ያልተገባ የተጨዋቾች ባህሪ እና መዘዙ

0
180

በሙያቸው የበቁ (profissional) የእግር ኳስ ተጫዋቾች ሥራቸውን ያከብራሉ፤ ለሙያቸውም ይታመናሉ፤ ለለበሱት መለያ የሚዋደቁ ናቸው።በሜዳ ውስጥም ሆነ ከሜዳ ውጪ ከዓላማቸው ዝንፍ የማይሉ እንደ አለት የጠነከረ ስብዕና ያላቸው እንደ ሆኑ የፊፋ ዶት ኮም (Fifa.com) መረጃ ያመለክታል።
ምንም እንኳ በጥናት ላይ የተደገፈ ባይሆንም ብቁ በሆኑ የእግር ኳስ ተጫዋቾች መመዘኛ በየደረጃው ባሉ የሀገራችን የእግር ኳስ ሊጎች የሚጫወቱ ተጫዋቾች ከደረጃ በታች መሆናቸውን በርካታ የዘርፉ ባለሙያዎች ያምናሉ። የተጫዋቾቹ በሙያቸው ብቁ (professional) አለመሆን ለእግር ኳሱ እድገት አንደኛው መሰናክል ተደርጎም ይወሰዳል። አንድ ተጫዋች በሙያው ብቁ (professional ) ስለመሆኑ ከሚገለጽባቸው መገለጫዋች፣ ሜዳ ውስጥ የሚያሳየው ባህሪ አንዱ ነው። ይህም በሀገራችን ዋነኛው ችግር ሆኖ በተደጋጋሚ ይነሳል። በሀገሪቱ በሁሉም የሊግ እርከኖች የሚገኙ ተጫዋቾች በሚያሳዩት ያልተገባ ባህሪ ብዙ ጊዜ የእግር ኳስ ሜዳዎች ወደ ጦር ሜዳነት ተቀይረው የተመለከትንበት አጋጣሚ ጥቂት አይደለም። በሁሉም የሊግ እርከን የሚገኙ ዳኞች በተጨዋቾች ተደብድበዋል፣ተዋክበዋል፣ በአጠቃላይ ኢ ሰባዊ ድርጊት ተፈፅሞባችዋል፡፡ በማስፈራራት ውሳኔያቸው ላይም ተጽዕኖ አሳድሮባቸዋል። ይህ ደግሞ በራሳቸው እና በቤተሰባቸው ላይ ከፍተኛ የሥነ ልቦና ጉዳት በማድረስ የራስ መተማመናቸው እንዲሸረሸር አድርጓል። ይህም የኋላቀሩ እግር ኳሳችን አንዱ መገለጫ መሆኑን ማሳያ ነው።
በቅርቡ በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ በሰባተኛ ሳምንት መርሐ ግብር ባህር ዳር ከተማ ሀዋሳ ከተማን 2ለ1 ማሸነፉ ይታወሳል። በዚህ መርሐ ግብር የሁለቱም ክለብ ተጫዋቾች ዋና ዳኛው ስህተት ፈፅሟል በሚል ሲያዋክቡት ተመልክተናል። በዳኛው ላይ የደረሰውን ይህንን ወከባም፣ ብዙ የስፖርት ቤተሰብም ድርጊቱ ተገቢ ያልሆነ ነው በማለት ኮንነውታል።
ፕሪሚየር ሊጉ በቀጥታ የቴሌቪዥን ስርጭት በዲኤስቲቪ (DSTV) ስለተላለፈ ይህንን አሳፋሪ ድርጊት በቀላሉ በቴሌቪዥን መሰኮት ሁሉም ተመልክቶታል። የቀጥታ ስርጭት በማያገኙት በሌሎቹ የሊግ እርከኖች፣ ጨዋታዎችን የሚመሩ ዳኞች የከፋ ችግር እንደሚገጥማቸው አያጠያይቅም። ዘርፉ አሁን ባለበት ደረጃ ዳኞቹ ለምን? ተሳሳቱ አይባልም። የእግር ኳስ ስፖርት በተሻለ ደረጃ ባደገባቸው ሀገራት ሳይቀር በየጨዋታዎች ዳኞች ስህተት ሲሠሩ ማየት እንግዳ አይደለም። ችግሩ ከዚህ በፊትም የነበረ፣ ወደፊትም የሚቀጥል ነው።
በእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ከቅርብ ዓመታት ጀምሮ ጨዋታዎች በተንቀሳቃሽ የምስል ዳኝነት(VAR) ጭምር እየታገዙ ይገኛል። እንደዚህም ሆኖ የዳኞችን ጫና በማቅለል ችግሮችን በተወሰነ መልኩ ቀነሰ እንጂ ፣ሙሉ በሙሉ ግን ሊያጠፋ አልቻለም። ታዲያ እንደዚህ ዓይነት የላቀ ቴክኖሎጂ በሚጠቀሙ ሀገራት ችግሩ ሙሉ በሙሉ መፍትሄ ካላገኝ እንደ ኤሊ በሚጓዘው የእግር ኳስ እድገት ውስጥ በቀላሉ መፍትሄ ይገኛል ተብሎ አይታሰብም። የሚመለከታቸው አካላት ትኩረት ሰጥተው ከሰሩ ችግሩን ግን መቀነስ እንደሚቻል መዘንጋት የለበትም። በሌሎቹ ሀገራት የእግር ኳስ ዳኝነት ሙያ፣ እንደ አንድ መደበኛ ሥራ እንደሚሠራ ይታወቃል። በኢትዮጵያ ግን ከቀደሙት ጊዜያት ጀምሮ እንደ ተደራቢ ሥራ ተይዞ ጎን ለጎን መሠራቱ በሀገራችን ለሙያው ትኩረት አለመሰጠቱን ያሳያል።
የፌደራል ዳኛ አማን ሞላ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግን ለዓመታት በዳኝነት ሲያገለግል ቆይቷል። አሁንም እያገለገለ ይገኛል። የጨዋታ ሕጎችን (Laws of the game) በተመለከተ ሲያስረዳ ከ17ቱ የእግር ኳስ ጨዋታ ሕጎች መካከል ፣ ጥፋት እና ያልተገባ ባህሪ 12ኛ ሕግ ሆኖ መቀመጡን ያብራራል። አንድ ተጫዋች ከኳስ ጋር በታጋጣሚ ቡድን የሚሠራው ተገቢ ያልሆነ ድርጊት ጥፋት እንደሆነ በዳኞቹ ይታመናል። ያልተገባ ባህሪ ደግሞ አንድ ተጫዋች ከኳስ ጋር ግንኙነት ሳይኖረው የሚፈጽመው የሥነ ምግባር ግድፍት ነው። ይህም ጨዋታውን በሚመሩት ዳኞች ላይ የሚፈፀም ተገቢ ያልሆነ ድርጊትንም ያካትታል። የጥቃቱ ሰለባ የሚሆኑ ዳኞችም በሕጉ መሰረት፣ ለራሳቸው ውሳኔ የማስተላለፍ ኃላፊነት ተሰጥቷቸዋል።
ይሁን እንጂ በወቅቱ ሜዳ ላይ የነበሩት ዳኞች መወሰን ካልቻሉ አወዳዳሪው አካል በሚደርሰው በተቀረፀ ምስል እና ማስረጃ እርምጃ ይወስዳል። ተጫዋቾች በዳኞች ላይ በሚያሳዩት ያልተገባ ባህሪን በተመለከተ ግን ራሳቸው ውሳኔ የማስተላለፍ ግዴታ እንዳለባቸው ሕጉ እንደሚያስረዳ ባለሙያው አማን ሞላ ያስገነዝባል። ተጫዋቾቹ ውጤት በመፈለግ ከዳኞቹ ጋር እሰጣ ገባ ውስጥ በመግባት በአጠቃላይ ያልተገባ ባህሪ ማሳየት አንዱ የጨዋታው አካል እስኪመስል ድረስ በሀገራችን በሁሉም ሊጎች ባህል እየሆነ መጥቷል። ይህ ችግር የሚፈጠረውም አንደኛ ጨዋታውን የሚመሩ ዳኞቹ በትክክል ሕጉን ሲያስከብሩ፣ ተጫዋቾቹ በመበሳጨት በዳኞቹ ላይ ያልተገባ ባህሪ ያሳያሉ።
ሁለተኛው ደግሞ ዳኞቹ ተገቢ ያልሆነ ውሳኔ ሲወስኑ(ስህተት ሲሠሩ ) መሆኑን የፌደራል ዳኛው አማን ያስረዳል። ችግሩም የከፋ እና አሳሳቢ ደረጃ ላይ ደርሷል። በቀጥታ የቴሌቪዥን ስርጭት በሚተላለፈው የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ መሰል ተደጋጋሚ ችግር ተመልክተናል።
ከፕሪሚየር ሊጉ በታች ባሉ በሌሎች የሊግ እርከኖች ግን ጉዳዩ ከዚህም የከፋ መሆኑን የዘርፉ ባለሙያ ተናግሯል። በተለይ የከፍተኛ ሊግ ፣ የአንደኛ ሊግ፣ የአማራ ሊግ ጨዋታዎችን የሚመሩ ዳኞች በየጨዋታው በተጫዋቾቹ በሚደርስባቸው ወከባ እና እንግልት ምክንያት ሜዳ ውስጥ ተሳቀው እንደሚገቡም ባለሙያው ይመሰክራል።
ተጫዋቾቹ በዳኞች ላይ የሚያሳዩት ያልተገባ ባህሪ ጨዋታዎች እንዲቋረጡ አለፍ ሲልም ነውጥ እንዲነሳ ምክንያት ሲሆኑ ተመልክተናል። ያልተገራው ይህ የተጫዋቾች ያልተገባ የሜዳ ላይ ባህሪ ሌሎች ተጫዋቾችን ፣አሰልጣኞችን እና ደጋፊዎችንም ለፀብ እና ለብጥብጥ ሲያነሳሳም ዓይተናል። ለአብነት ሚያዚያ 27 2010 ዓ.ም መቻል ከወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ በነበራቸው መርሐ ግብር ተጫዋቾች፣ አሰልጣኞች እና የቡድን መሪዎች ዳኛው ላይ ከፍተኛ ድብደባ መፈጸማቸው ይታወሳል፡፡ በወቅቱ ጨዋታውን የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን በቀጥታ ስርጭት እያስተላለፍው ስለነበር የተፈጸመውን አሰቃቂ ድርጊት ዓለም መመልከት ችሏል፡፡
ከከፍተኛ ሊግ ጀምሮ ባሉ ሊጎች ጨዋታዎች የሚደረጉባቸው ብዙ ሜዳዎች በክፍት ወይም ተጫዋቾችን እና ዳኞችን ከደጋፊዎች የሚለያቸው አጥር ባለመኖሩ ዳኞቹ በቀላሉ የጥቃቱ ሰለባ እየሆኑ እንደሚገኙ ጭምር ከዳኞች ኮሚቴ በተደጋጋሚ ከሚነሱ ቅሬታዎችና አቤቱታዎች መረዳት ይቻላል።
ችግሩን ለመቅረፍም ሁሉም የሚመለከተው ባለ ድርሻ አካላት ትኩረት ስጥቶ ሊሰራ ይገባል የፌደራል ዳኛው አማን ሞላ ምክረ ሀሳብ ነው።እግር ኳሱ ባደገባቸው በአውሮፓ ሀገራት ተጫዋቾች ከታክቲክ እና ከቴክኒክ ስልጠናዎች እኩል የጨዋታ ሕጎችንም እንዲሰለጥኑ እና እንዲገነዘቡ ይደረጋሉ ያለው የዘርፉ ባለሙያው፣ ብዙዎቹ ኢትዮጵያውያን ተጫዋቾች የጨዋታ ሕጎችን ባለማወቃቸው ጥፋቱን እንደሚፈጽሙ ተናግሯል። ታዲያ ችግሩን ለመቅረፍ አወዳዳሪው አካል ለክለቦቹ ፣ለተጫዋቾቹ የግንዛቤ ፈጠራ ሥራ መሥራት እንደሚኖርባቸው ባለሙያው አስገንዝቧል።
ሜዳ ውስጥ በዳኛ ፊት ያልተገባ ባህሪ ያሳየ ተጫዋች ከጥፋቱ እንዲታረም አሁን ላይ ተግባራዊ እየተደረገ ካለው ቅጣት በላይ ከበድ ማለት እንዳለበትም ተጠቁሟል፣ሕግ እና ደንቦች መሸርሸር ስለሌለባቸው በተጫዋቾች እና ክለቦች ላይ የማያዳግም እርምጃ በመውሰድ በቅጣት በማስተማር የጨዋታ ሕጎችን እንዲረዱ እና እንዲገነዘቡ ማድረግም ይኖርባቸዋል።
ክለቦቹም ቢሆኑ ተጫዋቾቻቸው የዳኞችን ውሳኔ በፀጋ የማይቀበሉ እና ለዳኛ ተገዢ ካልሆኑ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የገፈቱ ቀማሽ እንደሚሆኑ አያጠያይቅም። ታዲያ ችግሩ ከመድረሱ በፊት በስነ ምግባር እና በሥነ ስርዓት የማይደራደሩ መሆን ይገባቸዋል።
(ስለሺ ተሾመ)
በኲር ታኀሣሥ 8 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም
በአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን ዘወትር ሰኞ የምትታተመውን የበኲር ጋዜጣን ሙሉ ፒዲኤፍ
በhttp:// www.ameco.et/Bekur
በቴሌግራም – https://t.me/bekur123 ላይ ማግኘት ይችላሉ።

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here