በሩሲያ ካንቲ ማንሲስክ ውስጥ የፋብሪካ ሰራተኛ የሆነ ግለሰብ ከሚሰራበት ኩባንያ ወደ ግል የሂሳብ ቁጥሩ በስህተት የገባለትን ስምንት ሚሊዬን ሰባት መቶ ሺህ ብር እንዲመልስ ተጠይቆ ፈቃደኛ ባለመሆኑ በፍርድ ቤት ተከሶ ክርክር ላይ መሆኑን ኦዲቲ ሴንትራል ድረ ገጽ ከሳምንት በፊት ለንባብ አብቅቶታል::
በያዝነው የአውሮፓውያኑ ዓመት መጀመሪያ ነበር 7,112, 254 “ሩብል” የሩሲያ ገንዘብ ወይም 8,700,000 ብር ከሚሰራበት ፋብሪካ ወደ ግል የሂሳብ ቁጥሩ የገባለት – ለቭላድሚር ሪጋቾቭ:: ገንዘቡ እንደደረሰው የሚሰራበት ፋብሪካ በዓመቱ ትርፋማ ሆኖ በማጠናቀቁ “ጉርሻ ለሰራተኞቹ ይሰጣል” የሚል ወሬ ሰምቶ ነበር እና የተናፈሰው ወሬ እውን ሆነ ብሎ ጮቤ ይረግጣል::
ብዙም ሳይቆይ ግን በስልክ ጥሪ ይጨናነቃል:: ከሚሰራበት ፋብሪካ የሂሳብ ክፍል በስህተት የ38 ሰራተኞች ደሞዝ ወደ ግል የሂሳብ ቁጥሩ እንደተላለፈለት ይነግሩታል:: ተመላሽ እንዲያደርግላቸው ቢጠይቁትም እምቢተኛ ይሆናል፡
በዚሁ መካከል ገንዘቡን ወደ ሌላ የባንክ ሂሳብ ቁጥር ሳያዘዋውር ኩባንያው ለባንክ በፃፈው ደብዳቤ ገንዘቡ ከእንቅስቃሴ ይታገዳል::
የሚሰራበት ኩባንያ የሕግ ክፍልም በፍርድ ቤት ክስ መስርቶ ክርክር ይጀመራል:: በመጀመሪያው ደረጃ የፍርድ ቤት ክርክርም ቪላድሚር ሪጋቾቭ ሰባት ሚሊዬን “ሩብሉ”ን መመለስ እንደሚጠበቅበት ይወሰናል:: ተስፋ ሳይቆርጥም ይግባኝ ያቀርባል- የመጀመሪያ ፍርድ ቤት የወሰነው ውሳኔ ይፀድቅበታል::
የ87 ሺህ ዶላር ወይም የ7,112,254 “ሩብል” የይገባኛል ክርክሩ ቀጥሏል:: በሩሲያ የሚገኙ መገናኛ ብዙሃንም ከተከሳሽም ሆነ ከከሳሽ የኩባንያው ኃላፊዎች ሁነቱን ለማጣራት ሞክረዋል:: የኩባንያው ከፍተኛ አመራር ተወካይ የሆኑት ሮሞን ቱዳችኮቭ የገንዘብ ዝውውሩ የተሳሳተ መሆኑን ጠቅሰው የፋብሪካው የህግ ክፍል ጉዳዩን ይዞ በስርዓቱ ለማስመለስ እየሰራ መሆኑን ከመጥቀስ ውጪ ተጨማሪ አስተያየት እንደማይሰጡ በመጥቀስ አደማድመዋል::
(ታምራት ሲሳይ)
በኲር የህዳር 8 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም


