ጥልቀት የሌላቸው የባሕር ዳርቻዎች ከፍተኛ መጠን ያለው በካይ ትነትን ወደ ከባቢ ዓየር በመልቀቅ የሙቀት መጨመርን እንደሚያባብሱ ሳይንስ ዴይሊ ድረ ገጽ ሰሞኑን ለንባብ አብቅቶታል፡፡
የሮያል ኔዘርላንድስ የባህር ምርምር ተቋም ባደረገው አዲስ ምርምር የውቅያኖስ ላይ ነፋስ እና የወቅቶች መለዋወጥ ጥልቀት በሌለው የባህር ዳርቻ የበካይ ትነት ምንጭን የሚበሉ ጥቃቅን ተህዋስያንን በመገደብ ትነቱ ወደ ከባቢ ዓየር ገብቶ የሙቀት መጨመርን እንደሚያባብስ አረጋግጧል፡፡
ቀደም ባሉት ጊዜያት ሰው ሰራሽ የበካይ ትነት (ሚቴን) ምንጮች በውል የተጠኑ ሲሆን ተፈጥሯዊ የበካይ ትነት ምንጮች ግን ብዙም ትኩረት እንዳልተሰጣቸው ነው ለንባብ የበቃው፡፡ ጥልቀት በሌለው እና በተለዋዋጭ ስነ ምህዳሮች ባህሮች “በሚቴን” የበለፀጉ ናቸው፡፡ ምክንያቱ ደግሞ ውሃው ጥልቅ ስላልሆነ “ሚቴን”ን የሚበሉ ጥቃቅን ተህዋስያን (ሜታኖትሮፍስ) የተሰኙት ወደ ከባቢ ዓየር ከመውጣቱ በፊት ለማጥፋት ጊዜ ስለማይኖራቸው መሆኑ ነው በአጥኚዎቹ የተደረሰበት፡፡
ጥናቱ ሦስት ቀጣናዎችን ለይቶ ነው የተካሄደው፤ በሰሜን ባህር “ዶገር ባንክ”፣ “ደች ዋደን” ባህር እና አርክቲክ “ስቫል ባርድ” አቅራቢያ በሚገኝ የባህር ዳርቻ፡፡ በማጠቃለያ ውጤቱም በቀዝቃዛ ወቅት “ሚቴን”ን የሚያስቀሩ ተህዋስያን እንቅስቃሴ ይገደባል፤ ይህን ተከትሎም በሞገድ እና ወጀብ በሚከሰት የውኅ መቀላቀል በካይ ትነት ወደ ከባቢ ዓየር እንደሚገባ ነው የተሰመረበት፡፡ አጥኚዎቹ በመስክ በተለዩ ተፈጥሯዊ ቀጣናዎች ካደረጓቸው ክትትል እና ምርምር ባሻገር በቤተ ሙከራዎችም ጥልቅ ምርምሮችን አካሂደዋል፡፡
በጥናቱም “ሚቴን”ን የሚበሉ ተህዋስያን ሥነ ምህዳሩ ወይም ቀጣናው ሲቀየር የሚገኙበትን በመላመድ መፋፋት እና መስፋፋትም እንደሚችሉ ነው ያረጋገጡት፤ ተመራማሪው ዶክተር ቲም ደ ግሩት፡፡
(ታምራት ሲሳይ)
በኲር የጥር 26 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም