የኢትዮጵያ ሊግ ደካማ ከሆኑ የአፍሪካ ሊጎች መካከል በግንባር ቀደምትነት ተጠቃሽ ነው። ብሄራዊ ቡድኑም የዓለም እና የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያዎችን ማለፍ ተስኖት ዛሬም እንደቆዘመ ነው። የአፍሪካ ሀገራትን የሊግ ደረጃ በየጊዜው የሚያወጣው ቲም ፎርም የተባለው ድረግጽ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ከደካማዎች ተርታ እንደሚሰለፍ አስነብቧል።
ተጫዋቾች በሙያቸው ብቁ( professional) አለመሆናቸው፣ በአካል ብቃት፣ በቴክኒክ እና በታክቲክ አረዳዳቸው እንዲሁም የአሸናፊነት ስነ ልቦናቸው ጠንካራ አለመሆኑ ሊጉን እና ብሄራዊ ቡድኑን ደካማ ያደረጉት ምክንያቶች ናቸው። ለአንድ ሀገር እግር ኳስ እድገት ከታች ከስር ( Grass root level) መሠራት እንዳለበት የኢንሳይድ ፊፋ መረጃ ያመለክታል። ታዲያ በኢትዮጵያ የታዳጊ ወጣቶች እግር ኳስ ልማት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻለ ነው ቢባልም መሬት ላይ ያለው ሀቅ ግን ሌላ መሆኑን ብዙዎች ይናገራሉ።
የቀድሞው የባሕር ዳር ከነማ እና የአውስኮድ ክለብ አሰልጣኝ የሆኑት ፈንታዬ አባተ ከአሚኮ ስፖርት ጋር በነበራቸው ቆይታ በኢትዮጵያ የታዳጊ ወጣቶች ስልጠና ውጤታማ እንዳልሆነ ይናገራሉ። በሀገራችን በየአካባቢው እና ሰፈሮች የሚሰጡ የታዳጊ ወጣቶች ስልጠናዎች በታዳጊ ወጣቶች ላይ የሚሠራው ሥራ በተገቢው መንገድ እየተሠራ አይደለም ብለዋል። ስልጠናው እውቀትን እና ልምድን ያማከለ አለመሆኑ፣ የመሰረ ልማት እጥረት መኖሩ፣ በቂ እና ምቹ የሆኑ ሜዳዎች አለመኖራቸው እና የስልጠና ቁሳቁስ አለመሟላት በሀገራችን የታዳጊ ወጣቶች ስልጠና መሻሻል እንዳይታይባቸው ያደረጉ ምክንያቶች ናቸው። በሀገራችን በሁሉም ቦታዎች የታዳጊ ወጣቶች ስልጠና ጎዳና ላይ ወይም በተበላሹ ሜዳዎች ላይ እንደሚሰጥ የአደባባይ ሀቅ ነው። ባህል የሆነ፣ ወጥ እና ተመሳሳይ የእግር ኳስ አስተሳሰብ ተግባራዊ የሚደረግበት የስልጠና ሰነድ እንደሌለም አሰልጣኝ ፈንታዬ ተናግሯል።
ብቁ የሆኑ አሰልጣኞች አለመኖራቸውም ሌላኛው የችግሩ ምክንያት ነው። የካፍ ቢ ወይም ኤ ፈቃዳ ያላቸው አሰልጣኞች ዝቅ ብለው ታዳጊ ወጣቶችን አለማሰልጠናቸው ብዙ ተሰጥኦ ያላቸው የመጪው ዘመን ኮከቦች እንዳይወጡ እና እንዲጠፉ አድርጓቸዋል። አብዛኞች የታዳጊ ወጣቶች ፕሮግራም በግለሰቦች ድጋፍ ላይ የተመሰረቱ በመሆናቸው ዘላቂነት እንደሌላቸው የእግር ኳስ ባለሙያው ተናግሯል።
ለተጫዋቾች ዝውውር ረብጣ ሚሊዬን ገንዘብ የሚያፈሱት የኢትዮጵያ ክለቦች ታዳጊዎች ላይ ሲሰሩ አይስተዋሉም። ይህም የታዳጊ ወጣቶች ስልጠና ውጤታማ እንዳይሆን ካደረጉት ምክንያቶች ሌላኛው ነው። በኢትዮጵያ የአሰልጣኝ ሰውነት ቢሻው እግር ኳስ አካዳሚ፣ የኢትዮጵያ ስፖርት አካዳሚ፣ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት እና ጥቂት የፕሪሚየር ሊግ ክለቦች አካዳሚ እንዳሏቸው ይታወቃል። ነገር ግን ከአካዳሚዎች ወደ ክለቦች የሚያደርጉት ሽግግር አዝጋሚ በመሆኑ ታዳጊዎች ተስፋ እንዲቆርጡ እና ዘርፉን እንዲሸሹት አድርጓቸዋል ብሏል አሰልጣኝ ፈንታዬ።
ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በመንግስት እና በፊፋ የእግር ኳስ ፕሮግራሞች የተጀመረ ሲሆን የትምህርት ቤቶችን ስፖርቶች ይበልጥ ለማስፋፋት እድል ሰጥቷል። ይህ መሆኑ ታዲያ የታዳጊ ወጣቶች ስልጠናን በማበረታት እግር ኳሱ እንዲሻሻል ያደርጋል። የኢትዮጵያ ህዝብ አብዛኛው ወጣት በመሆኑ ለእግር ኳስ እምቅ የተጫዋች አቅም መኖሩን የፊፋ ኢንሳይድ መረጃ ያስነብባል። ይህ ደግሞ ብቁ እና ባለተሰጥኦ ተጫዋቾችን ለማፍራት ትልቅ አጋጣሚ ነው ይላል መረጃው።
ይሁን እንጂ የታዳጊ ወጣቶች ስልጠና በተገቢው መንገድ ሂደቱን ጠብቆ እየተሰጠ ባለመሆኑ ውጤታማ እንዳይሆን አድርጎታል ብለዋል ባለሙያው። የታዳጊ ወጣቶች ስልጠና ከአምስት ዓመት እድሜ ጀምሮ መሰጠት እንዳለበት የፊፋ ዶት ኮም መረጃ አመልክቷል። የዓለም አቀፉ የእግር ኳስ የበላይ አስተዳዳሪ (የፊፋ) የእግር ኳስ ልማት ዳይሬክተር የሆኑት የቀድሞው የአርሴናሉ አሰልጣኝ አርሰን ቬንገር ይህንን ሀሳብ አጠናክረውታል። ታዳጊዎችን ማሰልጠን ቤት እንደመገንባት መሆኑን በምሳሌ ያስረዳሉ።
“የመጀመሪያው ምዕራፍ መሰረት ነው። የታዳጊዎች ዋናው መሰረት ቴክኒክ ነው፤ ይህን ስልጠና የሚወስዱበት ጊዜ ደግሞ ከሰባት እስከ 14 እድሜአቸው ነው። አንድ ታዳጊ በ14 ዓመቱ የቴክኒክ ክህሎት ከሌለው እግር ኳስ ተጫዋች አይሆንም። ሁለተኛው ምዕራፍ ደግሞ ከአካል ብቃት ጋር የተያያዘ ነው። ከ14 እስከ 17 ዓመት እድሜ በአካል ብቃት ጠንካራ እና ፈጣን የሚሆኑበት የእድሜ ክልል ነው። የቤቱ ሁለተኛው ወለል ማለት የታክቲክ ግንዛቤ እና አረዳድ ነው፤ ጨዋታን እንዴት ማንበብ ይቻላሉ? ከኳስ ጋርስ ምን ማድረግ ይችላሉ? የሚሉት ይገመገሙበታል። የመጨረሻው ምዕራፍ የሚወሰነው ከ18 እስከ 19 እድሜአቸው ውስጥ ነው፤ በምን መንገድ ስኬታማ ተጫዋች እንደሚሆኑ የሚያውቁበት ጊዜ ነው” ይላሉ የእግር ኳስ ሊቁ አርሰን ቬንገር።
እንደ አሰልጣኝ ፋንታዬ ማብራሪያ ዓለም የሚከተለውን ዘመናዊ የስልጠና መንገድ ከተከተልን በጭር ጊዜ ውስጥ በታዳጊ ወጣቶች ስልጠና ላይ ለውጥ ማምጣት እንደሚቻል አስገንዝበዋል። የሀገራችን የስልጠና መንገድ አሁንም በቆየው ኋላቀር አሠራር እያዘገመ መሆኑን የገለጹት ባለሙያው የታዳጊ ወጣቶች ስልጠና ላይ በደንብ የተደራጀ ስርዓት መዘርጋት ቀዳሚው ተግባር ነው ብለዋል።
የእግር ኳስ አካዳሚዎችን ለመክፈት እና ለመስራት የሚያስፈልጉ መስፈርቶችንም መሟላት አለባቸው ነው የተባለው። ተጫዋቾች በየትኛው እድሜ ላይ የቴክኒክ ክህሎት፣ የአካል ብቃት እና የእግር ኳስ ፍልስፍና መማር እንዳለባቸውም መገንዘብ ያስፈልጋል ባይናቸው ባለሙያው። ታዳጊዎች ከአምስት እስከ ሰባት ዓመታቸው ሕግ እና ደንብ ሳይቀመጥላቸው ኳስን በነጻነት እንዲጫወቱ እና እንዲወዱ የሚደረጉበት የእድሜ ክልል ነው። ከሰባት እስከ 12 እድሜ ታዳጊዎች የቴክኒክ ክህሎታቸውን የሚያዳብሩበት በተለይ ደግሞ መሰረታዊ የእግር ኳስ ክህሎት የሚባሉትን ኳስ መግፋት፣ መቀበል እና መቆጣጠርን የሚያዳብሩበት ወቅት ነው። እንዲሁም መሰረታዊ የሆኑ የታክቲካል ግንዛቤ የሚጨብጡበትም እንደሆነ አሰልጣኝ ፈንታዬ ያብራራሉ። በዚህ የእድሜ ክልል አሰልጣኞች አቅማቸውን ተጠቅመው ታዳጊ ተጫዋቾችን ብቁ የሚያደርጉበት ነው። ከ13 እስከ 16 የእድሜ ክልል ደግሞ መሰረታዊ የታክቲካል እውቀት የሚይዙበት እና በአካል ብቃት የሚጎለብቱበት ጊዜ ነው ተብሏል። ብቁ እና ባለተሰጥኦ የሆኑ ታዳጊዎች በሽግግር ወቅት ክለቦችን የሚቀላቀሉበትን መንገድ ማመቻቸት ያስፈልጋል። ታዳጊዎችም ትዕግስት ሊኖራቸው ይገባል ተብሏል። ብሄራዊ ቡድኑ እና ሊጉ የታዳጊ ወጣቶች ነጸብራቅ በመሆኑ በታዳጊዎች ላይ ትኩረት ተሰጥቶ መሰራት ይኖርበታል- የባለሙያው አሰተያየት ነው። ብቁ ተጫዋቾች የሚፈጠሩ ብቁ አሰልጣኞች ሲኖሩ ነውና ይህንንም እግር ኳስ ፌዴሬሽኑ ሊያስብበት የጋባል ባይ ናቸው- ባለሙያው።
(ስለሺ ተሾመ)
በኲር የግንቦት 18 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም