ያልተገባ የንግድ ሥራ

0
207

ተገቢ ያልሆነ ንግድ ወይም ያልተገባ የንግድ ሥራ በተለምዶ ሕገ ወጥ ንግድ ማለት ነው:: ይህም “ንግድን የሚመለከቱ የሕግ ድንጋጌዎችን የሚጥስ ማንኛውም ተግባር ነው” በሚል በንግድ ውድድር እና ሸማቾች ጥበቃ አዋጅ ቁጥር 813/2006 አንቀፅ ሁለት ንዑስ ቁጥር 9 እንዲሁም በንግድ ምዝገባ እና ፈቃድ አዋጅ ቁጥር 980/2008 አንቀጽ ሁለት18 ትርጉም ተሰጥቶታል::

ተገቢ ያልሆነ የንግድ ተግባር በርካታ ተግባራትን የሚመለከት ሲሆን ለዚህ ሳምንት የፍትሕ አምድ ጽሑፋችን በተወሰኑት ላይ መረጃ የሰጡን የአማራ ክልል ፍትሕ ቢሮ የኢኮኖሚ ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዐቃቤ ሕግ አቶ ስንታየሁ ቸኮል ናቸው::

አቶ ስንታየሁ እንዳብራሩት ንግድን የተመለከቱ ድንጋጌዎችን የሚጥሱ ተግባራት ወይም ተገቢ ያልሆነ ንግድ ከሚባሉት አንዱ በበላይነት የተያዘን ገበያ ያለ አግባብ የመጠቀም አዋጅ ቁጥር 813/2006 አንቀጽ አምስት በግልም ሆነ ከሌሎች ጋር በመሆን በአስመጭነት ወይም በአከፋፋይነት ምርትን በበላይነት ይዘው ተፅዕኖ የማድረግ ተግባር ነው::

በግልጽም ሆነ በስውር ምርትን በመገደብ ወይም የንግድ ዕቃዎችን በማከማቸት /በመደበኛው የንግድ መስመር እንዳይሸጡ ማድረግ፣ ተገቢ ያልሆነ የንግድ ውድድር (ሥራ)፣ ሀቀኛ ያልሆነ፣ አሳሳች /አታላይነት ያለበት እና የተወዳዳሪን የንግድ ጥቅም የሚጎዳ /ሊጎዳ የሚችል/ ድርጊት መፈጸም እንደሆነ አዋጅ ቁጥር 813/2006 አንቀጽ 8 ተቀምጧል::

በሌላ በኩል ተስማምቶ ዋጋ መቀነስ እና መጨመር፣ ተስማምቶ ሸቀጥ መደበቅ፣ ያለ ፈቃድ መነገድ ተገቢ ያልሆነ የንገድ ተግባር ሆኖ በበርካታ ሁኔታዎች የሚገለፅ ተግባር ነው:: ሌላው ተገቢ ያልሆነ ንግድ የሚባለው ፈቃድ ሳያወጡ መነገድ /የንግድ ምዝገባን ፈቃድ አዋጅ ቁጥር 980/2008 አንቀጽ 22 ንኡስ ቁጥር አንድ ላይ በዝርዝር ተቀምጧል/ ወይም ባልታደሰ ፈቃድ መነገድ ይገኝበታል::

ተገቢ ያልሆነ በሌላ ሰው ፈቃድ መነገድ፣ ፈቃዱ ከተሰጠበት አላማ ውጭ መሥራት የመጠቀሚያ ጊዜ ያለፈባቸውን ሸቀጦች ለሽያጭ ማቅረብ /መሸጥ / ደግሞ በአዋጅ ቁጥር 813/2006 ፣ አንቀጽ 22 ንኡስ ቁጥር 10 ተቀምጧል::

ከላይ የተጠቀሱት ተግባራት በንግድ ሕግ እና መመሪያ የተለያየ የቅጣት ደረጃ እንዳላቸው የገለፁት የሕግ ባለሙያው አቶ ስንታየሁ ለአብነትም ሕጋዊ ነጋዴም ሆኖ የመጠቀሚያ ጊዜ ያለፈባቸውን ሸቀጦች ለሽያጭ በማቅብ /በመሸጥ/ ሕገ ወጥ ተግባር ሲሳተፍ ከተገኘ  ከገንዘብ ቅጣት አንስቶ እስከ ወንጀል ተጠያቂነት የሚሄድበት ዕድል አለው::

ለምሳሌ በተግባሩ የተሳተፈው ነጋዴ ከዓመታዊ ገቢው  ከስድስት እስከ ዐሥር ከመቶ ገቢ የቅጣት መቀጮ  እንዲሁም ከሦስት እስከ ሰባት ዓመት በሚቆይ እስራት ሊያስቀጣው ይችላል:: ይህ የቅጣት ሂደት በጤና ላይ ያደረሰውን ጉዳትን በመመልከት በፍርድ ቤት የሚቀርበውን ማቅለያ እና ማክበጃ ታይቶ ሊወሰን እንደሚችልም ባለሙያው አስንዝበዋል::

በተመሳሳይ በመድኃኒቶች፣ በፈሳሽ መልክ እና በደረቅ ምግብነት የተዘጋጁ የምግብ ሸቀጦች ላይ ተገቢ ያልሆነ ዋጋ መጨመር ይታያል፤ ይሁን እንጂ በሀገር ደረጃ የምርት እጥረት በሚታይባቸው ምርቶች ላይ በጥናት ተለይተው የዋጋ ተመን ሊወጣላቸው ይገባል፤ ሲል ሕጉ ያስቀምጣል:: ነጋዴው በምርቱ ላይ የምርቱን የቆይታ ጊዜ እንዲሁም ዋጋ በጽሑፍ የማስቀመጥ ግዴታም አለበት:: ከተቀመጠው የዋጋ ተመን በላይ ዋጋ ጨምሮ መሸጥ ተገቢ ያልሆ የንግድ ሥራ ተግባር ነው::

በሌላ በኩል እንደ ስኳር፣ ዘይት፣ ነዳጅ፣ ፊኖ ዱቄት እና የመሳሰሉት የንግድ ዕቃዎች በገበያ ያለውን ወቅታዊውን ሁኔታ ከግምት ውስጥ በማስገባት ዋጋው እንደሚወጣ ግምት ውስጥ ማስገባት ያስፈልጋል::  ከዚህ ውጭ ያሉ እና የገበያ እጥረት አለባቸው የሚባሉትን ምርቶች ግን ለይቶ የዋጋ ተመን ማውጣት ተገቢ መሆኑን ሕጉ ያስገነዝባል::

ሌላው ተገቢ ያልሆነ ንግድ የሚባለው እንዲሠራ ከተፈቀደለት አካባቢ ውጭ የንግድ ሥራ መሥራት ነው፤ የንግድ ዕቃን አልሸጥም ማለት፣ በተመሳሳይ ደረጃ ባሉ ነጋዴዎች መካከል ግብይት መፍጠር፣ በአንድ ፈቃድ ደርቦ ሌላ የንግድ ሥራ መሥራት ተገቢ ያለሆኑ የንግድ ተግባራት በመሆናቸው ተጠያቂነትን ያስከትላል::

የኢትዮጵያ የንግድ ሥራ ፈቃድ መስጫ መደብ መመሪያ ቁጥር 17/20011 እንደሚያዝዘው ለአንድ የንግድ ሥራ ፈቃድ መደብ አንድ ፈቃድ ብቻ ይሰጣል፤ ሌላ ተጨማሪ የንግድ ሥራ መደብ ላይ መነገድ የሚፈልግ ተጨማሪ ፈቃድ

ያስፈልገዋል:: እያንዳንዱ የንግድ ፍቃድ ምን ምን ሊኖረው እንደሚገባ በዚህ መመሪያ በዝርዝር ስለተቀመጠ ሥራን ከመሥራት በፊት ማየት ይገባል::

አቶ ስንታየሁ ህብረተሰቡ ይህንን ተገቢ ያልሆነ ንግድ ችግር ለማስወገድ አስፈላጊውን ጥቆማ በመስጠት ማሳወቅ እንዳለበት አንስተዋል፤ መንግሥታዊ እና ሌሎች የሚመለከታቸው ተቋማት፣ የሸማች እና ነጋዴ ማሕበራት እንዲሁም ሕጋዊ የሆነው ነጋዴ ደግሞ ችግሩን በትብብር የመከላከል የድርሻቸውን ሊወጡ ይገባል ብለዋል::

(ማራኪ ሰውነት)

በኲር ጥቅምት 18  ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here