ያልተሰማው ተማጽኖ

0
190

“ሰላም ሰፍኖ ትምህርት ቤቶች መቼ ይከፈታሉ፣ ስጋት የሌለበት ያልተቆራረጥ ትምህርት የምንማረውስ መቼ ይሆን?” ይህ ጥያቄ ከአንድ ዓመት ከመንፈቅ በላይ በተማሪዎች ሲጠየቅ፣ በወላጆች ሲደገፍ፣ በመምህራን እና የትምህርት ባለ ድርሻ አካላት ጥረት ሲደረግበት የከረመ ጉዳይ ነው:: ይሁን እንጂ በ2016 ዓ.ም ብቻ ከ2 ነጥብ 4 ሚሊዮን የሚበልጡ ተማሪዎች ከትምህርት ውጪ ሆነው አልፈዋል:: ከሦስት ሺህ በላይ ትምህርት ቤቶችም ሰኔ ላይ እንደተዘጉ ዓመቱን ደፍነዋል::

የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ በ2016 ዓ.ም ያጋጠመው ችግር በ2017 ዓ.ም እንዳይደገም አስፈላጊው ዝግጅት አድርጎ ተማሪዎችን በዘመቻ መልክ ለመመዝገብ ጥረት አድርጓል:: ሰባት ሚሊዮን ተማሪዎችን መዝግቦ ማስተማር ደግሞ ግቡ ነበር::

ይሁን እንጂ ያጋጠመው የጸጥታ ችግር በዓመቱ ለማሳካት ያቀደውን የተማሪ ቁጥር እንደቀደሙት ዓመታት ሁሉ በአጭር ጊዜ እንዳያሳካ አድርጎታል:: እስከ የካቲት 30 ቀን 2017 ዓ.ም የተማሪ ምዝገባ መርሀ ግብር በተቀመጠበት ሁኔታ በመጀመሪያው ወሰነ ትምህርት መመዝገብ የተቻለው ከ2 ነጥብ 7 ሚሊዮን ያልበለጡ ተማሪዎችን ብቻ መሆኑን የክልሉ ትምህርት ቢሮ አስታውቋል:: ከዚህም ውስጥ ከ400 ሺኅ በላይ የሚሆኑት ወደ ትምህርት ቤቶች አልሄዱም::

856 ትምህርት ቤቶች የሚገኙበት የሰሜን ወሎ ዞን በዓመቱ 444 ሺህ 652 ተማሪዎችን መዝግቦ ለማስተማር ዕቅድ ነበረው:: ይሁን እንጂ በጸጥታ ችግሩ ምክንያት ባለፉት ስድስት ወራት በተማሪ ምዝገባ ላይ የነበሩ ትምህርት ቤቶች ቁጥር 774 ብቻ መሆናቸውን የመምረያው ኃላፊ አቶ ሰጠ ታደሰ ተናግረዋል:: የተመዘገቡ ተማሪዎች ቁጥርም 265 ሺህ 530 ብቻ ናቸው:: በዚህም ቁጥራዊ አኃዝ መሠረት እስካሁን 179 ሺህ 122 ተማሪዎች አልተመዘገቡም:: ከተመዘገቡትም ውስጥ 62 ሺህ ተማሪዎች በትምህርት ገበታቸው ላይ አልተገኙም::

የደቡብ ጎንደር ዞን ምክትል አስተዳዳሪ እና የትምህርት መምሪያ ኀላፊ ደሥታ አስራቴ በበኩላቸው የጸጥታ ችግሩ በመማር ማስተማር ሂደቱ እና በትምህርት ተቋማት ላይ እያደረሰ ያለው ጉዳት ከፍተኛ መሆኑን ገልጸዋል:: ዞኑን ወደ ቀደመ ሰላሙ ለመመለስ ከሚደረገው ጥረት ጎን ለጎን ትምህርት ለማስጀመር እየተሠራ ያለው ሥራ የተሻለ መሆኑን ተናግረዋል::

ማኅበረሰቡ የልጆች ትምህርት መቋረጥ የለበትም ብሎ አቋም በያዘባቸው አካባቢዎች ትምህርት ቤቶች ተከፍተው ወደ መማር ማስተማር መገባቱን ኃላፊዉ ጠቁመዋል:: በዚህም በዞኑ ከሚገኙ አንድ ሺህ 173 ትምህርት ቤቶች ውስጥ 657ቱ በማስተማር ላይ ይገኛሉ::

የትምህርት መቋረጥ ምን ያህል ጉዳት እንደሚያደርስ ግንዛቤ ባልተፈጠረበት አካባቢ ደግሞ ትምህርት ተቋርጧል ነው ያሉት። በዚህም አሁንም 516 ትምህርት ቤቶች እንዳልተከፈቱ በስድስት ወራት ዕቅድ አፈጻጸማቸው ወቅት አስታውቀዋል::

በግጭቱ ከ685 በላይ ትምህርት ቤቶች ለጉዳት መዳረጋቸውን ጠቁመዋል:: ተቋማቱን ጠግኖ ወደ መማር ማስተማር ለማስገባት ከኅብረተሰቡ እና አጋር አካላት ጋር በትብብር እየተሠራ መሆኑን ገልጸዋል::

ባለፈው ዓመት በአንድ ትምህርት ቤት ብቻ የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና ያስፈተነው የሰሜን ጎጃም ዞን ዘንድሮም የችግሩ ስፋት አሳሳቢ እንደሆነበት አስታውቋል:: የትምህርት መምሪያ ኀላፊዉ ነጋልኝ ተገኝ በዞኑ ከሚገኙ 503 ትምህርት ቤቶች ውስጥ የስድስት ወራት የስራ እንቅስቃሴ እስከተገመገመበት ጊዜ ድረስ 448 ትምህርት ቤቶች ከተማሪ እና መምህራን ጋር አልተገናኙም:: በትምህርት ላይ የሚገኙት 55 ትምህርት ቤቶች እንደሆኑ ተመላክቷል:: መማር ከነበረባቸው 448 ሺህ ተማሪዎች ውስጥ በመማር ላይ የሚገኙት ከ30 ሺህ የማይበልጡት ብቻ መሆናቸው ለችግሩ ማሳያ ሆኖ ተጠቁሟል::

የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ የ2017 የትምህርት ዘመን የስድስት ወር ዕቅድ አፈጻጸም ግምገማውን በአዲስ አበባ አካሂዷል:: በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የማኅበራዊ ዘርፍ አስተባባሪ እና የትምህርት ቢሮ ኀላፊዋ ሙሉነሽ ደሴ (ዶ/ር) በ2017 ዓ.ም ለመመዝገብ ከታቀደው ውስጥ እስካሁን ማሳካት የተቻለው 40 በመቶ ብቻ መሆኑን አስታውቀዋል:: አሁንም ከአራት ሚሊዮን በላይ ተማሪዎች አልተመዘገቡም:: ከተመዘገቡትም ውስጥ 400 ሺህ የሚልቁት በትምህርት ገበታቸው ላይ አልተገኙም:: ሦስት ሺህ 337 ትምህርት ቤቶችም አልተከፈቱም:: ክልሉ ወደ ቀውስ ከገባ ጊዜ ጀምሮ ለተለያየ አይነት ጉዳት የተዳረጉት ትምህርት ቤቶች ቁጥር ከሁለት ሺህ በላይ መሆናቸው ሌላው የተጽእኖው ማሳያ ሆኖ ተነስቷል::

እንደ ዶ/ር ሙሉነሽ በሰሜኑ ጦርነት ባጋጠመው የትምህርት ቤት ፍርሰት 136 ሺህ ተማሪዎች ትምህርት ቤት አልሄዱም:: ውስጣዊ ግጭቱ በሰሜኑ ጦርነት የወደሙትን መልሶ ለመገንባት የሚደረገው ጥረት ሁሉ እንዳደናቀፈው ገልጸዋል:: በጦርነቱ ከወደሙ ከአራት ሺህ 200 በላይ ትምሀርት ቤቶች ውስጥ መልሶ መገንባት የተቻለው 10 በመቶ ብቻ መሆኑን ማሳያ አድርገው አንስተዋል::

ባለፈው ዓመት ከ58 በመቶ ያልበለጡ ተማሪዎች ትምህርታቸውን ሲከታተሉ መክረማቸውን ያስታወቁት ኃላፊዋ ሕጻናትን ከትምህርት በማራቅ አትራፊዉ ማነው፣ የሚያተረፉትስ ምንድን ነው ሲሉ ጠይቀዋል::

እስካሁን ያልተመዘገቡ እና ተመዝግበውም ከትምህርት የራቁ ተማሪዎች ቁጥር በዓለም አቀፍ ደረጃ በሀገርነት ከተመዘገቡ 106 ሀገራት የሕዝብ ቁጥር የሚበልጥ መሆኑ ተመላክቷል:: ታዳጊዎች ከትምህርት እንዲርቁ በማድረግ የሚፈጠረው የትውልድ ክፍተት ያሉት ዶ/ር ሙሉነሽ “ዛሬ ካላስተማርን ሀገር አሻጋሪ ትውልድ፣ ቤት ገንቢ ኢንጂነር፣ ሥራ ፈጣሪ አዕምሮዎች ያሳጣናል” ብለዋል። ይህም የትውልድ ክፍተት በተውሶ የማይሞላ ከባድ ውድቀት የሚያመጣ፣ የነገን ጉዞ የሚያደበዝዝ መሆኑን በማስመር ተናግረዋል::

ነጋቸውን በትምህርት ለማየት ወደ ትምህርት ቤት መሄድን ጓጉተው ይጠብቁ የነበሩ ታዳጊዎች ዛሬ ላይ ወደ ትምህርት ቤት እንዳይሄዱ በመደረጋቸው ብቻ ለስደት፣ ለያለ ዕድሜ ጋብቻ፣ ለጾታዊ ጥቃት እና ለተስፋ መቁረጥ መዳረጋቸውን ዶ/ር ሙሉነሽ ገልጸዋል::

ዶ/ር ሙሉነሽ የሰላም መደፍረሱ በታዳጊዎች ሕይወት ላይ እያደረሰ ያለውን ተጽኖ በመረዳት ለችግሩ ማብቃት ሁሉም የበኩሉን አስተዋጽኦ ሊወጣ እንደሚገባ አሳስበዋል::

(ስማቸው አጥናፍ)

በኲር የካቲት 3 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here