ያልተኮረጁ ህልሞች

0
148

አስረስ የዩኒቨርሲቲ መግቢያ ውጤት አምጥቶ ሰላሌ ዩኒቨርሲቲን ከተቀላቀለ ድፍን አንድ ወር ሆነው። ሰንቆት ከመጣው ተስፋ በቀር በሶውም ሆነ ዳቦ ቆሎው አልቋል። በትንሹም ቢሆን ዩኒቨርሲቲውን መላመድ ጀምሯል። ጠይም ቀጠን ያለና ጥሩ የሚባል መካከለኛ ቁመት ያለው ሲሆን የወቅቱ ቀዝቃዛ አየርና የሚነፍሰው ነፋስ ተደማምረው ትንሽ ጠቆር አድርገውታል።

በተደረገው የትምህርት ክፍል ምርጫ የአማርኛ ቋንቋና ስነ-ጽሁፍን መርጧል። የትምህርት ክፍሉ ከስነ-ጽሑፍ ዝንባሌው ጋር የሚሄድ በመሆኑ ወዶታል። ነገር ግን ጓደኞቹ ሌሎች የትምህርት ክፍሎችን መምረጥ የሚያስችል ጥሩ ውጤት እያለው ይሄን የትምህርት ክፍል በመምረጡ እንደ ቂል ይቆጥሩት ጀምረዋል። ከዚህ ሁሉ በላይ ለአስረስ ከባድ የሆነበት ቤተሰቦቹን እንዴት እንደሚያስረዳቸው ነው፤ በተለይ አባቱን!

እናቱ እንኳ ከልጃቸው ደህንነት በቀር ይሄን ያህል የትምህርት ነገር የሚያሳስባቸው ሰው አልነበሩም። ከዚህ ይልቅ የዳቦ ቆሎውና በሶው ማለቅ አሳስቧቸዋል። በደወሉ ቁጥር “ጨምረህ ያዝ እያልኩህ እምቢ ብለህ ይሄው በራብ ልትሞት ነው” ይሉታል። ስለ ግቢው አጠቃላይ የምግብ ሁኔታ ሊያስረዳቸው ቢሞክርም “ኤዲያ! ከዛ ሁሉ እልፍ አላፍ ተማሪ ጋር ተሻምተህ በልተህስ ጎንህ ሊቀና” ይሉታል በምሬት። ስቆ ዝም ይላቸዋል። ህልም ባዩ ቁጥር ሌሊት ነው ቀን ነው ሳይሉ ወዲያው ይደውላሉ።

“ልጄ በተስኪያን አትቅር! እሱን ያመነ ወድቆ አይወድቅም፤ ጉም ማይሸፍነው፣ ተራራ ማይጋርደው አምላክ ይጠብቅህ!”ይሉታል። ሁሌም የወሬያቸው ማሳረጊያ ይሄ ነው።

አንድ ቀን ቅዳሜ ጧት ተነስቶ ቤተ-ክርስቲያን ደርሶ ከመጣ በኋላ ለአባቱ ለመደወል ወሰነ።  ላመነበት ነገር ፈጣን የውሳኔ ሰው ነው። ደወለላቸው፤ እሳቸውም እንደተለመደው ስልኩን ፈጥነው አነሱና ሰላምታ ከተለዋወጡ በኋላ ሳያመነታ ወደ ጉዳዩ ገባ፤ ወደ ገደለው እንዲሉ።

“አባባ! የምንማረውን ትምሕርት ክፍል መረጥን’ኮ።”

“ እንዴ ልጄ መልካም እንጂ፣ ታዲያ ምን መረጥክ አስረሴ?”

“ኧይ…አባዬ የመረጥኩት እንኳ የምፈልገውን ነው፤ ነገር ግን ህግ አይደለም” አላቸው።

“ኧይ የኔ ልጅ! ምንስ ቢሆን ለኛ ደስ የሚለን ለዚህ መብቃትህ ነው። የኛ ወረታ፤ የኛ ካሳ’ኮ ይሄው ነው።

ለመሆኑ ምን መረጥክ ልጄ? “

አስረስ ድምፁ እየተቆራረጠ መለሰ፣

“ አባዬ የ…መረጥኩት የአማረኛ ቋንቋና ስነ-ጽሑፍ ነው። አንተ ህግ እንድማር ብትፈልግም እኔ ግን ይሄን መረጥኩ፤ ይቅርታ!” ብሎ ከአባቱ የሚመጣውን መልስ በጉጉት መጠባበቅ ጀመረ። አባቱ ምንም የጠባይ ለውጥ ሳይታይባቸው ቀጠሉ።

“ኧይ ልጄ! ይቅርታው ለምኑ ነው? ሕይወትህ ያንተ ነው፤ ያንተን ህይወት እኔ አልኖርልህም። ስለዚህ ምርጫውም ያንተነው ሊሆን ሚገባ” አሉ አባቱ ፍፁም በተረጋጋ አንደበት። አስረስ ፍርሃቱ ለቀቀው። “ አመሰግናለሁ አባቴ!” አለ ድንገት እንባውን መቆ ጣጠር እያቃተው።

“ልጄ! እኔ ለሰላሳ ዓመታት ፍርድ ቤት ደጃፍ ተቀምጨ ማመልከቻ እየፃፍኩ ኑሬያለሁ፤ ስለዚህ ዘወትር የህግ ባለሙያዎችን አያለሁ፤ ልጄም ተምረህ እንደነሱ እንድትሆን እፈልግ ነበር፤ ይሄ የኔ ምኞት ነው ልጄ፣ ከምኞት ያለፈ አይደለም። ስለዚህ ሳትሳቀቅ የመረጥከውን ተማር። የትምህርት ቀላል አሊያም ርካሽ የለውም፤ ሁሉም ዋጋው ውድ ነው። ልጄ! እንኳን ሌላ፣ ቃል ገጣጥሞ ማመልከቻ መፃፍ’ኮ ይቸግራል” አሉ ለስለስ ብሎ ምክር ባዘለ የድምፅ ቃና። አስረስ ቀኑን ሙሉ በአባቱ ንግግር ተደስቶ ዋለ።

ቢሆንም ግን አጎቱን ማስረዳት እንደቀረው ትዝ ሲለው እንደገና በሀሳብ ተዋጠ። አጎቱ የሒሳብ መምህር ናቸው፤ ቁጥር የሌለው ነገር እንደማይጥማቸው ያውቃል። ሲያመነታ ከቆየ በኋላ ወዲያው ደወለላቸው። ደውሎላቸው የተለመደ ቁጥብ ሰላምታ ከተለዋወጡ በኋላ ጉዳዩን አጠር አድርጎ አስረዳቸው። አጎቱ እንደተለመደው ንግግራቸውን በረጅሙ አየር ስበው ጀመሩ፣ “ዌል እ..እ ልጅ አስረስ የትምህርቱን ይዘት በደምብ ተረድተኸው የወሰንክ አልመሰለኝም! ለመሆኑ የቁጥር ትምህርት አለው?” ሲሉ ነገሩ ባልጣመው የድምፅ ቃና ጠየቁ። አስረስ እንደሌለው ጠቅሶ ስለትምህርቱ ይዘት የተወሰነ አብራራላቸው።

አጎቱ ንግግሩን በደምብ ካደመጡ በኋላ ቀጠሉ፣

“ ልጅ አስረስ ግጥም የሚያጠና አስለቃሽ ነው፤ ቅኔ ያልክ እንደሆነም ምንም ብትራቀቅ ከተዋነይ እልፍ አትልም! ቃል አገባቡን እንደሆነም ሩቅ ሳትሄድ አባትህ ያስተምርህ የለም?ለመሆኑ ለአባትህ ነግረኸዋል?”

“ አዎ!”

አለ አስረስ ፊቱን ቅጭም አድርጎ።

“ምን አለህ?” አሉ መልሰው።

“ምንም?” አስረስ መለሰ።

“ ልጅ አስረስ ቁጥር እንደ ጨው ነው፤ ቁጥር የሌለበት ነገር አይጣፍጥም። ዓለምና የሰው ልጅ የተፈጠረው በቁጥር፤ በቀመር ነው። ይሄን እንዴት ትዘነጋለህ?” አሉት።

አስረስ ሲፈራ ሲቸር መልስ ሰጠ፣

“ አጎቴ! በሱ ካየነውማ’ኮ ቃል የሌለበት ምንም ነገር የለም ማለት ይቻላል። ታላቁ መፅሐፍ ቅዱስ እንኳ ‘መጀመሪያ ቃል ነበረ..’ ይላል” አላቸው።

አጎቱ ለማስረዳት ብዙ ጥረት አድርገው አድማጭ እንዳላገኙ ሲገባቸው ተሰናብተው ስልኩን ዘጉ። አስረስ ቅልል አለው ፤  ነገር ግን ስለአጎቱ የስልክ ንግግር ማሰላሰል ማቆም አቃተው።

አስረስ አምሽቶ ወደ ዶርም ሲመለስ ጓደኛው ብቻውን እያለቀሰ አገኘው፤ ግራ ገብቶት የሚያለቅስበትን ምክንያት እንዲነግረው ወተወተው። ልጁ ከተወሰኑ ደቂቃዎች በኋላ ተረጋግቶ ማውራት ጀመረ።

“ዛሬ ጓደኞቼ ተሳለቁብኝ” አለ ልጁ።

“ለምን” ጠየቀ አስረስ።

“ያው የትምህርት ክፍል ምርጫዬ ግብርና በመሆኑ ነው” ልጁ መለሰ።

“ ታዲያ ምን ነውር አለው?”

አስረስ ግራ ተጋብቶ ልጁን አተኩሮ እየተመለከተ ጠየቀው። ልጁ ትንሽ ፋታ ወስዶ ማሰላሰል ጀመረ።

“ምን እንዳሉኝ ታውቃለህ? ‘ከግብርና ግብርናማ ለምን እዚህ ድረስ ትለፋለህ? አባትህ በደምብ ያስተምርህ አልነበር’ እያሉ መሳለቂያ አደረጉኝ” ብሎ አንገቱን ደፍቶ ማሰላሰሉን ቀጠለ። ልጁ ትንሽ አሰብ ካደረገ በኋላ ንግግሩን ቀጠለ፥

“ከግማሽ በላይ የሚሆኑ ዜጎቿ በግብርና ሙያ ተሰማርተው ለሚተዳደሩባት ሃገር በውኑ ግብርናን ማጥናት የሚናቅ ጉደይ ነው? ይሄ ጉደይስ ስልጣኔ መሆን ይችላል? ለዘመናት በበሬ እያረስን፣ ገበሬዎቻችን እንደ ድካማቸው ምርት ማግኜት ባለመቻላቸው በደምበር ገፋኸኝ ገፋኸኝ ሰበብ በየፍርድ ቤቱ ሲካሰሱ እየዋሉ ግብርናን ማጥናት ታዲያ እንዴት እንደ ቀላል ይወሰዳል?” አለ ልጁ በምሬት። አስረስ በመገረም ሲያዳምጥ ቆየና ድምፁን ለስለስ አድርጎ ንግግሩን ጀመረ።

“ ይሄን ጉደይ ባንተ ብቻ የደረሰ አድርገህ አትመልከተው፣ በሁላችንም የደረሰ ነው። ከፈተና ኩረጃ እኩል ህልምና ርዕይም ይኮረጃል፤ የአብዛኛው ተማሪ ህልም የተኮረጀ ነው። የራስ ያልሆነን ህልም ለማሳካት መጣር ደግሞ  ልፋት ነው። ለማሸነፍና ውጤታማ ለመሆን የምትወደውንና የምታውቀውን ጨዋታ መጫዎት አለብህ ይባልየለ?” አለ አስረስ ትከሻውን እየሰበቀ። ብዙ ከተጨዋወቱ በኋላ የሰላሌ ነፋስ በስሱ መንፈስ ስለጀመረ ተያይዘው ወደ ዶርማቸው አዘገሙ፤

ዓመታት ነጎዱ ከእለታት አንድ ቀን አዳራሹ በሰው ተሞልቷል፣ ተማሪዎች የመመረቂያ ጋዎናቸውን አድርገው ከወዲያ ወዲህ ይንጎራዱዳሉ። “እንኳን ደስ አላችሁ” የሚለው ጥዑም ዜማ ተከፍቷል። ከወዲያ ወዲህ የተማሪዎች የደስታ ጩኸት ይሰማል። አብዛኞቹ ተማሪዎች በናፍቆት እየተቃቀፉ የማስታወሻ ፎቶ ይነሳሉ። የተቀሩት ደግሞ ሊያስመርቋቸው ከመጡ ቤተሰቦቻቸው ጋር እየተጨዋወቱ ይሳሳቃሉ።

ከጥቂት ደቂቃ በኋላ መርኀ ግብሩ ተጀመረና በአዳራሹ ፀጥታ ሰፈነ። ተጋባዥ እንግዶች በየተራ መልዕክታቸውን አስተላለፉ። የምረቃ ስነ-ስርዓቱ ሪቫን በማዞር ተከናወነ፤ የየብሔረሰቡ ሙዚቃ በየተራ ተጨፈረ። መርሃግብሩ ተገባዶ የሽልማት ስነ-ስርዓቱ ብቻ ቀረ። የዓመቱን የዋንጫና የሜዳሊያ ተሸላሚ ተማሪ መድረክ መሪዋ ለጆሮ በሚማርክ ድምፅ አስተዋወቀች። ከጥቂት አፍታ በኋላ አንድ ጠይም፣ ቀጠን ያለ ወጣት አንገቱን ደፍቶ ፈጠን ፈጠን እያለ ወደ መድረኩ ወጣ። ልጁ ሽልማቱን ከተቀበለ በኋላ የድምፅ ማጉያውን ተቀብሎ የሚከተለውን መልዕክት አስተላለፈ፣

“ካልበረቱ የትምህርት ቀላል፣ ከበረቱ የትምህርት ከባድ፣ ሚዛናዊ ከሆኑ ርካሽ የሚባል ነገር በትምህርት ዓለም የለም!” ወሳኙ ነገር በተማሩበት እና በተሰማሩበት ሙያ ራስን እና ሀገርን መጥቀም ነውና ሁላችንንም የተግባር ሰው ያርገን! አመሰግለሁ! ሲል ጭብጨባው ቀለጠ፤ ለተሳታፊዎች እጅ ነስቶ ከመድረክ ሲወርድም ‘‘ኦስረስ! አስረስ! በሚል የደስታ ጩኸት የደመቀ የተመራቂዎቹ ጪብጨባ አጀበው፡፡

(ደረጀ ደርበው)

በኲር የካቲት 17 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here