በካናዳ – ኩቤክ ባልና ሚስት የአባወራውን ልደት ለማክበር በዝግጅት ላይ እያሉ ቤታቸው በተኩላ መንጋ ተከቦ በማየታቸው ሁነቱ ያልጠበቁት፣ የማይረሳ አጋጣሚ ሆኖ ማግኘታቸውን እና በምስል ቀርፀው ማጋራታቸውን ኤንዲቲቪ ድረ ገጽ አስነብቧል::
የ34 ዓመቱ ሚቹ ጁልስ እና የ33 ዓመቷ ባለቤቱ ማያ ጁልስ የአባወራውን የልደት በዓል ለማክበር በዝግጅት ላይ ነበሩ:: በዚሁ መካከል ያልጠበቁትን ሁነት መመልከት ችለዋል::
በመኖሪያ ቤታቸው አካባቢ ተኩላዎች ስለ መኖራቸው ማስጠንቀቂያ ሲነገር ቢሰሙም በዚህ መልኩ በመስታዉት የተሸፈነው ቤታቸው በሚጨኹ በርካታ ተኩላዎች ይከበባል ብለው አላሰቡም ነበር::
34ኛ ዓመት የልደት በዓሉን የሚያከብረው አባወራው ሚቹ ጁልስ በኒው ጀርሲ ፎቶ ግራፍ አንሺ ባለሙያ በመሆኑ የቀረፀውን ምስል ለኒው ዮርክ ፖስት አጋርቶታል:: ባለሙያው በህይወቱ በዚህ መልኩ ተኩላዎችን በቅርበት ተመልክቶ አለማወቁን እና አስደሳች የህይወት ገጠመኙ መሆኑንም ነው ያሰፈረው::
ፎቶ ግራፍ አንሺው ባለሙያ ለዱር እንስሳት ጥልቅ ፍቅር ያለው መሆኑን ገልፆ ጥንዶቹ ለሳምንት ያህል በክፍላቸው በቆዩባቸው እለታት ተኩላዎቹን በቅርበት መመልከታቸውን አብራርቷል::
ከተኩላዎቹ ጋር በቅርበት ፊት ለፊት በመተያየቱ እድለኛ መሆኑን ነው የገለፀው፤ ፎቶግራፍ አንሺው ባለሙያ ርቀቱን ጠብቆ የቤቱን በር ሲከፍትላቸውም አለመሸሻቸው እንዳስገረመው ነው ያረጋገጠው::
ፎቶ ግራፍ አንሺው ሚቹጁልስ በህይወቱ ለመጀመሪያ ጊዜ ባገኘው ገጠመኝ መደሰቱን ጠቁሞ ይህንኑ ገጠመኝ ዳግም ለመመልከት ወደ ካናዳ እንደሚመለስ ቃል መግባቱን አስነብቧል::
በማጠቃለያነት እንደ ዓለም አቀፉ የእንስሳት ደህንነት ፈንድ ካናዳ ከሩሲያ ቀጥላ ባላት የተኩላዎች ቁጥር በሁለተኛ ደረጃ ላይ መቀመጧን እና ብዛታቸውም 50 ሺህ እንደሚገመት ሰፍሯል::
(ታምራት ሲሳይ)
በኲር ጥቅምት 18 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም