፕሊክ ለመማር ፈተና የሆነባቸው ሀገራት ናቸው:: ታዲያ አሁንም ግጭቶች መፍትሄ ባልተሰጡባት ኢትዮጵያ 17 ሚሊዮን የሚጠጉ ተማሪዎች ከትምህርት እንደራቁባት ዓለም አቀፉ የሕጻናት መርጃ ድርጅት (ዩኒሴፍ) እ.አ.አ ነሐሴ 8 ቀን 2024 ይፋ ያደረገው መረጃ ያሳያል::
ከ2013 ዓ.ም ወዲህ በይፋ የቀጠሉት ጦርነቶች ግጭቶች የትምህርት ተቋማት እንዲወድሙም አድርጓል:: ግሎባል ሲቲዝን ትኩረቱን ትምህርት ላይ አድርጎ የሚሠራ ድርጅት ነው:: እስከ 2013 ዓ.ም መጨረሻ ከሰባት ሺህ በላይ የትምህርት ተቋማት ለጉዳት መዳረጋቸውን ይፋ ማድረጉ ይታወሳል:: ለሁለት ዓመታት ተካሂዶ የነበረው የሰሜኑ ጦርነት በአማራ ክልል ብቻ 2 ሺህ 935 የትምህርት ተቋማትን ለተለያየ አይነት ጉዳት እና ውድመት መዳረጉን በክልሉ በጦርነቱ የተጎዱ አካባቢዎች መልሶ ማቋቋም እና ልማት ፈንድ ጽሕፈት ቤት መረጃ ይጠቁማል::
2015 ዓ.ም መጨረሻ ላይ አማራ ክልል የተቀሰቀሰው በትጥቅ የታገዘ ግጭት ግን አሁንም በመቀጠሉ አብዛኛዎቹ ተማሪዎች ከቤታቸው እንዲውሉ እያደረገ ነው:: ባለፈው ዓመት ከ2 ነጥብ አራት ሚሊዮን በላይ ተማሪዎች እና ከሦስት ሺህ በላይ ትምህርት ቤቶች ተዘግተው የከረሙበት አማራ ክልል ዘንድሮም ሰባት ሚሊዮን ተማሪዎችን መዝግቦ የማስተማር ዕቅዱ አሁንም ጥያቄ ምልክት ውስጥ እንደገባ ነው:: ገና ከጅምሩ ግማሽ ያህሉ ተማሪዎች እንዳልተመዘገቡ የክልሉ ትምህርት ቢሮ መረጃ ያሳያል:: በመሆኑም እየተደረገ ያለው በትጥቅ የታገዘ ግጭት የታዳጊዎችን የነገ ሕይወት የሚጎዳ፣ በምጣኔ ሐብትም ወደ ኋላ የሚያስቀር፣ ማኅበራዊ ግንኙነትን የሚያሻክር በመሆኑ ችግሩ በሰላማዊ የትግል አማራጮች እንዲቋጭ መረባረብ ይገባል:: ኢትዮጵያ ሰላሟ ተመልሶ ዛሬም እንደ ድሮው የአፍሪካ ብሎም የዓለም የሰላም ማስከበር አርማ ትሆን ዘንድ ትግሉ ከጠብ መንጃ ወጥቶ በብዕር እና ወረቀት እንዲሆን መትጋት ከእያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ እና ከምሑራን ይጠበቃል::
(ስማቸው አጥናፍ)
በኲር የጥቅምት 25 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም