ያልተከበረዉ ሕገ መንግሥታዊ ድንጋጌ

0
190

ማንኛውም ሰው ሰብዓዊ በመሆኑ የማይደፈር እና የማይገሰስ በሕይወት የመኖር፣ የአካል ደህንነት እና የነፃነት መብት እንዳለው ኢትዮጵያ በ1987 ዓ.ም ባጸደቀችው ሕገ መንግሥት አንቀጽ 14 ላይ ተመላክቷል:: ማንም ሰው በሕይወት የመኖር መብት እንዳለውና ሕግ ከሚደነግገው ውጪ የመኖር መብቱን ሊያጣ እንደማይችልም በአንቀጽ 15 በጉልህ ይታያል:: የአካል ደህንነት መብትን በተመለከተ በአንቀጽ 16 የሰፈረው ሐሳብም ማንኛውም ሰው በአካሉ ላይ ጉዳት እንዳይደርስበት የመጠበቅ መብት እንዳለው ደንግጓል::
ሕገ መንግሥቱ በስብእና ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎችን አስመልክቶ በአንቀጽ 28 እንዳሰፈረው ከሆነ ደግሞ እገታ ወንጀል ነው:: በመሆኑም በአስገዳጅ ሁኔታ ሰዎችን በሰወሩ ወይም ኢሰብዓዊ የድብደባ ድርጊቶችን በፈጸሙ ሰዎች ላይ ክስ ማቅረብ በይርጋ አይታገዱም፤ በሕግ አውጪው ክፍልም ሆነ በማንኛውም የመንግሥት አካል ውሳኔዎች በምሕረት ወይም በይቅርታ አይታለፉም በማለትም አስፍሯል:: ታዲያ እነዚህ የመብት ድንጋጌዎች መሬት ላይ ካለው እውነታ ጋር ለምን ተቃረኑ? የሚለው ሐሳብ የትንታኔያችን አንኳር ጭብጥ ነው::
ኢትዮጵያ አሁን ባለችበት ዘመኗ ከፍተኛ የርስ በርስ ግጭት መገለጫዋ ሆኗል:: በተለይም ከጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም ጀምሮ አሁንም ድረስ አማራ ክልልን ጨምሮ በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች የቀጠለው ግጭት ንጹሀንን ለሞት እና ለአካል ጉዳት እየዳረገ ይገኛል::
በእጅጉ አሳሳቢ እየሆነ የመጣውን ግጭት ተከትሎ ግለሰቦችን በማገት ገንዘብ ለማግኘት የሚደረጉ ጥረቶች እየተበራከቱ መምጣታቸው ይገለጻል:: ይህም ኢትዮጵያ በሕገ መንግሥቷ ልዩ ትኩረት ሰጥታ ያጸደቀችውን የሰብዓዊ መብት ድንጋጌዋን እንዳታከብር አድርጓታል ወደሚል ድምዳሜ ይወስዳል::
አዲስ ማለዳ የታጋቾችን ሰብዓዊ መብት ከማስከበር ጋር በተያያዘ ዓለም አቀፉ የቀይ መስቀል ኮሚቴ አሳወቀ ብሎ በ2015 ዓ.ም እንደዘገበው ኢትዮጵያ ከመንግሥት የጸጥታ ኀይሎች ውጭ በታጣቂዎች እገታ ከሚፈጽምባቸው ቀዳሚ ሀገራት መካከል አስቀምጧታል:: ኮሚቴው በርካታ ታጋቾች ካሉባቸው ሀገራት መካከል ኮንጎ፣ ሶሪያ፣ ኮሎምቢያ እና ኢትዮጵያ ዋነኞቹ መሆናቸውን ጠቁሟል::
እገታ መቼና እንዴት ይፈጠራል ብሎ መጠየቅም ተገቢ ነው:: እገታ በኢትዮጵያ ልክ እንደ አሁኑ በግልጽ ባይሆንም ባለፉት ዓመታት ከሕዝብና ከፀጥታ ኀይሎች ወጣ ብለው በሚገኙ አካባቢዎች ይፈጸም ነበር::
ኢትዮጵያ ወደ ከፍተኛ የርስበርስ ግጭት ከገባችበት ከ2013 ዓ.ም ወዲህ ግን ችግሩ እየሰፋ መጥቷል:: ለእገታው የሚጠየቀው የገንዘብ ዝውውር የሚፈጸመውም በባንክ በኩል መሆኑ እገታ በግልጽ እየተፈጸመ ለመሆኑ ማሳያ ነው:: ታዲያ ይህ ሐሳብ የሚያስረዳው መንግሥት ለሰብዓዊ መብቶች ድንጋጌ ትኩረት ካለመስጠቱም ባሻገር የተጠያቂነት ሥርዓቱ የላላ መሆኑን የሚያመላክት ነው:: ሌላው ለችግሩ መከሰት የመንግሥት ሰላምና ደኅንነትን የማስጠበቅ አቅም መዳከም ነው ተብሎ ይታሰባል:: በአሁኑ ወቅት ያለው የርስበርስ ግጭት ደግሞ ችግሩ እንዲባባስ አድርጓል የሚሉ አሉ::
እገታ እና ግድያ በኢትዮጵያ በተጨባጭ እየተፈጸመ ለመሆኑ በመንግሥት በኩል በተደጋጋሚ መግለጫ የተሰጣቸው ሐሳቦች ያስረዳሉ:: ኅዳር ወር 2012 ዓ.ም ከደምቢ ዶሎ ዩኒቨርሲቲ ወደ መኖሪያ ቀያቸው ሲመለሱ የነበሩ ተማሪዎች መታገታቸው፣ ከአማራ ክልል ወደ አዲስ አበባ የሚገቡ መንገደኞች እየታገቱ ገንዘብ መጠየቃቸው፣ በሀገሪቱ አማራ ክልልን ጨምሮ የተከሰተውን ግጭት ተከትሎ ሰዎችን አስገድዶ በመሰወር የማይደፈር የገንዘብ መጠን መጠየቅ የተለመደ እየሆነ መጥቷል:: ማንነትን መሰረት ባደረገ ፍረጃ ዜጎች በነጻነት ተንቀሳቅሰው መሥራት አልቻሉም::
ስማቸው እንዳይገለጽ የፈለጉና ነዋሪነታቸውን በሰሜን ጎንደር ዞን አዲአርቃይ ወረዳ ነዋሪው ግለሰብ አማራ ክልል የተፈጠረው የጸጥታ መደፍረስ ሰዎች ከቦታ ቦታ ተንቀሳቅሰው እንዳይሰሩ፣ ተማሪዎች ተረጋግተው ትምህርታቸውን እንዳይከታተሉ ይልቁንም ማቋረጥን አማራጫቸው እያደረጉ መጥተዋል:: ከምንም በላይ ደግሞ የሰዎች እገታ አሳሳቢ እየሆነ መምጣቱን ተናግረዋል:: የሚጠየቀው ገንዘብ ደግሞ ከአቅም በላይ መሆኑ ብዙዎች ሕይወት ለማዳን ሲሉ ለልመና መዳረጋቸውን ገልጸዋል:: ይሁን እንጂ የፀጥታ ችግሩ ከኑሮ ውድነቱ ጋር ተዳምሮ የተጠየቀውን ገንዘብ በልመና ለማግኘት ፈተና ሆኗል ይላሉ:: በክልሉ እየተስተዋለ ያለው ግጭት የክልሉን ሕዝብ ያልተገባ ዋጋ እያስከፈለው ነው ያሉት ግለሰቡ መንግሥትም ሆነ ተፋላሚ ኃይሎች ፍላጎቶቻቸውን በሰላማዊ መንገድ ማሳካትን አስበው እንዲንቀሳቀሱ ጠይቀዋል::
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የእገታ ወንጀል አሳሳቢ እየሆነ መምጣቱን በሰብዓዊ መብት ላይ ትኩረት አድርገው የሚሠሩ አካላት ይገልጻሉ:: የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባዔ (ኢሰመጉ) የካቲት 19 /2016 ዓ.ም” በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች እየተፈጸመ ያለው እገታ እና ግድያ መንግሥት የዜጎችን ደህንነት የመጠበቅ ኃላፊነቱን በአግባቡ እየተወጣ አለመሆኑን በግልጽ የሚያሳይ ነው” ብሏል::
ጉባዔው በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ምሥራቅ ሸዋ ሀገረ ስብከት ዝቋላ ደብረ ከዋክበት አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ገዳም በአምስት አባቶች ላይ የካቲት 1 ቀን 2016 ዓ.ም በታጣቂዎች የተፈጸመውን እገታ እና ግድያ ማሳያ አድርጎ ያነሳል:: ከታገቱትም ውስጥ አራቱ መገደላቸውን በማስታወቅ ድርጊቱን አውግዟል::
በገዳሙ ላይ ጥቃቱን የፈጸሙ አካላት ቀደም ብለውም በገዳሙ ላይ ጉዳት ማድረሳቸውን ጉባዔው አስታውቋል:: ነገር ግን የሚመለከተው አካል ጊዜውን የጠበቀ ተገቢውን ምላሽ ባለመስጠቱ አሁን ላይ በተፈጸመው ድርጊት የከፋ ጉዳት መድረሱን አስታውቋል::
ጉባዔው የካቲት 6 ቀን 2016 ዓ.ም በባለ ሦስት እግር ተሸከርካሪ/ በባጃጅ/ ተሳፍረው ከአጣዬ ወደ ኤፍራታናግድም ወረዳ ሲጓዙ የነበሩ በስድስት ንጹሃን ዜጎች ላይ የተፈጸመውን ግድያ በመጠቆም መንግሥት ለዜጎች ደኅንነት ትኩረት ሰጥቶ እንዲሠራ ጠይቋል::
በመሆኑም የፌዴራል መንግሥቱ እየተፈጸሙ ላሉ የእገታ ድርጊቶች ተገቢውን በቂ ትኩረት እንዲሰጥ እና ፈጻሚዎችን ተጠያቂ እንዲሆኑ የሚያስችሉ ሕጎችን እና ፖሊሲዎችን በማርቀቅ ተፈጻሚ የሚሆኑበትን መንገድ እንዲያመቻች ኢሰመጉ ጠይቋል::
ዜጎች ከቦታ ቦታ ተንቀሳቅሰው ሀብት እና ንብረት የማፍራት መብታቸውን እንዲያረጋግጡ በተለያዩ ቦታዎች የሚንቀሳቀሱ ታጣቂ ቡድኖች ሰላማዊ መንገድን አማራጭ የትግል ስልት አድርገው ወደ ንግግር እንዲመጡ አስታውቋል:: የሚዲያ አካላት፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የማህበረሰብ አንቂዎች፣ የሰብዓዊ መብት እና ሰላም ግንባታ ላይ የሚሠሩ አካላት በሀገሪቱ ዘላቂ ሰላም እንዲመጣ የበኩላቸውን አሰተዋጽኦ እንዲወጡ ጥሪ ቀርቧል::
ስድስተኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 3ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 14ኛ መደበኛ ስብሰባ በተካሄደበት ወቅት ደግሞ ከምክር ቤት አባላት ለተነሱ ጥያቄዎች ምላሽ እና ማብራሪያ የሰጡት ጠ/ሚ ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የራስን ሕዝብ በማሰቃየት እና ስቃዩን በማራዘም የፖለቲካ ትርፍ ለማግኘት የሚደረግ የትግል ስልት ከመጠፋፋት ያለፈ ትርጉም እንደማይኖረው ገልጸዋል:: ለአብነት የሸኔ እንቅስቃሴን ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ሸኔ በአሁኑ ወቅት ተሰማርቶ የሚገኘው ተሽከርካሪ ማቃጠል፣ ግለሰቦችን ማገት፣ ልማት እንዳይሠራ ማድረግ ላይ መሆኑን ተናግረዋል::
ቡድኑ በረሀ የገባው እታገልልሀለሁ ለሚለው ሕዝብ መብት፣ ልማት እና ሰላም ተጨንቆ ከሆነ ያንኑ ሕዝብ ማገት፣ ልማትን ማስተጓጎል፣ ዘረፋ መፈጸም ዓላማው በተቃርኖ ላይ የቆመ መሆኑን የሚያረጋግጥ መሆኑንም አንስተዋል::
“ሕዝብን በማሰቃየት የሥልጣን ፍላጎታቸውን ለማሳካት የሚጥሩ አካላት ሕዝብን የማስተዳደር ዕድሉን ቢያገኙ በምን ሞራል ነው ያገቱትን፣ የገደሉትን፣ የዘረፉትን እና ከልማት ውጪ ያደረጉትን ሕዝብ መምራት የሚችሉት?” ሲሉ ጥያቄ አዘል ሀሳባቸውን ገልጸዋል:: በመሆኑም ሁሉም አካላት ከጥፋት መንገድ ወጥተው ለሀገራዊ አንድነት ወደ ሰላም መድረክ እንዲመጡ ጠይቀዋል::
መንግሥት ግጭትና ጦርነቶችን በሰላማዊ መንገድ ከመፍታት ጎን ለጎን ሰላማዊ በሆኑ አካባቢዎች ሳይቀር እየተፈጸሙ ያለውን የሰዎች እገታ እና ግድያ ያለበትን አሁናዊ ሁኔታ በመመልከት ዘላቂ መፍትሄ ሊያስቀምጥ ይገባል:: በመሆኑም በድርጊቱ ተሳታፊ የሆኑ አካላትን በፍጥነት ወደ ሕግ በማቅረብ ተጠያቂ ማድረግ፣ እገታ በተደጋጋሚ የሚፈጸምባቸውን አካባቢዎች ለይቶ ልዩ ጥበቃ ማድረግ፣ ጠንካራ የፀጥታ መዋቅር መገንባትና ከሕዝብ ጋር ያለን ግንኙነት ማጠናከር እገታና የፀጥታ ስጋት በዘላቂነት መፍትሄ እንዲያገኝ አማራጭ የመፍትሄ ሐሳቦች ናቸው::
(ስማቸው አጥናፍ)
በኲር መጋቢት 2 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here